* ሕዝቡን በማሳተፍ ከቀበሌ ጀምሮ አዳዲስ የአስተዳደር መዋቅር ይደራጃል — አብርሃም በላይ (ዶ/ር)
በትግራይ ክልል ሕዝቡን በማሳተፍ ከቀበሌ ጀምሮ አዳዲስ የአስተዳደር መዋቅሮች እንደሚደራጁ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለፁ። አብርሃም በላይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት፤ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት በትኩረት እየሠራ ይገኛል። በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ለማምጣት ሕዝቡ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት አዲስ መዋቅር እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ክልሉን ከሕገ-ወጥ ኃይሎች እያጸዳ እንደሚገኝ የጠቆሙት አብረሃም፣ ይህንን ተከትሎም ከቀበሌ ጀምሮ አዳዲስ የአስተዳደር መዋቅሮች በሕዝቡ ሙሉ ተሳትፎ እንደሚደራጁ አስታውቀዋል። የአስተዳደር መዋቅሩን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ በወራት ጊዜ ውስጥ ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አብርሃም በላይ (ዶ/ር) አብራርተዋል።
በሰሞኑ ውጊያ የሻዕቢያ (የኤርትራ) ሠራዊት መሣሪያ ይዞ፣ ግንባር በመውሰድና የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ከትህነግ ጋር አብሮ ሆኖ መዋጋቱን አብርሃም በላይ (ዶ/ር) አስታውቀዋል። በዚሁ ውጊያ በርካታ የኤርትራ ሠራዊት መሳሪያዎች የተማረኩ ሲሆን፣ የሞቱም እንዳሉ ተገልጿል።
ዶክተር አብርሃም በላይ አክለው እንዳመለከቱት፣ ሻዕቢያ ለፈጸመው አጥፊ ተግባር በእጥፍ ምላሽ ይሰጠዋል። የአንድን ሀገር መንግስት ከባንዳ ጋር አብሮ መውጋት ምን ያህል ዋጋ የሚያስከፍልና ምን ሊያስከትል እንደሚችል በምላሹ ያገኘዋል ሲሉ ሚኒስትሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ በጥብቅ አስጠንቅቀዋል።
በሁሉም ግንባሮች የትህነግ ሠራዊት መበተንና የከፍተኛ አዛዦች እልቂት
በሌላ በኩል፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ የሰላም ኃይል በሁሉም አቅጣጫዎች ባካሄዱት የተቀናጀ የማጥቃት እርምጃ፣ ለወራት ሲዘጋጅ የቆየው የትህነግ ታጣቂ ቡድን በሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መበታተኑ ታውቋል። በራያ፣ በደቡብ እና በምዕራብ ግንባሮች የተሰለፉት የቡድኑ አርሚዎች ከባድ ውድመት አስተናግደው አዛዦቻቸው ከተደመሰሱ በኋላ፣ የተረፉት ደግሞ በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይገኛሉ።
በደቡብ እና በራያ ግንባር በተደረገው ውጊያ የትህነግ አርሚ 11፣ 22 እና 92 ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተበተኑ ሲሆን፣ የአርሚ 43 አዛዥ ኮሎኔል ትንሱ እና የአርሚ 15 አዛዦች ተደመሰሰዋል።
በዚሁ ኦፕሬሽን ከባድ ጉዳት አስተናግዶ በባጃጅ ለማምለጥ ሲሞክር የነበረው የቡድኑ የደቡብ ግንባር አዛዥ ጀነራል ዮሐንስ መዲድ፣ ባጃጇ ተገልብጣ አሽከርካሪዋ ወዲያውኑ ሲሞት እሱ ከሞት ለጥቂት አምልጧል። ጀነራል ዮሐንስ መዲድ በአሁኑ ወቅት በአይደር ሆስፒታል በጽኑ ህሙማን ክፍል በማሽን እርዳታ እየተነፈሰ የሚገኝ ሲሆን፣ ከአስቸኳይ ህክምና ክፍሉ ለጎልጉል የደረሱ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ከሞት የመትርፈው ዕድል እጅግ አነስተኛ ነው።
“መከላከያን መቋቋም አልቻልንም” — የአርሚ 17 ስጋት
በወዲ አዙል መሪነት እና በልጅ አለም የመረጃ ሀላፊነት የሚመራው አርሚ 17 በሠራዊቱ ክንድ ከባድ ኪሳራ እንደደረሰበት ታውቋል። የአርሚው የመረጃ ኃላፊ ልጅ ዓለም ለኤርትራ የመረጃ ሰዎች በሰጠው እምነት፣ “የኛ አቅም ከመከላከያ ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ መቋቋም አልቻልንም፤ ከመከላከያ አቅም ጋር የሚወዳደር አቅም ስለሌለን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንሸነፋለን” ሲል መናገሩ ታውቋል።
በሽሬ ተፈናቃይ ታጣቂዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ
ከራያ ግንባር ከተሰነዘረው ከባድ ምት ተርፈው በእግራቸው ወደ ሽሬ የሸሹት የአርሚ 11 ታጣቂዎች በቡድኑ አመራሮች እና በካምፕ አዛዦች ከፍተኛ ግፍ እየተፈጸመባቸው ይገኛል። አመራሮቹ “ጦርነት ፈርታችሁ መጣችሁ” በማለት የታገቱትን ታጣቂዎች በግድ ወደ ግንባር እንዲመለሱ እያደረጉ የሚገኙ ሲሆን፣ በአካባቢው ያሉ ካምፖች ምንም አይነት ምግብ እና መጠጥ እንዳያገኙ በመከልከላቸው ታጣቂዎቹ በከፍተኛ እንግልት ላይ ይገኛሉ።
የመከላከያ ሠራዊት ገስጋሴ እና የሕዝቡ አቀባበል
በሌላ በኩል የሀገር መከላከያ ሠራዊት በማይፀብሪ፣ በጠገዴ እና በወልቃይት በኩል ወደ ሽሬ ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ እየገሰገሰ የሚገኝ ሲሆን፣ በደቡብ በኩል ደግሞ መቀሌን ተቆጣጥሯል። ሠራዊቱ እና የትግራይ ሰላም ኃይል በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች የትግራይ ሕዝብ ደስታውን ወደ አደባባይ ወጥቶ በነጠላ እያበሰረ ይቀበላቸዋል። ሕዝቡ ለሠራዊቱ እያሳየ ያለው ውግንና እና ደጀንነት ያስደነገጣቸው የትህነግ አመራሮች በሕዝቡ ላይ የነበራቸው ተስፋ ሙሉ በሙሉ በመሟጠጡ፣ ከመቀሌ እና ከሌሎች ከተሞች በመውጣት ላይ ይገኛሉ።
“መሬት ላይ ያለው እውነታ የሰማይ እና የምድር ልዩነት አለው” — የጀነራል አብርሃ ድንኩል ስብሰባ
የትግራይ ሕዝብ ለቡድኑ እያሳየ ያለውን ጥላቻ እና ለመከላከያ ሠራዊቱ ያሳየውን ፍቅር በተመለከተ የትህነግ የምዕራብ ግንባር አዛዦች በሽሬ ከተማ ለሁለት ቀናት የቆየ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገዋል። በጀነራል አብርሃ ተስፋ (ድንኩል) በተመራው በዚህ ስብሰባ ላይ፣ “ሕዝቡ ከምናስበው በላይ ጠልቶናል፤ መጀመሪያ የተነገረን እና መሬት ላይ የሚታየው እውነታ የሰማይ እና የምድር ያህል ልዩነት አለው፤ ሕዝቡ ከኛ ይልቅ ለመከላከያ ሠራዊቱ ደጀን እየሆነ ነው” የሚሉ ሀሳቦች ከአርሚ አዛዦች ተነስተዋል።
ይህን እውነታ ተከትሎ አብርሃ ድንኩልን ጨምሮ የትህነግ የምዕራብ ግንባር ኮር አመራሮች ሙሉ በሙሉ ተስፋ በመቁረጥ፣ በሱዳን አድርገው ለማምለጥ ውስጥ ለውስጥ እየተነጋገሩ እንደሆነ ታውቋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply