ራሱን የትግራይ ነጻ አውጪ ግምባር (ትህነግ) በማለት የሚጠራው ሕገወጥ የወንበዴዎች ቡድን ተክሎብን እና ጥሎብን የኼደው መርዝ እስካኹን አልፋታ ብሎን የመከራ ዘመናችንን አርዝሞታል። ሀገርን በዘር ከፋፍሎ፤ ሕዝብን እንደ ከብት በክልል ወስኖ፤ ኢትዮጵያዊነትን በሰፈርና በወንዝ ወስኖ፤ ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ በጠላትነት እንዲተያይ አድርጓል። እንዳሰበው ባይሳካለትም ሀገራችን ከመፍረስ ድና አኹን ያለችበት ቁመና ላይ ትገኛለች። ትህነግ ግን ነጻ አወጣዋለኹ ብሎ ሲነግድበት የነበረውን ሕዝብ የምድር ሲዖል ውስጥ ጨምሮ እያሰቃየው ይገኛል።
ወደ ጉዳያችን ስንመለስ፤ ትህነግ መርዙን ተፍቶብን ወደ ትግራይ ኼዶ ቢመሽግም አሁንም ግን ግድያ፣ ደም ማፍሰስ፣ ማፈናቀል፣ አልቆመም። በሀገሪቱ ላይ የሚፈጽመው ዕልቂት የገፊና ጎታች ሤራ እንደሆነ በተደጋጋሚ ያነሳነው ጉዳይ ነው። ጎልጉል በዚህ ላይ የዘገበውን ማንበብ የሤራውን አካሄድ ለመረዳት ያስችላል።
ኾኖም ግን ግድያ በተፈጸመ ቁጥር “የታጠቁ ኃይሎች፣ ጽንፈኛ ቡድኖች፣ ያገራችን ብልጽግና አልዋጥ ያላቸው” ወዘተ እያሉ የዳቦ ስም እየሰጡ እስካኹን “ሸኔ” ከሚለው የወል መጠሪያ ውጪ በግለስብ ደረጃም ይኹን በቡድን ስለ ገዳዮች ግልጽ ማንነት የተሠራ ዘገባ፣ ለፍርድ የቀረቡ ግለሰቦች፣ የተሰጠ ፍርድ፣ ምንም የሰማነውና ያየነው የለም።
ገዳዮች በዕቅድ ነው የሚገድሉት፤ መንግሥት ዕውቅና እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፤ ያደረሱን ጉዳት የሚለኩት መንግሥት በሚሰጠው የአጸፋ ምላሽ ነው፤ መንግሥት አልናገርም ብሎ ዝም ሲል ዝምታውን ለፖለቲካ ፍጆታ ይጠቀሙበታል። “ባደርገውም እወቀሳለኹ ባላደረገውም እወቀሳለኹ” (damn if you do, damn if you don’t) የሚል አጣብቂኝ ውስጥ መንግሥትን የሚከትና የታቀደ ሰይጣናዊና እኩይ አካኼድ ነው።
ስለዚህ እየኾነ ያለው፤ የ“ተገደሉ” ዜና ይሰማል፤ የዜናው “አብሳሪዎች” ከገዳዮቹ ጋር ወይም ከአስገዳዮቹ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ናቸው (ይኼ ወለጋ ላይ በተደጋጋሚ የታየ ሐቅ ነው)፤ ዜናው በዲጂታል ሠራዊቱ ይጦዛል፤ ሕዝብ ይናደዳል፤ ያለቅሳል፤ ቤተ ክህነት መግለጫ ያወጣል፤ የሃይማኖት ጉዳዮች ጉባኤ በመግለጫው ግድያውን ያወግዛል፤ የሰላም ሚኒስቴር ድርጊቱን በተመለከተ ከቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጋር ውይይት ያደርጋል፤ አጣሪ ቡድን ጉዳዩን ይመረምራል ይባላል፤ ተፈናቃዮች ላይ ትኩረት ይደረግ ይባላል፤ ግድያውን ለመዘገብ የተሽኮረመሙት የመንግሥት ሚዲያ አውታሮች የተፈናቀሉት ሲመለሱ የድል ዜና ያበሥራሉ፤ የአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት ይፋ ሳይደረግ፤ የገዳዮች ማንነት ሳይታወቅ፤ ሕይወት እስከሚቀጥለው ግድያ ይቀጥላል።
ስለዚህ እና እንጠይቃለን፤ ገዳዩ ማነው? አስገዳዩስ ማነው?
መቼም ገዳዮች በድንገት ከሰማይ አይወርዱም፤ ወይም ከባሕር ብቅ አይሉም፤ ማንነት አላቸው፤ ሲመለመሉ፣ ሲሰለጥኑ፣ መረጃ ሲቀበሉ፣ ሲያቀብሉ፣ የሎጂስቲክ ሥራ ሲሠሩ፣ ሲደራጁ፣ ወዘተ ቆይተው ነው መጨረሻ ላይ ጥቃት የሚፈጽሙት። እንጂ ምትሀት ወይም ጋኔን አይደሉም፤ ልቡሰ ሥጋ ሰብዓዊ ፍጡራን ናቸው። ከገደሉስ በኋላ የት ነው የሚሄዱት? የት ነው የሚደበቁት? ወይስ እንደ እንፋሎት ይተናሉ ወይም ወደ ሰማይ ያርጋሉ?
ገዳዩ ማነው? አስገዳዩስ ማነው?
ገዳዮችን መልምለው፣ አደራጅተው፣ አስታጥቀው፣ መመሪያ ሰጥተው፣ ተልዕኮ ነድፈው፣ የሚልኳቸው አስገዳዮችስ ማናቸው? በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ከገዳዮች ጋር መረጃ ሲለዋወጡ፣ ብር ሲቀባበሉ፣ ስምሪት ሲሰጡ፣ ወዘተ እንዴት አይታወቁም? እንዴት ከገዳዮችም ወገን ይኹን ካስገዳዮች ምሥጢር የሚያወጣ ይጠፋል? ለምን የገንዘብ ሽልማት ተመድቦ ገዳዮችንም ኾነ አስገዳዮችን የሚያጋልጥ መረጃ አይበተንም?
ገዳዩ ማነው? አስገዳዩስ ማነው?
ጃዋር ነው አስገዳዩ? ብልጽግና ውስጥ የሚገኙ ካድሬዎች ናቸው? አኹንም ትህነግ በሰፋላቸው የዘር ቁምጣ የሚወጣጠሩ የኦሮሞ ብልጽግና ሰዎች ናቸው? የአካባቢው አመራሮች ናቸው? ቤተ ክህነት ውስጥ ያሉ ናቸው? ራሱን በነጻ አውጪ ግምባር ልክ ያደራጀው ሞዐ ተዋሕዶ ነው? የአማራ ጽንፈኞች ናቸው? የሻዕቢያ ቅጥረኞች ናቸው? የግብጽ ተላላኪዎች ናቸው? ወይስ ኹሉም በኅብረትና በቅንጅት የሚፈጽሙት ውሉን ለመለየት ያስቸገረ ትብትብ ነው?
በፌዴራል ደረጃ ያሉ ባለሥልጣናት ለምንድነው ጉዳዩን ሚዲያ ፊት ቀርበው በዝርዝር የማያስረዱት? ለምሳሌ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ አቶ ዳንኤል ክብረት ለምንድነው የማይናገሩት? እንዲያውም እርሳቸው ከቤተ ክህነት ጋር ካላቸው ትሥሥር አኳያ እና ካላቸው ከፍተኛ ሥልጣን ጉዳዩን በደንብ በጥሩ አማርኛ ማስረዳት የሚችሉ ናቸው። (ይህንን ርዕሰ አንቀጽ እያዘጋጀን ሳለ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ግድያውን የሚያወግዝ መግለጫ ወጥቷል)።
ወይም የፌዴራል ኃላፊዎች የሰላም ሚኒስቴርም ኾን ሚኒስትር ዳንኤል ክብረት ከአካባቢው ነዋሪ ጋር ግልጽ ውይይት የማያደርጉት ለምንድነው? እንዲህ ዓይነት አስከፊ ጉዳት ሲደርስ መልሶ ማቋቋሙ አስፈላጊ ኾኖ ሳለ በበርካታ ሀገራትም እንደሚደረገው ከነዋሪው ጋር ውይይት (townhall meeting) ይደረጋል። ሰዎች ምሬታቸውን እንዲናገሩ፣ በነጻነት የደረሰባቸውን እንዲያስረዱ መደረግና ለሕዝብ እንዲተላለፍ ማድረግ ወሳኝ ተግባር ነው። ከዚህ ይልቅ የመንግሥትም ኾነ የክልል ኃላፊዎች ሚዲያው መሸሽ አንዱ የሥራ ድርሻቸው ኾኗል። በዚህ ድርጊታቸውም ሕዝቡን የማኅበራዊ ሚዲያ ሰለባ እንዲኾን አሳልፈው ሰጥተውታል።
ለምሳሌ ቲክቫህ “ወደ ኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በእጅ ስልካቸው ብንደውልም አይነሳም። የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አራርሳ መርዳሳ ደግሞ፣ ማብራሪያ እንዲሰጡ እየጠየቅናቸው ስልካቸውን ዘግተዋል፤ ድጋሚ ሲደወል አያነሱም” ብሎ ዘግቧል። ለምንድነው የማያነሱት? ለምድነው ለሚዲያ ምላሽ ለመስጠት የማይፈልጉት? ታዲያ ቦታው ላይ ምን ሊሠሩ ተቀመጡ? ወይስ ሌላ የሚሸፋፍኑት ጉዳይ አለ?
ከዚህ በፊት በአማራም ይኹን በዚኹ የደም ምድር በኾነው አሩሲ ኅብረተሰቡን የማነጋገርና የደረሰውን ምን እንደኾነ የማስረዳትና የማጋለጥ ተግባር የሠራው የፈረደበት መከላከያ ነው። በአካባቢው ያሉ ጥቂት የቤተ ክህነት ሰዎችም በዚኹ ተባብረዋል። ከዚህ ውጪ ግን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ኾነ በፌዴራል በዚህ ልክ ርቆ የኼደ የለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋናው ተግባራቸው “ከተማ ማብለጭለጭ፤ ፓርክ ማስመረቅ ነው” ወይም “ዜጎችን ማስገደል” እንደኾነ ተደርጎ በየቦታው ስማቸው ሲብጠለጠልና ያንኑ ተከትሎ “መንግሥት የለም” እየተባለ ዲስኩር ሲነፋ ከካድሬ እስከ ሚኒስትር ትንፍሽ አለማለቱ አኹንም ገዳዩ ማነው? አስገዳዩስ ማነው? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።
የመጀመሪያው ተጠያቂ መንግሥት ነው (በተለይ የክልል ኃላፊዎች)፤ አላውቅም፤ እያጣራኹ ነው፤ ወዘተ የሚል ሰንካላ መልስ መስጠት መልሶ ራሱን የሚጎዳ ብቻ ሳይኾን ሀገርንም ነው። ገዳዮችንና አስገዳዮችን በስም ጠርቶ በግልጽ ለሕዝብ መናገር አለበት። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሳተፉ ሀገራት ካሉም “ታሪካዊ ጠላቶቻችን” የሚል ስም መስማት ስለሰለቸን በግልጽ ግብጽ ነች ይበለን፤ ሻዕቢያም ከኾነ እንዲኹ። ሌላም ሀገር ካለ ሕዝብ ይወቀው።
ቤተ ክህነቱም በውስጡ የተሰገሰጉትን ያጋልጥ፤ ግድያ ሲፈጸም ለመግለጫ እንደሚቸኩለው ገዳዮችንና አስገዳዮችንም ለሕዝብ ይፋ ያድርግ። በስሙ የሚነግዱ ካሉ ማንነታቸውን ይፋ ያውጣ፤ ሕዝብ በማስገደል የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት የሚሠሩት ቆብ የደፉ ጳጳሳት፣ የጠመጠሙ ካህናት ቢኾኑ ያጋልጥ፤ ከሌሉም አጣርቼ የሉም ይበልና ቃሉን በፈጣሪ ስም በመኃላ ይስጥ።
ሕዝብ ይተባበር፤ መቼም ገዳይና አስገዳይ ቤተሰብ፣ ወንድም፣ እህት፣ ወላጅ፣ ጓደኛ፣ አላቸው። ወፍዘራሽ አይደሉም፤ ከሰማይ አልወረዱም። እንዲህ ዓይነት ሰይጣናዊ ተግባር የሚፈጽም የቤተሰብ አባልም ኾነ ጓደኛ ማጋለጥ በምድር ከሚፈጽሙ የተቀደሱ ሥራዎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነውና በሀገር ውስጥም ኾነ በውጪ ያለው ሕዝብ ይተባበር። መንግሥትም ወንጀለኛውን ለሚያጋልጥ አካል የመረጃ ጥቆማ ብር ይመድብ።
የማኅበረሰብ ጥናት ሳይንስ መሥራች የሆነው ማክስ ዌበር (Max Weber) በአንድ ወቅት እንደጻፈው፤ መንግሥት “ኃይልንና ጥቃትን በሕጋዊ መንገድ የመጠቀም መብትን በብቸኝነት የተቆጣጠረ” ብቸኛ ተቋማት ነው (“monopoly on the legitimate use of physical force”) ይላል። ነገር ግን መንግሥት ይህንን ሕጋዊ የኃይል የበላይነቱን ማንነቱ ለማይታወቅ ድብቅ የታጣቂ ኃይል አሳልፎ ሲሰጥ ምን ይከሰታል?
ለዓመታት ንጹሐን ዜጎች በማንነታቸውና ባሉበት ቦታ እየተመረጡ፣ መከላከያ በሌላቸው መንደሮች ውስጥ በማያቋርጥና ደጋግሞ በሚከሰት አሰቃቂ የጭፍጨፋ አዙሪት ውስጥ እያለፉ ነው። እነዚህ ስም የለሽ ታጣቂዎች ንጹሐንን ፈጅተው፣ ሰላማዊ ማኅበረሰብን በትነው ልክ እንደ ጉም በነጻነት ይጠፋሉ። መንግሥት ግን እነዚህን አካላት ፈጽሞ አላጋለጣቸውም፣ ስማቸውንም አልጠራም፣ ድርጊቱንም አላስቆመም። ይህን መሰል እጅግ የተቀናጀ፣ ስልታዊና ዘግናኝ ጥቃት መፈጸም ከፍተኛ የገንዘብ አቅምንና የባለሥልጣናትን ከለላ ይጠይቃል። አንድ መንግሥት የብዙኃንን ገዳይ ለማጋለጥ ፈቃደኛ ካልሆነ፤ ገዳዩን ማጋለጥ ማለት ከጀርባው ያለውን የገንዘብ ምንጭ፣ የተሰጠውን ተልዕኮ እና ይህ እንዲሆን የፈቀዱትን ባለሥልጣናት ማጋለጥ ስለሚሆን ነው ተብሎ ቢወሰድ ስህተት አይኾንም። ገዳዩ ምንም ይሁን ማን፣ ይህንን አሰቃቂ ድርጊት ያላስቆመውና በዜጎች ላይ ለደረሰው ጥፋት ቀዳሚውንና ዋናውን ኃላፊነት የሚወስደው ራሱ መንግሥት ነው።
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ™” አቋም ነው።

Leave a Reply