• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ሻዕቢያ “አክሱም ገብቶ ወጣቶች በጅምላ ሲረሽን ጸብ ተፋፍሟል …”

February 4, 2026 01:15 pm by Editor Leave a Comment

ሻዕቢያና ትህነግ ጽምዶ ሲመሠርቱ ሻዕቢያ ለትህነግ ሰዎች እንደ ቅድመ ሁኔታና እንደ ትዕዛዝ የሰጠው ሁለት ነጥቦች ያካተተና አፋችሁን ዝጉ የሚል ነበር። አንደኛው ሻዕቢያ በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘር ፍጅት ወይም ጄኖሳይድ ፈጽሟል ብላችሁ መናገር አቁሙ፤ ሁለተኛው የሻዕቢያ ታጣቂ የትግራይን ሴቶች ደፍሯል የሚለውን ትንፍሽ ስትሉ እንዳንሰማ የሚሉ ነበር። ሌሎችም አሉ፤ እነዚህ ግን ዋንኞቹ ናቸው።

ትህነጋውያንም ጌታና ፈጣሪያቸው ለሆነው ሻዕቢያ መታዘዝ ተፈጥሮአዊ ግዴታቸው ነውና “ጌታ ሻዕቢያ ሆይ! ፍላጎትህ ለኛ ትዕዛዝ ነው፤ እንደ ፈቃድህ ይሁንልህ” ብለው “ጄኖሳይድ” የሚለው ቃል ትግሪኛ እስኪመስል ድረስ ሲጮኹበት የነበረው ልሳናቸው ተዘጋ፤ ሚዲያቸው ጸጥ እረጭ አለ፤ ሻዕቢያም መልካም ነው፤ አሁን ወደ ጽምዶ እንቀጽል አለ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትላንቱ የፓርላማ ውሎ ከዚህ በፊት በመንግሥት ደረጃ ያልተሰማ አንድ አዲስ መረጃ ተናግረዋል፤ ስለ ሻዕቢያ፤ እንደ ቀድሞውም የኤርትራ መንግሥት ብለው ሳይሆን ሻዕቢያ በማለት የኢሳያስ አፈወርቂን ወንጀል የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች በተገኙበት ለዓለም ይፋ አደረጉ። የጽምዶ አጋፋሪዎች ተሸበሩ፤ የሻዕቢያ ተከፋዮች ከዲሲ ማጓራት ጀመሩ።  

ከዚህ በፊት ዓለምአቀፍ ሚዲያ የዘገበው፣ የትግራይ መስተዳድር በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አስጠንቶ በማስረጃ ያውጣው፤ በበርካታ የትግራይ ተወላጆች በማስረጃ የተነገረው፤ በአቡነ ሰላማ የተወገዘው የሻዕቢያ ግፍ ዐቢይ ሲናገሩት ጽድቅ ሆነ። “ገዱ የውጭ ጉዳይ አልነበረም”፤ “ዐቢይ መዋሸት ልማዱ ነው”፤ “ኤርትራን ለመውጋት በማሰብ ነው”፤ ወዘተ የሚሉና የኢትዮጵያን ፖለቲካ የማይከታተል ፊጂ ደሴቶች በእስር የሚገኝን ሰው እንኳን የማያሳምን ነገር መወራት ወዲያ ጀመረ። ትዕዛዙ የተሰጠው ከአስመራ ሲሆን ትዕዛዝ ሰጪው የማነ ገብረመስቀልም ይህንኑ አስተጋብቷል።በትላንቱ የፓርላማ ውሎ የተነሱ ሌሎች ጉዳዮችም አሉ፤  ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥትን የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ዝርዝር ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጥያቄዎቹ ጠቅለል ባለ መልኩ እነዚህ ነበሩ፤

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተመራጭ የሆኑት ዶ/ር አበባው ደሳለው፦

የሰላም እጦት በዋነኝነት ግጭት ባለባቸው በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ ትግራይ እና ጋምቤላ ይስተዋላል። ነገር ግን ግጭት በሌለባቸው የዲሞክራሲ መብታቸውም ለማስጠበቅ በሚሞክሩ ‘የመዋቅር እና የማንነት ይከበርልን’ ጥያቄ ባነሱ ግለሰቦችም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳለ ለምሳሌ በደቡብ ክልል አባላት በተደጋጋሚ ጊዜ ይጠቅሳሉ።

ይህንን የሰላም እጦት ለመቅረፍ በተደጋጋሚ ጊዜ የታጠቁ ኃይሎች መካከል እውነተኛ ድርድር እንዲደረግ፣ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ፣ የንጹሃን ጥቃት እንዲቆም ላለፉት ሶስት አመታት ወትውተናል። ሆኖም መንግሥት ቀደም ብሎ ከኦሮሚያ ታጣቂዎች ጋር በቅርቡ ደግሞ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የታጣቂ መሪዎች ጋር “ድርድር አደረግኩ” ቢልም ምንም የተሻሻለ የሰላም ሁኔታ እንደሌለ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

አፋብን ወይም አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ የሚል መጠሪያ ያለው 15 አመራሮችን የያዘ ድርጅት፤ አማራ ክልል ያሉ ታጣቂዎች መስርተናል እያሉ ባሉበት ወቅት መንግሥት ደግሞ “እነዚህ ኃይሎች ከድርድር አግደናቸዋል” ከሚሏቸው ኃይሎች ጋር ድርድር ላይ መሆኑ ለሰላሙ ምን ያህል ይጠቅማል? አዲስ ከተመሰረተው አፋብን ተብሎ ከሚጠራው ድርጅት ጋርስ መንግሥት ድርድር ጀምሯል ወይ?

እውነተኛ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ መንግሥት አፈንግጠው ከሚወጡ ታጣቂዎች ጋር ከመደራደር፤ ለምንድን ነው ብዙ ጦር ሰራዊት ካላቸው እና በአግባቡ ከተደራጁ ታጣቂዎች ጋር እውነተኛ ድርድር አድርጎ ለሀገራችን ሰላም የማያጎናጽፈው? መንግሥትዎ የውስጥ ሰላምን ሳያረጋግጥ በተደጋጋሚ የሚነሳውን በርካታ የልማት ጥያቄ፣ የወደብ ጥያቄ፣ ስኬታማ ምርጫ እና ሀገራዊ ምክክር እንዴት ሊያሳካ ይችላል?

መሐመድ ሹኩር (ዶ/ር)፦

ኢትዮጵያ በፈረመችው የአቡጃ ዲክላሬሽን ሀገራት ከ15 በመቶ በታች ያልሆነ ነው የሚመድቡት (የጤና በጀት) የእኛ ዓመታዊ በጀታችን ገና 3 በመቶ ነው።

ብዙ ሀገራት ይህን አሳክተዋል፤ ጎረቤቶቻችንም ይህን ያህል ባይደርሱም ከእኛ የተሻለ እየመደቡ ነው ያሉት።

የእኛ የጤና በጀት ካለው የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችና የመድኃኒቶች ዋጋ መጨመር፣ ካዳዲስ በሽታዎች መከሰት፣ ከሕክምና ውጭ ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እንዲቻል የታሰበ ነገር ቢኖር?

አብርሃም ባርታ (ዶ/ር)፦

በአሁኑ ወቅት የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን በዝምታ ውስጥ ሆነው የምርጫ ድባብ እንዳይኖርና ሂደቱ በተቀዛቀዘ ሁኔታ የቀጠለበት ሁኔታ ስላለ ይህ የሆነበት ምክንያት ማብራሪያ ቢሰጥ።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን የሚገልጹበት እኩል ሜዳ በሌለበት ሁኔታ የምርጫ ውድድር እንዴት ጤነኛ ሊሆን ይችላል? ከዚሁ ጋር በተያያዘ የምርጫው ታማኝነትና ተቀባይነት እንዲያጣ በቅድመ ምርጫ ወቅት በተለየ ሁኔታ የሕግ ሂደትን ባልተከተለ ሁኔታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የዘፈቀደ እስር፣ ማዋከብና ማንገላታት እየተፈጸመባቸው ይገኛል።

የኢዜማ አባላትን ጨምሮ የታሰሩበት ሁኔታ አለ። ይህ የመወዳደሪያ ሜዳና ምህዳሩን በከፍተኛ ሁኔታ ያጠባል።

በመሆኑም መንግሥት ቁርጠኛ ነኝ የሚልበትን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ ጥያቄ ውስጥ አይገባም ወይ?

አቶ ይሳቅ ቦሩ፦

ነዳጅ ላይ በየወሩ የዋጋ ጭማሪ የሚደረግበት ዋነኛ ምክንያት ምንድነው? እንዲሁም አሁን ድረስ ያልተቀረፈው የነዳጅ ስርጭት ችግሮች በየጊዜው የሚታዩ ረጅም የነዳጅ ፍለጋ ሰልፍና የአቅርቦት መቆራረጥ መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው?

አቶ ተረፈ ጎዴ:-

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባት የሀገር ውስጥ ባንኮችን የአቅም ውስንነት ተወዳዳሪነት ሊያዳክም ይችላል የሚል ስጋት እየተነሳ ይገኛል።

ይህንን ስጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት የውጭ ባንኮች መግባት በሀገር በቀል ባንኮች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስና ፍትሃዊ ውድድር እንዲኖር ለማድረግ ምን አይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ተወስደዋል?

መብራቱ አለሙ (ዶ/ር)፦

ምርጫ ሲደርስ በተለይ በታችኛው አመራር የዲሞክራሲ ምህዳሩን የማጥበብ፣ እጩዎችን፣ ታዛቢዎችን፣ ደጋፊዎችን የማዋከብ፣ የማሰር፣ የሚዲያ ነጻነትን የመጋፋት አዝማሚያዎች ይታያሉ።

በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባሸነፉባቸው አካባቢዎች ላይ በፓርቲ አመራሮች፣ በመራጩ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ሰብአዊ መብት ጥሰት መራጩ ሕዝብ ዳግም ተፎካካሪ ፓርቲ እጩዎችን እንዳይመርጥ የስነ ልቦና ጫና እየፈጠረ ይገኛል።

እነዚህን ችግሮች እልባት እንዲሰጣቸው ጭምር በተደጋጋሚ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታ ብለናል፤ ምርጫ ቦርዱም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር፣ ከገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እየመደበ ሶስትዮሽ ኮሚቴ እያዋቀረ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ጥረቶች ተደርገዋል፤ አሁንም ግን በዘላቂነት አልተፈቱም።

በመጪው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች እንዳይደገሙና ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ታማኝ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የመንግሥት ቁርጠኝነት ምን ይመስላል? ምን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል?

ከምክር ቤቱ ለተነሱት ጥያቄዎች ጠቅላዩ የሰጡት ማብራሪያና ምላሽ ከዚህ በታች በርዕስ ተከፋፍሎ ተቀምጧል።

በኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛ የሆነውን የኤአይ (AI) ዩኒቨርሲቲ።

“ወጣቶችን ለነገ ውድድር ከወዲሁ ማዘጋጀት ያስፈልጋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከዚህ አንጻር ከኢትዮጵያ አምስቱ የእደገት ምሶሶዎች አንደኛው ቴክኖሎጂ እንዲሆን በማደርግ ለትውልድ ሲሰራ ቆይቷል” ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኤአይ ተጠቃሽ መሆኑን በኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛ የሆነውን የኤአይ ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

“ዩኒቨርሲቲው በሚቀጥለው አንድ ዓመት ውስጥ ስራ ይጀምራል። ይህ ዩኒቨርሲቲ አባቶቻችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ገንብተው ስመጥር እንዳደረጉት ሁሉ ለልጆቻችን ለነገ የተሻለ ዘመን ይዞ ይመጣል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምንም ዓይነት እርዳታም ሆነ ብድር አለመውሰዷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ለሕዳሴ ግደቡ ግንባታ ከማንም ምንም ዓይነት እርዳታ ሆነ ብድር አልወሰድንም።

“በሕዳሴ ላይ አንድም ብር እርዳታ፣ አንድም ብር ብድር ኢትዮጵያ አልወሰደችም” ያሉ ሲሆን “በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቁርጠኛ አቋም በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን በቁርጠኝነት ጨክነው በጋራ ቆመው ስለሰሩ የተከወነ ፕሮጀክት ነው” ብለዋል።

“ህዳሴን ካለ አንድ ብር እርዳታ፣ ካለ አንድ ብር ብድር ያሳካ መንግሥት ፕሮጀክት አይሰራም ሊባል አይችልም ግፍ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “አሜሪካ ህዳሴ ግድቡን በገንዘብ ረድታለች፣ እኛ ደግፈን ነው የተሰራው ” በማለት ከሦስት ጊዜ በላይ መናገራቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ በዋይትሃውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፣ “ዩናይትድ ስቴትስ የህዳሴ ግድብን በገንዘብ በማገዟ ኃላፊነት ትወስዳለች” ሲሉ ተደምጠው ነበር።

“ለግድቡ ማን እንደከፈለ ታውቃላችሁ? ዩናይትድ ስቴትስ” ሲሉ በራሳቸው ጠያቂና መላሽ ሆነው የተስተዋሉት ትራምፕ፣ “ይች ሀገር በገንዘብ አግዛለች፣ አላውቅም ምናልባት የሪፐብሊካን መሪ ሊሆን ይችላል፣ ግን ነው ብዬ አላስብም፣ የዲሞክራት ይመስለኛል” ነበር ያሉት።

ዐቢይ “በህዳሴ ላይ አንድም ብር እርዳታ፣ አንድም ብር ብድር ኢትዮጵያ አልወሰደችም” ያሉት ሜጋ ፕሮጀክቶች እምብዛም ስለሌሉ ወጣቶች ለስራ አጥነት ጨምር እየተጋለጡ በመሆኑ ለዚሁ ምላሽ እንዲጠሱ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ ሲሆን፣ “ከዚህ ንግግራቸው አስከትለውም፣ ” ግን በዚህ አላበቃም፤ ህዳሴ ከአፍሪካ አንደኛውን ሰርተናልና ሌላ አያስፈልግም እኮ አላለችም ኢትዮጵያ” ብለዋል።

“በአፍሪካ ሦስተኛውንም ኮይሻ እየገነባን ነው ያለነው። የንፋሱን ሳንጨምር። በርካታ ፕሮጀክቶች ይሰራሉ” ነው ያሉት።

“‘ፕሮጀክቶ ቋሟል፤ ሜጋ፣ ሜጋ ፕሮጀክት የለም’ ለተባለው። እውነት ነው ፕሮጀክት የለም። ግን ከአፍሪካ አንደኛው ኤርፓርት ኢትዮጵያ ውስጥ ተጀምሯል። እንደዚህ ያለ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ አስባም ሰርታም አታውቅም” ሲሉ መልሰዋል።

“እውነት ነው ፕሮጀክት ቀንሷል የማዳበሪያ ፋብሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጀምሯል። ፕሮጀክት ቀንሷል የጋዝ ፌዝ ዋን ጨርሰን ፌዝ ቱ እና ሪፋይነሪ እየሰራን ነው” ሲሉ በርካታ ግዙፍ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን አሳውቀዋል።

“በሜጋ ፕሮጀክት፣ በፕሮጀክት ክትትል፣ በፕሮጀክት አፈጻጸም፣ በፕሮጀክት አመራር እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ድፍን አፍሪካ ገና ከኢትዮጵያ ይማራል” ብለዋል።

“ሰባት ቀን – ቀን እና ማታ በየጥሻው ውስጥ የምንዞረው ፕሮጀክት ተጀምሮ ሳያልቅ እንዳይቆም ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ነዳጅን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን አሉ ?

“ነዳጅ ባለፈው አመት ከ60 ዶላር እስከ 90 ዶላር ዋዥቋል መካከለኛው ምስራቅ በነበረው በምታውቁት ቴንሽን በቀይ ባህር በኢራኑም ጉዳይ የነዳጅ ዋጋ ከፍና ዝቅ ብሏል።

በየጊዜውም መዋዠቁ ከእኛ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም የምንገዛው ጉዳይ ስለሆነ ሻጮች ሲጨምሩ ይጨምራል ሲቀንሱ ይቀንሳል።

በየጊዜውም ዋጋ ተቀያየረ ለተባለው እንደዚህ አይመስለኝም በሌላው ዓለም እኔ ማውቀው በነዳጅ ማደያ በየቀኑ የነዳጅ ዋጋ ይለጠፋል በየቀኑ አንዴ ይጨምራል አንዴ ይቀንሳል።

እኛ ባለፈው አንድ አመት ተኩል የነዳጅ ዋጋ የቀየርነው ሰባት ጊዜ ብቻ ነው እየተሸከምን አብዞርብ እያደረግን በየቀኑ ሲጨምር ከጨመርን ህዝባችን ይጎዳል በሚል ማለት ነው።

በዋጋ ደረጃ ስንመለከት ጅቡቲ ነዳጅ ከተማው ውስጥ 269 ብር፣ ናይሮቢ 220፣ ካምፓላ 218 ብር አዲስ አበባ 129 ብር ነው ህጋዊ ዋጋው።

በፈለጋችሁት መመዘኛ ሳናመርት ከውጭ ገዝተን ፖርት ሳይኖረን በየመሀሉ እየተቀሸበ በድጎማ ሃይል ግን ከእኛ ሰፈር ካሉና ፖርት ካላቸው አገራት ያነሰ ዋጋ ነው የምናቀርበው።

ከዚህ ቀደም ከምናስገባው ቁጥር ይበልጣል አሁን የምናወጣው ወጪ።

ታዲያ ሰልፉንና ችግሩን ምን አመጣው ያላችሁ እንደሆነ ስግብግብ ሰዎች ከዚህ ድጎማ ለመቀራመት የሚያደርጉትን ጥረት በበቂ መቆጣጠር አልቻልንም ሲስተሙ ለዛ ስለማይመች።

እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ጫፍ አካባቢ ብትሄዱ ሱማሌ ክልል ብትሄዱ ቦረና ብትሄዱ ጫፍ ጫፍ አካባቢ ማደያ ማለት ልክ እንደ ፋሽን መጥቷል።

ለምን ከዚህ ድጎማ እየወሰዱ ለመሸጥ? በእኛና በጎረቤት አገራት መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት እዚህ ያለውን ነገር ለማመሰቃቀል ምክንያቱ ነው።

ይሄን ለመፍታት የአውቶሜሽን ስራ እየሰራን ነው እያንዳንዱ ቦቴ ካለበት እስከሚገባበት ለመቆጣጠር እንድንችል ሁለተኛ ከገባ በኋላ በእያንዳንዱ ማደያ ያለውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስራ ለመስራት እየሞከርን ነው።

ሲስተሙ ሲያልቅ በተወሰነ ደረጃ ይቀንሳል በቅርቡም ጅቡቲ በነበረን ጉዞ ዋነኛ አላማው እነዚህ ከፖርት የሚወጡ ምርቶች መሀል ላይ በሬልዌይና በፖርት መካከል ክፍተት ስላለ ያን ክፍተት የሚዘጉ ስራዎች ለመስራት ለመነጋገር ነው የሄድንው” ብለዋል።

“የቸገረን የወልቃይት አካባቢ ነው” 

“እኔ አልወስንም የወልቃይትን ጉዳይ፣ እናንተም አትወስኑም፤ የሚወስነው የዚያ አካባቢ ህዝብ ነው!”

ከፓላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በተፈናቃዮችን ጉዳይ ተናግረው በስፋት ስለወልቃይት ጉዳይ አብራርተዋል።

“መፈናቀልን በሚመለከት ኢትዮጵያውያን በፈለጉት ከባቢ በሰላም ሰርተው መኖር ህገመንግሥታዊ መብታቸው ነው። ማንም የሚሰጣቸው የሚከለክላቸው ጉዳይ አይደለም፤ መብት ነው።

“የተፈናቀሉ ሰዎች መመለስ ይፈልጋሉ፤ ቀድመው የነበሩበት አካባቢም ‘ይምጡልን ይላሉ’። ማነው የያዛቸው? ነው ጉዳዩ አሁን። ለምሳሌ ጦርነት ሲጀመር ከኢሉባቡር ሸሽተው ትግራይ የሄዱ አርሶ አደሮች ነበሩ። ከዛ የመጣችሁ ሰዎች አጥኑ ይሄን ጉዳይ ትክክለኛ መረጃ ነው።

“ሰዎቹ ሸሽተው ትግራይ ገብተዋል፤ ኢሉባቡር ያሉ አርሶአደሮች ከእነርሱ ማሳ ቡና ለቅመው ሸጠው ገንዘቡን በአካውንታቸው ያስገባሉ፤ ሰዎቹ የሉም። ከእርሻቸው ላይ የተመረተ ምርት ሸጠው ገንዘቡን በራሳቸው አካውንት ያስገባሉ።

“ሰዎቹ ‘የኛ ሰዎች በሌለንበት ሰርተው አካውንታችን እያስገቡ ነውና በቃ እንመለስ’ ብለው ተመልሰው ኢሊሉባቡር አሉ አሁን፣ እየኖሩ ነው” ብለዋል።

ወልቃይትን በተመለከተ ምን አሉ?

“በራያ አይታችኋል፤ ሰው ተመልሷል እየኖረ ነው። በጸለምት አይታችኋል፤ ሰው ተመልሷል እየኖረ ነው። ብዙው ኦሮሚያ አካባቢ ተመልሷል እየኖረ ነው። የቸገረን አሁን የወልቃይት አካባቢ ነው።

“ልክ ገበሬ ዘር ዘርቶ ከዝናብ በኋላ ምርት እንደሚጠብቀው፣ አምኖ ዘር ዘርቶ ከሆነ ከወራት በኋላ የተሻለ ያፈራል ብሎ እንደሚጠብቀው ስደት፣ መፈናቀል፣ ስቃይ ዘርተው ከሌሎች ኃይል እርዳታ የሚጠብቁ ሰዎች አሉ።

“ስቃይ ዘርተው፣ መከራ ዘርተው፣ ችግር ዘርተው። የተፈናቀለን ‘አትሄድም’ ብለው ይዘው ማለትተ ነው። ተፈናቃይ ያልተመለሰበት አካባቢ ሰው እንዳይመለስ ስለፈለገ ሳይሆን፣ ሰዎቹ መመለስ ስለማይፈልጉ ሳይሆን ተፈናቃይ መያዣ ያደረገ ፓለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖሩ ነው።

“ልክ መንገድ ላይ ስትሄዱ የኔ ቢጤዎች ልጆቻቸውን መለመኛ እንደሚያደርጉት፣ ልጆቻቸውን ታቅፈው ይለምኗችኋል፤ ልክ ብር ስትትጧቸው ልጆቻቸውን ተቀበል፣ ተቀበይ ይላሉ። ከተቀበሉና ከሄዱ በኋላ ወዲያውኑ እነርሱ ይቀበሏቸዋል።

“የኔ ቢጤዎች ልጅቻቸውን መለመኛ እንደሚያደርጉት አንዳንድ ፓርቲዎች ተፈናቃይን የራስ ህልውና ማቆያ ያደርጓቸዋል። ይሄን ለማሻሻል ብዙ ሙከራ ተደርጓል። ብዙ ስራ ተሰርቷል።

“የይገባኛል ጥያቄ በአማራ እና በትግራይ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል። ሁለቱም ክልሎች ማስረጃ አስደግፈው ተቀባይነት ይኑረውም አይኑረውም ‘ይሄ ቦታ ይገባኛል’ ይላሉ።

“ፌደራል መንግሥት እያለ ያለው ሰው አይፈናቀል። ወደነበረበት ይመለስ። ራሱን ያስተዳድር እራሱ ይወስነው ነው። አንድ ሰው እዚህ ተቀምጦ ከሚወስን በሪፈረንደም በህጉ አግባብ ይወሰን ነው።

“ማን መወሰን ይችላል በዚያ ህዝብ ህልውና መሻት ላይ? … የትኛው ባለስልጣን ነው የሚገባህ እዚህ ነው ብሎ መወሰን የሚችለው?

“በዚህ ምክንያት የወልቃይት ህዝብ እንደየትኛውም ኢትዮጵያዊ በጀት መደገፍ፣ ትምህርት ማግኘት ሲገባው፣ ፌደራል መንግሥት ማገዝ የሚገባውን ነገር ሳያግዘው እንዲቆይ ያደረገው ጉዳይ፦ ይሄ ጉዳይ በሰላም ቢፈታ ይሻላል፤ ሁለት ወንድማማች ህዝብ በሚያባላ መንገድ ሊፈታ አይገባውም ከሚል ጽኑ እምነት ነው።

“እኔ አልወስንም የወልቃይትን ጉዳይ፣ እናንተም አትወስኑም፤ የሚወስነው የዚያ አካባቢ ህዝብ ነው። ለዚያም ፓርቲዎች አስቻይ ነገር መፍጠር የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል” ብለዋል።

“የእኛ ባንኮች ባንክ መሆን አለባቸው እቁብ ናቸው ብዬ አላሳንሳቸውም፣ ግን ባንክ መሆን አለባቸው”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ” የውጭ ባንኮች መግባት በሀገር በቀል ባንኮች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስና ፍትሃዊ ውድድር እንዲኖር ለማድረግ ምን አይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ተወስደዋል?” በሚል በፓርላማ አባል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ “ባንኮች ባንክ መሆን ባለባቸው ደረጃ የማደግ ሂደታቸው በውድድር መታጣት ምክንያት ውስንነት ገጥሞታል” ብለዋል።

“ለዚህም ሲባል የውጭ ባንኮች ቢገቡ ካፒታል (capital) እና ቴክኖሎጂ ስለሚያመጡ ለአጠቃላይ እድገት ብቻ ሳይሆን የእኛንም ፋይናንሻል ሴክተር የማሳደግ ሚና ይኖራቸዋል ” ሲሉም ተደምጠዋል።

“ሁሉም ባንኮች ለማደግ ጥረት እያደረጉ ነው ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ለውጭ ባንኮች ሴክተሩ መከፈቱ ችግር አያመጣም ወይ? የእኛዎቹን አያቀጭጭም ወይ? አይጎዳም ወይ? እንዴት ይታያል? የተባለው ትክክለኛ ኮንሰርን (concern) ነው።

“ላለፉት ሃያ ሰላሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ባንኮች ያለ ውድድር ብቻቸውን እንዲሰሩ ሙከራ ተደርጓል በዚያም የተገኘ ውጤት፣ ልምድ፣ ሀብት አለ ግን ሀብቱ ማደግ ባለበት ደረጃ እያደገ አይደለም ባንኮች ባንክ መሆን ባለባቸው ደረጃ የማደግ ሂደታቸው በውድድር መታጣት ምክንያት ውስንነት ገጥሞታል።

“ለዚህም ሲባል የውጭ ባንኮች ቢገቡ ካፒታል (capital) እና ቴክኖሎጂ ስለሚያመጡ ለአጠቃላይ እድገት ብቻ ሳይሆን የእኛንም ፋይናንሻል ሴክተር የማሳደግ ሚና ይኖራቸዋል።

“የእኛ ባንኮች ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያላቸው ድርሻ ከአምስት እስከ ሰባት ፐርሰንት (5-7%) ብቻ ነው።

“ኬንያ ግን ስንሄድ ከስድስት እስከ ስምንት ፐርሰንት ድርሻ አላቸው፣ ናይጄሪያ ስንሄድ ከአስር እስከ አስራ ሁለት ፐርሰንት፣ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ከአስራ ሶስት እስከ አስራ አምስት ፐርሰንት (13-15%) ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው የባንክ ሴክተር ድርሻ አለው ለምን? ለረጅም ጊዜ የፕራይቬት ባንኮች በደረጃ አቅም ስለገነቡ የውጭውን ጨምሮ ይህንን እድል ማጣት የለብንም።

“በአንድ በኩል በቂ ብድር አይቀርብም፣ ፋይናንሻል ዲፕኒንግ (financial deepening) ይቀረዋል፣ ፋይናንሻል ኢንክሉዥን (financial inclusion) ስራ ያስፈልገዋል እያልን፣ በሌላ በኩል ደግሞ እውቀትና ቴክኖሎጂ የሚገኝበትን ዘርፍ መዝጋት ይጎዳል እንጂ አይጠቅመንም በሚል እምነት ነው የተሰራ ያለው።

“ያ ሲሆን ግን ከውጭ የምናስገባቸው ባንኮች እንዳለ መጥተው የእኛን ባንክ አቅም፣ የእኛን ባንክ ውስን ልምድ የሚያንኮታኩቱ እንዳይሆኑ ምን ጥንቃቄ ይደረጋል ለሚለው፦

“አንደኛ የውጭ ዜጋ በዜጋ ደረጃ በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ ኢንቨስት (invest) ማድረግ የሚችለው ቢበዛ (maximum) ሰባት ፐርሰንት (7%) ነው።

“ሁለተኛ ተቋማት (institutions) ከሆኑ ማክሲመም አስር ፐርሰንት (10%) ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉት።

ስትራቴጂክ ኢንቨስተር (Strategic investor) የምንላቸው በፋይናንሻል ሴክተር የሚገቡ ከሆኑ ማክሲመም አርባ ፐርሰንት (40%) ነው ሼር (share) መያዝ የሚችሉት።

“በድምሩ የውጭ ባንኮች በተሰራው ሪፎርም (reform) የተከፈተው ማክሲመም አርባ ዘጠኝ ፐርሰንት (49%) ሼር እንዲይዙ ነው።

“የግል፣ የተቋም፣ የእነዚያ የስትራቴጂክ ኢንቨስተር ተደምሮ አርባ ዘጠኝ ፐርሰንት ሼር ነው የሚይዙት ይህ ራሱ የሚሆነው አምስት ለውጭ ባንኮች የሚሰጥ ላይሰንስ (license) በአምስት ዓመት ጊዜ ይፈጸም ነው ያልነው።

“ለምክር ቤቱ ጥያቄ ካለበት ‘በጣም ኮንሰርቫቲቭ (conservative) ናችሁ፣ ከፈት አድርጉት በቂ አይደለም’ ካላችሁ ትክክለኛ ነው።

“እኛ ስላለቀቀን የድሮ በሽታ በጣም በትንሹ ነው የከፈትነው እንጂ ያን ያህል የእኛንም ባንኮች በሚያጠፋ መንገድ የተከፈተ አይደለም።

“አምስት ላይሰንስ በአምስት ዓመት፣ ማክሲመም አርባ ዘጠኝ ፐርሰንት ሼር ምን ጉዳት አለው? ከመጣ የግድ ከእኛ ባንኮች ጋር ይሰራል ማለት ነው።

“የእኛ ባንኮች ባንክ መሆን አለባቸው እቁብ ናቸው ብዬ አላሳንሳቸውም፣ ግን ባንክ መሆን አለባቸው ባንክ ለመሆን ደግሞ በቂ አቅም አላቸው።

“ዝም ብሎ በየሰፈር ከሚከፈቱ ሰብሰብ ሰብሰብ እያሉ ሰውንም ካፒታልንም ቢደምሩ ትላልቅ ባንክ መሆን ይችላሉ እንደ ሱቅ ቤት መሆን የለበትም ባንክ ለኢትዮጵያ ጠንካራ አምስት አስር በቂ ነው።

“አሁን እንደምታውቁት ዲጂታል (digital) ዓለም ስለሆነ በዛም ስለምንጠቀም ማለት ነው በየቦታው ከምንከፍት ሰብሰብ ቢሉ ይመከራል፣ ይመረጣል አልያ ውድድሩ ቀላል አይሆንም ማለት ነው።

“እስካሁን ባለው የፋይናንሻል ሴክተር ሂደት እነሱ እንዳይጎዱብን በጥንቃቄ ስለሆነ የውጭዎቹ ሲገቡ ተጨማሪ ካፒታልና ቴክኖሎጂ እናገኛለን እንጂ የሚፈራው ስጋት እምብዛም ይኖራል ብዬ አላስብም በተለይ ባንኮቹ ላይ ባንክ መሆን የቻሉት ብዙ የሚጎዱ አይመስለኝም።

“ሌሎቹ ደግሞ ከሌላው ጋር እየተሰናሰሉ ለማደግ ጥረት እንደሚያደርጉ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማያውቀው ስለ ኤርትራ/ሻዕቢያ የተናገሩት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በፓርላማ ማብራሪያቸው፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ስለነበረው የኤርትራ ተሳትፎና የሕወሓት ጉዳይ እስከዛሬ በይፋ ያልተናገሩትን ይፋ አድርገዋል።

በዚህም ከኤርትራ ጋር “ጸቡ የተጀመረው” በቀይ ባህር ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጸዋል። “አክሱምን ይዘን ስናልፍ አክሱም ገብቶ ወጣቶች በጅምላ ሲረሽን ጸብ ተፋፍሟል። ዓድዋን ይዘን ስናልፍ ዓድዋ ሄዶ ፋብሪካዎች ሲፈታ፣ ሲሰርቅ ጸብ ተጋግሏል፣ ጸቡ የተጀመረው ብዙዎች እንደሚያስቡት የቀይ ባህር ጉዳይ ሲመጣ አይደለም!” ብለዋል።

ሲያብራሩም…

“ኤርትራ ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል Issue ነበር፤ ታውቃላችሁ። እኛ ከመጣን በኋላ አያስፈልግም፣ ይቅርብን ብለን መክረናል። አምስት አመት ለመምነናል።

“ጸቡ የተጀመረው ብዙዎች እንደሚያስቡት የቀይ ባህር ጉዳይ ሲመጣ አይደለም።

“በትግራይ ውጊያ ሲጀመር በመጀመሪያው ዙር ውጊያ ሽሬን ካስለቀቅን በኋላ የኤርትራ ጦር ከኋላ ኋላ ተከትሎ ሽሬ ገብቶ የአንዳንድ ግለሰቦች ቤት ማፍረስ፣ ፎቅ ማፍረስ ሲጀምር ጸብ ተጀምሯል፤ አልተናገርንም እንጂ።

“አክሱምን ይዘን ስናልፍ አክሱም ገብቶ ወጣቶች በጅምላ ሲረሽን ጸብ ተፋፍሟል። ዓድዋን ይዘን ስናልፍ ዓድዋ ሄዶ ፋብሪካዎች ሲፈታ፣ ሲሰርቅ ጸብ ተጋግሏል። ዓዲግራት ደርሰን የመድኃኒት ፋብሪካውን የሚነቀለውን ነቅለው የማይነቀለውን ሲያፈራሱ ጸቡ ጫፍ ደርሷል።

“ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ያኔ በዚህም፣ በዚያም ለመዋጋት አቅም አልነበረውም። ውስን ኃይል ነበረን፤ ሽሬን ከያዝን በኋላ ያጠቃውን ጠላት እንከተል ነበር እንጅ የያዝነውን ቦታ እያጸናን አንሄድም ነበር።

“ይሄ ጉዳይ ለዛሬ ዋጋ የለውም። ለታሪክ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ ግን አክሱም ወጣቶች ሲገደሉ፣ ዓድዋ ሲዘረፍ፣ ዓዲግራት ሲዘረፍ በርካታ ሰዎች ወደ ኤርትራ ልኬያለሁ።

“የላኳቸው ሰዎች ገሚሱ አሁን ከኛ ጋር የሉም። ለምሳሌ ክቡር አቶ ገዱ ያኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። ከአንዴም ሁለቴ ኤርትራ ልኬያቸዋለሁ። የላኳቸው የትግራይ ህዝቤን አታጎሳቁሉ፣ ሀብቱን አትዝረፉ፣ ጸቡ ከTPLF እንጅ ከትግራይ ህዝብ አይደለም በሚል ነው (ይህን መልዕክት ለኤርትራ እንዲያሳውቁ ማለታቸው ነው)።

“አቶ ገዱ አሁን እኛ ጋ የሉም። ግን ክር/ማተብ አላቸው፤ ህሊና አላቸው። ዛሬ ቢደብቁ በታሪክ ውስጥ ይወጣል። ስለምን ጉዳይ እንደተነጋገሩ እሳቸውም ያውቃሉ፤ ሻዕቢያም ያውቃል፤ እኛም እናውቃለን። አሉ አልሞቱም። እሳቸው (ገዱ) Access ይደረጋሉ ሊናገሩ ይችላሉ።

“ጉዳዩ በእሳቸው መፈታት ሲያቅተው አቶ ደመቀን ልኬያለሁ። አቶ ደመቀ አሁንም እኛ ጋ የሉም፤ በህይወት ስላሉ ለእምነታቸው ለህሊናቸው ሊጠየቁ ይችላሉ። ለምን ጉዳይ እንደሄዱ ያውቃሉ።

“ታስታውሱ ከሆነ መቐለ ልንገባ ትንሽ ሲቀረን የሦስት ቀን ‘አልቲማተም’ ብለን አውጀን ነበር። ብዙው ምስጢሩ አልገባውም።

“የቸገረን እኛ ሽሬን ስንለቅ ከኋላ ይገባሉ። አክሱም ስንለቅ ከኋላ ይገባሉ። መቐሌ ስንገባ ደግሞ ገብተው ትልቁን ከተማ Damage ያደርጋሉ ብለን፥ ካሁን በኋላ ከውቅሮ እናልፋለን ብትሉ ወያኔን ትተን ወደእናንተ ነው የምንዞረው በውጊያው ብለን ውቅሮ ላይ የሚጠብቅ ኃይል አስቀምጠን ነው መቐሌ የገባነው።

“ይሄ ጸብ ተፋፍሞ ሄዶ የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲፈረም ‘እንዴት TPLF ሳይጠፋ፣ ትግራይ ሳይወድም ፊርማ ይደረጋል?’ በሚል ነው የመጨረሻ ጫፍ የደረሰው ጸቡ። ከዚህ ኃይል ጋር ነው እንግዲህ ያኔ የTPLF ሰዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንስራ ያሉት።

“የትግራይ ህዝብን የሚጎዳ እና የሚጠቅም ነገር ይሄ መንግሥት ነው የሰራው ወይስ TPLF? (ሁሉም TPLF ላይሆን ይችላል፤ አክራሪ TPLF በሚል ይውሰድ) ማነው? የሚለው ዛሬ ብዙ Emotion፣ ብዙ ፕሮፓጋንዳ፣ ብዙ ውሸት ስላለ ነው፤ ነገ ግን ታሪክ ያወጣዋል።

“ማንም ሰው እውነትን ለጊዜው መሸፈን እንጅ ከነአካቴው ማጥፋት አይችልም። እኛ መጨረሻ ፕሪቶሪያ ስንፈራረም መቐለ ለመግባት አንድ ቀን ነበር የቀረን፤ አሸንፈናል ጦርነቱን።

“ግን መቐለ መግባት ድል አይደለም። ህዝባችንን የማንጠብቅ ከሆነ ተመልሶ ይዘረፋል፣ ይገደላል። ያ ከሚሆን ሰላም ይሻላል። የኛው ህዝብ ነው ከሚጎዳብን ይቅርብን ብለን ነው የወሰነው።

“ዛሬ የTPLF አንዳንድ ሰዎች ያላቸውን አቋም ሳይ ምን ያክል ህዝባቸውን እንደሚጠሉ፣ ምን ያክል የህዝባቸው በደል እንዳማያማቸው ነው የሚገባኝ።

“እውነተኛው ፈራጅ ስለሚያይ ማንም አያሸንፈንም። TPLF በኤርትራ ወታደር ዘረፋ እንዳይካሄድበት ስንጠብቀው ኖረን አማራ ክልል ሲገባ ያደረገው ነገር ያሳፍራል። ፋብሪካዎች አፍርሷል። ት/ቤት አቃጥሏል። ባንክ ዘርፏል።

“የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መቐለ ነበረ በብቸኝነት፤ TPLFን አባሮ ሻዕቢያን ሳያስገባ። መቐለ አንድ ቤት የፈረሰ አታገኙም።

“TPLFስ ቢሆን አማራ ክልል መጥቶ እንደዚያ አይነት ነገር ማድረግ ነገ ለሚቀየር ታሪክ አስፈላጊ ነበር? እንደዚህ ያለው ኢትዮጵያን ያላስቀደመ ለጊዜው ለሚዲያ ጫወታ የሚደረግ የፓለቲካ ስብዕና በዘላቂነት በራሳችን ህዝብ ላይ ጉዳት የሚያመጣ ብቻ ሳይሆን በታሪክ መነጽር ሊጋባው በየነን ዛሬ ታሪክ እንዳነሳቸው በታሪክ ውስጥ ይነሳል” ብለዋል። (Ethiopian Insider, @tikvahethioia)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Politics, Slider Tagged With: eplf, ethiopian terrorists, Genocide by Eritreans, operation dismantle tplf, tplf terrorist

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የተንጋደደው የገዱ መልስ February 6, 2026 03:05 pm
  • ሻዕቢያ “አክሱም ገብቶ ወጣቶች በጅምላ ሲረሽን ጸብ ተፋፍሟል …” February 4, 2026 01:15 pm
  • አደራ ጠባቂው የኢሉአባቦር ሕዝብ February 4, 2026 12:14 pm
  • የአውሬው ሪፖርተር ቀላቢዎች፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን January 28, 2026 09:56 am
  • በአሜሪካ ጥምር ዜግነት እንዲቀር ጥያቄ ቀረበ January 27, 2026 03:05 pm
  • “ከህወሓት፣ ከሻዕቢያ፣ ከግብፅ ሰዎች ጋር ሆኖ እንዴት የአማራን ጥያቄ ማስመለስ ይቻላል?” ኮሎኔል ፈንታው January 25, 2026 04:23 am
  • የኢትዮጵያ አየር ኃይል: ለአፍሪካ ሀገራት የመጀመሪያዎቹን የአየር ኃይል አብራሪዎች ያሰለጠነ ተቋም January 25, 2026 03:50 am
  • የአማረ ሪፖርተር እያደረሰ ያለው የብሔራዊ ደኅንነት አደጋ January 22, 2026 01:56 am
  • የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማርያምን ማዕረግ ዝቅ አደረገች December 12, 2025 09:27 pm
  • ኢህአፓ: ከነጭ ሽብር ወደ “አዲስ አበባ ትናገር” የጎዳና ሽብር? December 12, 2025 09:11 pm
  • EOC Bans Haile Gebrselassie Over Are­qie Comments Linked to Doping November 21, 2025 07:47 pm
  • በሥራ ማቆም አድማ ጥሪ ዘርፍ ባለሙያው ጃዋር ሌላ ጥሪ አቀረበ November 17, 2025 09:25 am
  • የ-አብሮነት ማኅበር የመረጠው ሕቡዕ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፋ ሆነ November 5, 2025 12:06 pm
  • “የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው … “ፅምዶ” ራዕይ ዓልባ” ነው – ሼትል ትሮንቮል October 26, 2025 10:15 pm
  • አሜሪካ ስላልተቀበለችው ነው “የሽሽግር መንግሥት” ስብሰባው በአምስተርዳም ተካሄደው October 25, 2025 11:09 pm
  • በዓባይ ግድብ ምረቃ፡ የሕዝብ ደስታ፣ የቴድሮስ ካሳሁን ዝምታ September 14, 2025 04:27 am
  • ኢትዮጵያ የውኃ ኑክሊየር ማብላያዋን ልታስመርቅ ነው  August 29, 2025 11:46 pm
  • መከላከያ በፋኖ አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ፤ ዘመነ በ“አንድ ማንኪያ ቅንነት” አንድ እንሁን አለ August 23, 2025 12:35 am
  • ፋኖን በፋይናንስና በሎጂስቲክስ የሚደግፉ የጎጃም ባለሃብቶች ከስደት ሊመለሱ ነው August 14, 2025 12:42 am
  • የበቀለ ገርባ የአሜሪካ ጥገኝነት ማመልከቻ ውድቅ ተደረገ August 13, 2025 12:16 pm
  • ሞዐ ተዋሕዶ “ነጻ አውጪ ግምባር” – ሞነግ August 13, 2025 12:58 am
  • የሃይማኖትና የመንግሥት ጥምረት በረከት ወይስ መርገም?  August 5, 2025 09:18 pm
  • የባከነ የስደት ሕይወት ከደባርቅ እስከ ኖርዌይ July 29, 2025 05:44 pm
  • “በዚህ ዓመት መጨረሻ ትግራይን እንቆጣጠራለን”፤ ቲፒኤፍ July 22, 2025 01:28 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2026 · Goolgule