የተዛባ እና የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና ከዚያ በማትረፍ ሕዝብን ማደናገርና ሀገርን መበጥበጥ የገፊና ጎታች ሤራ ዋነኛ አካሄድ ነው። የአርሲው ትንሽ ጋብ ሲል ሰሞኑን ደግሞ የታርጋ ጫጫታ አየሩን ሞልቶታል። በተለይ እንደ ኤሊያስ መሠረት ያሉ ከሙያም፣ ከስብዕና እጅግ በጣም የወረዱ ሰዎች ለሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው የሚያሰራጩት መረጃ የብልጽግና ካድሬ እና የመንግሥት መዋቅሩ የተረዳው አይመስልም ወይም ሆን ብሎ እያገዛቸው ነው።
ለታርጋ ሃምሳ ስድስት ሺህ ብር እንዲከፍል ሕዝቡ ተገደደ፣ የአይ ኤም ኤፍ ስልታዊ የግብር ስብሰባ ሕዝቡን እያደኸየው ነው፤ እንደ ኬኒያ ሀገሪቱ ልትናወጥ ነው፤ ሆ ብሎ መነሳት አሁን ነው፤ የግፍ አገዛዝ ገመዱን እያጠበቀው ነው፤ በየማኅበራዊ ሚዲያ የሚታየው ጭስ ይህ ነው።
አይ ኤም ኤፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ ብድር ለመፍቀድ እና በፊት ከነበረችበት የዕዳ አዘቅት እያገገመች መሆኗን ተረድተው ተገቢውን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ወደ ውሳኔ እየደረሱ ነው። እንደ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ቅዱስና ለሕዝብ የሚያስብ የመላዕክት ስብስብ ነው የሚል ተላላ የለም። ግን ይህንኑ ተቋም በጥንቃቄ መጠቀምና የሀገርን ጥቅም ማስከበር ይቻላል።
እነ አይ ኤም ኤፍ ብድር ሲከለክሉ አየሩን የሚሞላው ወሬ ሲፈቅዱ ግን የለም። ከነዚህ ዓይነት ተቋማት ጋር የሚደረግ ድርድር ያለ ውጤት ሲበተን ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው፤ ምዕራባውያን ፊት አዞሩባት፣ ወዘተ የሚሉት እንደ ኤሊያስ ዓይነቶች የዜና ቁራጭ አስነብበው ለተቀረው ብር ክፈሉ የሚሉ ከሰውነት ተራ የወጡ ስግብግቦች መሪ ዜና ነው።
ለነገሩ በወያኔም ጊዜ መንግሥትን እቃወም ነበር ብሎ በኃይለማርያም ደሳለኝ ዘመን ለፈረንጅ አለቆቹ የላከውን ሃያ ተመሳሳይና የተዘገበ ዜና እንደ ማስረጃ ከሚጠቅስ እንደ ኤሊያስ ዓይነቱ ከዚህ የበለጠ አይጠበቅም። ይልቁንስ ከወያኔዎች ጋር በብዙ መልኩ በመመሳጠር ከእነ ሔኖክ ሰማእግዜር ጋር ቡድን መሥርቶ ከስብዕና የወረደ ተግባር ውስጥ መግባቱ ምናልባትም ካገሩ እንዲወጣ ያደረገው መሆኑን ለሚያውቁ ዝም ያልነው ልጆችህንና እናታቸውን አክብረን ነው ማለታቸው ተደብቆ እንደማይቀር ማሳያ ነው። ከነጭ ጋር እየሠሩ “ነጻ ምሳ የለም”።
ወደ ጉዳዩ ስንመለስ … አሁን ላይ አይ ኤም ኤፍ ብር እንደሚሰጥ ሲሰማ ማክሸፊያውን በተገኘው አጋጣሚ መፈለግ እንደ ካድሬ ሆድ እንጂ ጭንቅላት የሌላቸው ጸረ ኢትዮጵያ ግለሰቦች ራስ ምታት ነው። ለዚህ ደግሞ የተገኘው ጥሩ መረጃ የታርጋው ዋጋ ነው። ታርጋ ስልሳ ሺህ ብር ሆነ የሚለው መረጃ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለዓመፅ የሚያነሳሳው ይመስል ሕዝቡ ተቆጥቷል፤ መንግሥት የሚቀጥለው ዓመት ከግብር አንድ ትሪሊዮን እሰበስባለሁ ብሏል፤ አሁኑኑ ጀመረው፤ ይህንን ሥርዓት በቃ ልንለው ይገባል፤ ወዘተ እያሉና እያስባሉ ነው። ሌላ አጀንዳ እስኪያገኙ መቆያ መሆኑ ነው።
ሕዝብ ሊያውቀው የሚገባ ጥሬ መረጃ
በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው መቶ ሰላሳ ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ አጠቃላይ ያለው መኪና ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን አይበልጥም። ይህ ማለት የቤት፣ የመንግሥት፣ የንግድ፣ ባለ ሁለት እግር፣ ባለ ሦስት እግር ወዘተ ሁሉንም ጨምሮ ነው። በዚህ ስሌት መሠረት ኢትዮጵያ ከዓለም በመኪና ብዛት እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከሚባሉት አስር ሀገራት ውስጥ ነው የምትመደበው። ማለትም ከአንድ ሺህ ሰው ውስጥ ከአምስት እስከ ሰባት አካባቢ ሰው ነው መኪና ያለው።
ይህንኑ ስሌት ወደ ኬኒያ ብንወስደው ከአንድ ሺህ ሰው ውስጥ ከሠላሳ በላይ ሰው በኬኒያ መኪና አለው። በአፍሪካ ከሺህ ሰው ወደ ስልሳ የሚሆነው መኪና አለው። በዓለም ደግሞ ከሺህ ሰው ውስጥ ወደ ሁለት መቶ አስር አካባቢ ሰው መኪና ሲኖረው እነ ኤሊያስ ሊያነጻጽሩት የፈለጓትን አሜሪካንን ስንመለከት ከሺህ አሜሪካውያን ውስጥ ወደ ዘጠኝ መቶ የሚሆን ሰው መኪና አለው።
ወደ ሀገራችን ስንመለስ፤ ከላይ ከተጠቀሰው የመኪና ቁጥር ውስጥ ስድሳ አምስት በመቶ የሚሆነው የመንገደኛ የሚባል ሲሆን ከዚሁ ውስጥ ደግሞ ግማሽ ያህሉ ባለ ሁለት እግር (ሞተር ሳይክል) እና ባለ ሦስት እግር (ባጃጅ) ናቸው። የመኪናውን ስብጥር ስንመለከት ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ ካለው መኪና ግማሽ ያህሉ የሚገኘው በአዲስ አበባ አካባቢ ነው። ለዚህ ነው አዲስ አበባ አካባቢ ያለ ሰው በሀገሪቱ እጅግ ብዙ መኪና ያለ የሚመስለው።
ከላይ ከተጠቀሰው አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን መኪና ውስጥ ወደ ሦስት መቶ ሺህ የሚሆነው ነው የግል መኪና የሚባለው፤ ከአጠቃላዩ ሕዝብ ነጥብ ሁለት በመቶ (0.2%) ማለት ነው። እነዚህ የግል መኪናዎች ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ (ዘጠና በመቶው) የሚገኙት በአዲስ አበባ ነው። አሁንም ሰዉ ሁሉ ባለመኪና የሚመስለን አዲስ አበባ ላይ የሀገሪቱን መኪና ክምችት ስለምናይ ነው። ዋጋው ትክክልና ተመጣጣኝ ነው ባይባልም ከነዚህ ነው እንግዲህ ስልሳ ሺህ ብር የታርጋ የተጠየቀው። እና ይህ ጥያቄ ነው መንግሥት እስከማስቀየር የሚደርስ የሕዝብ ነውጥ የሚቀሰቅሰው።
ይህንን ነው እንግዲህ ሦስት መቶ ሚሊዮን መኪና ካላት አሜሪካ ጋር እነ ኤሊያስ ሊያነጻጽሩ የሚፈልጉት። የአሜሪካ ሕዝብ ብዛት ሦስት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ነው። አንድ መኪና ላንድ ሰው ቢባል በአሜሪካ መኪና የሌለው ሰው ሃምሳ ሚሊዮን ነው ማለት ነው። ለንጽጽር፤ ኢትዮጵያ አሁን አላት ከሚባለው መቶ ሠላሳ ሚሊዮን ሕዝብ መኪና የሌለው መቶ ሃያ ስምንት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ነው።
እንግዲህ ከሀገራችን ሕዝብ 0.2 በመቶ እንኳን የማይሆነው ሕዝብ የታርጋ ዋጋ ተወደደብኝ ብሎ ለዓመፅ የሚነሳው፤ በቃኝ የግፍ አገዛዘ የሚለው እና ሥርዓቱን አስወግዶ የሽግግር መንግሥት የሚመሠርተው። ይሄ ነው እንግዲህ ወደ አራት ኪሎ የሚወስደው ሕዝብን የማታገያ አጀንዳ።
ታርጋው መቀየሩ በጣም አስፈላጊና መሆን የሚገባው ነው። በተለይ ሕዝባችንን ለዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ እንዲሁም የአስተሳሰብ ዝቅጠት የዳረገው እንደ መዥገር ለሰላሳ ዓመት የተጣበቀን የወያኔ አገዛዝ ታርጋን እንኳን ሳይቀር ዘረኛና ጎጠኛ አድርጎ ነበር። ታርጋ መቀየሩ ዋናው አጀንዳ መሆኑ ቀርቶ የመንግሥት ኃላፊዎች ባሳዩት ንዝህላልነት አጀንዳው ሌላ ሆነ። ግንቦት ሃያ የሚባል የቀን መቁጠሪያ ላይ መሰረዝ የሚገባውን ቀን ያስቀረና አሁን ደግሞ በዚያው ልክ ሊያስወድሰው የሚገባውን የታርጋ መቀየር አሠራር የጀመረው አካሄድ ሙሰኞችና በሁለት ቢላ የሚበሉ ባንዳዎች አጀንዳውን አሳልፈው ሰጡት።
በምንም መሥፈርት ስልሳ ሺህ ብር ለታርጋ ተገቢ ወጪ ነው ሊባል አይችልም። ታርጋውን እንዲሠራ ኮንትራት የተሰጠው አካልና በመካከል ከዚህ የሚጠቀሙ ሆድአደር ባለሥልጣንናትና ካድሬዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ መመርመር አለበት። ታርጋ እንዲሠራ ከወጣው ጨረታ ጀምሮ ያለው ሒደት ሊጣራና ይፋ ሊደረግ ይገባል። ለአንድ ታርጋ ይህንን ያህል ብር ለምንድነው የሚከፈለው የሚለው በግልጽ መታወቅ አለበት።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሠራሩን በማዘመንና ቪዛና መሰል ጉዳዮችን በኤሌክትሮኒክ መንገድ ለመፈጸም በተደረገው ውሳኔ ከበላይ አመራር ጀምሮ እንዴት ያለ ምዝበራ እንደተካሄደ ይፋ ያልወጣ ጉዳይ ነው። የጨረታው ሒደት ላይ የተደረገው ማጭበርበር፤ ከዚያም በኋላ የተፈጸሙ ውንብድናዎችና የሌብነት ተግባራት በታርጋው አሠራርም ላይ ለመፈጸሙ ብዙ ጠቋሚዎች አሉ። የመንግሥትና የፓርቲ አሠራር በትልቁ ተሰምሮ እስካልተያየ ድረስ ይህንን መሰሉ ዝርፊያና ሌብነት የሚፈጽሙ ካድሬዎችና የመንግሥት ሹመኞች መኖራቸው የማያቆም ነው። ይህ ደግሞ ሕዝቡን ስለሚያስመርረው ውሻ በቀደደበት ለመግባት የሚፈልጉ ያሰፈሰፉ ጅቦች የሁልጊዜ ተስፋ ሆኖ ይቀጥላል።
“ሞላ ጎደለ” እያሉ በታርጋ የሚጫወቱ ልጆቻችን ሳይቀሩ ስነልቦናቸው ተሰልቦ፣ ዘረኛ እና ጠባብ ሆነው እንዲያድጉ በወያኔ ሆን ተብሎ የተፈጠረው ታርጋ ወደ ግብዓተ መሬት በመውረዱ ሀገር እልል ማለት ይገባታል። አጀንዳው መሆን የነበረበት ይህ ነው። እያንዳንዱ ወያኔ የተከለው መርዝ እንዲህ እየተነቀለ ሀገር ከርኩሰቷ መንጻትና መፈወስ አለባት። በመንግሥት አሠራር ውስጥ የተሰገሰጉት ከላይ ጀምሮ ያሉትን ሙሰኛ (ሌባ) የፓርቲ ሰዎችና ካድሬዎች ላይ ቀጥተኛ የማጋለጥና ተገቢውን ቅጣት የመበየን ሥራ ካልተሠራ ስቃያችን ይረዝማል፤ ዞረውም ለራሱ ለመንግሥት ኅልውና አደጋ መሆናቸው የማይቀር ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ


Leave a Reply