
ተሃድሶ ጥሩና መጥፎ ጎኖች አሉት። በተለይ ሥርነቀል አቢዮት በተለመደባት አገራችን ተሃድሶ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ያንን መዘርዘር ግን አሁን አስፈላጊ አይደለም። የዚህ ርዕሰ አንቀጽ ዓላማ በተሃድሶ ምክንያት እየደረሰ ያለውና መረን የለቀቀ ተግባር እርምጃ እንዲወሰድበት ለመጠቆም ነው።
ትህነግ ያላሰበውን ሥልጣን ተቆጣጦሮ አዲስ አበባ ሲገባና ካድሬዎቹ የዲዛይነር ልብስ መልበስ ሲጀምሩ የተበላሸው ጭንቅላታቸው ያው በበረሃው እሳቤ ነበር የቀጠለው። ከዓመታት በኋላ የድርጅቱን መበስበስ እንደማያውቅ ሆኖ ያስደነቀው ሊቀጳጳስ መለስ ዜናዊ “እስከ እንጥላችን ገምተናል” ነበር ያለው። የዘራውን እንደሚያጭድ አለማሰቡ ዕውቀት ጸዴ በረኸኛ መሆኑን በራሱ አስመስክሮበታል።
ያገኙትን ሁሉ መዝረፍ ሙያቸው አድርገው የተካኑት ትህነጋውያንና ኢህአዴጋውያን ሊቀ ደናቁርት ካድሬዎች በለውጥ ስም ልክ እንደ ማብሪያና ማጥፊያ ተገለበጡና ተደመሩ። አሰሱም ገሠሱም “ግሙም” ሁሉም አብሮ ተደመረ፣ ተደማመረ፣ ተቀየጠ። ሕዝብም ይሁን ይቅር ብለናል፤ ከተሻሻላችሁ ላገራችን ስንል እንቀበላለን ብሎ ማራቸው።
ሆድ እንጂ ጭንቅላት የሌለው ካድሬ ምንም ይሉኝታና ምህረት አያውቅም። ዘረፋው፣ ሌብነቱ፣ ዘረኝነቱ፣ ቅሚያው፣ ቀጠለ። ከንቲባ አዳነች በቅርቡ እንደተናገሩት በተዘረፈ መሬት ላይ ሕንጻ የሚሠሩ ገና መሠረት ሳይጥሉ እንዳይታገዱ አስቀድመው የፍርድቤት ማዘዣ ያወጣሉ። ከዚህ በኋላ እኔ ነኝ ያለ ወንድ ግንባታውን አያስቆማቸውም።
በአገራችን ላይ መረን የለቀቀው ሌብነት፣ ምዝበራና ንቅዘት አሁን በይቅርታ ዝም ተብለው ከኢህአዴግነት ወደ ብልጽግና የተገላበጡ ካድሬዎችና አዲስ በተደመሩ የለውጥ ተረኛ ዘራፊዎች የተቀናጀ ተግባር ነው። እነዚህ ካድሬዎች የሚያውቁትና ዋነኛ የነበረው ሥራቸው ዝርፊያ ነው። ዘርፈው የፓርቲያቸውን ኅልውና እስካስቀጠሉና ወጥተው እስከለፈለፉ እይነኬ ናቸው። ኢህአዴግም እስከ ዕንጥሉ በስብሶ ይዟቸው ቆየ። ያለ እነሱ ኅልውናው አደጋ ላይ የሚወድቅ እንዲመስለው ራሳቸው ካድሬዎቹ አሳምነውታልና።
ኃይለማርያም ደሳለኝ የአስፈጻሚውን ሥልጣን ሲቆጣጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው በአገሪቷ የተንሰራፋው ብለው ካቢኔያቸውን በዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች ሞሉት። በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን እንደመጨመር ሆነና ኢህአዴግ በለውጡ ተበላ። ከለውጥ ይልቅ ሥር ነቀል አቢዮት ቢደረገ ኖሮ ከነጻ እርምጃ እስከ እስር ይገባቸው የነበሩ ብዙዎቹ ተደምረው አመለጡ። አንዳንዶቹም እጅግ ዘግናኝና ሊታሰብ በማይችል ሁኔታ በአደባባይ የሚወገዱ ነበሩ። ካድሬ ግን ውለታ አያውቅም።
ባለንበት ወቅት ትህነግ የጫረው ጦርነት፣ የሸኔ ግፍ፣ የሲሚንቶ ዋጋ ያለ ምክንያት መናር፣ ከመጠን በላይ የደረሰው የኑሮ መወደድ፣ ጽንፈኝነት፣ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል ዓይነት ተረኝነት፣ የረቀቀ ሌብነት፣ ወዘተ የተነጣጠሉና ምንም ግንኙነት የሌላቸው ናቸው ብሎ የሚያስብ ወይ ራሱ ሌባ ካድሬ ነው፤ አለበለዚያ ገዳም የራቀው ንጹህ የእግዜር ሰው ነው።
“በስብሰናል፣ ገምተናል” እያለ እንደ ደህና ነገር በሚዲያ ሲያወራ የነበረው ትህነግ/ኢህአዴግ የተገረሰሰው በግፍ ብዛት ነው። በመልካም አስተዳደር ዕጦት ነው። ብልጽግናም ይህ የኅልውና አደጋ ፊትለፊቱ ተጋርጧል። “ኅብረተሰቡ ሙሰኞችን ያጋልጥ፣ ኅብረተሰቡ ይተባበር፣” ወዘተ የምትለው የካድሬ አዝማች እየተነሳ ያለውን ቁጣ የማያበርድበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
መንግሥት ከአናቱ ጀምሮ በየጉያው ሥር የተሸጎጡ ዘራፊዎችና ሌቦች እነማን እንደሆኑ ጠንቅቆ በማስረጃ ያውቃል። እዚህ እና እዚያ ጥቃቅንና አነስተኛ ጉቦ ተቀባዮችን እጅ ከፍንጅ ያዝኩ ብሎ ግዳይ እንደ ጣለ ጀግና በብሔራዊ ሚዲያ መለፈፍ የትም አያደርስም። ዓሣ መሸተት የሚጀምረው ካናቱ ነው እንዲባል ሌብነት የዕዝ ሠንሠለት አለው። ተዋረዱን ጠብቆ ካናት ነው እየተንቆረቆረ የሚወርደው፤ ስለዚህ ካናት መጀመር ነው አዋጪው።
ስለዚህ
- መንግሥት በሥሩ የተሰገሰጉትን እና “ብልጽግናችን” እያሉ ቀን ተሌት ሕዝቡን የሚያደነቁሩትን ካድሬዎች ያሰናብት፤
- በዘመነ ትህነግ በየሚዲያው ሲለፈልፉ ስናያቸው የነበሩ ደናቁርትን በጡረታም ይሁን በፈለገው መንገድ ከሥልጣን ያስወግድ፤
- በሚኒስትር ማዕረግ እያሉ ጠቅላይ ሚ/ር ጽሕፈት ቤት ማጎር ሳይሆን ሌቦችን ከሲስተሙ ጠራርጎ ያጽዳ፣
- በሌብነት ላይ የሚደረገው ዘመቻ መቀጣጫና ማስፈራሪያ እንዲሆን በካቢኔ ደረጃ ካሉ ታዋቂ ሌቦች ይጀመር፤
- የካድሬ አሠራርና ሹመት በሜሪት ይቀየር፤ እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው።
ብልጽግና ለራስህ ስትል ስማ። ይህንን ካላስተካከልህ እንደ ትህነግ ሩብ ክፍለ ዘመን ሳይሆን የምትቆየው “ሕዝብን ላገለግል ተመርጫለሁ” ለምትልበት የአምስት ዓመት ሩብ መድረስህን ቀልብህ ይንገርህ።
ትህነግ ሲያሾረው የነበረው ኢህአዴግ የተገረሰሰው በመልካም አስተዳደር ዕጦት ነው። ኮሮና ነው፣ ጦርነቱ ነው፣ ዓለም አቀፍ የኑሮ ውድነት ነው፣ የነዳጅ መወደድ ነው፣ ይሄ ነው፣ ያ ነው እያሉ በምክንያት መኖር ለትህነግም አልበጀውም። ያንተም መጻዒ ዕድል ከዚህ አይለይም። ነግረናል ቤት ይቃጠላል ብለናል ብላለች ሴትየዋ።
መደምደሚያ፤ ይህ ርዕሰ አንቀጽ ዋናው ሐሳቡ ኢህአዴግን ከተሃድሶው እንቅስቃሴ ጋር በማነጻጸር “ኢህአዴግ ማረኝ” ለማለት አይደለም። ትህነግንም ሆነ ኢህአዴግን የሚያስናፍቅ ምንም ነገር የለም። እንዲያውም ትውልድ የሚሻገር ውድመት በማምጣቱ መጪው ትውልድ ጠንቅቆ እንዲማርበትና ትህነጋዊ አስተሳሰብ ገና ሲያቆጠቁጥ እንዲቀጨው በየትምህርት ቤቱ በመጽሐፍ፣ በየቦታው በሐውልትና በየጊዜው በሚዲያ መነገር ያለበት ነው።
አሁን መከራ ለሆነብን ተቋማዊ ዝርፊያ ዓይን ያወጣ ሌብነት ዋናው ተጠያቂ ማን ሆነና ነው በንጽጽር “ትህነግ ማረኝ” የምንለው? ከዚህ ይልቅ አሁን በአመራር ላይ ያለው ኃይል የትህነግ/ኢህአዴግ ውላጅ በመሆኑ የሠራውን ግፍ ይቅር ብሎ ቀጥል ያለውንና ምሕረት ያደረገን ሕዝብ እየበደለ መሆኑ ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ዓይነት ነው። ሕዝብ ምሕረት ያደረገው የተሠራውን ስላላወቀ ሳይሆን ብልሕ ሆኖ ነው። ይቅርታ ያደረገን ሕዝብ ደግሞ ማታለልና ደግሞ ግፍ መሥራት የትም አያደርስም። ይቅርታ የተደረገበት ፋይል አልተቃጠለም፤ ይቅርታውን ለሚንቅ የበደሉን መዝገብ መምዘዝ ብዙ የሚከብድ አይደለም።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ™” አቋም ነው።
Leave a Reply