በሀገር ውስጥ ለግማሽ ምዕተዓመት የሽብር ተግባራትን ሲፈጽም የነበረውና ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ትህነግ/ህወሃት) ተብሎ የሚጠራው ሕገወጥ የአሸባሪዎች ቡድን፤ በፍጥነት ዓለምአቀፍ አሸባሪ ወደመሆን እየተጓዘ እንደሆነ በቅርብ የሚወጡ ሪፖርቶች እየጠቆሙ ነው።
በሰኔ ወር 2026 የወጣውን የሚሊተሪ ታይምስ (Military Times) ዘገባ መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ የዜና እንዳለው ዩናይትድ ስቴትስ ጦሯን መቀነሷን ተከትሎ በአፍሪካ የአሸባሪዎች ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑ ያስረዳል።
የአሜሪካ ጦር በአፍሪካ አህጉር ያለውን ውክልና እና የሠራዊት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ተከትሎ፣ በሳህል እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች የጂሃዲስት ቡድኖች ተጽዕኖ እና ጥቃት በአስደናቂ ሁኔታ እያደገ መሆኑን የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል (CSIS) ባወጣው ዓመታዊ የደህንነት ስጋት ግምገማ በጥብቅ ማስጠንቀቁን ሪፖርቱ ያስረዳል።
ማዕከሉ “የዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት ስጋት ግምገማ 2026” በሚል ባወጣው ሪፖርት፤ በአሁኑ ወቅት ከአውሮፓና ከመካከለኛው ምስራቅ በተለየ መልኩ በአፍሪካ የሚንቀሳቀሱ የአልቃኢዳ እና የኢስላሚክ ስቴት (አይሲስ) አጋር ቡድኖች በሰው ኃይል፣ በፋይናንስ አቅም እና ሰፊ ግዛቶችን በመቆጣጠር ረገድ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ መሆናቸውን ጠቁሟል።
ሪፖርቱ የተለያዩ የሽብር ቡድኖችን ቁመና በማንሳት የዘረዘረ ሲሆን፣ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውና ከአልቃኢዳ ጋር ትስስር ያለው አልሸባብ በአህጉሪቱ ትልቁና ጠንካራው የሽብር ቡድን መሆኑን አመልክቷል፣ ቡድኑ የአሜሪካን ጥቅም የመምታት ግልጽ ፍላጎት እንዳለው ተጠቅሷል። ሆኖም ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ትኩረቱ ቀጣናዊ አጀንዳዎች ላይ በመሆኑ በአሜሪካ ምድር ላይ አስቸኳይ የደህንነት ስጋት የመሆን ዕድሉ አነስተኛ እንደሆነ የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ስጋቱን በማስጠንቀቂያ መልክ አስቀምጧል።
አሜሪካ በአፍሪካ የነበራትን የሠራዊት ስምሪት በ75 በመቶ መቀነሷ፣ ይህን ተከትሎ የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ (AFRICOM) አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን ለአገራቸው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በሰጡት ቃል፤ የአሜሪካ እና የሕብረ ብሔር ጦር ከአካባቢው መውጣት በአህጉሪቱ ላይ “የመረጃ ጥቁር ቀዳዳ” (Intelligence Black Hole) መፍጠሩን አመልክተዋል። አዛዡ አክለውም ዕዛቸው በአሁኑ ወቅት በጣም አነስተኛ በሆነ የሰው ኃይልና ግብዓት እየሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ መሆኑ ደግሞ በአህጉሪቱ ለሚነሱ ድንገተኛ ቀውሶችና የጸጥታ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ የመስጠት አቅምን በእጅጉ አዳክሞታል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ምሁራንና አካባቢው ላይ የሚሠሩ የጸጥታ መዋቅር አካላት ከዚህ ጥናትና ማሳሰቢያ እንዲሁም ከጄኔራሉ ስጋት የተቀዳውን የኢትዮጵያን፣ የእስራኤልንና የአሜሪካን የቀይ ባህርን ስትራቴጂካዊ የጋራ ስምምነት ያነሳሉ። ሲቀጥሉም ይህ አዲስ ጥምረት ኢትዮጵያን የአፍሪቃ ቀንድ ቁልፍ እንዳደረጋት መረዳት አለመቻል፣ ፖለቲካዊ “ጨዋነት” ወይም አብዛኞች እንደሚሉት “ቆሞ ቀርነት” የሚባለው ወቅትን መረዳት ያለመቻል “የአስተሳሰብ ማረጥ” ነው።
በቅርቡ ይፋ የሆኑ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ መካከል በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በተመለከተ የተደረጉት ዋና ዋና የደህንነት እና የዲፕሎማሲ ስምምነቶች ትኩረት በዋናነት በቀጣናዊ ፀጥታ፣ በሽብርተኝነት መከላከል (በተለይም አል-ሸባብን በመዋጋት) እና በስደተኞች አያያዝ ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው።
ሚዛኑን ስቶ የነበረው የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከታደሰ በኋላ ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በሶማሊያ ያለውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር እና የአል-ሸባብን ስጋት ለመቀነስ በጋራ ለመሥራት ስምምነታቸውን አድሰዋል። ስምምነቱ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የምታደርገውን የዓቅም ግንባታ እና የመረጃ ልውውጥ (Intelligence Sharing) ማጠናከርን የሚያካትተው ነው።
በአፍሪካ ቀንድ ካለው የምግብ ዋስትና እጥረት እና ከጎረቤት ሀገራት (እንደ ሱዳን እና ሶማሊያ) ወደ ኢትዮጵያ ለሚሰደዱ ወገኖች የሚውል የፋይናንስና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ለማድረግ እና በየጊዜው በአፍሪካ ቀንድ በሚከሰቱ አዳዲስ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች (ለምሳሌ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ያለው የባህር በር ውጥረት) ዙሪያ በጋራ ለመምከር የሚያስችል የዲፕሎማሲ መስመር ዘርግተዋል። “በሰላማዊ መንገድ” የሚለውን በማከል ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር የምትመለስበትን አግባብ እንደሚደግፉና እንደሚያግዙ ይፋ አድርገዋል።
ሁለቱም ሀገራት ይህንን ስምምነት የፈለጉበት የየራሳቸው ጠንካራ ብሔራዊ ጥቅም እና ስልታዊ ምክንያቶች እንዳላቸው ይታመናል። ዋናውና ትልቁ ጉዳይ የቀይ ባህር እና የኤደን ባህረ ሰላጤ ደህንነት ጉዳይ እንደሆነ ያለአንዳች ማቅማማት ተመልክቷል።
እናም አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ በኩል የሚያልፈውን ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ከየመን አማፂያን (ሁቲዎች) እና ከሌሎች ስጋቶች ለመጠበቅ በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አጋር ያስፈልጋታል። ኢትዮጵያ ደግሞ በቀጣናው ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር በመሆኗ ለአሜሪካ ስልታዊ አጋር አድርጓታል። ከምንም በላይ የገነባቸው ጠንካራ መከላከያ ተመራጭነቷን አጉልቶታል።
ከዚህም በላይ አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ኃይል በመቀነሷና በምስራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባህር አካባቢ የቻይና፣ የሩሲያ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተፅዕኖ እያደገ በመምጣቱ፣ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት በማጠናከር ተፅዕኖዋን ለማስጠበቅ ይፋዊ እንቅስቃሴ ጀምራለች።
ከዚሁ ፍላጎቷ በመነሳት ኤርትራ፣ ትግራይ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ በመመላለስ ቃል በቃል ይፋ ባይሆንም ጥቅሟን ለማስከበር ከጀመረችው ጉዞ በተቃራኒ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲገቱ አሳስባለች። አሁን ከኢራን ጋር ካለው ጦርነት በተጨማሪ ሌላ ጦርነት በአፍሪቃ ቀንድ ማየትም መስማትም እንደማይፈልጉ ከአማራጭ ጋር ማቅረቧን ዲፕሎማቶች አመልክተዋል።
እንግዲህ ትህነግ ይህ ሁሉ እየሆነ ነው “ጽምዶ” በሚል ከኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሶማሌ፣ በተለያዩ አገራትና ድርጅቶች ከሚረዱ የኢትዮጵያ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ኅብረት ፈጥሮ ጦርነት ለመግጠም እየተንደረደረና፣ ሲያሻውም እየሞከረ ያለው። “በውጤቱ ማን ያሸንፋል” የሚለው ጉዳዩን በጥሞና የሚከታተሉት አያሳስባቸውም።
የሚያሳስባቸው በዚህ በግብጽና ስማቸውን ደብቀው ከኋላ ድጋፍ የሚሰጡት ይህ “ጽምዶ” አማካይነት እየተቆሰቆሰ ያለው ጦርነት ከተቀሰቀሰ የሚያስከትለው ጠባሳ ነው። መንግሥት በግልጽ እንዳለው እነዚህ አካላት ቅዠታቸውን መሬት እናወርዳለን ካሉ “እንደ ሰም ይቀልጣሉ”፤ ይህ ማለት ምላሹ በሰው ለሰው ውጊያ ሳይሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ እንደሚሆን አመላካች ነው።
ከኢትዮጵያ ወገን “ከተነካሁ” ስትል በተደጋጋሚ እያስታወቀች ካለችው እና ጥምረት ፈጠርን የሚሉት በጋራ ከሚያሰራጩት መረጃ አንጻር አሁን ላይ መረዳት የሚቻለው ጥቃት ቢሰነዘር የዓለም የድጋፍ ሚዛን ወደየት እንደሚያጋድል ነው። ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ከአሜሪካ ጋር ተበላሽቶ የነበረውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ እና የአሜሪካን የልማትና የፋይናንስ ድጋፍ (ለምሳሌ የአይ ኤም ኤፍ/IMF እና የዓለም ባንክ ድጋፎችን) በይበልጥ መጠናከር፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ስልታዊ የሀይል ሚዛን (Regional Hegemony) ለማስጠበቅ እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ባሉ የዲፕሎማሲ ውጥረቶች ወቅት የዋሽንግተንን ድጋፍ ወይም የገለልተኝነት አቋም ግልጽ መሆን ይህንኑ አመላካች ነው።
በቪዲዮና በሰው ምስክሮች እንዲሁም በስምና በአደረጃጀታቸው የሚታወቁ የትህነግ የታጠቁ ኃይሎች በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በቅጥረኛነት (Mercenarism) እየተሳተፉ መሆኑን የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት እና ራሳቸው ሱዳን ውጊያ ላይ ያሉት የትህነግ ወታደሮች በይፋ አስታውቀዋል። ይህ ዓለም ያየው፣ ጸሐይ የሞቀው ሃቅ አሜሪካና አውሮፓውያኑ ከያዙት የአቋም ለውጥና የሚጨበጥ ድጋፍ ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ ለምትወስደው እርምጃ ፍትሃዊነት ማረጋገጫ ነው።
ከሙስሊም ወንድማማቾች ህብረት እንቅስቃሴና ከኢራን የሽብር ስር ጋር በማያያዝ ከተፈረጁት ጄኔራል አልቡርሃን ወታደሮች ጋር ያበሩት የትህነግ ተዋጊዎች አንድ መንደር ይዘው በድል ስሜት ሲጨፍሩ የሚያሳይ ቪዲዮ ሰሞኑን በራሳቸው በተዋጊዎቹ መለቀቁን ተከትሎ በትህነግ አመራሮች፣ ተባባሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ የተጣለው የቪዛ ዕግድ ከላይ አሜሪካ ከያዘቸው አቋም አንጻር ብዙ የሚናገር ስለመሆኑ ዜናውን ተከትሎ የወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ። በተመሳሳይ ትህነግ ድሮ ተሰፍሮበት ከነበረው የሽብር ታርጋው ጋር መላቀቅ አለመቻሉንና አሁንም ወደዚሁ የኖረ የሽብር ወጉና ታሪኩ እየተምዘገዘገ መመለሱን የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም ማረጋገጫ ነው።
ትህነግ ለዚህ ተግባሩ ሕፃናትን በግዳጅ የማፍስ (Child Soldier Recruitment) ድርጊት መፈጸሙ በቪዲዮና በሰው ማስረጃ መረጋገጡ ጉዳዩን ከአጠቃላይ የፖለቲካ ቀውስ ወደ ከባድ ዓለም አቀፍ የወንጀል ተጠያቂነት (International Criminal Liability) እንደሚያሸጋግረው የሕግ ባለሙያዎች እየወነጀሉ ነው። ትህነግ ድሮ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል መከራከሪያ የሚጠቀምበት ሂውማን ራይትስ ዋች ማክሰኞ ዕለት ባወጣው ሪፖርቱ የትህነግን አሁኑን ቁመናውን አነውሮታል። ይህ በማስረጃ የተደገፈ የትህነግ ጥፋት በድርጅቱ መሪዎችና አዛዦች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ዓለም አቀፍ የሕግ ጣጣ የሚያብራሩ፣ ትህነግ “ወደነበርኩበት የሽብር ቋትና ማዕረጌ መልሱኝ። ሁሉንም መስፈርት አሟላለሁ” በሚል ሙግት የከፈተ እንደሚመስል በማውሳት ያሸሙሩታል።








ሕፃናትን ለጦርነት መመልመልና ማሰማራት በዓለም አቀፍ ሕግ ፍጹም የተከለከለና በቀጥታ የጦር ወንጀል (War Crime) ተብሎ የተፈረጀ መሆኑ ትህነግን በዚህ አግባብ ተጠያቂ ያደርገዋል። አሁን ብቻ ሳይሆን ባለፉት ጦርነቶች በሰው ማዕበል ህጻናት በጅምላ ማስጨረሱ ሊነሳበት ይችላል። ከዚህም በላይ በኢራንና ቱርክ ከሚደገፈው የሙስሊም ወንድማማቾች ህብረት ጋር ተያያዞ በሽብር ከተፈረጁት የሱዳኑ መሪ ጋር ወታደር በሽያጭ እያቀረቡ መተባበር በበዙ መልኩ የሽብርም ተጠያቂ እንደሚያደርግ እየተገለጸ ነው።
ህፃናት ሳይቀሩ ማሰለፉ ብቻ ሳይሆን አሸባሪ ከተባለ አገር መሪ ጋር በማበር የቅጥረኝነት ስምምነት (Mercenary Convention) መፈጸሙ ሌላው የትህነግ ወንጀል ነው። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) እና በአፍሪካ ሕብረት (AU) የቅጥረኝነት መከላከያ ስምምነቶች መሠረት፣ ወታደሮችን ለገንዘብ ጥቅም ሲሉ በሌላ ሀገር ግጭት ውስጥ ማሳተፍ ሕገ-ወጥ እንደሆነ የሚገልጹ የህግ አዋቂዎች “ትህነግ ወታደሮችን በቅጥረኛነት ሸጦ የሚያገኘውን ሃብት ወደ ቋቱ የሚከትበት ህጋዊ የገንዘብ ማዘዋወሪያ አገባብ ስለሌለው በዚህም ወንጀል ይከሰሳል። የብሩ ምንጭም ሌላው ከሽብር ጋር አብሮ የሚታይ ቁልፍ ጉዳይ ነው”።
ወጣቶችን ያለፍላጎታቸው በግዳጅ በማፈስ፣ ድንበር አሻግሮ ለሌላ ጦር ኃይል አሳልፎ መስጠት እና ከእነሱ በስተጀርባ የገንዘብ ጥቅም መሰብሰብ በዓለም አቀፍ ሕግ የሰዎች ማገትና ሕገ-ወጥ ዝውውር (Human Trafficking for Forced Labor/Military Service) ተብሎ ይፈረጃል። ይህም ጉዳዩን ከተራ ወታደራዊ ግጭት አውጥቶ ከድንበር ተሻጋሪ ዓለም አቀፍ የተደራጁ ወንጀሎች (Transnational Organized Crimes) ተርታ ይመድበዋል። እናም ትህነግ ያልተነከረበት የወንጀል ዓይነት የለም።
በሱዳን ጦር (SAF) እና በትህነግ (TPLF) መካከል ወታደሮችን በገንዘብ ስለመሸጥ እና በዚሁ ዙሪያ የሚካሄደው ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር (Illicit Financial Flows)፣ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና በደህንነት መዋቅሮች እይታ “ከፍተኛ ስጋት ያለበት የተደራጀ ወንጀል” በመሆኑ ክትትል እንደሚደረግበት የማይገባው ለትህነግ እንጂ ለሌላ ለማንኛውም አካል ግልጽ ነው።
በሁለቱ ቡድኖች መካከል የሚደረገው የገንዘብ ዝውውር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ህግና ሉዓላዊነት በጣሰ መልኩ የሚከናወን በመሆኑ ጉዳዩን የኢትዮጵያ መንግሥት ሲከታተለው እንደነበርና ሌሎች ወዳጅ አገራትም በከፍተኛ ደረጃ ሲሰሩበት እንደነበር መንግሥት በግልጽም ባይሆን በተዘዋዋሪ ማስታወቁን ማስታወስ ልብ ይሏል።
በተለያዩ መገለጫዎች ትህነግ በአገር ቤት ለፈለፈላቸው ሽብርተኛ ቅርንጫፎቹ፣ ዜጎች በነጻነት እንዳይወጡና እንዳይገቡ፣ በነጻነት ከቦታ ወደቦታ እንዳይንቀሳቀሱ፣ በሰላም ውለው እንዳያድሩ፣ ህጻናት እንዳይማሩ፣ ወዘተ “መደብ በማውረድ” መሳሪያና በጀት እየመደበ አገሪቱን እንደሚያምስ በጎልጉልም ሆነ በሌሎች የተዘገበ ስፍር ቁጥር መረጃ አለ። የአገር ውስጡ አልበቃ ብሎ ከሶማሌው አልሸባብ፣ ከየመኑ ሃውቲ፣ በኢራንና በቱርክ ከሚደገፉት ኃይሎችና ሽብርተኞችን በመቀፍቀፍ ቀጠናውን በማወክ ሚናዋን ከምትጫወተው ኤርትራ ጋር ገጥሞ “የሽብርተኛነት ታፔላውን” ከለበሰ ቆይቷል።


“ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ ከደሙ የተዋሃደውን የሽብር ታሪኩ ሳይፈለግ የተፋቀለት ትህነግ ዳግም በዚሁ ማዕረጉ ሊያሸበርቅ ዳር መድረሱን አስቀድሞ ማብሰር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። እናም “ውድ ትህነግ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ እንደሚባለው አሸባሪ ነህና በስምህና በወግህ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ ማንነትህ ለመጠራት ያደረከው ጥረት ሁሉ ተሳክቶልሃልና እንኳን ደስ አለህ” እንልሃለን።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply