
በክህደት የሚታወቀው ትሕነግ “ዝረፉ፣ ጨፍጭፉ፣ አውድሙ” ብሎ ልኮ ላስጨረሳቸው ሁሉ በጅምላ “የሰማዕትነት ማዕረግ” አከናንቦ ሐዘን አውጇል። ይህ የትሕነግ የሰማዕትነት ማዕረግ የመንዙን መብረቅ እሸቴን፣ ኮሎኔል ማራኪዋ ምክትል ዐሥር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄን፣ የክምር ድንጋዩ ትንታግ ጌጤ መኳንንት አባ ረፍርፍ፣ በስልኩ ብቻ 15 የጁንታ ታጣቂዎችን ማርኮ፤ 40ዎቹን እንዲደመሰሱ ያደረገው የጋይንቱ ጀግና ሰፊው በቀለ ናደው፣ የምድር ድሮኖች (አፋር) – የዕቶን ውስጥ ነበልባሎችን፣ አገር ብለው ከየአቅጣጫው የተመሙ የኢትዮጵያን ልጆች “አሸባሪ” አድርጎ መፈረጅ መሆኑን ስንቶች ተረዳን?
ሸዋ ደብረብርሃን አፍንጫ ሥር፣ ወሎ፣ ጎንደር፣ አፋርን አካልሎ ደጋግሞ የወረረ፣ የዘረፈ፣ መነኩሴ የደፈረ፣ ንጹሐንን የጨፈጨፈና ንብረት ያወደመ፣ እንስሳት ሳይቀር የረሸነ፣ በዕቅድ ተደራጅቶ ለጥፋት የተሰማራ፣ በትሕነግ ፕሮፓጋንዳ ተሞልቶ፣ በወላጅ ቤተሰብ ተመርቆ የዘመተ ወራሪ ኃይል “ሰማዕት” ተብሎ “የክብር” ሃሐን ታወጀለት። ይህ የዘመናችን ጉድ ራሳቸውን “ሚዲያና ጋዜጠኛ፣ አክቲቪስትና ታጋይ” ብለው በሰየሙ ተጋላቢዎች፣ ተቀጣሪዎችና በብሔር ቫይረስ የተጠቁ ወዘተ ዕውቅና ሲሰጠው ዝም ብሎ ማየት የትሕነግን ውንብድና የማወደስና የመቀብል ያህል ነው። ከዚያም በላይ በጀግንነት ያለፉትን የኢትዮጵያ ልጆ ደም መርገጥና ማዋረድ ነው።
የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ትሕነግ) በማለት ራሱን የሚጠራው ቡድን በዓለምአቀፉ የአሸባሪ ቋት ተመዝግቦ የሚገኘው የወንበዴዎች ስብስብ ነው። ይህ ቡድን ለሁለት ዓሥርተ ዓመታት ሲያገለግለው የነበረውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተኛበት አርዷል። ይህንኑ የክህደት ታሪኩን “በኢትዮጵያ ላይ መብረቃዊ ጥቃት ሰነዘርን” ሲል ደረቱን ነፍቶ ነግሮናል። በክህደቱና ውንብድናው የሚመጻደቅ ይህ እንግዴ ቡድን በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ተዛብቷል። መለያቸውን አዋርዷል። በሕይወት እያሉ በመኪና ጨፍልቋቸዋል። እንደ ባዕድ በአደባባይ አሰልፎ ተሳልቆባቸዋል። እንዲህ ያለው ክህደቱን እንደ ሞገስና ክብር ቆጥሮ በአፈቀላጤውና በየደረጃው ባሉ መንጋዎቹ ይፋ ማድርጉ ሊካድ እንዳይችል ሆኖ በዘመነ ዲጂታል ተመዝግቦ የተቀመጠ የኛ፣ የዚህ ትውልድ ዘመን ታሪክ ነው።
ትሕነግ ይህንን አሸባሪ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ ሲተማመንበት የነበረውን ልዩ ኃይል፣ ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና ከእያንዳንዱ የትግራይ ቤተሰብ የተበረከተለትን ሕዝባዊ ሠራዊት ይዞ፤ በትግራይ ለዓመታት ያከማቸውን መሣሪያ አንግቦ፣ የተወሰነውንም ከሰሜን ዕዝ ዘርፎ ኢትዮጵያን ለመውጋት እና ወደ ሥልጣን ለመምጣት ጦርነት በይፋ ከፍቷል። የዘረፈውን ሃብት እየረጨ ድፍን ኢትዮጵያን በቅጥረኞቹ፣ በሚዲያና በቅጥር ነፍሰ ገዳዮች አድምቷል። መከራ እንዲቀበሉ አድርጓል።
ለሦስት ዓሥርተ ዓመታት “ተራራ ያንቀጠቀጠ” ብሎ ባልተጻፈና ባልተከሰተ ታሪክ በባዶ ራሱን ያሳበጠውና ተከታዮቹን በትዕቢት የወጠረው ትሕነግ፣ ፈጽሞ ባልጠበቀው ሁኔታ በለኮሰው ጦርነት ተሸንፎ፤ የሚመካባቸው መሪዎቹ እንዳይመለሱ ተሰናብተው፤ ጭራውን ቆልፎ ወደ ትግራይ ሲገባ እና ወደ በረኻ ሲሸሽ ተመልሶ እንደሚመጣ ተገማች ነበር።
ትሕነግ እንደለመደው ለሁለተኛና ለሦስተኛ ጊዜ ወረራ ሲያካሂድ ዓላማው ሥልጣን መያዝ እንዳልሆነ ራሱ ቢያውቀውም ከተማረኩት ታጣቂዎቹ በተደጋጋሚ ሲነገር የተሰማው ግን ሌላ ነው። “የአማራን ክልል ሄዳችሁ ውረሩ፤ ለሁለት ዓመት የሚሆናችሁን ቀለብና ሃብት ዘርፋችሁ ትመጣላችሁ፤ የዘረፋችሁት የራሳችሁ ይሆናል” ተብለን ነው የመጣነው ያሉት ጥቂት የማይባሉ ምርኮኞች ነበሩ።
እንዳሉትም በተቀናጀ ሁኔታ ዘረፋ አካሂደዋል፤ ማሽን በጥንቃቄ የሚነቅል የሰለጠነ ኃይል፤ የተነቀለውን በሥርዓት ወደ መኪና የሚጭን፤ የሚነቀለው ማሽን የሕክምና መሣሪያ ሲሆን ለዚያ ተብሎ የተዘጋጀ ቡድን ከታጣቂውና እነርሱ ቲዲኤፍ (የትግራይ ዲፌንስ ፎርስ) ብለው ከሚጠሩት የዘረፋና የውንብድና ቡድን ጀርባ እየተከተለ ግዳጁን የሚፈጽም ነበር። ይህ ቡድኑ ምን ያህል ለጥፋት የሚተጋ፣ ደግነትና ቀናነት የነጠፈበት የሤራ ቋት መሆኑንን የሚያመላክት ነው። እንግዲህ እንዲህ ያደረገውና ያስደረገው ትህነግ ነው “ሰማዕት” ብሎ ዜና የሚያሠራው፤ “ሚዲያውና ጋዜጠኞችም” ይህንኑ የሚያሰራጩት።
ነው ወይስ ሰማዕት ማለት “ስለ እውነት መሰዋት፣ መሰደድ፣ መገፋት፣ ዋጋ መክፈል፣ ለእውነት መሞት፣” ወይም የመዝገበ ቃል ትርጉሙ “ለሃገሩ፣ ለእምነቱ፣ ለሃይማኖቱ መስዋዕት መሆን” የሚለው ተዘንግቷቸው ነው?
ለሁለተኛና እና ሦስተኛ ጊዜ ለዘረፋ እና ለውንብድና ትሕነግ ያሰማራው ኃይል ከሰብዓዊ ፍጡር አልፎ ከብቶችን፣ ውሻ ሳይቀር ጨፍጭፏል፣ የገበሬዎች ማሳ እና መንደር በአይጥ እንዲወረር ድመቶችን ገድሏል፤ በየሰፈሩ እየሄደ የገበሬ ሃብት ከመዝረፍ አልፎ በጾም ቀን ገበሬው የራሱን በሬ አርዶ እንዲያበላው አስገድዷል፤ “ሃይማኖቴ አይፈቅድልኝም እምቢ” ያሉትን “ያንተ አምላክ ያድንህ እንደሆነ እናያለን” እያሉ እዚያው ቤተሰቡ ፊት ረሽኗቸዋል፤ ከዕፅዋት ሳይቀር ወርሮ የያዛቸውን አካባቢዎች ሲለቅ ዛፎችን ጨፍጭፎ እንደወጣ በተለይ በነፋስ መውጫ ወደ ጋሸና በሚወስደው መንገድ ላይ የታየ ሐቅ ነው።
“አይጥ ጎተራ እንዳይገባ፣ እህል እንዳያበላሽ የሚጠብቁ ድመቶችን ገደሉ። አውሬ ሲመጣና በረት ሲጠጋ የሚጮኹ ውሾችን ሳይቀር ረሸኑ። ጥለው ሲወጡ ዛፉን ሁሉ አናት አናቱን ቆረጡት… እንዲህ ያለ ጉድ አይቼ አላውቅም። ይሄ ጉድ …..” የሚል የዓይን ምስክርነት የተሰጠባቸው ናቸው እንግዲህ “ሰማዕት” የተባሉት። “አክቲቪስት ነን” ባዮችም ጌታቸው ረዳን ተቀብለው ማረጋገጫ እየሰጡ ያከረሙት።
ይህ ወራሪና ፍጹም አሸባሪ የሆነ ኃይል ቀድሞ ሂድና ዝረፍ ባሉት በክልሉ መሪዎች የሐዘን ቀን ታውጆለታል፤ “ትግራይ ትስዕር” ሲሉ የነበሩ ሁሉ “ትግራይ ታልቅስ” እንዲሉ ቀን ተቆጥሮ ተሰጥቷቸዋል፤ ሐዘኑና ማቅ መልበሱ በትግራይና በዳያስፖራ እንዲሆን አፉን ስለከፈተና ስለጮኸ ብቻ “ጋዜጠኛ” ተብሎ የሚጠራ ሁሉ “የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል” በማለት ጌታቸው ረዳን እና ታደሰ ወረደን ጠቅሰው ዘግበዋል። አያያዛቸው የሚያበቃ አይመስልም፤ ነፍሰበላዎቹ የትሕነግ ታጣቂዎች “ሰማዕት” እንዲባሉ እነ ጌታቸው ያስተላለፉትን መልዕክት ከባለቤቶቹ በላይ ያስተጋቡት ተጋላቢ “ጋዜጠኞች” ሚዲያና በውጭ አገር በጀት ቀለብ የሚሰፈርላቸው “ባንዳዎች” እነ እሸቴን “አሸባሪ” የማለት ያህል ይህንን ወሮ በላ ድርጅት የሰማዕትነት ባለ ማዕረግ እያደረጉት ነው።
መጠየቅ፣ መመርመር፣ ዞር ብሎ ማየትና ሚዛን ሰፈራ ብሎ ነገር የማያውቀው “ሚዲያ ነኝ” ባዩ ስብስብ የትሕነግ አሸባሪዎች ሙሉ በሙሉ ሰማዕት እንዲባሉ ሲወተውት፣ ሲያውጅና ማብራሪያ ሲሰጥ፣ ከትሕነግ የወረደለትን ዜና እንዳለ ሲረጭ ለመሆኑ በሸዋ ሮቢት የትሕነግን ታጣቂዎች ደምስሶ መጨረሻ የተሰዋውን ጀግናው እሸቴ ሞገስና ልጁን ይታገሱ እሸቴን ምን ብሎ ሊጠራቸው አስቦ ነው? የትሕነግ ታጣቂዎች ሰማዕት ከተባሉ እነ እሸቴ አሸባሪ ናቸው ማለት ነው?! በአንድ አገር ሁለቱም ሰማዕት ሊባሉ አይችሉምና ይህ ጥያቄ ምላሽ ይሻል። የሰው ልጅ ሞት ቢያሳዝንም፣ አሟሟት ለየቀል ነውና “ሚዲያ ነን” ባዮች ነፍሰ ገዳዮችን ስትቀድሱ፣ ለህልውናቸው የተዋደቁትን ሁሉ “አሸባሪ” በማለት እያረከሳችሁ መሆኑንን ታሪክ እንዲመዘግበው ይህ ተጽፏል። ይህ ተሰንዷል።
“ኮሎኔል ማራኪ” እያሉ ባልተፈጸመ ገድል ለዓመታት ከበሮ ሲደልቁ የነበሩትን በትክክል ኮሎኔል ማራኪ ምን ማለት እንደሆነ ያስመሰከረችውና ሽንት ቤት ተሸሽጎ የነበረውን ኮሎኔል ሰለሞን ገብረዮሐንስን ማርካ፤ ጫማውን አስወልቃ፤ ሽጉጡን የተረከበችው ጀግና ምክትል ዐሥር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ ምን ልትባል ነው? ተማራኪው ኮሎኔል በሕይወት ካለ “ጀግና” ከሌለ ደግሞ “ሰማዕት” የሚባል ከሆነ ምክትል ዐሥር አለቃ ገበያነሽ አሸባሪ ነች ማለት ነው።
አስራ አንድ የትሕነግ ታጣቂዎችን ወደማይመለሱበት የሸኘው በደቡብ ጎንደር ዞን የክምር ድንጋዩ ጌጤ መኳንንት (አባ ረፍርፍ) መቼም የገደላቸው ሰማዕት ከተባሉ የፈጸመው ገድል ስሙ ተቀይሮ አሸባሪ ተግባር መባል አለበት እንጂ እሱ ጀግና፣ የገደላቸው ሰማዕት ተብለው ሊጠሩ አይችሉም።
በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ቀበሌ 03 ነዋሪ የሆነው፤ በስልኩ ብቻ 15 የጁንታ ታጣቂዎችን ማርኮ፤ 40ዎቹን እንዲደመሰሱ ያደረገው ጀግና ሰፊው በቀለ ናደው ጀብድ የፈጸመባቸው አሁን “ሰማዕት” ተብለው ሲጠሩ ሲሰማ “እነሱን ሰማዕት ብላችሁ ከዘገባችሁላቸው እኔንስ ምን ብላችሁ ልትጠሩኝ ነው?” ብሎ ጋዜጠኛ ነን ባዮቹን ቢጠይቅ መልሳቸው ምን ይሆን? ካላፈሩ ሰፊው ናደውን በትክክለኛ ስሙ “ንጹሐን ጨፍጫፊ”፣ “አረመኔ” ማለት ነው ያለባቸው፤ ምክንያቱም እነሱ “ፕሬዚዳንት” ያሉትና አሁን “ሰማዕት” ተብለው ይጠሩ ያላቸውን “ሔዳችሁ አማራ ላይ ሒሳብ አወራርዱ” ብሎ የላካቸው ጌታቸው ረዳ የነገራቸው ከዚህ የተለየ ስላልሆነ ነው።
ወንበዴና አሸባሪ የሆነውን ትሕነግን የተፋለሙ ተዘርዝረው ስለማያልቁ ይህንን እዚህ ላይ እንግታው።
ለትውስታ ያህል አሁን በመሪዎቹ ሰማዕት የተባለውና አገር ሲያወድም የነበረው ጨፍጫፊ ቡድን በአማራ እና አፋር ሕዝብ ላይ ሒሳብ እንዲያወራርድ በነጌታቸው በተላከ ወቅት የፈጸመውን ጥቂቱን እንዘርዝር (ሊንኩን በመጫን በወቅቱ ያወጣነውን ዝርዝር ዘገባ ማንበብ ይቻላል)፤
- እናቱ በግፍ የተገደለችበት ጨቅላ ሕጻን አማሟቷን ሲናገር “እናንዬን ድው አደረጋት” ብሏል፤
- በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከለከለውን በርካታ ሚስማር መሰል ፍንጣሪ (flechette) የተሰገሰገባቸውን በከባድ መሣሪያ ጭምር የሚተኮሱትን የሚስማር ጥይቶች በንፁሃን በሕዝብ ላይ አዝንቧል፤
- በደቡብ ወሎ አይሻ ሰይድ ነገ “ሰማዕት” የሚባለው የትሕነግ አሸባሪ እንዴት እናቷን እንደገደለባት ስትገልፅ “የ75 ዓመት አዛውንት የሆነችውን እናቴን ገድለው በጅብ አስበሏት” ብላለች፤
- ኢትዮጵያን የምናፈርስበት “ዓመት፣ ወር፣ ቀን እና ሰዓት አሁን ነው” ሰነድ ሰንዶ አገር ለማፍረስ በትጋት ሰርቷል፤
- በደብረ ዘቢጥ ነዋሪ የሆኑት በድህነት ከተቆራመዱ እማሆይ ሲሳይ ዋጋው የዕለት ቀለባቸውን ዘርፏዋል፤
- በዛሪማ ትውልድ ሲያስታውሰው የሚኖር ዘረፋ ፈጽሟል፤ ይዞ መሄድ ያቃተውንም አቃጥሏል፤
- የ30 ዓመት የትዳር ጓደኛቸውን እርሻቸው ላይ በአረም ሥራ ሳሉ የተገደሉባቸው ወ/ሮ ጦይባ ሙሐመድ እነ ጌታቸው “ሰማዕት” ብለው የዳቦ ስም ስላወጡለት አሸባሪ እንዲህ ብለው ነበር፤ “አላህ ይፍረደኝ የልጆቼን አባት አንገላተው ገደሉብኝ፤ ጌታ ይፍረደኝ በወጉ ሳልቀብር ጅብ አስበሉብኝ ብጥስጣሽ ልብሱ ውርማ ተገኘ”፤
- ከአፋር ክልል ጥቂት የምትርቀው በወሎ የምትገኘውን አጋምሳ መንደርን እንዳልነበረች አድርጎ ሲያወድም ማስረጃው በሳተላይት ተቀርጾዋል፤
- የትሕነግ ታጣቂዎች የ(USAID) መጋዘኖችን ሰብረው መዝረፋቸው በወቅቱ በድርጅቱ ኃላፊ ተነግሯል፤
- እነ ጌታቸው ሰማዕት ብለው የሰየሙት ምኑ ይሆን ሰማዕት ያስባለው …?
- “አደንዛዥ ዕጽ በበርሜል ሻይ አፍልተው” እየሰጡ ሕጻናትን ለጦርነት ከማሰለፍ ባለፈ ለማይሽር የአእምሮ በሽታ ዳርጓል፤ ይህ ይሆን ሰማዕት የሚያስብለው?
- “አማራ ሆነህ ከመፈጠር ትግራይ ውስጥ ዕቃ ሆነህ ብትፈጠር ይሻልሃል”፤ “ከአማራ የማይሰራ አህያ ይሻላል”፤ ወዘተ የሚሉ አጸያፊ ስድቦችን ለአማራ ሕዝብ በቤቱ ጽፈውለት መሄዳቸው ተረስቶ ይሆን?
- አስገድዶ መድፈር ባሕሉ የሆነበት፣ በራሱ ክልል ሴቶችን አልፎ ወንድ ሕጻናትን (ከአንድ ዓመት ጀምሮ አንዳንዴ በታችም ያሉትን) አስገድዶ መድፈሩ ሆን ሰማዕት ያስባለው?
- “ውረሩ፣ ያገኛችሁትን ግደሉ እየተባልን ነው የምንመጣው” በማለት እጃቸውን የሠጡ የትህነግ ታጣቂዎችን ይሆን ሰማዕት እንዲባሉ ነጋ ጠባ መከራ የምናየው?
- “መግደልም መድፈርም መብታችን ነው” ሲሉ የነበሩትን ነው ትህነግ ሰማዕት እንዲባሉ እየሠራ ያለው?
- ወይስ አዛውንት ጓደኛቸውን እንዲሁ ደፍረው ለአካላዊና ሞራላዊ ሕመም በመዳረጋቸው ይሆን ሰማዕት የሚለው የክብር ስም የወጣላቸው?
ይህ ሲፈጠር ጀምሮ እርስ በርስ የመጫረስ አባዜ የተጠናወተው ቡድን፣ የፈጸማቸውን የግፍ፣ ርኩሰት፣ ታሪካዊ ሸፍጥ፣ ሤራና አገር እንድትበተን አድርጎ ሒሳብ የቀመረ ቡድን የትኛው በጎ ነገሩ ሰማዕት ሊያሰኘው እንደሚችል ማሰቡ በራሱ ህምም ነው። ከዚያ በላይ ደግሞ “ፕሬዚዳንት ጌታቸው” እያሉ ዜና የሚያራቡት “ሚዲያ” ተብዬዎች የሚሠሩትን ማየት ስሜትን ይፈታተናል። “ጦርነት ባሕላዊ ዘፈናችን ነው” እያለ ሲያቅራራ ለነበረ ቡድን ይህንን ያህል ማሽቃበጥ ማንነትን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ እውነታ ነው።
ወንበዴው ትሕነግ “ትግራይን ነጻ ለማውጣት” በሚል ተነስቶ በባንዳነት አገር ለማፍረስ ከምዕራባውያን ከገንዘብ እስከ ሃሳብ እየተደጎመ ኢትዮጵያን ሲያደማ ለኖረበት 17ዓመታት በባንዳነት የሞቱትን “ሰማዕታት” እያለ በሐሰት ትርክት ለሠላሳ ዓመታት ሲያደነቁረን ኖሯል፤ በመቀሌም ሐውልት ገትሯል። በ17ቱ ዓመታት አካላቸውን ያጡትን፣ ዓይናቸው የጠፋውን፣ እጅና እግራቸው ተቆርጦ ጉንድሽ የሆኑትን፣ የውሸት ትርክትና የውንብድና መሪ የነበረው መለስ ዜናዊ “እነዚህን ቆሻሾች፣ ጉድፎች አስወግዱልኝ፣ ከፊቴ አጥፉልኝ” ማለቱ በወቅቱ የሰሙ መስክረዋል። እንደዚህ በጸያፍ ቃል የጠራቸውን ነው ለሠላሳ ዓመታት “ጀግና ሰማዕታት፤ ዘላለማዊ ክብር ለሰማዕታት” እያለ በራሱ ሕዝብ ሲያላግጥ የኖረው። ያሁኑም ከዚህ የባሰ እንጂ ያነሰ እንዳልሆነ አካላቸውን የተቆራረጡትንና 6ሺህ ብር ተሰጥቷው ደህና ሁኑ ተብለው የተሸኙትን ጠጋ ብሎ መጠየቅ በቂ ነው።
ትሕነግ በትግራይ የሐዘን ቀን ያወጀው በአገር ውስጥና በውጪ ለሚኖሩት ተከታዮቹ ነው። በትግራይ ያለው ነዋሪ ትሕነግ አድርግ ያለውን ማድረግ ገዴታው ነው ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም ቀለብ ሰፍሮ የሚሰጠውም ትሕነግ ስለሆነ ነው። በዳያስፖራ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ግን አስጨፍጫፊዎቹን እነ ጌታቸውን ለፍርድ ማቅረብ ሲገባቸው በምን ሒሳብ ነው ማቅ ለብሰው ሐዘን የሚቀመጡት? እንዴት በዚህ የትሕነግ አጀንዳ ይሳተፋሉ? መልሱን እኛው እንስጥ፤ እነርሱ የትግራይ ተወላጆች ቢሆኑም ሥርዓቱን ለማስቀጠል በኤርትራዊ ስምና ማንነት ከአገር የወጡ ትሕነጎች ስለሆኑ የሚሠሩት፣ የሚያስቡት ትሕነግ በፈቀደላቸው መጠንና በሰጣቸው ጭንቅላት ስለሆነ ነው።
እናብቃ … ከላይ የተዘረዘሩት የኢትዮጵያ ጀግኖች፣ ሰላም ብለው በተኙበት በክህደት የታረዱትን የአገር አለኝታዎች፣ ኢትዮጵያ ዛሬ ድረስ እንዳትረጋ ሆና መከራ የምታጭድበትን ዋና ምክንያት ሲታሰብ ትሕነግ ከፊት የሚሰለፍ እፉኚት መሆኑ ተረስቶ “ሰማዕት” ብሎ ራሱን ከነጀሌዎቹ ሰይሞ ድንጋይ ሲተክል ማየት ያሳዝናል። አማራና አፋር፣ እንዲሁም ፌዴራል መንግሥት ትውልድ የኢትዮጵያ ሰማእቶችንና ገድላቸውን በክብር እንዲያስብ መታሰቢያ ማነጽ ሲገባቸው “አሸባሪ” ሲባሉ ዝም ብለዋል። ወራሪ “ሰማዕት” ሆኖ ለኅልውናቸውና ለአገራቸው የሞቱ፣ የሰማዕትነት ጽዋ የጠጡ “አሸባሪ” ተብለው እንዲጠሩ ፈቅደዋል። አሁንም አልረፈደምና ይህ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። በአገርዓቀፍ ደረጃ ትሕነግ በለኮሰው ጦርነት ሲፋለሙ ለሞቱ፣ ለቆሰሉ፣ ለልጆቻቸው አልሸነፍም ባይነትን ያወረሱ፣ ለአገራቸው ደማቸውን ያፈሰሱና አጥንታቸውን የከሰከሱ በአገርዓቀፍ ደረጃ ቀን ተመድቦላቸው፣ ሐውልት ቆሞላቸው ትክክለኛ የሰማዕትነት መብታቸው ሊከበር ይገባል። ወንበዴን ሰማዕት ማለት ኢትዮጵያን ማዋረድ፤ ጀግናን አሸባሪ ማለት ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ™” አቋም ነው።
ወያኔ የወስላቶችና የደም አፍሳሾች ጥርቅም ነው። ሲጀመር ጀምሮ በሻቢያ የነፍስ አባትነት ትጥቅና ስንቁን አሳምሮ የትግራይን ህዝብ ለመከራ የዳረገው ወያኔ ነጻ አውጭ ሳይሆን ባርነትና መከራ አፍላቂ እንደሆነ ከራሱ ጉያ ያመለጡና አብረው ግፍን የፈጸሙ በይፋ ተናግረዋል። ከወርቃማው ህዝብ መወለዳቸውን የለፈፉት የቀድሞው ጠ/ሚ ከአሸለቡ ወዲህ ደግሞ ወያኔ በዚህም በዚያም ሲንቆራጠጥ ሳይታሰብ በኦነግ ተተክቶ ይኸው እንሆ የሆነው ሁሉ ሆኖና በመሆን ላይ ይገኛል። በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ተፍረክራኪ ታሪክ ውስጥ እንደ ወያኔ ያለ ሃገርን ገቢያ አውጥቶ የሚሸጥ አማራ ጠል መንግስት ተፈጥሮ አያውቅም። እርግጥ ነው ይህን ሬኮርድ ኦሮሞዎቹ ሊሰብሩት እየጣሩ ነው። ግፈኛን ሌላ ግፈኛ ሲተካው ቁጭ ብለን እያየን ነው።
ግን የአማራ ጥላቻ መሰረቱ ምንድን ነው? የአማራ ጥላቻ መሰረቱ የኢጣሊያን ወራሪዎችና የሃበሻ ተላላኪዎቻቸው የፈጠሩት የሃሰት ትርክት ነው። ይህን የሃሰት ትርክት እንደ ወረደ ለህዝቡ በቅድሚያ የጋተው ሻቢያ ነው። ዛሬ በህይወት ተርፈው በአውሮፓና በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የቀድሞ የሻቢያም ሆነ የሌሎች ተፋላሚ ሃይሎች የሚነግሩን የቱን ያህል ህዝቡን አማራ ጠላትህ ነው እያሉ በሃሰት ትርክት እንዳሰለጠኑት ይተነትናሉ። ያው እንደሚታወቀው የድርጅት ሚስጢር አናወጣም በማለት ብዙ ጉድ እያወቁ አፈር የተመለሰባቸው የሃበሻ ፓለቲከኞች እልፍ ናቸው። ዛሬ ላይ ቆመን ያለፈውንና አሁን የምናየውን የጥላቻና የዘር ጡሩንባ ስንመለከት ይህ ህዝብ በምንም መንገድ አያልፍለትም ብሎ መደምደም ይቻላል። ለውጥና ሽግግሩ ከክፋት ወደ ክፋት፤ አፍራሽን ሌላ አፍራሽ እየተካው እያየን ስለሆነ።
ወያኔ በራሱ የፓለቲካ እይታ የሰከረ፤ የሰው ስብዕና በውስጡ የሌለው አረመኔ ድርጅት ነው። የሚያሳዝነው ግን አሁንም አሁንም ለትግራይ ህዝብ ተዋግተን እያሉ ሲመጻደቁ መሰማቱ ነው። መብረቃዊ ጥቃት ፈጽመን ሰሜን እዝን ተቆጣጥረነዋል ያሉት ወያኔዎች ወረራ ነው የተደረገብን፤ የዘር ማጥፋት ነው የተፈጸመብን በማለት ለዓለም በተለይም ለአሜሪካ እሪታ ሲያሰሙ ተመድ በጉዳዪ 12 ጊዜ መሰብሰቡ የቱን ያህል ወያኔ ለአሜሪካ ተላላኪ እንደነበረ በግልጽ ያመለክታል። በሶስት ጊዜ ወረራው እልፍ ሰው ያስጨረሰውና የጨረሰው ወያኔ አስቀያሚና አጸያፊ ነገሮችን ፈጽሞ የበዳይ አልቃሽ በመሆን ለዓለም ኡኡታውን መልቀቁ የድርጅቱን መሰሪነት ያሳያል። የትግራይ ህዝብ ከመከራ ወደ ሌላ መከራ እየተራመደ በእነዚህ የሰው አውሬዎች ዛሬም ተጠፍሮ ይገኛል። ይህን ማየት የተሳነው አፍቃሪ ወያኔ የውጭና የሃገር ስብስብ ከአረመኔው ወያኔ የሚሻሉበት ምንም መንገድ የለም። ሰው ከእውነት ጋር ሲቆም ለራሱም ሰላም ይኖረዋል። እነዚህ በሃበሻ ምድር ዛሬ ላይ ብቅ ብቅ ባሉ የፓለቲካ ድርጅቶችም ሆነ በነባሮቹ ስር ተሰልፈው በሃሰት የሚወላገድ ሁሉ ዝናብ እንደ ሌለው ደመና ከንቱዎች ናቸው። ለህዝብ መቆም በዘርና በቋንቋ፤ በሃይማኖትና በክልል አያሰልፍም። በሰውነት ላይ ብቻ ተመርኩዞ ለሁሉም የሰው ልጆች መብት ይታገላል እንጂ። ግን በራፉ ላይ ቆሞ የክልሉን ባንዲራ እያውለበለበ ዓለሙ ሁሉ ይህ ነው ብሎ ለሚያስብ ጠባብ ብሄርተኛ ሃሳቡን የሚያስቀይር መድሃኒት አይገኝም።
ከወያኔ ላይ ስልጣኑን የነጠቀው የድህነቱ መንግስት ብልጽግና ይኸው እንሆ የወያኔ ጊንጦችን አቅፎ አማራ ላይ ሰፊ ጥቃት በማራመድ ላይ ይገኛል። ለዚህ ነው የሃበሻ ፓለቲካ የመገዳደል ፓለቲካ ነው የምለው። ትላንት በጨነቀው ጊዜ ድረሱልኝ፤ ማርካችሁ ታጠቁ ያለው የኦነግ መሪ ዛሬ ላይ ትጥቅ አስፈታለሁ ማለቱ ለአሜሪካ ታዛዥ ለመሆን እንደሆነ የፓለቲካ ተንታኞች ያመላክታሉ። በአንጻሩ ሰራዊቱ ላይ መኪና የነዳበት፤ ያን ሁሉ መከራ በአማራና በአፋር በሰሜን ሽዋ በሶስት ጊዜ ተደጋጋሚ ወረራ ይህ ነው የማይባል መከራ ያዘነበውን ወያኔን አቅፎ እሽሩሩ በማለት ላይ ይገኛል። አልፎ ተርፎም ሬቻን በቀይ ባህር እናከብራለን፤ አሰብን እናስመልሳለን እያሉ የጅል ወሬ ማውራት መጀመራቸው አሜሪካዊው ግፊት ጎልቶ መውጣቱን ያሳያል። ነጩ ዓለም እኛ ስንጋደል ደስ ይለዋል። ቁጥር ቅነሳ ነው። ያኔም ዛሬም ወደፊትም በእጅግ አዙርና በቀጥታም እንድንገዳደል ለማድረግ ስራ ፈትተው አያውቅም። ግን አንድ ነገር አንባቢ እንዲረዳ እፈልጋለሁ። የኢትዪጵያን መፈራረስ በገንዘብ፤ በወታደራዊ ትጥቅና ስልጠና ሻቢያን ከሻቢያ ከእርሱ በፊት የነበረውን ድርጅት፤ ወያኔን፤ ኦነግን ወዘተ የረድ ሃገሮች ዛሬ ላይ የሉም። ሶሪያ፤ ሊቢያ፤ ኢራቅ፤ የመን ወዘተ … ሰው የሌላውን ቤት ሲያፈርስና እሳት ሲያቀጣጥል ሳይታሰብ ዝንተ ዓለም ይቆማል የተባለው ህንጻም ይደረመሳል። ታሪክ የሚያሳየን ይሄን ነው። በሰው እንባ የሚስቁ፤ የነፍሰ ጡር ሴት ሆድ የሚቀድ፤ ቤት ዘግተው ሰውና እንስሳት ላይ እሳይ የሚያጋዪ የቁም እብዶችና የብሄር ታጋዪች ለእነርሱም ጊዜ እንደሚፋረዳቸው አይገባቸውም። የተሳከረ የዘርና የቋንቋ ፓለቲካ ጢምቢራቸውን ያዞራቸው እነዚህ የቁም ሙቶች ከአለፈው ስህተታቸው እንኳን ተምረው ህዝብን ለመካስ የሚያደርጉት አንድም የባህሪ ለውጥ የለም። ለዚህ ነው ትላንትም ዛሬን የሚመስለው። ለዚህ ነው የብልጽግናው መንግስትም ከወያኔ የማይሻለው። ጠ/ሚ አብይ አንድ መድረክ ላይ ሲናገሩ ” በአዲስ አበባ ኦሮሞ ጠል ሰዎች አሉ” ይህ አንዲትን ሃገር ከሚያስተዳድር መሪ የሚወጣ ቃል አልነበረም። ግን ያው ሊበሉ የፈለጉትን አሞራ ጅግራ ነው ይሏታል አይነት ሆነና እሱም በጊዜው የዘር ፓለቲካ መጫወቱ ነው። ግን ምን ቢዘላብድ ከጊዜ በትር ማምለጥ አይቻልም። ወያኔም ጊዜ እየቆጠረ እንጂ ጠ/ሚሩን መበቀሉ አይቀሬ ነው። ብቻ ተያይዞ ገደል ማለት የሃበሻ ፓለቲካ ነው። በቃኝ!