* ሚስጥረ፤ “ወደ ምርጫው የገባኹት አምኜበት አይደለም”
የኢህአፓና የትብብሩ ዋና ጸሐፊ የሆነችው ሚስጥረሥላሴ ታምራት ከአዲስ ኢንሳይደር ጋር ባደረገችው ውይይት ወደ ምርጫው የገባችው አምናበት እንዳልሆነ ተናገረች። ትብብሩ የተከፋፈለ መሆኑን ያልካደችው ሚስጥረ የአውሮጳ ኅብረትና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ምርጫውን አስመልክቶ የሰጡት መግለጫ “ለእኛ” ከነገሩን ጋር የተለያየ ነው በማለት ኅብረቱ የሐሰት መግለጫ እንዳወጣ እንደምታ የሚሰጥ አስተያየት ሰጥታለች።
ከምርጫው በፊት ቅድመ ሁኔታ እንዳስቀመጡና እነዚያ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ወደ ምርጫ መግባታቸውን በተመለከተ ስትመልስ እንዲህ ብላለች፤ “ወደ ሰባት የሚሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠን እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ የሚደረግ ምርጫ አምባገንነትን ነው እንጂ የሚያዋልደው በፍጹም የዲሞክራሲ መገለጫ ሊሆን አይችልም በሚል … ወደ ምርጫ እስከ አለመግባት የሚያደርሱ የፖለቲካ ውሳኔዎችን እንወስናለን ብለን ተናግረን ነበረ። … ነገር ግን በድጋሚ የመጨረሻ ውሳኔውን ለመወሰን በተደረገው ስብሰባ ላይ በአብላጫ ድምጽ በምርጫ ውስጥ ተሳትፈን በሒደቱ ውስጥ ስናጋለጥ እንደቆየነው ሁሉ ምርጫውንም ከውስጥ ሆነን ነው ማጋለጥ ያለብን እና እንዲሁ የድርጅት ደኅንነትን ከማስጠበቅ አንጻር … በምርጫ ሒደት ውስጥ መቀጠል አለብን በሚል በአብላጫ ድምጽ የተወሰነበት ሁኔታ ነው ያለው” ብላለች።
እርሷ በግሏ በሒደቱ ሳታምንበትና ፓርላማ መግባትን ሳትፈልገው ለምን በዕጩነት እንደቀጠለች ለተጠየቀችው የሰጠችው ምክንያት፦ “እኔ እዚህ ምርጫ ውስጥ የገባሁት አምኜበት አይደለም፤ ከመጀመሪያውም ጀምሮ … ለአብላጫ ድምጽ ተገዝቼ ነው። ግን አንዳንድ ነገሮች ደግሞ እስከዚህ ድረስ ነው የሚሄደው፣ እስከዚህ ድረስ ነው የምገዛው የምትላቸው ነገሮች አሉ። ለኔ ፓርላማ ውስጥ መግባት ኦፕሽን (አማራጭ) አይደለም፤ በፖለቲካ ሕይወቴ ውስጥ ላደርገው የምፈልገው ነገር አይደለም። … በዚህ ምርጫ ስቀጥልም ለአብላጫው ድምጽ ተገዝቼ በዚህ ውስጥ ብቀጥልም፣ በኋላ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን እዛ ውስጥ ግን መግባት አልችልም፣ አልፈልግም፤ ይሄ የኔ ውሳኔ ነው” በማለት የተናገረችው ለራሷም ባይገባት ግን ቃላት ደርድራ አምልጣለች። አንድ ፖለቲከኛ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ወደ ፓርላማ አልገባም ብሎ አስቀድሞ ከወሰነ ሌላ ያልታወቀ ጥቅም ከሌለው በስተቀር ለምን ይህንን ያህል የምርጫን መንገድ ይጓዛል?
መንግሥት ለመመሥረት የሚያበቃ ተወዳዳሪ ያላቀረበው ትብብር ተሳክቶለት ሁሉም ዕጩዎቹ ቢመረጡ እንኳ መንግሥት መረከብ አይችልም። በምርጫ ክርክር ወቅት ግን “ምርጫውን አሸንፈን መንግሥት ስንመሠርት ይህንን እናደርጋለን ያንን እንፈጽማለን” እያሉ የሐሰት ተስፋ ሲገቡ እንደነበር ሕዝብ የሰማቸው አይመስላቸውም። ለሕዝብ ያላቸው ንቀት ወደር የሌለው ሆኖ ስለ ሕዝብ ሰላምና ነጻነት በአደባባይ ማውራታቸው ለሰሚያቸው እጅግ የሚያሳፍሩ ናቸው። ይልቅስ የሚቀርብላቸው ጥያቄ ይህንን ሁሉ እያወቃችሁ ለምን በምርጫ ተወዳደራችሁ የሚለው ነው። ለዚህም መናገር ከዝምታ የተሻለ ተደማጭነት ያስገኛል ብላ ያመነችው ሚስጥረ “መልስ” ነው ያለችውን ተናግራለች።
ምርጫው ሕጋዊ አይደለም እያሉ፤ እንዲያውም ምርጫው ብቻ ሳይሆን ሒደቱም የተጭበረበረ ነው እያሉ የኢህአፓም ሆነ የትብብሩ ሰዎች በምርጫው ግን ተሳትፈዋል፤ መመረጣቸውን አናውቅም እንጂ መርጠዋል። ሚስጥረም ስትመርጥ ፎቶ እንዳትነሳ ብትለምንም እና ብታስፈራራም ተደብቃ የሰጠችው ድምፅ በፎቶ ማስረጃ ቀርቦባታል። ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ “የጨረባ ምርጫ” ነው በማለት እሷና ጓደኞቿ መግለጫ አወጡ። በመግለጫቸውም ምናልባት የተመረጡ ዕጩዎች እንኳን ቢኖሩ ወደ ፓርላማ መግባት የለባቸውም በማለት እንደ ካህን ውጉዝ ከመአርዮስ ብለው ፖለቲካዊ ግዝት ገዘቱ።
ይህንን አስመልክቶ ሚስጥረ ለራሷም ያልገባትን ምላሽ እንዲህ ብላ ሰጥታለች፤ “ትክክለኛ ምርጫ አልተካሄደም እያልን፣ ትክክለኛ ባልሆነ ምርጫ እና የጨረባ ምርጫ ብለን በገለጽነው ሂደት በተመሠረተ ፓርላማ ውስጥ መግባት ማለት ፓርላማው በትክክልም በሕጋዊ ሂደት ነው የተመሠረተው የሚል ኢምፕሊኬሽን (ትርጉም) አለው (ሌጂትሜት ይሆናል)፤ እና እኛ ያ እምነት የለንም። ስለዚህ እምነታችን ካልሆነው በተቃራኒ ደግሞ ቆመን አባላቶቻችን የተመረጠው ፓርላማ ውስጥ ይግቡ የምንልበት እንትኑ የለንም” ብላለች – “እንትኑ” ምን እንደሆነ ግን አልተናገረችም።
በዚህ ምላሽዋ ሚስጥረ ሳታስበው ከባድ መረጃ ነው ያወጣችው። ኢህአፓ ከዳያስፖራው ጽንፈኛ ጋር በጥምረት (ጽምዶ) ሲሠራ ነው የሰነበተው። ለኢህአፓ የተሰጠው የቤት ሥራም በትብብሩ ውስጥ የበላይ አመራሩን እንዲይዝና ትብብሩን ወደተፈለገው የፖለቲካ መጠቀሚያነት እንዲቀይር ነው። ለዚህ ነው የመኢአድና የሌሎቹ ፓርቲ ሰዎች በትብብሩ ውስጥ ጎልተው የማይታዩት፤ ምክንያቱም ኢህአፓ እነ ነአምን ዘለቀ ከሻዕቢያ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በሀገር ውስጥ የሚያስፈጽም ነው፤ ይህም ተልዕኮ ምርጫውን ሕገወጥ ወይም “ዲሊጂቲማይዝ” ማድረግ ነው።
ታዲያ በጽንፈኛ የዳያስፖራ ስብሰባዎች በዙም (Zoom) ስብሰባዎች ስትካፈል የኖረችው ሚስጥረም ፓርላማ እንደማይገቡና ምርጫው “የጨረባ ነው” እያሉ ለምን እንደተሳተፉ ለተጠየቀችው የመለሰችው “ትክክለኛ ባልሆነ ምርጫ እና የጨረባ ምርጫ ብለን በገለጽነው ሒደት ውስጥ በተመሠረተ ፓርላማ መግባት ማለት ፓርላማው በትክክልም በሕጋዊ (በሌጂትሜት) ሒደት ነው የተመሠረተው የሚል ኢምፕሊኬሽን (ትርጉም) አለው” በማለት ነበር። ሻዕቢያው ነአምን ዘለቀ በኢህአፓዋ ሚስጥረ አፍ ይህንን ይመስላል!
ሚስጥረና ኢህአፓዎች ከነአምን የተሰጣቸው ተልዕኮ ምርጫውን እንሳተፋለን ብለው ይመዘገባሉ፤ ቅስቀሳ ያካሂዳሉ፤ በምርጫ ወቅት ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በየሚዲያው እየወጡ ምርጫውን ያንቋሽሻሉ፤ ከዚያም በዚህ መልኩ እስከ መጨረሻው ይቀጥሉና ልክ ምርጫው ሊሆን ጥቂት ቀናት ሲቀር ከምርጫው ራሳቸውን በማግለል የሚዲያውን አየር ይሞሉታል፤ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብና ሚዲያው ደግሞ “ተቃዋሚዎች ያልተሳተፉበት ምርጫ” በማለት ይደሰኩራሉ፤ ምርጫውም፣ ውጤቱም ሕገወጥ (ዲሌጂቲማይዝድ) ይሆናል ከዚያ የሽግግር መንግሥት ይመሠረታል። ይህ ነው እንግዲህ ጸጉር ዓልባ በሆነው ጭንቅላቱ ነአምን ዘለቀ ያሰበውና አጀንዳ አድርጎ ለነሚስጥረ ያደለው። እነ ሚስጥረ/ትብብሩ ከዳያስፖራው “ለሥራ ማካሄጃ” ተብሎ ዳጎስ ያለ ዶላር ተልኮላቸዋል። ከሀገር ውስጥ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ውድድር የሚውል እንዲሁ ብር ለግሷቸዋል። ከሁለት የበሉ ሆነው መጨረሻ ላይ ማጣፊው ወዳጅ አልባ አደረጋቸው።
በሕጉ መሠረት አንድ ፓርቲ ከምርጫው ራሱን የሚያገልለው ከምርጫው አንድ ወር በፊት ነው። ከዚያ በኋላ ከምርጫ ልውጣ የሚል ፓርቲ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ብር መመለስ አለበት። እነ ሚስጥረ ደግሞ ከወር በፊት ሚያዚያ 24 ቀን 2018ዓም ተሰብስበው ሳለ “በምርጫው እንሳተፍ” የሚለው ድምፅ በዝቶ ሳይወዱ በግድ በምርጫ እንዲገቡ ሆነ። እነ ሚስጥረ ለዳያስፖራው እና ለነአምን ግን “አይዟችሁ ለምርጫው ሦስት ቀን ሲቀር ጉድ ነው የምናደርጋቸው” ብለው የሰጡትን ተስፋ በምርጫ ጣቢያ ሔደው በመምረጥ ፈጸሙት። ዳያስፖራው የተገባለት ተስፋ እውን ሳይሆን እንዲያውም ሚስጥረ ድምፅ ስትሰጥ የተነሳችውን ፎቶ ሲያይ በየሚዲያው እየጠራ የስድብ ናዳ አወረደባቸው፤ ሁኔታው ሲያስደነግጣቸው ትንሽ ለማለሳለስ ብለው “የጨረባ ምርጫ ነው፤ የተወዳደራችሁ ብታሸንፉም ፓርላማ አትገቡም” ብለው ቄሳራዊ መግለጫ አወጡ።
በቃለ ምልልሱ የሚስጥረ ምላሽ ግራ ያጋባው ጠያቂ፤ “ብትመረጡም ፓርላማ አትግቡ ማለት ሕዝብን መናቅ እና እኛ የተሻለ እናውቃለን ማለት አይሆንም? ሕዝብ ድምፅ እየሰጣችሁ እንዴት ነው ድምፅህን አንቀበልም የምትሉት?” በማለት ለጠየቀው ቃላት መደርደር የማይሳናት ሚስጥረ ስትመልስ፤ “አሁን ላይ ፓርላማ ገብቶ ድምፅ ማሰማት የሚለው ብዙ ውሃ የሚያነሳ መከራከሪያ ነው ብዬ አላምንም እኔ በግሌ … ፓርላማ ውስጥ ገብቶ ሕዝብ እንደዚህ እየሆነ ነው ማለት ብቻ ለውጥ ያመጣል ብለን አናምንም፤ ስለዚህ የሎንግ ተርሙን (የረጅም ጊዜውን) በማየት ነው ይሄን ውሳኔ የወሰንነው” ብላለች። የፓርላማ ዋና ሥራ ታዲያ ምን ሆነና? የሕዝብን ብሶት ማሰማት አይደል?
ለምን በግልሽ ከምርጫው አልወጣሽም ስትባል ለአብላጫ ድምፅ ተገዝቼ ወደ ምርጫ ገባሁ ያለችው ሚስጥረ፤ ፓርቲው እንኳን ወደ ፓርላማ እንግባ ብሎ ቢወስን አልገባም ነው ያለችው። እነዚህ ሁለቱ አባባሎች መሠረታዊ የሆነ ተቃርኖ ያላቸውና አንዳች አመክንዮ የሌላቸው ናቸው። በአንድ በኩል የድርጅቱን የአብላጫ ድምፅ መርህ አከብራለሁ ብላ ሳታምንበት በምርጫው እስከመጨረሻው እየተወዳደረች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ድምፅ ሰጥቶ ቢመርጣት እንኳ የድርጅቱን መርህ ጥሳ ፓርላማ እንደማትገባ መናገሯ ለጤንነቷ እንድናስብ የሚያደርግ ነው።

መደነቅ ያላቆመው ጋዜጠኛ ምናልባት በዚህ ይሳካልኛል ብሎ “የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ አንዳንዶች ምርጫው በጥሩ ሁኔታ ተከናውኗል የሚል መግለጫ አውጥተዋል፣ ለነሱ ምን ትላላችሁ?” ብሎ ለጠየቃት ጥያቄ፣ የአውሮፓ ኅብረት መግለጫ “እንኳን ደስ አላችሁ” የሚል እንዳልሆነ ለመከላከል ስትሞክር እንዲህ ብላለች፦ “ለኛ ያሉን ሌላ ነው፤ እነሱ ያሉት ምርጫው ተካሂዷል … ምርጫው ተከናውኗል፣ አልፏል የሚል ደግሞ ዓይነት መግለጫ ነው ያወጡት። ለነሱም በትክክል ያለው ሁኔታ ምን እንደሆነ ስንገልጽላቸው፤ እኛ ኮንግራጁሌሽን አላልንም፣ ያልነው ምርጫው ተካሂዷል፤ ጥልቅ ግምገማችንን ከዚህ በኋላ በሚቀጥሉት ጊዜያት ነው የምናሳውቀው ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው” በማለት ኅብረቱ በይፋ ያወጣውን መግለጫ ክዳለች።
ሚስጥረ ብዙ ምስጢራዊ አካሄዶች ያሏ “ድንቅ” ሴት ነች። በቃለ ምልልሷ ወቅት ይኼኛው ምርጫ በወያኔ ጊዜ ከተካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ የባሰ የዘቀጠና በጣም የወረደ ነው ብላ ገልጻዋለች። ለዚህ አንዱ ምክንያት ብላ ያነሳችው የሚዲያ ነጻነት አለመኖርን ነው። ጋዜጠኞች ምንም ነጻነት የሌላቸው መሆኑን የገለጸችው የኢህአፓ እና የትብብሩ ዋና ጸሐፊ፤ ጋዜጠኞች እንደፈለጉ መዘገብ አይችሉም፤ በውስን ነጻነት እንዘግብ የሚሉት ደግሞ ለእስርና ለእንግልት ተዳርገዋል ብላለች።
ጎልጉል በማስረጃ ማረጋገጥ የሚችለው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሚስጥረ ሀገር አቋርጣ እነ መሳይ ዩትዩብ ላይ ስትወጣ ሀገር ውስጥ ያለ ሚዲያ ዜና ለማመጣጠን እና የትብብሩንም አቋም በዜናው ላይ ለመግለጽ ቃለ ምልልስ እናድርግ ብሎ በተደጋጋሚ ሲገልጽላት በመጀመሪያ የጠየቀችው የሚዲያውን ድረገጽ ነበር። ከዚያም ቆየት ብላ የኛን አቋም የሚያንጸባርቅ፤ እኛን የሚደግፍ ሚዲያ አይደለም፤ ጤናማ ሚዲያ ስላልሆነ ከናንተ ጋር ለመነጋገር እና ሃሳባችንን ለማጋራት አንችልም የሚል ምላሽ ነው የሰጠችው።
ትብብር፣ ኢህአፓ፣ ሚስጥረ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው። ትብብሩ በሕጉ መሠረት ምርጫው ከተካሄደ በኋላ ከስሟል። ኢህአፓ ተሰንጥቋ፤ በቅርቡ ለሁለት ተከፍሎ አባላቱም ይበታተናሉ። ሚስጥረና አብረዋት ያሉት የኢህአፓና የእናት ፓርቲው ጌትነት አይነቶች መንግሥትን እናዋርዳለን፤ እናጋልጣለን፤ “ምርጫውን ሕገወጥ (ዲሌጂቲማይዝ) እናደርጋለን” የሚል ተስፋ ለዳያስፖራው ሸጠው ሻዕቢያ በነአምን በኩል የላከላቸውን ብር በልተዋል። ምርጫ እንወዳደራለን ብለው ከምርጫ ቦርድም በልተዋል። ይህም በሀገር ውስጥም ይሁን በውጪ ያለው ሕዝብ በነሚስጥረ ላይ እጅግ ከፍተኛ ምሬት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፤ ተክደናል እያለ፤ በየማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የሚጻፈው እጅግ የሚያስደነግጥ ነው።
የትብብሩ ቁመና፤ የኢህአፓ ቀጣይ አካሄድና የሚስጥረን የወደፊት የፖለቲካ ሕይወት መገለጽ የሚቻለው በአመክንዮ፣ በውይይት፣ በቃለ ምልልስ ሳይሆን በሌሊት ወፏ ታሪክ ብቻ ነው።
በጥንት ዘመን በምድር እንስሳት (አራት እግር ባላቸው) እና በሰማይ አእዋፍ (ክንፍ ባላቸው) መካከል አለመግባባት ተከስቶ ትልቅ ጦርነት ይነሳል። ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸውን ሠራዊትና አጋዥ ማሰባሰብ ይጀምራሉ። ይህንን ያስተዋለችው የሌሊት ወፍ፣ ወደ አእዋፍ ዘንድ ትሄድና ክንፎቿን እያሳየች፦ “እኔ እኮ ክንፍ አለኝ፣ ከእናንተ ወገን ነኝ! በጥሩ ቀን እረዳችኋለሁ፣ ጠላቶቻችሁን እበቀልላችኋለሁ” እያለች ከአእዋፍ ወገን ከፍተኛ ድጋፍ፣ ክብርና ስንቅ (ጥቅማጥቅም) ትቀበላለች።
በሌላ በኩል ደግሞ ተዓምረኛዋ የሌሊት ወፍ ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ ወደ ምድር እንስሳት ዘንድ ትሄድና ጥርሶቿንና ፊቷን እያሳየች፦ “እኔ እኮ እንደ እናንተ ነኝ፣ ጥርስ አለኝ፣ እንደ እናንተ አራት እግር ባይኖረኝም አጥቢ ነኝ፤ ከእናንተኮ ወገን ነኝ! አእዋፍን እነሱን መስዬ እስከመጨረሻው ከነሱ ጋር አስመስዬ መጨረሻ ላይ ጉድ ነው የምሠራቸው” እያለች ከምድር እንስሳትም እንዲሁ በውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ድጋፍና ጥቅማጥቅም ትሰበስባለች።
የሌሊት ወፍ ከሁለቱም ወገኖች የምታገኘውን ጥቅም ብቻ እየሰበሰበች፣ እውነተኛው የውሳኔ ቀን (የጦርነቱ ዕለት) ሲቃረብ ውግንናዋን በገሃድ ታሳያለች ስትባል ለማንም ሳትሰለፍ በስተጀርባ ትደበቃለች። ከዲያስፖራውም ሆነ ከመንግስት (ከምርጫ ቦርድ) ገንዘብ ወስዶ፣ መጨረሻ ላይ “እኛ ለመሸነፍም ለማሸነፍም አይደለም የገባነው፣ ለማጋለጥ ነው” እያሉ ሁለቱንም ወገን ምንም ሳይጠቅሙ መሃል ላይ እንደቀሩት እንደነሚስጥረ ማለት ነው።
በመጨረሻም፣ ሁለቱ ወገኖች (እንስሳትና አእዋፍ) ተነጋግረው እርቅ ሲያወርዱ የሌሊት ወፍ ሤራ ይገለጣል። አእዋፍም እንስሳትም ያታለቻቸውን የሌሊት ወፍ መሆኗን ሲያውቁ አምርረው ተጸየፏት፤ አገለሏት። ከሁለቱም ወገን “ብሯን” በልታ ለአንዱም ታማኝ ባለመሆኗ፣ በቀን ብርሃን እንዳትወጣ፤ በሌሊት ብቻ እንድትንቀሳቀስ ተወገዘች። ከዚያ ቀን ጀምሮም ስሟ “የሌሊት ወፍ” ተባለ፤ በቀን ብርሃን ማንነቷ እንዳይታወቅ ተደብቃ፣ በጨለማ ብቻ ለሆዷ የምትንቀሳቀስ ፍጥረት ሆነች።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ


Leave a Reply