የትህነግ ልዩ ዓላማ እየተተገበረ ያለበትን የአማራ ክልል ቀውስ ለማስታገስ የወጣው የአስቸኳይ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ የድምጽ ስሌት አቅርቦ የአማራ ብልጽግና ከዋናው ብልጽግና የተለየ አቋም እንዲይዝ የቢሆን ስሌትና ምኞት ያለበት ዜና አሰራጨ። አብንና ኢዜማንም ደምሯል።
ምንም እንኳን በሪፖርትር ስሌትና “የቢሆንልኝ” ምልከታ የድምጽ መመጣጠን ሊፈጠር የሚችልበት አጋጣሚ ሊታሰብ እንደማይችል የገለጹ እንደሚሉት፣ የዜናው ምኞትና አቅጣጫ ትህነግ የሚከተለውን “በብሄር አስብ” የሚለውን ርዕዮት የሚያንጸባርቅና አማራ ክልል በዚህ ቀጥሎ በሁከት ሲናጥ ትህነግ የከሰራቸውን ኪሳራዎች መልሶ እንዲያገኝ ለሚያደርገው ዝግጅት መንገድ ለመጥረግ እንደሆነ አመልክተዋል።
“… በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክር ቤቱ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማፅደቅ ይኖርበታል” በሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊፀና የሚችለው ከአጠቃላይ የምክር ቤቱ አባላት ማለትም በስድስተኛው ዙር ተመርጠው በምክር ቤቱ መቀመጫ ከያዙት 427 ተወካዮች መካከል 285 የሚሆኑት የድጋፍ ድምፅ ከሰጡ ነው። ከተጠቀሱት 427 ተመራጮች ውስጥ 142 የምክር ቤት አባላት የተቃውሞ ድምፅ ከሰጡ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀሪ ሊሆን ይችላል” ይላል ስሌቱን አመላክቶ ሪፖርተር ምን ያህል ድጋፍ ቢያገኝ አዋጁ ውድቅ ሊደረግ እንደሚችል ባመላከተበት ዜና።
ሪፖርተር አክሎም “በምክር ቤቱ ወንበር ካገኙ አጠቃላይ 427 አባላት ወስጥ 410 የሚሆኑት በብልፅግና ፓርቲ አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 125 ያህሉ በአማራ ብልፅግና ፓርቲ አቅራቢነት የተወዳደሩና የክልሉን ሕዝብ የሚወክሉ ናቸው” ሲል አማራ ብልጽግናን ከዋና አገራዊ ፓርቲ ብልጽግና የተገነጠለ አድርጎ ዘራቸውን ቆጥረው ምርጫውን እንዲያሰሉ አቅጣጫ አሳይቷል።
“ከብልፅግና ፓርቲ ውጪ” አለ ሪፖርተር “ከብልጽግና ፓርቲ ውጪ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ አምስት የሕዝብ ተወካዮች ሲኖሩ፣ በኢዜማ አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ ሌሎች አራት የሕዝብ ተወካዮች እንደሚገኙም ይታወቃል” ሲል ከአማራ ብልጽግና ወኪሎች ጋር ሊዳመሩ እንደሚችል በዜና መልክ “ተባበሩ” ብሏል። በሌላ አነጋገር ተባበሩና የትህነግን ዓላማ አሳኩ በማለት የአማራ ክልል በጥብጥ ዋናው ባለቤት ማን እንደሆነ አሳብቋል።
የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ አጀንዳ ተካይና “ነጻ” መስሎ በብቸኛነት የሚዲያ ንግድ ላይ ያለው ሪፖርተር፣ ከለውጡ በኋላ በኮድ የታሰሩና እናት ፓርቲው ትህነግን ዳግም ለማዋለድ አዲስ አበባ የተቸከለ አድብቶ ተዋጊ ሚዲያ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸውን ሪፖርቶች የሚከታተሉ ይገልጻሉ። ሪፖርተር በአማራ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ፣ ዘረፋና ማህበራዊ ቀውስ እንዳላየ ሆኖ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳይጸና የትህነግን ፍላጎት አንግቦ የሚሰራዉን ዘገባ የሚመለከታቸው እንዲያጤኑት፣ በጥብቅ እንዲገመግሙት ጥቂት የማይባሉ የሚሰጡት አስተያየት ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply