በኢትዮጵያ ሰማይ ስር በየዘርፉ የሚገርሙ ትዕይንቶች ይታያሉ። ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ጉዳዮች ይሰማሉ። አንዳንዶቹ መረጃዎች ደግሞ “መንግስት ሆይ የት ነህ?” የሚያሰኙ ናቸው። ፍትህን በጋራ ወይም ተቧድነው በተዋረድ የሚያዛቡ የማፍያ ይዘት ያላቸው ካድሬዎች በለውጥ ውስጥ ተሰግሰገው ከርመው አሁን አሁን በአደባባይ ቀና ብለው ከነካባቸው እየታዩ ነው። አቧራቸውን አራግፈው ከየስርቻው የወጡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቅጥቅጦች ላይ መንግስት ከተፋዘዘ ህዝብ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ዕምነት እንዲያጣ ይገደዳል። ይህ ከስር የቀረበው ጉዳይ ስንጣሪ ማሳያ ነው። ጉዳዩን አዝረጥርጠን ያላቀረብነው ያልተቋጩም ጉዳዮች ስላሉ ነው።
አዶር አዲስ ሆቴል የማን ነው? ባለቤቶቹን የፍርሃት ቆፈን ውስጥ የጣላቸው “የብሌን ዓይኑ ሰራዊት”
ይህ ብዙም ሳይጋፋ፣ ባለው መረጃ መሰረት ጠልቆ ሳይሄድ ለጥቆማና ለማንቂያ ያህል የቀረበው ዘገባ “በጠራራ ጸሐይ ንብረቷን የተዘረፈችው ቤተክርስቲያን ወግ” በማለት ርዕስ የተመረጠው ከስር ሙሉ ስሙ የተገለጸው የንግድ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅና አጃቢዎቻቸው የሆኑ የአሮጌው ስርዓት ሹመኞች ድር የፈጸመውን አስገራሚ የከተማ ውስጥ የአደባባይ ድራማ ለማሳየት ነው። “ገና አስር ዓመት ፍርድ ቤት እናመላልሳችኋለን” የሚሉት የአሮጌው መንግስት ወኪሎችን የሚታገሰው መንግስት “ለራሴ ሲል” ብሎ ሊያጸዳው የሚገባ የጡንቸኞች ድር መኖሩንም ለማሳየት ነው።
ይህ ሪፖርት የተዘጋጀው “የፍትህ ስርዓቱን በአሮጌው ካባ ማሻሻል አይቻልም” በማለት የሰላ ትችት ለሚሰነዝሩ ዜጎች ይበልጥ ድምጽ ለመሆን ታስቦ ነው። ለውጡን ተከትሎ የፍትህ ዘርፉ ላይ የጥራትና የአገልጋይነት፣ እንዲሁም ሌብነትን ለመግታት መንግስት የተለያዩ ርምጃዎች ወስዷል። ሽምሽር አድርጓል። ይበጃል ያላቸውን አሰራሮች ዘርግቷል። ይሁን እንጂ በፍትህ ደጆች፣ በተለይም በፍርድ ቤቶች አካባቢ ለቅሶው በሚፈለገው መጠን አልቀነሰም። ይልቁኑም የፈረሰው መዋቅር አክተሮች በገሃድ መረባቸውን ጥለው ፍትህ ሲያዛቡ፣ አንዳንዴም የማይታመን ተግባር ሲፈጽሙ ይታያል። እንደምሳሌ “አዶር አዲስ” የሚባለውን ሆቴል ጉዳይ እናንሳ።
ፍትህን ስለሚያዛቡ የተለያዩ መረቦች በወጉ ለሚረዱ ሁሉ እንዲህ ያለ አይን ያወጣ፣ በህግ የተደገፈና የተሞሸረ፣ ጉልበተኞች የሚመሩት ተግባር ሲፈጸም ብዙም አይገርማቸውም። በራሳቸው ላይ ተመሳሳይ በደል የደረሰባቸው ወገኖች “የፍትህ ያለህ” በማለት በችሎት ሳይሆን በጓዳቸው የሚያለቅሱ እንደሚሉት ከሆነ ትብትቡ ያስፈራል። የአዶር አዲስ ሆቴል ድራማም የሚያጠነጥነው በዚሁ የቀድሞ ባለጡንቾች መረብ በመሆኑ ስጋቱ በጉዳዩ ዙሪያ ያሉትን ሁሉ እገሌ ከገሌ ሳይል በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ከቷቸው ቆይቷል።
“አዶር አዲስ ሆቴል” የከተማ መሐል የፎቅ ዝርፌያ
“አዶር አዲስ ሆቴል” ተብሎ የተሰየመው ሕንጻ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ፔንሺን፣ ኢንሹራንስና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሲሆን፣ በ2011 ዓ.ም BZAYNU ለተባለ ኃ.የተ.የንግድ ማህበር በኪራይ ይሰጣል። የንግድ ድርጅቱ በሁለት እህታማቾች በወ/ሮ ብሌን ዓይኑና በወ/ሮ ዘቢብ እኩል ሽርክና የተመሰረተ ሲሆን፣ በመሰረቱት የንግድ ድርጅት ስም ተከራይተው አስፈላጊው የተባለ ለውጥ ተደርጎ ሕንጻው “አዶር አዲስ ሆቴል” ተብሎ ስራ ጀመረ።
ደሳለኝ ሆቴል ጎን የሚገኘውን ይህን አዶር አዲስ በንግድ ድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ተብለው በተሾሙት በወ/ሮ ብሌን ዓይኑ በስራ አስኪያጅነት ሲመራ ቆይቶ ከሁለት ወር በፊት ተዘጋ። በፍርድ ቤት ውሳኔ ከታገደው የድርጅቱ ገንዘብ ተፈቅዶ የተወሰነ ክፍያ ቢደረግም፣ አሁንም በወቅቱ ያልተከፈላቸው ሰራተኞች አሉ። የተወሰኑት ለጎልጉል እንዳሉት ከሆነ መብታቸውን በህግ ለማስከበር ጠበቃ የሚቀጥሩበት ገንዘብ ስለሌላቸው ዝም ብለው የሚሆነውን እየጠበቁ ነው።
አዶር አዲስ በውሉ መሰረት እንዲከፍል የተጠየቀውን የቤት ኪራይ ከመክፈል ይልቅ ወ/ሮ ብሌን “ሁከት ይወገድልኝ” ሲሉ በህንጻው ባለቤትና በሽርካቸው ወ/ሮ ዘቢብ ላይ ክስ መሰረቱ። የንብረቱን ባለቤቶች ንብረታቸው አካባቢ ድርሽ እንዳይሉ የተከሰው ኮሚሽኑ እንዳይከስ ሰግቶ፣ ዝም እንዳይል ንብረት ሆኖበት ዙሪያውን ሲዞር ቆየ። “ለፈጣሪ ቅርብ ነን” ያሉ ጉዳዩን ወደ አምላካቸው እያቀረቡ፣ “ቤተክርስቲያን እንዴት ክስ ቦታ ትሄዳለች” በሚል ሲያዘግሙ ያልተከፈለው የቤት ኪራይ ዕዳ 22 ሚሊዮን ብር አለፈ።
እኩል ባለድርሻ የሆኑት ወ/ሮ ዘቢብ ቀደም ሲል የድርጅቱ አካሄድና አሰራር ለኪሳራ እንደሚዳርግ በመረዳት፣ ለውሳኔ ያበቃቸውን ምክንያት በመዘርዘር ወ/ሮ ብሌን ሆቴሉን በሚገባ መምራት ባለመቻላቸውና ለኪሳራ በመዳረጋቸው ከስራ አስኪያጅነታቸው እንዲነሱ በግምት ከአስር ወር በፊት ክስ ሲመሰርቱ ድርጅቱ ኦዲት እንዲደረግ፣ የኦዲት ኮሚሽንና አዲስ አስተዳደር እንዲሰየም ጠይቀው ነበር።
ወ/ሮ ዘቢብ የመሰረቱት ክስ ክርክሩ ተሰምቶ ካለቀ በኋላ “ለማንበብ ጊዜ አጣሁ” ከሚለው ሰንካላ ምክንያት ጀምሮ ለሰሚ ግራ፣ ለህግ አዋቂዎች የህልም ያህል በሚገርም አኳኋን ሲገላበጥ የቆየው ጉዳይ ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም እጅግ አድካሚና “ፍትህ ከወዴት ነሽ” ያስባለው ክስ ውሳኔ አገኘ። ወ/ሮ ብሌን ከኃላፊነታቸው ወይም ከስራ አስኪያጅነታቸው እንዲነሱ፣ ድርጅቱ የሂሳብና የንብረት ኦዲት እንዲደረግ፣ የኦዲት ኮሚሽንና አስተዳደር እንዲቋቋም ተወሰነ።
ያልተጠየቀ ዳኝነት በማስወሰን፣ ዳኛ በማስቀየር፣ ቀጠሮ በማጓተት፣ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን በቅጽበት በማስቀየር የሚታወቁት ከላይ የተጠቀሱት የወ/ሮ ብሌን አጋፋሪዎች ነገ ምን እንደሚያስወስኑ ባይታወቅም፣ ሲፈሩና ሲቸሩ የነበሩት ዳኛ ይህን ፍርድ ለመስጠት በአምስተኛ ቀጠሮ ችሎት ባስቻሉበት ተመሳሳይ ቀን “ወ/ሮ ብሌን ከአገር እንዳይወጡ፣ በሌሎች አክሲዮኖቻቸው ያላቸው ድርሻ እንዲታገድ” በሚል የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ፔንሺን፣ ኢንሹራንስና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባቀረበው ክስ ላይ ብይን ተሰጠ።
ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ፔንሺን፣ ኢንሹራንስና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባቀረበው መሰረት ወ/ሮ ብሌን “ምስጋና እና ብሌን ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር” (ሴቨር ሬስቶራንት) ውስጥ ያላቸው የሃምሳ በመቶ ድርሻ፣ BMTZ ትሬዲንግ ስም በአያት ማዞሪያ ከተገነባው ባለ ስምንት ወለል ህንጻ ያላቸው የሃያ አምስት ከመቶ ድርሻ እንዲታገድ ፍርድ ቤቱ ወሰነባቸው። ከአገር እንዳይወጡ የተጠየቀው ጥያቄ ለጊዜው ውሳኔ ሳያገኝ ቀረ።
በስማቸው የሚታወቁ ንብረቶችና የባንክ የሂሳብ አካውንቶች ሙሉ በሙሉ የታገዱባቸው ወ/ሮ ብሌን “NOURISH HEALTH / ኖሪሽ ሄልዝ” በሚል ስም ከተከፈተ ሬስቶራንት አንድ ከመቶ ባለድርሻ ካደረጓቸው ስራ አስኪያጅ ወ/ት አበባ አብርሃም እና 99% የሼር ድርሻ ባለቤት ከሆነችው ፍሬህይወት አራት ውክልናዎች በመውሰድ በውክልና የራሳቸውን ድርጅት እየመሩ ስለመሆኑ ጎልጉል መረጃ አለው። ይህ የሆነበት ምክንያት በከፈቱትና በተከፈተባቸው አስር የሚሆኑ ክሶች እግድ እንዳይጣልባቸው ለመከላከል እንደሆነ መረጃውን ያጋሩ አካላት ያስታውቃሉ። በሌላ በኩል የሚቀርብባቸው ምክንያት ሼር ካላቸው ድርጅት ጋር ተመሳሳይ ቢዝነስ በመክፈታቸው ሳቢያ ተጠያቂ ላለመሆን ሲሉ በራሳቸው ድርጅት አራት የተለያዩ አሳሪ ውሎችን መፈጸማቸውን የውክልና መረጃውን ያጋሩ ይናገራሉ።
- መመ 1000727/1/2017 (26/12/2017)
- መመ 1000728/1/2017
- መመ 1000725/1/2017 (26/2/2017)
- መመ 000878/1/2018 (5/1/2018)
ወ/ሮ ብሌን በዚሁ የራሳቸው እንደሆነ በሚታወቀውና ከላይ በተጠቀሰው መሰረት በፍርሃቻ 99 እና አንድ በመቶ ባለድርሻ ካደረጓቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ሙሉ ውክልና እየመሩት ባለው ኖሪሽ ሄልዝ ሬስቶራንት ተገልጋዮች ክፍያ ከሚፈጽሙባቸው የሂሳብ አካውንቶች መካከል ስራ አስኪያጅ ሆነው በተቀጠሩት በአበባ አብርሃም ስም የተመዘገበ አካውንት እንደሚገኝ ጎልጉል በማስረጃ አረጋግጧል። ጎልጉል ተገልጋዮች ተገልግለው ክፍያቸውን በተጠቀሱት ሰራተኛ ስም ገቢ ማድረጋቸውን የሚያሳይ ደረሰኞች ተልከውለታል። የትኛውም የመንግስት አካል የደረሰኙን ግልባጭ ከፈለገ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ዝግጅት ክፍሉ አስቀድሞ ያስታውቃል።
በተመሳሳይ በአዶር አዲስ ሆቴልም ከደንበኞች የአገልግሎት ክፍያ በድርጅቱ ከሚታወቅ የሂሳብ አካውንት በተጨማሪ ሜላት ፓውሎስ በሚባሉ የስራ ኃላፊ ስም በተመዘገበ የሂሳብ አካውንት አማካይነት ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያ ይፈጽሙ እንደነበር ለጎልጉል የደረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህንንም በተመሳሳይ ህጋዊ የሆነ የመንግስት አካል ከፈለገው ዝግጅት ክፍሉ እንደሚያጋራ ከወዲሁ ያስታውቃል። ወ/ሮ ብሌንም ሆኑ ስማቸው የተጠቀሱ አካላት ማስተባበያ ካላቸው ወይም ደረሰኙ ትክክለኛ ስለመሆኑ መሞገት ከፈለጉ የጎልጉል ድረ-ገጽ ጋዜጣ እንደሚያስተናግዳቸው ከወዲሁ ያስታውቃል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ደረሰኞቹን በየደረጃው የሚያትማቸው መሆኑን ያስታውቃል።
የዚህን ሪፖርት አቅራቢ ቀልብ የሳበው በሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በሌላ ችሎት “የንብረት ክፍፍልና የልጆች አስተዳደግ” በሚል ከዓመት በላይ የከረመው ክስ ይታይ በነበረበት ወቅት የተከሰተው ጉዳይ ነበር። የንብረት ክፍፍልና የልጆች አስተዳደግ በሚል ከዓመት በላይ በከረመው ክስ ቀጠሮ ላይ ለመገኘት ሲመጡ ወ/ሮ ብሌን አምስት ሆነው ነበር። ለውጡን ተከትሎ ከስልጣናቸው የተነሱት የቀድሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጸጋዬ አስማማው፣ ቀደም ሲል አቃቤ ህግ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ ታዬ፣ ጠበቃ ጳውሎስ ጌታቸው፣ ጠበቃ ሙሉቀን ጌታቸው አጅበዋቸው ሲመጡ የጎልጉል ተባባሪ እዛው ነበር።
አቶ ጸጋዬ አስማማው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም ሲሆን፣ ለ3 ዓመታት ከ8 ወራት ያህል በስልጣን ከቆዩ በኋላ በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ለውጡ በፍርድ ቤቶች አሰራር ላይ ሪፎርም ለማድረግ በሚል ከኃላፊነታቸው ካነሳቸው ባለስልጣናት መካከል ናቸው። ነገሩ በሪፎርም ይገለጽ እንጂ በርካታ የስነ-ምግባር ችግሮች የሚሰሙባቸው እኚህ የቀድሞ ሹመኛ በምን መነሻ እዚህ ችሎት ደጃፍ እንደተገኙ ማጥራት የጎልጉል ተባባሪ ቀዳሚ ተግባር ነበርና በቀጣይ በዝርዝር የሚቀርብ መረጃ ያቀርባል። ለጊዜው ግን ስለ አቶ ጸጋዬ የሚከተለውን መረጃ ለግንዛቤ እንዲሆን አቅርበናል።
አቶ ጸጋዬ ከ1987 ጀምሮ እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ በመቀሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ በትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል፣ “ኢህአዴግ መቶ በመቶ አሸነፈ” በሚባልበት የአዲስ አበባ ምርጫ ቦርድ ቢሮ ኃላፊ፣ ከዛም እንደገና ወደ ትግራይ ክልል በመመለስ የክልሉ የጸጥታና አስተዳደር ጉዳዮች ወይም የደህንነት ቢሮ ኃላፊ፣ የትግራይ ክልል የርዕሰ-መስተዳድሩ የሕግ አማካሪ ሆነው ያገለገሉ የህወሃት አባል ናቸው። በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ያገለገሉት አቶ ጸጋዬ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ኃላፊነትን የተረከቡት ከአቶ መድኅን ኪሮስ እንደነበርም አይዘነጋም።
የቀድሞው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጸጋዬ አስማማው ከወ/ሮ ብሌን ጋር ህጋዊ ጠበቃ ወይም ወኪል ሳይሆኑ የታዩበት አግባብ ከቀድሞ ጀምሮ ይነሱ የነበሩ ጉዳዮችን የሚያስታውስ በመሆኑ ጎልጉልን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሚያውቋቸውን ጭምር ያስገረመ ጉዳይ ነው። አመጣጣቸው እንዳይታወቅ ያደርጉት የነበረው ጥረት ደግሞ ሌላ ድራማ ነበር።
አቶ ፀጋዬ በሙስናም ክፉኛ እንደሚታሙ። በጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ቆይታቸው “ፋይል ይዘው መቅረት የሚያዘወትሩ” እና “በአየር ላይ ተደጋጋሚ ቀጠሮ” በመስጠት ጠበቆችን ያማረሩ እንደነበሩ ዋዜማና ሌሎች ሚዲያዎች ምስክሮችን ጠቅሰው መዘገባቸው አይዘነጋም።
ለኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ፔንሺን፣ ኢንሹራንስና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቅርብ የሆኑ የመረጃዎቻችን ሁሉ ምንጭ “ስለ አዶር አዲስ ሆቴልም ሆነ ስለ ማናቸውም ጉዳይ ማንሳት ያስፈራል። በራሱ ህንጻ ድርሽ እንዳይል የተከለከለው ኮሚሽኑ በዚህ ደረጃ የፈራበትን ምክንያት ከጉዳዩ ጀርባ ያለው ኃይል ነው። ነገሩ ለመንግስትም የማስጠንቀቂያ ደወል ነውና ያስብበት። መንግስት በድሮው ካባ በሚጫወቱ ኃይሎች ወደ ኋላ እየተጎተተ፣ ዜጎች በፍትህ ስርዓቱ ላይ ዕምነት እንዳይኖራቸው እየተደረገ መሆኑን ይረዳ። የመንግስት ሚዲያዎችም የፍትህ ተቆርቋሪ ከሆኑ ቦርዱ ጋር ጎራ ይበሉ። ከአስር ክሶች ጀርባ ያለውን ድራማና መረብ ያገኙታል” ብለዋል።
ጎልጉል በዚህ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የፍርድ ቤት ጉዳዮችና የፍትህ አግባቦች ተከታታይ መረጃዎችን በማሰባሰብ ተከታታይ ሪፖርቶች የሚያቀርብ ሲሆን፣ ይህን ሪፖርት ተከትሎ መንግስት ታክስ በመሰወርና በገንዘብ አጠባ ላይ ያለውን ቁርጠኛ አቋም በመከታተል እንደሚያትም ያስታውቃል።
እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 1959 የተመሰረተችው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ የረጅም ጊዜ አገልግሎቷንና የአገልጋዮቿን ማህበራዊ ዋስትና ይበልጥ ለማጠናከር ያቋቋመችው የጡረታ፣ ኢንሹራንስና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን “ሙሉውን ሰው ማገልገል” (Holistic Ministry) የተሰኘውን መርህ መነሻ በማድረግ የተቋቋመ ነው፤ ይህ ኮሚሽን፣ በዋናነት የአገልጋዮችንና የሰራተኞችን ህይወትና ማህበራዊ ዋስትና የማረጋገጥ ስራዎችን ያከናውናል። ኮሚሽኑ በጡረታ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና ሰራተኞች አስተማማኝ ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን፣ ጥራት ያለው የኢንሹራንስና የካሳ አሰጣጥ ሥርዓትን በመዘርጋትም ተቋማትንና ሰራተኞችን ከአደጋ የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ዓላማው ያስረዳል። በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያኒቱን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግና ራሷን እንድትችል ለማገዝ የተለያዩ የልማትና የኢንቨስትመንት ስራዎችን በበላይነት እየመራ ይገኛል።
የኮሚሽኑ ዓላማ እንደሚያስረዳው ኮሚሽኑ በተቀመጠለት ዓላማ መንቀሳቀሱን የመቆጣጠር ዓላማ ያላት ቤተክርስቲያን በመሆኗ ጎልጉል ይመለከታቸዋል ላላቸው አካላት ጥያቄ አቅርቦ ነበር። አብዛኞቹ መረጃ የላቸውም። “ገና አስር ዓመት እንሞግታለን” በማለት ያስፈራሩት አካላት እዳቸው ተወዝፎ ሃያ ሚሊዮን ሲያልፍ ዝምታን የተመረጠበት አግባብ እግረ መንገድ ሊዳሰስ እንደሚገባ መረጃውን በሰነድ አስደግፈው ያጋሩን አመልክተዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply