ሕገወጡ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ትህነግ) ሰሞኑን “በትግራይ ዲፕሎማሲ እና አድቮኬሲ ካውንስል” ስም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአውሮፓ ኅብረት እና ለአፍሪካ ኅብረት የጻፈው ደብዳቤ የራሱን ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ለመሸፈን እና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማታለል የሞከረበት የተለመደ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ነው። የደብዳቤውን ይዘት እና ወቅታዊ እውነታዎችን መሠረት በማድረግ እውነታውን በሚከተለው መልኩ እናቀርባለን፦
1. የፕሪቶሪያን ስምምነት ስለማፍረስ እና ስለመሻር
ደብዳቤው የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ጥሷል ሲል ይከሳል። ነገር ግን እውነታው ፍጹም ተቃራኒ ነው። ትህነግ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመሰረዝ በትግራይ ክልል የነበረውን ጊዜያዊ አስተዳደር በኃይል እና በሕገ-ወጥ መንገድ አስወግዷል። ትህነግ በራሱ ፍላጎት የሰላም ስምምነቱን ያፈረሰ፣ ሁሉንም የክልሉን እንቅስቃሴዎች የዘጋ እና የራሱን ሕገ-ወጥ የክልል መንግሥት ያዋቀረ ኃይል በመሆኑ፣ ስለ ሰላም ስምምነት መከበር የመናገር የሞራልም ሆነ የህግ መብት የለውም።
2. ስለ “ትግራይ ሠራዊት” ሕገ-ወጥነት እና የሽብር ትብብር
ደብዳቤው “በመደበኛ ሥራቸው ላይ በነበሩ የትግራይ ሠራዊት ላይ (በኢትዮጵያ መንግሥት) ድብደባ ተፈጸመ” በማለት የትግራይን ታጣቂዎች እንደ ሕጋዊ መከላከያ ሠራዊት ሊያቀርብ ይሞክራል።
- ሕጋዊ መሠረት አልባነት፦ ትህነግ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰረዘ እና ምንም ዓይነት ሕጋዊ እውቅና የሌለው ስብስብ ነው።
- ሕገ-ወጥ ታጣቂ ቡድን፦ በአንድ ሉዓላዊት ሀገር ውስጥ ከተገቢው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ውጪ ሌላ ትይዩ ሠራዊት ማቋቋም ሙሉ በሙሉ ሕገ-ወጥ ነው።
- ቁጥሩ 12 የሚሆን የሠራዊት መኪና ወዴት ነው ይንቀሳቀስ የነበረው? በውስጡ የነበረው በርግጥ ሰዎች ናቸው ወይስ የጦር መሣሪያ?
- የጥፋት ጥምረት (ፅምዶ)፦ ትህነግ ከውጭ ኃይሎች፤ ከኤርትራና ሱዳን አካላት ጋር “ፅምዶ” የተባለ ሕገ-ወጥ ጥምረት በመፍጠር፤ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በዝግጅት ላይ ይገኛል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በዝግጅት ላይ ባሉ ታጣቂዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ሕጋዊ እና ሀገርን የማዳን ተግባር እንጂ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተደረገ ጥቃት አይደለም።
3. የሀብት ብክነት እና የጦርነት ዝግጅት መጋለጥ
ትህነግ ሰላማዊ መስሎ ለመታየት ቢሞክርም፣ ከበስተጀርባ ግን ከፍተኛ የጦርነት ዝግጅት እያደረገ እንደነበር ይፋ የሆኑ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። የትህነግ ከፍተኛ አመራሮች በደላሎች አማካኝነት ከምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የድሮን ማክሸፊያ (Drone Jamming) ቴክኖሎጂ ገዝተው በኩሃ አካባቢ በሚገኘው የሰሜን አየር ዕዝ ላይ ሲገጣጥሙ ቆይተዋል።
ይህ ተግባር ቡድኑ አሁንም ለጦርነት እንጂ ለሰላም እየሠራ እንዳልሆነ የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ የገዙት መሣሪያ ጊዜ ያለፈበት (Second-hand) በመሆኑ እና ዘመናዊ ድሮኖች የላቀ የፀረ-ጃሚንግ (Anti-Jamming) መከላከያ ስላላቸው ሳይሠራ ቀርቷል። ይህ የሚያሳየው የትህነግ አመራሮች የሕዝብን ሀብት ለጦርነት ደላሎች ሲሳይ እያደረጉ መሆኑን እና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የሚዋሹበትን የ“ተጠቂነት” ትረካ ለማድመቅ የጦርነት መዋቅር እየገነቡ እንደነበር ነው። የድሮን ማክሸፊያ መገዛቱን የተናገረው ዳዊት ከበደ (አውራምባ ታይምስ) ነው፤ ስለዚህ ከዚሁ ጋር አብሮ መነሳት ያለበት ጉዳይ 400 ሚሊዮን ዶላር ከየት ተገኘ? የሚለው ይሆናል።
4. “የበጀት እና የኢኮኖሚ ጦርነት” የሚለው የሃሰት ክስ
ደብዳቤው የፌዴራል መንግሥቱ በጀት እና ደሞዝ በመክልከል “የኢኮኖሚ ጦርነት” ከፍቷል ሲል ይከሳል። የፌዴራል መንግሥት የበጀት እና የደሞዝ ድጎማ የሚያደርገው በሕግ እውቅና ላላቸው የክልል መዋቅሮች ነው። ትህነግ ሕጋዊውን መዋቅር በኃይል አፍርሶ፣ በምርጫ ቦርድ የተሰረዘ ድርጅት ሆኖ ሳለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለጦር መሳሪያ መግዣ እያባከነ የሀገሪቱን ሀብት ለራሱ ታጣቂዎች ማጠናከሪያ እንዲሰጠው መጠየቁ ፍጹም ዘራፊነት እና ሕገ-ወጥነት ነው።
ትህነግ በዚህ መልኩ በሕገወጥነት የሚንቀሳቀስ አሻባሪ ቡድን ቢሆንም እና ምንም ዓይነት ገንዘብ ከፌዴራል ሊላክ የማይገባ ቢሆንም የትግራይ ሕዝብ እንዳይቸገር በሚል የፌዴራል መንግሥቱ አሁንም ድረስ ለሕዝቡ የበጀት፣ የነዳጅ፣ የመድኃኒት፣ ወዘተ ድጎማ አላቋረጠም።
5. “ጄኖሳይድ” የሚለውን ቃል ለፖለቲካ መጠቀሚያ ስላማድረግ
ደብዳቤው በተደጋጋሚ “ዳግም ጄኖሳይድ” (ሁለተኛ ዙር የዘር ማጥፋት) የሚሉ ቃላትን በመጠቀም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ስሜት ለመግዛት ይሞክራል። ይህ የጥፋት ቡድን የትግራይን ሕዝብ እንደ መከላከያ ጋሻ በመጠቀም እና በውሸት ፕሮፓጋንዳ በማታለል የራሱን የሥልጣን ጥም ለማርካት የሚጥር መሆኑን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊገነዘበው ይገባል። እውነተኛው ስጋት የኢትዮጵያ መንግሥት ሳይሆን፣ ሰላምን የማይፈልገው፣ ስምምነቶችን የሚያፈርሰው እና ሀገሪቱን ወደ ሌላ የእርስ በእርስ ጦርነት ለመክተት አዲስ የጦርነት ግንባር እየከፈተ ያለው ትህነግ ራሱ ነው።
ይህ የትህነግ አካሄድ በሀገር ውስጥ ካሉ ተፎካካሪ ፓርቲ ነን ከሚሉ ጋር በደንብ ተናብቦ የተሠራ ለመሆኑ ጠቋሚዎች አሉ። የትብብር አመራር የሆኑት ጌትነት ወርቁ በአርሲ ስም ለጠቅላይ ሚኒስቱ የጻፉትን ግልፅ ደብዳቤ አስመልክቶ “በሐዘንና ግልፅ ደብዳቤ ስም የተሸፈነ የድህረ ምርጫ ሀገር የማተራመስ ስትራቴጂ” በሚል ርዕስ ጎልጉል አንድ ዘገባ ሠርቶ ነበር። የአቶ ጌትነት ጽሑፍና የትህነግ ደብዳቤ በይዘትም በአቅጣጫም በጣም የተመሳሰሉ ናቸው። ትህነግ “ዘር ማጥፋት/ጄኖሳይድ” ይላል፤ ጌትነትም የጄኖሳይድ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ነን ይላሉ። እየተናበቡ ለመሥራታቸው እንደ ማሳያ መቅረብ የሚችል ነው።
እንደ መዝጊያ፤
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የፕሪቶሪያው ስምምነት ታዛቢዎች በተለይ ደግሞ የትግራይ ተወላጆች የዚህን ደብዳቤ የሐሰት ትርክት ውድቅ ሊያደርጉት ይገባል። ትህነግ የሰላም ስምምነቱን የጣሰ፣ ሕጋዊ ተቋማትን ያፈረሰ፣ ለጦር መሣሪያ ዝግጅት ሚሊዮኖችን የሚያባክን፣ የትግራይ ልጆችን እንደገና ለማስጨፍጨፍ እያፈነ ወደ ጦር ካምፕ የሚወስድ እና አዲስ ጦርነት ለመጫር ከውጭ ኃይሎች ጋር የተሰለፈ የትርምስ ምንጭ ነው። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊያወግዘው የሚገባው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሳይሆን፣ ሕገ-ወጥነቱን ይዞ በየመድረኩ የሚጮኸውን የትህነግን የጥፋት ቡድን ነው። የትግራ ተወላጆች ደግሞ ቀዳሚ መሆን ይገባቸዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply