ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የወጣው ውሳኔ ይፋ ከሆነ ወዲህ በአዲስ አበባና በማኅበራዊ ሚዲያ የጋዜጠኝነትና የፖለቲካ መንደሮች ውስጥ ዋና የመነጋገሪያ ርዕስ የሆነው የሪፖርተር ጋዜጣ ዕጣ ፈንታ ነው። ለበርካታ ዓመታት በህትመትና በዲጂታል ዘርፍ የቆየው “ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር” (ሪፖርተር አማርኛ፣ ዘ ሪፖርተር እንግሊዝኛ እና የኦንላይን ፕላትፎርሙ) የምዝገባ ምስክር ወረቀት ከሰኞ ጥቅምት 23/2017 ዓም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዲታገድ ተወስኗል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ባደረገው የይዘት ክትትል፣ ተቋሙ ተደጋጋሚ የሕግና የሙያ ሥነ ምግባር ጥሰቶችን ፈጽሟል ሲል በደብዳቤው ገልጻል።
ባለሥልጣኑ ለውሳኔው መነሻ ያላቸውንና ከአንድ ዓመት በላይ የተደረገ የይዘት ክትትል ውጤት እንደሆኑ የጠቆማቸውን ዋና ዋና ጥሰቶች በሚከተለው መልኩ ዘርዝሯቸዋል፡-
“በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጻረሩ ይዘቶችን ማሰራጨት፤ በሀገር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በማንሳት ከሚሰጣቸው አርዕስት (Headline) ጀምሮ ማጮህ (Sensationalize)፤ በተለያዩ መድረኮችና ሪፖርቶች ላይ የሚገኙ ሀገራዊ መረጃዎችን አጠቃላይ አውዱን ተገንዝቦ መረጃን ከማድረስ ይልቅ በቁንጽል እይታ ላይ ተመስርቶ በመዘገብ በህብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬና ብዥታን መፍጠር፤“
“የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና ዲፕሎማሲ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨት፤ የሀገር ገጽታን የሚያጠለሹ፣ የሀገርን ብሄራዊ ደህንነትን የሚጎዱ፣ የሕዝቦችን አብሮነትና እሴት የሚሸረሽሩ መረጃዎች ማሰራጨት፣ ሚዛናዊነት የጎደለው አድሏዊ ዘገባዎችን ማሰራጨት፤ ከራስ ጥቅምና የግል ፍላጎት በመነሳት ባልተረጋገጠ መረጃ የተቋማትን ስምና ገጽታ ማጠልሸት…”
ባለሥልጣኑ አክሎም፣ እነዚህን ግድፈቶች እንዲያርም ላለፈው አንድ ዓመት ከሚዲያው ባለቤትና ዋና አዘጋጆች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ሲደረግ መቆየቱንና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶም መሻሻል ባለመታየቱ እርምጃው መወሰዱን አስታውቋል።
ይህ እርምጃ ድንገት የመጣ አለመሆኑን የሚያሳዩ ድምጾች ቀድመው ሲሰሙ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ከሚዲያ አካላት ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ፣ የሪፖርተርን አሰራር አስመልካች ከባድ አስተያየት ሰንዝረው ነበር። በወቅቱ ተቋሙን ወክሎ ለተገኘው አካል “የማናውቅ እንዳይመስለው፤ ሰውየውን ምከሩት፣ ንገሩት” ማለታቸው የመንግሥት ትዕግሥት እየተጠናቀቀ እንደነበር ግልጽ ማሳያ ነበር።
ከዚህ በፊት የተዘገበውን ወደ ጎት ትተን ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ፣ ሪፖርተር የሚያትማቸው ይዘቶች ሀገራዊ አንድነትንና ጥቅም የሚጎዱ መሆናቸውን በመረጃ አስደግፎ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል። “አውሬ ነው፤ በስፖንሰርሺፕ እና በማስታወቂያ ስም ቀላቢዎቹም አውሬ ነው የሚቀልቡት” በማለት፣ በተለይም የሕዝብና የንግድ ድርጅቶች ለተቋሙ የሚሰጡትን የገንዘብና የማስታወቂያ ድጋፍ ሊያቆሙ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲወተውት ቆይቷል።
ጎልጉል ካተማቸው የቅርብ ጊዜ ዘገባዎች ጥቂቶቹን ከዚህ በታች ለአብነት አስቀምጠናቸዋል፤
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጣለው ይህ ላልተወሰነ ጊዜ የዘለቀ የህትመትና የስርጭት እገዳ፣ ተቋሙ የተጣሉበትን የሕግና የሙያ ሥነ ምግባር ግዴታዎች ሙሉ በሙሉ አሟልቶ እስኪያቀርብ ድረስ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የባለሥልጣኑን ደብዳቤ ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ሰፍሯል፤
የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር ኃ.የተ.የግል ማህበር (ሪፖርተር እና ዘሪፖርተር ጋዜጣ) የምዝገባ ምስክር ወረቀት ላልተወሰነ ጊዜ ታግዷል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠዉ ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት መገናኛ ብዙሃን ተግባራቶቻቸውን በሀገራችን ሕግ፣ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እና የሙያ ስነ ምግባር አክብረውና ጠብቀው ተግባራቸውን ማከናወናቸውን የይዘት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፣ ለመገናኛ ብዙኃን ፈቃድና ምዝገባ የምስክር ወረቀት መስጠት፣ የማደስና እንዲሁም ከዚህ በተቃራኒ በህገ ወጥ የይዘት ስርጭት ላይ ተሰማርተው ሲገኙ ማገድ እና መሰረዝ ይገኝበታል።
ስለሆነም በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር ኃ.የተ.የግል ማህበር ስር በሚታተሙ ሪፖርተር አማርኛ፣ ዘ ሪፖርተር እግሊዝኛ እንዲሁም ኢትዮጵያን ሪፖርተር የዲጂታል ፕላትፎርም ላይ የሚሰራጩ ይዘቶች ላይ ከአንድ ዓመት በላይ በባለስልጣኑ በተደረገው የይዘት ክትትል ተደጋጋሚ የህግና የሙያ ስነ ምግባር ጥሰቶች በሚዲያው መፈጸሙ ተረጋግጧል።
በዚህም መሰረት በሪፖርተር አማርኛ፣ በዘሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣና የኦንላይን ስርጭት አስመልክቶ በባለስልጣኑ በተደረገው የይዘት ክትትል የሚከተሉት የህግና የሙያ ስነ ምግባር ጥሰቶች ተለይተዋል። ከእነዚህም መካከል፡-
- በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጻረሩ ይዘቶችን ማሰራጨት፣
- በሀገር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በማንሳት ከሚሰጣቸው አርዕስት/Headline/ ጀምሮ ማጮህ /Sensationalize/፣
- በተለያዩ መድረኮችና ሪፖርቶች ላይ የሚገኙ ሀገራዊ መረጃዎችን አጠቃላይ አውዱን ተገንዝቦ መረጃን ከማድረስ ይልቅ በቁንጽል እይታ ላይ ተመስርቶ በመዘገብ በህብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬና ብዥታን መፍጠር፣
- የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና ዲፕሎማሲ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨት፣
- የሀገር ገጽታን የሚያጠለሹ፣ የሀገርን ብሄራዊ ደህንነትን የሚጎዱ፣ የህዝቦችን አብሮነትና እሴት የሚሸረሽሩ መረጃዎች ማሰራጨት፣ ሚዛናዊነት የጎደለው አድሏዊ ዘገባዎችን ማሰራጨት፣
- ከራስ ጥቅምና የግል ፍላጎት በመነሳት ባልተረጋገጠ መረጃ የተቋማትን ስምና ገጽታ ማጠልሸት፣
በመሆኑም ሪፖርተር ከላይ የተመለከቱት የህግና የሙያ ስነ ምግባር ጥሰቶችን እንዲያርም ላለፈው አንድ ዓመት ባለስልጣኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ከሚዲያው ባለቤትና ዋና አዘጋጆች ጋር ባካሔደው ውይይት መታረም ያልቻለ በመሆኑ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም በሚያሰራጫቸው ይዘቶች ላይ መሻሻሎች ባለመታየታቸው በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሰረት የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር ኃ.የተ.የግል ማህበር (ሪፖርተር አማርኛ፣ ዘሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣ እና የኦንላይን ስርጭቱ) የህግና የሙያ ስነ ምግባር ግዴታዎችን ተሟልተዉ ተግባራዊ እስኪደረጉ ድረስ የምዝገባ ምስክር ወረቀቱ ከሰኞ ጥቅምት 23/2019 ዓ/ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ከህትመትና ከስርጭት ሙሉ በሙሉ ታግዶ እንዲቆይ የተወሰነ በመሆኑ ይሔው ተግባራዊ እንዲደረግ ባለስልጣኑ በጥብቅ ያሳስባል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply