ላለፉት 50 ዓመታት በትግራይ ሕዝብ በማስጨነቅና በማሸበር በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን ሲሸማቅቁ የኖሩት የትህነግ የሚዲያ ተቋማት ስም ባስቸኳይ መቀየር ይገባል። እነዚህ በትግራይ ክልል የሚገኙና የሕዝብ ሀብት የሆኑ የሚዲያ ተቋማት አሁንም ድረስ የሕዝቡን ስነ-ልቦና በነጻነት ለመገንባትና ገለልተኛ ሆነው ለማገልገል የተሸከሙት ስምና ማንነት ከፍተኛ ማነቆ ሆኖ እንደሚቆይባቸው ምንም ጥርጥር የለም። በተለይ እንደ ድምፂ ወያነ እና የትግራይ ቴሌቪዥን ያሉ ተቋማት ከደርግ ሥርዓት በኋላ ላለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ያህል የትህነግ (ሕወኃት) የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ማሽን ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል።
እነዚህ የሚዲያ ተቋማት በ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ሠላሳ ዓመታት፣ አገር ወዳዱን የትግራይ ሕዝብ አእምሮ ለመቆጣጠርና የቡድን አስተሳሰብን ለመርጨት እንደ ዋና መሣሪያ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ይህ አይነቱ የሚዲያ አጠቃቀም ሕዝብን ነጻ ከመልቀቅ ይልቅ ለአንድ ፖለቲካዊ ኃይል ብቻ ታማኝ እንዲሆንና የራሱን እውነት እንዳያይ የሚያደርግ “የማደንዘዣ” ስልት ሆኖ ማገልገሉ የአደባባይ ምሥጢር ነው።
ዛሬ ላይ በትግራይ ክልል አዲስ የሰላምና የሽግግር ምዕራፍ እየተጀመረ ባለበት ወቅት፣ እነዚህ የሚዲያ ተቋማት ለአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ለትግራይ ሕዝብ፣ ለፌዴራል መንግሥቱና በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩልና ገለልተኛ አገልግሎት መስጠት ይኖርባቸዋል። ሆኖም ግን፣ ተቋማቱ አሁንም ድረስ በትህነግ ዘመን የተሰጧቸውንና ያንን ዘግናኝና አምባገነናዊ አገዛዝ የሚያስታውሱ ስሞችን ይዘው እንዲቀጥሉ መፈቀዱ ትልቅ ስህተት ነው።
እዚህ ላይ አንድ ግልጽ የሆነ የስነ-ልቦና እውነት ማንሳት ተገቢ ነው። “ይሁዳ” የሚለው ስም በራሱ መጥፎ ስም አይደለም። በትርጉሙ “የእግዚአብሔር ምስጋና” ወይም “የሚመሰገን” ማለት ነው። ስሙ በራሱ መልካምና ጥልቅ ትርጉም ያለው ቢሆንም፣ በታሪክ ውስጥ በፈጸመው ክህደት ምክንያት ግን ዛሬ ዓለም ላይ ማናቸውም እናቶች አዲስ ለሚወለደው ልጇ “ይሁዳ” የሚለውን ስም ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለችም። አንዲት እናት ልጇ በይሁዳ ለምን እንዲጠራ እንደማትፈልግ ምክንያቱ ለሁሉም ግልጽ ነው። ስሙ የተሸከመው የታሪክ ጠባሳና ክህደት ከስሙ ትርጉም በላይ ስለሚገዝፍ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ለመጠቆም የምንፈልገው፤ እንደ ፋና ያሉ የሚዲያ ድርጅቶች ስም ምንም እንኳን ራሱ መልካም ትርጉም ያለውና ጥሩ ስም ቢሆንም፣ ልክ እንደ ይሁዳ ስም ሁሉ ካለው ታሪካዊ ጠባሳና ግንኙነት አንጻር መታየት አለበት። በትግራይ ያሉ የሚዲያ ስሞችም ጉዳይ ልክ እንደዚሁ ነው። “ወያነ” የሚለው ቃል ትርጉሙ ምንም ይሁን ምን፣ ዛሬ ላይ ግን የተሸከመው ታሪክ የጭቆና፣ የጦርነትና የሕዝብ ስቃይ ማስታወሻ ነው።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ብንመለከት፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማክተም በኋላ በጀርመንም ሆነ በማንኛውም የዓለም ክፍል የ“ናዚ” ስም፣ ዓርማም ሆነ ማናቸውም የጭቆና ማስታወሻዎች እንዲኖሩ አልተፈቀደም። እነዚያ ስሞችና ተቋማት ለታሪክ ማስታወሻነት ወደ ሙዚየም እንዲወርዱ ተደርጓል እንጂ ዛሬም ድረስ ሕዝብን እንዲያገለግሉ አልተተዉም። የትህነግ አምባገነናዊ አገዛዝ ማስታወሻ የሆኑት እነዚህ የስም መጠሪያዎችም በተመሳሳይ መልኩ ተሰብስበው ወደ ታሪክ ሙዚየም መግባት አለባቸው።
ስለሆነም፣ በአሁኑ ወቅት ክልሉን ለስድስት ወር እንዲያስተዳድር የተመደበው ጊዜያዊ አስተዳደር አዲስ አመራርና የፌዴራል መንግሥቱ በዚህ ጉዳይ ላይ በቁርጠኝነት ሊሠሩ ይገባል። እነዚህን የስም ማሻሻያዎች በአስቸኳይ ካልተገበሩ፣ በተዘዋዋሪ አሁንም ድረስ የትህነግ ደጋፊዎችንና አቃጣሪዎችን ማበረታታትና የልብ ልብ መስጠት ይሆናል። እነዚህ አሮጌና የጭቆና ምልክት የሆኑ ስሞች ከሕዝብ እይታ ሙሉ በሙሉ ሲጠፉና አዳዲስ ብሔራዊና የትግራይን ሕዝብ ክብር በሚመጥኑ ስሞች ሲተኩ ብቻ ነው የትህነግ ፀሐይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መጥለቋንና አዲስ የነጻነት ዘመን መባቻ መድረሱን ደጋፊዎቻቸውም ሆኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተግባር ሊረዱት የሚችሉት።
የተቋማቱ መዋቅርና ንብረት የሕዝብ እንደመሆኑ መጠን አገልግሎታቸው ይቀጥል፤ የጭቆናውና የፕሮፓጋንዳው መታወቂያ የሆኑት ስሞቻቸው ግን በአስቸኳይ ይቀየሩ!
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ™” አቋም ነው።

Leave a Reply