• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የጽምዶ ልክፍት

June 9, 2026 12:49 am by Editor Leave a Comment

ትሕነግ (የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር – ህወሃት) ከ2010 ዓም ለውጥ በኋላ ሦስት መጠነ ሰፊ የተባሉ ወረራዎችን እንደፈጸም ይታወሳል። በእነዚህ ተዋጊዎችን እንደ ማዕበል (human wave) የማሰለፍ ስልት ከራሳቸው አንደበትና የጽሑፍ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ የትግራይ ተወላጆች ህይወት አልፏል። የፕሪቶሪያውን የሰላም አማራጭ ስምምነት ተከትሎ በትግራይ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች እና የሽግግር ወቅት ጊዜያዊ አስተዳደሩ በጦርነቱ ወቅት ተሳታፊ ለመሆን ዕድል የተመቻቸለት ሻዕቢያ በትግራይ እህቶች፣ እናቶችና ተወላጆች ላይ የፈጸመው ግፍም የሚዘነጋ አይደለም። 

ትሕነግ ለውጡን ተከትሎ ወደ ትግራይ ካፈገፈገ በኋላ “የፌዴራሊስት ኃይሎች” ብሎ የፈረሰውን ኢህአዴግ የሚተካ ሌላ አደረጃጀት ፈጥሮ ወደ አራት ኪሎ ለመመለስ የሚያግደው ምንም ኃይል እንደሌለ “ጦርነት ባሕል ነው” በሚል ወጣቱን እየቀሰቀሰ፣ ሕዝቡን ለማነሳሳት ይጠቅመኛል ያለውን ትርክት በዲጂታል ሚዲያ እያራገበ ወደ ጦርነት ገባ። በወቅቱ የአገር መከላከያን አምስት እጥፍ በሰው ኃይልና መሳሪያ ይበልጥ ስለነበር፣ ጦርነቱ ሳይጀመር ድል አወጀ። 

የሚያስቡለት የነበሩት አመራሮች በተፈጥሮ ሞትና ድርጅቱ በሚከተለው ዶግማ ሳቢያ ስለተለዩት “ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ የሌለው” በሚል ክፉኛ የሚወቀሰው ትሕነግ፣ የመጀመሪያው ዙር ጦርነት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም እስከ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓም ሲካሄድ የተቀሰቀሰው ለሃያ ሁለት ዓመታት በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ የትግራይን ሕዝብና የኢትዮጵያን ድንበር ሲጠብቅ ዕድሜውን በጨረሰው የአገር መከላከያ ላይ “መብረቃዊ ድል” በማለት ራሱ በገለጸው የክህደት እርምጃ ነበር። 

በመጀመሪያው ዙር ጦርነት ትሕነግ ሽንፈት መራራ ጽዋ መጠጣት ብቻ ሳይሆን አንጋፋ መሪዎቹንም ጭምር አጣ። ለበቀል አድፍጦ ሲጠብቅ የነበረው ሻዕቢያ ከልካይ ስላልነበረው ትግራይ ላይ ዋኘና የሆነውን ሁሉ አደረገ። በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ደረሰ። 

የጽምዶ ልክፍት

በትህነግ ዘንድ ያለውን የጽምዶ ልክፍት አሁን በሚታዩት ተግባራቱ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። “በሬ ከመገበው ይልቅ ያኮላሸውን ይከተላል” እንዲባል ትህነግ “አኮላሽቶ” ከፈጠረው ሻዕቢያ ጋር ያለው ጽምዶ ዘመናትን ያስቆጠረ ልክፍት ነው። በጦር ሜዳ ይህ ልክፍት አልለቀቀውም፤ ሥልጣን ይዞ አልተፈወሰም፤ ከሥልጣን ከተባረረ በኋላ እንደተጠናወተው ቀጠለ፤ አሁንም ልክፍተ ጽምዶ መከራውን እያሳየው ነው። የቅርብ ዓመታቱን እንመልከት፤

ከጥቅምት እስከ ህዳር 2012 ዓም በመቀሌ ከተማ በተካሄደ ትልቅ ጉባኤ ላይ “የፌዴራሊስት እና የኮንፌዴራሊስት ኃይሎች ፎረም” የተባለ መድረክ ተመሠረተ። የሐሳቡ ጠንሳሽ ትህነጋውያን ቢመስሉም ሻዕቢያ ነበር ባለቤቱ፤ ለስብሰባ የተጠሩትም ሻዕቢያ ኤርትራ አስቀምጦ ወይም በሪሞት ሲቀልባቸው የነበሩ ድኩማን ናቸው።

በመቀሌው መድረክ ላይ የተሳተፉና የተሰባሰቡ ድርጅቶች፡- ትሕነግ (TPLF): ዋናው አስተባባሪና መሪ። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ – OLF)፤ በወቅቱ በዳውድ ኢብሳ ይመራ የነበረውና የተወሰኑ አመራሮቹ። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ – OFC)፤ በአቶ በቀለ ገርባና በዶ/ር መራራ ጉዲና የሚመራው (በፎረሙ መጀመሪያ ላይ ተሳትፎ የነበራቸው ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ግንባር ሲመሠረት ሙሉ በሙሉ አልገቡበትም)። የአገው ብሔራዊ ሸንጎ (Agew National Council)፣ የቅማንት ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት ንቅናቄ፣ የሶማሊ ዲሞክራሲያዊ ጥምረት፣ ቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (BPLM) ነበሩ። 

የወቅቱ ጽምዶ “ዋና ዓላማዬ” ብሎ የፌደራል መንግሥቱ ምርጫውን ለማራዘም ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም እና የፌደራል ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወድቋል በሚል በጋራ እንቅስቅሴ መጀመሩን አወጀ። አዲስ አበባ የተቀመጡ በኮቪድ ምክንያት አብዛኛው የዓለም አገሮች ያስተላለፉት ምርጫ “እንዴት ኢትዮጵያ ውስጥ አይካሄድም” በሚል “መንግሥት የለም” በማለት ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ የምትሆንበትን ቀን ቆረጡ። ጃዋርና ልደቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አብረው በአንድ ጋሪ ተሳፍረው ታዩ።

ከዚያም ከላይ በተገለጸው መልኩ ጦርነቱ ከትግራይ ዙሪያ እልፍ ሳይል ተጠናቀቀ። መንግሥት የነበረው ትሕነግ ከክልል አስተዳዳሪነትም ወርዶ በረሃ ገባ። ያለቀው አልቆ፣ የተቀሩት በቃሬዛ ከተደበቁበት ተለቅመው እስር ቤት ገቡ። የነበራቸውን ከስረው የትግራይን ሕዝብ “ተፈናቃይ” አደረጉት። በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ያላስታወሱትን ሕዝብ መደበቂያ ጋሻ አድርገው በመከራ አረንቋ ውስጥ ከተቱት።

ሁለተኛው ወረራ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተደረገ ማስፋፊያ ሲሆን ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓም እስከ ታህሳስ 2014 ዓም አጋማሽ የተካሄደ ነበር። በዚህም ወቅት በተመሳሳይ በትግራይም፣ በአፋርም፣ በአማራ ክልልም ለመግለጽ የሚከብድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ደረሰ። ወደፊት በገለልተኛ አካላት የሚጠና አስደንጋጭ ኪሳራ ደረሰ። ጦርነቱ ውስጥ እየተርመጠመጡ ከሚዘርፉት ጀምሮ ለመስማት የሚከብድ እልቂት ተፈጸመ። 

በዚህም ወቅት በተመሳሳይ ትሕነግ ይዟቸው አራት ኪሎ እንደሚገቡ ያመኑ ዳግም ቃዡ። ማንም ጉዳዩን ይከታተል የነበረ ዜጋ እንደሚያውቀው ሁለተኛው ዙር ጦርነት ከትግራይ ቢወጣም፣ አማራ ክልልን ገፍቶ ወልቃይትን ማስመለስ ሳይችል ዝሎ ወደ ትግራይ አፈገፈገ። 

የመጨረሻው ዙር ጦርነት ከነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓም እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓም የተካሄደ ሲሆን በርካቶች ያለቁበት ሆኖ ተመዝግቧል። ወቅቱ መከላከያ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት የተበሳጨው የኢትዮጵያ ሕዝብ በስፋት ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ እየገባ የአገር መከላከያን ያፈረጠመበት ነበር። በማፈግፈግ ራሱን እያደረጀ እንደነበር የተነገረለት የኢትዮጵያ መከላከያ እየተሸበሸበ፣ የትሕነግ ኃይሎች እየገፉ ደብረ ብርሃን ሲደርሱ ቀደም ሲል መቀሌ እንደተደረገው አሜሪካን አገር የሽግግር መንግሥት ኃይሎች ተከሰቱ። 

ጦርነት ወቅት የትሕነግ ኃይሎች /TDF ወደ አማራ ክልል ዘልቀው በመግባት ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ በጣም ተቃርበው የነበረው በጥቅምት እና በህዳር ወር 2014 ዓም ነበር። 

  • ጥቅምት መጨረሻ 2014 ዓም የትሕነግ ኃይሎች ስትራቴጂካዊ የሆኑትን የደሴ እና የኮምቦልቻ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ይፋ አደረጉ። ይህንን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው በዋናው መስመር ወደ ደቡብ አቅጣጫ በፍጥነት መግፋት ጀመሩ።
  • ከህዳር 10 – 20 ቀን 2014 ዓም ኃይሎቹ ካራቆሬ፣ ከሚሴ፣ ሰንበቴ እና ሸዋ ሮቢትን አልፈው፣ ወደ ደብረ ብርሃን መግቢያ በሆነችውና ከፍተኛ ውጊያ በተደረገባት ጠረምበር/ደብረ ሲና አካባቢ ደረሱ።
  • የደረሱበት ከፍተኛ ርቀት፦ የትሕነግ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ ባይገቡም፣ ከከተማዋ በስተሰሜን ጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኙት የደብረ ሲና እና የጠረምበር ተራራማ ቦታዎች ላይ መድረስ ችለው ነበር። ይህ ቦታ ከደብረ ብርሃን ከተማ በግምት ከ40 እስከ 50 ኪሎሜትር ብቻ የሚርቅ በመሆኑ በከተማዋ ላይ ከፍተኛ ስጋት ጥሎ ነበር።

የትሕነግ ኃይሎች እያጠቁ ወደ ደሴን ሲያልፉ፣ ጥቅምት 2014 ዓም ራሳቸውን “የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት እና ኮንፌዴራሊስት ኃይሎች ግንባር” (United Front of Ethiopian Federalist and Confederalist Forces) የተሰኘውን ጥምረት የመሠረቱት 9ቱ የፖለቲካ እና የታጠቁ ኃይሎች ራሳቸውን አስተዋውቁ። የትሕነግ አመራሮች ጌታቸው ረዳ፣ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፣ ጻድቃን ገብረ ትንሣኤ ወዘተ “ከዚህ በኋላ ከብልጽግና ጋር ንግግር የለም” በማለት ስለ እስርና ፍርድ ያወሩ ጀመር።

በወቅቱ የተመሠረተው ጽምዶ አባላት፤ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ትሕነግ / TPLF)፣  የኦሮሞ ነጻነት ጦር (ኦነግ ሸኔ / OLA – Oromo Liberation Army)፣ የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (ARDUF)፣ የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ADM)፣ የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (BPLM)፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ግንባር (GPLF)፣ የቅማንት ዲሞክራሲያዊ እና መብት ንቅናቄ / የቅማንት ማንነት እና መብት ኮሚቴ (QDRM)፣ የሲዳማ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (SNLF)፣ የሶማሊ ግዛት መቋቋም ግንባር (SRF) ነበሩ።

ይህ ጥምረት በወቅቱ የነበረውን የዶ/ር ዐቢይ አሕመድን መንግሥት በኃይል ለመጣል ወይም በሽግግር መንግሥት ለመተካት ያለመ የጋራ ግንባር ሲሆን ብልጽግናን በአባልነት እንኳን ለማካተት የወደደ አልነበረም። በደርግ ላይ የፈጸምነውን በብልጽግና ላይ እንደግመዋለን የሚለው የጽምዶው ዋና ዓላማ ነበር። ይህ ደግሞ በሻዕቢያ ትዕዛዝ ትሕነግ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው የዚያን ዘመኑ ጽምዶ ውጤት ነው።

ጦርነቱ የተለወጥበት ነጥብ (ወደ ኋላ ማፈግፈግ)

የትሕነግ ኃይሎች ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ ተቃርበው በነበረበት በዚሁ የህዳር ወር አጋማሽ ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር መሄዳቸውን አስታወቁ። ይህን ተከትሎ የፌደራል መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ፋኖ እንዲሁም የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) የተቀናጀ የመልሶ ማጥቃት እንዲወስዱ ተደረገ። 

በህዳር መጨረሻ የትሕነግ ኃይሎች የያዟቸውን የደብረ ሲና፣ የሸዋ ሮቢትና የከሚሴ አካባቢዎችን እየለቀቁ ወደ ኋላ ሸሹ። በጦርነቱ የተሳተፉ እንደመሰከሩት ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ የደረሰው በዚህ ወቅት ነበር። በተዋጊ ማዕበል ደብረ ብርሃን ግርጌ የደረሰው የትሕነግ ኃይል ክፉኛ ተጎዳ። ጌታቸው ረዳ እና ሌሎች ምስክሮች ወቅቱን በአስከፊነቱ ተረኩት። የአገር መከላከያ ወደ መቀሌ ደጆች በተቃረበበት ቅጽበት ሲ.ኤን.ኤን. “የትሕነግ ኃይሎች አዲስ አበባ ዙሪያ ደረሱ” በማለት በፎቶ የተደገፈውን ዜና ቢያነሳም ለዘገበው የሐሰት ዜና ግን ይቅርታ አልጠየቀም። ከአዲስ አበባ እንዲወጡ የታዘዙ ዲፕሎማቶች በነገሮች ቅጽበታዊ ለውጥ ሰከኑ።

ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓም በአፍሪካ ኅብረት (AU) መሪነት፣ በዋናነት በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ በቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና በደቡብ አፍሪካዋ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ የተመራ የሰላም ቡድን አደራዳሪዎች ድምጻቸው ተሰማ። 

ሁለቱም ወገኖች ማናቸውንም ዓይነት ወታደራዊ ግጭቶች እና የጥላቻ ቅስቀሳዎችን በአስቸኳይ ለማቆም ተስማሙ። የትግራይ ታጣቂዎች (የቲዲኤፍ/ትሕነግ ኃይሎች) ቀላልና ከባድ መሣሪያዎቻቸውን ደረጃ በደረጃ ለመከላከያ ሠራዊት ለማስረከብና ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ለመፍታት ተስማሙ። የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን (የአየር ክልል፣ ድንበር እና የፌደራል ተቋማትን ማስተዳደር) እንዲረከብ፤ ወደ ትግራይ ክልል ይገባ የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ እገዳ ተነስቶ በአስቸኳይ እንዲቀጥል፣ እንዲሁም የተቋረጡት ባንክ፣ መብራት፣ ስልክ እና ትራንስፖርት እንዲመለሱ፤ በትግራይ ክልል ትሕነግንና ሌሎችንም የፖለቲካ ኃይሎች ያካተተ ጊዜያዊ የክልል አስተዳደር (የመሸጋገሪያ መንግሥት) እንዲቋቋም፤ (በዚህም መሠረት በኋላ ላይ ጌታቸው ረዳ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ሆኗል) በጦርነቱ ወቅት ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ አገራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እንዲቀረጽ፤ ከስምምነት መደረሱ ይፋ ሆነ። አወዛጋቢ የወሰን እና የማንነት ችግር ያለባቸው አካባቢዎች በህገመንግሥቱ ማዕቀፍ እንዲፈታ ተወሰነ። 

ስምምነቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አመጣ።  ስምምነቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን መጠነ ሰፊ የዕለት ተዕለት ውጊያና የሰው ሕይወት ታደገ። ትሕነግ ቀደም ሲል በፓርላማ ተጥሎበት የነበረው “የሽብርተኝነት” ስያሜ እንዲነሳለት አደረገ። ስምምነቱ ጦርነቱን ቢያስቆምም፣ በሂደት ግን በራሱ በትሕነግ አመራሮች መካከል (በጌታቸው ረዳ እና በደብረጽዮን ገብረሚካኤል ቡድኖች መካከል) ለተፈጠረው ከፍተኛ የውስጥ የፖለቲካ ክፍፍል ሳቢያ ስምምነቱ በተደረገበት ፍጥነት የተጀመሩ ተግባራት ተቋረጡ። የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ሻዕቢያ “ተኮፊልና” በሚል ተበሳጨ። ቀደም ሲል ከአገር መከላከያ ጎን የነበሩ የሚዲያ ሰዎች፣ የአማራ ኃይሎች፣ የሚታውቁ አክቲቪስቶች ከሻዕቢያ ኩርፊያ ጋር ህብረት ፈጥረው ጸረ መከላከያ ሆኑ። 

ምንም ሳይቆይ በአማራ ክልልና ሲነቀሳቀሱ የነበሩ የፋኖ ኃይሎችና የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ የነበሩ መሳሪያቸውን አንግበው መንግሥትን መውጋት ጀመሩ። በፊት በፊት በሃሜት ይሰማ የነበረው ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይፋ እየሆነ መጣ፤ ሦስተኛው ጽምዶ ተመሠረተ። ከላይ ከተገለጹት ድርጅቶች በተጨማሪ ሻዕቢያን፣ ፋኖን፣ ሱዳንና የዕቅዱ ባለቤት የሆነችው ግብጽን ያካተተው አዲሱ ጽምዶ ወደ አራት ኪሎ ለመገስገስ ቀን እየመረጠ እንደሆነ እየተሰማ ነው። 

የጦርነቱ ዜና ያስደነገጣቸው የትግራይ ተወላጆች ወደ አዲስ አበባ እየተጓዙ ነው። የቻሉም በአፋር በኩል ወደ ጅቡቲ፣ የመን፣ ሳኡዲና ሊቢያ እየፈለሱ ነው። በየበረሃው የሚሞተውንና እስር ቤት የሚሰቃዩትን ቤቱ ይቁጠራቸው እንጂ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ጌታቸው ረዳን በጉልበት፣ ከታደሰ ወረደ ጋር በስምምነት ትግራይን እየመራ ያለው ትሕነግ አሁን በጦርነት ቋፍ ላይ መሆኑን በራሱ ደጋፊዎችና በፋኖ ሚዲያዎች እያስተዋወቀ ነው። 

ምግበይ “የአማራ ሕዝብ ከጎናችን ነው። ብልጽናን በአጭር ጊዜ እናደቀዋለን” እያሉ ነው። በትግራይ ዘጠኝ ድርጅቶች የተካተቱበት የፖለቲካ፣ የወታደራዊና የዲፕሎማሲ ካውንስል ተቋቁሞ በጋራ ብልጽግናን ለመመንገል መነሳታቸውን እነዚሁ ኃይሎች እየገለጹ ነው። ወሬውና ቅስቀሳው ልክ ገና ጦርነቱ ሲጀመር እንደነበረው ዓይነት ነው። በትግራይ ሁለትና ሶስት ልጆቻቸውን ያጡ እናቶች ዛሬም የተቀሩትን ልጆቻቸውን እንዲያሟጥጡ እየተፈረደባቸው ነው። 

ሻዕቢያ ካለበት ፍርሃቻ አንጻር ኢትዮጵያን በጦርነት ለመጥመድ ትሕነግን ዳግም ተሳፍሮበታል። ሻዕቢያ የኢትዮጵያ መከላከያ አሁን ላይ የደረሰበትን አቅም ስለሚረዳ ጦርነቱ ትግራይና አማራ ክልል እንዲቀር በያዘው እቅድ መሰረት ፋኖና ትሕነግን አቀናጅቷል። ከዚህ ቅንጅት ከሞትና አካልን ከመሰዋት ሌላ የትግራይ ሕዝብ ምን እንደሚያተርፍ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። 

ትሕነግ የትግራይን ልጆች ለሱዳን ሸጦ አገራቸውን ከሱዳን ጋር ሆነው እንዲወጉ የክህደት ታሪኩን አውርሷቸዋል። እንኳን ለመፈጸም ለማውራትና ለመስማት የሚከብድ ግፍ በትግራይ ላይ ከፈጸመው ሻዕቢያ ጋር ሊተገበር የማይችል ጽምዶ ፈጥሮ ትዕቢት ያረገዘው ትሕነግ ሌት ከቀን “ለማስፈራራት እንደሆነ” ቢታወቅም አፍሪቃ ቀንድን የሚያባራ ሁከት ውስጥ የሚከት ጦርነት እንደሚፈነዳ እያስታወቀ ነው። ሻዕቢያም “ጽምዶ ቅዱስ ተግባር ነው” በማለት ለትሕነግ የጦርነት ስካር ፈቃድ እያወጣለት ነው። ለመስከር ትንሽ የሚበቃው ትሕነግ የሻዕቢያ የጦርነት ቅራሬ እየተጋተ የትግራይን ልጆች በግድ እያፈሰ ወደ ጦር ሜዳ እያጋዘ ነው። 

የሰከሩት የጦር መሪዎችም በየቀኑ እየወጡ የስካር ፉከራ እያስተላለፉ ነው። ልክ የዛሬ ስድስት ዐመት ያደርጉት እንደነበረው የትግራይን እናት በሃዘን ላይ ሃዘን ለማስታቀፍ እየተክለፈለፉ ነው። ከዓመታት በፊት አምስት እጥፍ ይበልጡት የነበረውን፣ በወጉ መቆም እንኳን ያልቻለውን መንግሥት ሳያሸንፉ ዛሬ ላይ ውጊያ መሞከራቸው ስካር ብቻ ሳይሆን የርዕዮቱ ቴድሮስ ጸጋዬ እንዳለው “ካርቶን ራስ” የመሆን አባዜ ነው። “የጦርነት አንቴና ሆኖ እልቂት የሚስብ ሲግናል” እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። ልብ ያላችሁ የትግራይን እናቶችና ታዳጊዎች ታደጉ።

“በሬ ከመገበው ይልቅ ያኮላሸውን ይከተላል” እንዲሉ ትሕነግ አፈንድዶ እየተጋለበለት ያለው ሻዕቢያ ይህን ፈጽሞ ነበር፤ ዛሬም ብናስታውሰው ጥሩ ነው፤ ዘጋርዲያን “Rusted screws, metal spikes and plastic rubbish: the horrific sexual violence used against Tigray’s women” በሚል ርዕስ የዘገበው ሙሉ ጥንቅር እዚህ ላይ ይገኛል

Rusted screws, metal spikes and plastic rubbish: the horrific sexual violence used against Tigray’s women

በጥቅምት 2013 ዓም የተቀሰቀሰውን የትግራይ ጦርነት ተከትሎ፣ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት (ሻዕቢያ) በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የጦር ወንጀሎች መፈጸሙን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN)፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች (Amnesty International እና Human Rights Watch) ባደረጓቸው ምርመራዎች አረጋግጠዋል።

ሻዕቢያ በጦርነቱ ወቅት የፈጸማቸው ዋና ዋና ግፎች በአጭሩ የሚከተሉት ናቸው፦

  • በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመ ጭፍጨፋ (Massacres)፦ ሰራዊቱ ወደ ተለያዩ የትግራይ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች በገባበት ወቅት በንጹሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጭፍጨፋ ፈጽሟል። ለዚህ ማረጋገጫ ተደርጎ የሚወሰደው በህዳር 2013 ዓም በአክሱም ከተማ የተፈጸመውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን የተገደሉበት፣ እንዲሁም በማሕበረ ደጎ እና በሌሎች አካባቢዎች የተመዘገቡት የጅምላ ግድያዎች ናቸው።
    • ጎልጉል ያቀናበረው መረጃ እዚህ ላይ ይገኛል
  • ጾታዊ ጥቃት እና አስገድዶ መድፈር (Widespread Sexual Violence)፦ ጾታዊ ጥቃትን እንደ ጦርነት ስትራቴጂ (Weapon of war) በመጠቀም በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ እጅግ ዘግናኝና ስልታዊ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን ፈጽሟል። ይህ ጥቃት በቡድን የተፈጸመ፣ ሰለባዎቹን ለአካልና ስነ-ልቦና ስብራት የዳረገ ነበር።
  • የንብረት ዘረፋና ውድመት (Looting and Destruction)፦ የኤርትራ ሰራዊት በትግራይ ክልል የሚገኙ የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቶችን፣ የህክምና ተቋማትን (ሆስፒታሎችና ክሊኒኮችን)፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የግል መኖሪያ ቤቶችንና የንግድ ድርጅቶችን በስፋት ዘርፏል። መውሰድ የማይችለውን ንብረትና ማሽነሪ ደግሞ በማውደም የክልሉን የኢኮኖሚና ማህበራዊ መዋቅር ክፉኛ አናግቷል።
  • በሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ላይ የተፈጸመ ጥቃት፦ እንደ ዋልድባ ገዳም እና አል-ነጃሺ መስጂድ ያሉ ጥንታዊና ታሪካዊ የሃይማኖት ቦታዎች ላይ ጥቃት በማድረስ፣ በመዝረፍና የሃይማኖት አባቶችን በመግደል ረገድ የሻዕቢያ ሰራዊት ስም በሰፊው ይነሳል።
  • የኤርትራ ስደተኞችን ማጥቃት፦ በትግራይ ክልል (ለምሳሌ በሽመልባና ህጻፅ መጠለያዎች) ተጠልለው የነበሩ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚ ስደተኞችን በማደን፣ በመግደልና አንዳንዶቹን በኃይል ወደ ኤርትራ ጠልፎ በመመለስ አለም አቀፍ ህግጋትን ጥሷል።

እነዚህ ተግባራት በወቅቱ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ውግዘትን ያስከተሉ ሲሆን፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላም ቢሆን የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ወሰን ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ ግፊት እንዲደረግ ካደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

ለትሕነግ ታጣቂ ቲዲኤፍ ወይም የትግራይ መከላከያ ሠራዊት የሚለውን ስያሜ እንዳወጣላቸው የሚናገረውና አንዳንዶች “ነጩ ወያኔ” የሚሉት የምስራቅ አፍሪካ ተመራማሪው የኖርዌይ ተወላጁ ሼትል ትሮንቮል ትሕነግ ከሻዕቢ ጋር መጣመዱን አልደገፈም ነበር። በፍጹም ባልተጠበቀ ሁኔታ ጽምዶን የተቃወመው ሼትል ጽምዶን “ራዕይ አልባ እና የተንሸዋረረ” የሚል መደምደሚያ በመስጠት ይልቅ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ኢሳያስ ከሥልጣኑ በህወት ወይም በተፈጥሮአዊ ሞት ሲለቅ ኤርትራ ምን ትሆናለች የሚለው ነው ብሏል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባት በማለት መጠቆሙን ጎልጉል አዲስ ሪፖርተርን ጠቅሶ ጥቅምት ላይ መዘገቡ ይታወሳል።  

“የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው … “ፅምዶ” ራዕይ ዓልባ” ነው – ሼትል ትሮንቮል

የትሕነግ የጽምዶ ልክፍት ብዙዎች እንደሚገምቱት ቅርብ ጊዜ የጀመረው ሳይሆን እጅግ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። የተፈጠረው በሻዕቢያ ልክፍት ነው፤ ሻዕቢያ ተራራ ሥር ተሸሸጎ ሊሞት ሲጣጥር በነበረበት የሰሜኑ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልጆችን “ለሥልጠና” በማለት ወደ ኤርትራ ልኮ የሰዋቸው ትሕነግ ነው። ለዚህ “ውለታው” ሻዕቢያ ዕውቅና እንኳ አልሰጠውም። ግን አሁንም ካኮላሸው ሻዕቢያ ጋር ሌላ ጽምዶ በመመኘት የትግራይን ልጆች ለሌላ ዕልቂት እያሰናዳቸው ነው። አንዴ ስለተኮላሸ ከጽምዶ ልክፍት መውጣት አይችልም።

የልክፍት ዓይነቶች የተለያዩ እንደሆኑ ስለጉዳዩ የሚያውቁ ይናገራሉ። ከፊል ልክፍት፣ ዘዋሪ ልክፍት፣ ቅጽበታዊ ልክፍት፣ ወዘተ። ልክፍቱ መላ አካልን ሲቆጣጠርና ግለሰቡ የሚያደርገውና የሚፈጽመው ሁሉ ራሱ አስቦ ሳይሆን በለካፊው ውግ ብቻ ሲሆን ግን “ሙሉ ልክፍት” ይባላል። ሌሎቹ የልክፍት ዓይነቶች እንደምንም ይፈወሳሉ ይላሉ ዐዋቂዎቹ፤ ሙሉ ልክፍት ግን የመፈወስ ተስፋ የሌለውና መፍትሔው ሞት ብቻ የሆነ ልክፍት ነው።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Filed Under: Politics, Right Column Tagged With: eplf is a terrorist, ethiopian terrorists, operation dismantle tplf, tplf terrorist, Tsimdo

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

Recent Posts

  • ለሱዳንና ኤርትራ ሲከራከሩ የነበሩት አበባው ባለመመረጣቸው “በጣም ተድጃለሁ” አሉ June 26, 2026 12:29 am
  • “ትህነግ ወደ ዓለምአቀፍ ወንጀለኛነትና አሸባሪነት እየተምዘገዘገ ነው” June 25, 2026 01:00 am
  • አሜሪካ በሕገወጡ ትህነግ አመራሮች ላይ ጠንካራ የቪዛ እገዳ ጣለ June 18, 2026 10:29 am
  • እንደ ሌሊት ወፏ የሚንቀሳቀሰው ኢህአፓ/ትብብር   June 18, 2026 09:36 am
  • የታርጋ ጫጫታ June 15, 2026 05:16 pm
  • ፋንታኹን ዋቄ ከአሜሪካ የሃይማኖት እልቂት አወጁ June 15, 2026 02:12 am
  • ሕገወጡ ትህነግ ወጣቶችን ለዳግም ዕልቂት እያሰናዳ ለፈረንጆች “ኢትዮጵያን አውግዙልኝ” እያለ ነው June 11, 2026 12:57 am
  • በሐዘንና ግልፅ ደብዳቤ ስም የተሸፈነ የድህረ ምርጫ ሀገር የማተራመስ ስትራቴጂ June 10, 2026 12:19 am
  • የጽምዶ ልክፍት June 9, 2026 12:49 am
  • ገዳዩ ማነው? አስገዳዩስ ማነው? June 5, 2026 02:37 pm
  • ጽንፈኝነት ግን በኢትዮጵያ ምድር ፈጽሞ ቦታ የለውም! June 5, 2026 01:47 pm
  • የትብብሩ “ብናሸንፍም ፓርላማ አንገባም” መግለጫ “ወንበር ስታጡ ነው” የሚል ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ June 4, 2026 12:04 am
  • አዲሱ የትራምፕ የምርጫ መመሪያ፡ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን አፍ ያስዘጋ፤ ተቃዋሚዎች ተስፋ ያስቆረጠ June 3, 2026 08:50 pm
  • “ኢህአፓ ከምርጫው በኋላ ይሰነጠቃል” May 29, 2026 07:07 pm
  • ሪፖርተር፡ “ስውር ተልዕኮ” – በከባድ ወንጀል ሊከሰስ May 6, 2026 11:55 pm
  • የፋኖ ኃይል በደረሰበት ጉዳት ሃምሳ ሺህ የሚጠጋ ትጥቅ ጥሎ ጠፋ April 29, 2026 02:27 pm
  • አዲሱ የቴድሮስ ካሳሁን 888 ኮድ፤ እንደ 666?! April 15, 2026 05:53 am
  • ምኑ ነው ያሳቃችሁ፤ ያስደሰታችሁ? April 2, 2026 10:52 am
  • የጀዋር መሃመድ የፖለቲካ ማንነት እና የባዕዳን ተልዕኮ April 2, 2026 10:16 am
  • ከግብፅ በዳያስፖራ ትርምስ ጠማቂዎች በኩል ፋኖ ወደ አዲስ አበባ የላከው “ስጦታ” March 27, 2026 09:14 am
  • “ሰላማዊ ታጋዮቹ” እነ ልደቱ ከአራጁ ሸኔ ጋር ተጣምረዋል March 25, 2026 01:04 pm
  • ጸረ-ኢትዮጵያዊ የሆነው የሪፖርተር አዘጋገብ March 19, 2026 11:54 am
  • የአውሬው ሪፖርተር ቀላቢዎች፡ የኦሮሚያ የልማት ድርጅቶች March 18, 2026 10:48 am
  • የጃኖ ስጦታና የዶሮ ፖለቲካ በጎንደር March 10, 2026 09:24 am
Copyright © 2026 · Goolgule