አሜሪካ ያሉት መምህር ፋንታሁን ዋቄ “ለእምነታችሁ በደስታ ሙቱ” ሲሉ መንግሥት እንዲገለብጡ ለአዲስ አበባ፣ ለአሰላ እና ለአዳማ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ጥሪ አቀረቡ።
መምህር ፋንታሁን ዋቄ “እጃችህ ላይ መድኃኒት አለ” በማለት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት ተከታዮች መንግሥት ላይ እንዲነሱ ጥሪ አቅርበዋል። አሜሪካ ተቀምጠው “የሰማዕታትን ማረፍ በደስታ በማሰብ በክርስትና የሚሞት በዚህ ዘመን መኖሩ እያስደሰተን በማሰብ እንሙት” ብለዋል።
“ሞዐ ተዋህዶ” በሚል ስያሜ የሚጠራው የህቡዕ አደረጃጀት መሪ እንደሆኑ የሚናገሩት መምህር ፋንታሁን በቲክቶክ አውድ ሲናገሩ እንደተሰማው “ኃይል የእግዚአብሔር፣ ሠራዊት የጌዲዮን ነው” በማለት የዕምነቱ ተከታዮች “አሁን ብናገር ጠላት ይሰማል” በማለት ምሥጢር ያሉትን መድኃኒት እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።
“ፍርሃት ለፍቅር አድርሳን ትሰናበተናለች፤ ፍርሃት የተሰጠን ለመዳን ነው፤ መፍራት አለብን እንደሚገባን”፤ ካሉ በኋላ “ግን እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለነው ኦርቶዶክሶች የሚገድል ፍርሃት ነው የምንፈራው”፤ ሲሉ የዕምነቱ ተከታዮች ሊፈሩ እንደማይገባ አሳስበዋል። አክለውም “አሁን በሚዲያ አልናገርምንጂ ብዙ መሣሪያ አለ እጃችን ላይ፤ እጃችን ላይ አለ፤ አስቡበት፤ ብዙ መሣሪያ አለ፤ አንድ ቀን ነው የሚበቃው፤ አስቡበት፤ ከተናገርኹ ጠላትም ስለሚያውቀው፤ አዲስ አበባ ብቻ መድኃኒት መሥራት ይችላል፤ አዳማ ብቻ መድኃኒት መሥራት ይችላል፤ አሰላ ብቻ መድኃኒት መሥራት ይችላል” በማለት በአንድ ቀን መንግሥት ማስወገድ እንደሚቻል አስታውቀዋል።
“በዚህ ዘመን በክርስትና መሞት እያስደሰተን፣ የገዳዮቻችን ተላላኪ መኾናችን እያሳፈረን፤ የሐሰት መነኮሳት ልጆች መኾናችን እያሳፈረን” ልንሞት ይገባናል በማለት የቀሰቀሱት መምህር ንስሐ በመግባትና አንድ በመሆን በአንድ ቀን መንግሥትን ማስወገድ እንደሚቻል ተናግረዋል።
በውጭ አገርና እና በአገር ውስጥ በጋራ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ምርጫውን ማስተጓጎል ባለመቻሉ አዲስ የድህረ ምርጫ ዕቅድ (post-election plan) መንደፋቸውን ጠቅሶ የጎልጉል የዋሽንግቶን ዲሲ ተባባሪ የላከው መረጃ ይጠቁማል። በዚሁ መረጃ መሠረት ከአዲስ አበባ ወደ አሜሪካ የሄዱና ከመምህር ፋንታሁን ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በአቶ ነዓምን ዘለቀ አማካይነት ኤርትራ ኤምባሲ ውስጥ የሸዋ ኦሮሞ ኦርቶዶክሶችን “ኦሮ አማራ” በዕምነት ሰበብ ማነሳሳት የሚቻልበትን ጥናት አቅርበው ነበር።
ኢትዮጵያን እየመራ ያለው የብልጽግና ፓርቲ የፕሮቴስታንት እና የሙስሊም እምነት ተከታዮችን ስለሚያሰባስብና በምርጫም ዕጩ አድርጎ በማቅረቡ ከአማራ ተወላጆች በተጨማሪ በተጠቀሰው አካባቢ ያሉትን የኦሮሞ ተወላጆችን ማነሳሳት ነበር ዕቅዱ። ይህ ከሆነ በኋላ በአርሲ የተፈጸመውን የንጹሃን ግድያ አስቀድሞ ጃዋር መሀመድ ይፋ ሲያደርግ የቅሰቀሳው አካሄድ መልኩን የቀየረ መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ።
መምህር ፋንታሁን “አትፍሩ ለእምነታችሁ ሙቱ” የሚል ጥሪ ያስተላለፉት ብቻ ሳይሆን እንደ ኢኤምኤስ ያሉ ዩቲዩቦች “ኦርቶዶክሶች ድረሱልን እያሉ ነው” በማለት አስደንጋጭና ሰሚውን ግራ የሚያጋባ የትብብር ጥያቄ ቦታ፣ የደብር ስም፣ እንዲሁም የፍርሃቻውን ልክ በተቆራረጠና እጅግ የሰጋ በሚመስል ገጽ ማስተላለፍ ላይ ናቸው።
ፈር በለቀቀው የማኅበራዊ ሚዲያ አውድ ከዚህም ከዛም የሚወጡ ስሜት ቀስቃሽ፣ ቁጣን የሚዘሩና አንዱ ኃይማኖት ከሌላው እንዲጋጭ የሚጋብዙ ውትወታዎችን የገባቸው እየተቃወሙ ሲሆን፣ ሤራው ያልገባቸው ውትወታውን እየተቀባበሉ ይገኛሉ።
“በኃይማኖት ውስጥ መካከለኛ መንገድ ወይም ድርድር በአብዛኛው አስቸጋሪ ነው። እያንዳንዱ ወገን የራሱን እምነት እንደ ፍጹም መለኮታዊ እውነት፣ የተቃራኒውን ወገን ደግሞ እንደ ስህተት ወይም ክህደት ስለሚቆጥር፣ ችግሮችን በውይይትና በስምምነት ለመፍታት በጣም አዳጋች ነው” የሚሉ ወገኖች የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ይመክራሉ።
በተለያዩ መንገዶች ኢትዮጵያን ማተራመስና ማፍረስ ባለመቻሉ የኃይማኖቱን ክንፍ እንደ ዋናና የመጨረሻ ሙከራ አድርገው የተነሱ እንደሚሉት አሁን በተያዘው አግባብ በቅርቡ ዓመፅ ይነሳል። ሃይማኖት የአንድ ሰው ማንነት፣ የባኅል እና የኅልውና መሠረት ነው። ስለዚህ በሃይማኖት ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ወይም ግጭት እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ በሕይወት የመኖርና ያለመኖር አደጋ ተደርጎ ስለሚወሰድ፣ ሰዎችን በቀላሉ ለአመፅ እና ለከፍተኛ ስሜታዊነት የሚጋለጡበት በመሆኑ ይህንን አካሄድ መጠቀም ግጭት ጠማቂዎቹ እንደ መጨረሻ ዕድል ቆጥረውታል።
“በተራ ፖለቲካዊ ግጭቶች ውስጥ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ። በሃይማኖት ጸብ ውስጥ ግን ‘ለፈጣሪ ወይም ለእምነት መሞት ጽድቅ ነው’ የሚል እምነት ስለሚፈጠር፣ ሰዎች ራሳቸውን ለአደጋ አሳልፈው ለመስጠትና እስከ መጨረሻው ለመፋለም አይፈሩም። ይህ ደግሞ ግጭቱን እጅግ ደም አፋሳሽ ያደርገዋል” የሚሉ ወገኖች መምህር ፋንታሁንም ሆነ አብረዋቸው እየሠሩ ያሉት ክፍሎች ይህንን ጠንቀቀው ስለሚያውቁ አካሄዱን እንደመረጡት ያስረዳሉ።
የኃይማኖት ቂምና ቁስል በቀላሉ አይሻርም። በታሪክ የተፈጠሩ ግጭቶች በሃይማኖታዊ ትረካዎችና መዝገቦች ውስጥ እየተጻፉ ለቀጣዩ ትውልድ ስለሚተላለፉ፣ ከብዙ ዓመታት አልፎ ተርፎም ከዘመናት በኋላ እንኳ እንደገና የመቀስቀስ አቅም እንዳለው የሚገልጹት ወገኖች በዚህ መልኩ መንግሥት እንገለብጣለን ብለው የሚያስቡ ቡድኖች፣ አሳባቸው እውን ከሆነና ጂኒው ከጠርሙሱ አንዴ ከወጣ እነሱም እንደማያቆሙት በመግለጽ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ፖለቲከኞች በተለይም አክራሪ ኃይሎች የራሳቸውን ሥልጣንና ጥቅምና ለማስከበር ሲሉ የሕዝብን የሃይማኖት ስሜት በቀላሉ በማነሳሳት ለግጭት ሲጠቀሙበት ማየት የተለመደ መሆኑን የሚያመለክቱ ጥናቶች፣ እነዚሁ ቡድኖች ማኅበረሰቡን በዕምነቱ በ”እኛ” እና “በእነሱ” በመክፈል አገርን ማፍረስ የሚችል ትልቅ መሣሪያ አድርገው እንደሚጠቀሙበት ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ በግልጽ እንደሚታየው አንድ ማኅበረሰብ ለዘመናት የገነባቸውን የጋራ እሴቶች፣ የአጋርነትና የጉርብትና ትስስሮች የዕምነት ግድግዳ በመስራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማፍረስ ስለሚቻል ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነ የሚመክሩ፣ ዛሬ በኢትዮጵያ በዚሁ የፊት ለፊት እና ስውር ቅስቀሳ በአንድ መንደር ውስጥ በሰላም ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን እርስ በርስ እንዲጠራጠሩና በጠላትነት እንዲተያዩ እየተደረገ ነው። በአርሲ የታየውም ይህ ነው።
የሰማዕትነት ጥሪውን ያቀረቡት መምህር ፋንታሁን ወደ አሜሪካ ያቀኑት ለጊዜያዊ አገልግሎት ቢሆንም፣ ሳይመለሱ ቀርተዋል። አሜሪካ ከገቡ በኋላ የፋኖ ኃይል በሞዐ ተዋህዶ አደረጃጀት ስር የተዋቀረና የተመሰረተ፣ እንዲሁም የፋኖ ባለቤት ሞዐ ተዋህዶ እንደሆነ መዐዛ በሐመድ ጋር በተጋጩበት ቃለ ምልልሳቸው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። የፋኖ መሪዎችም በይፋ “ትግሉ መንፈሳዊ ነው” በማለት የንግሥና ቅባት እንደተቀቡ በተደጋጋሚ የሚናገሩት ጉዳይ ነው። መንግሥት ይህንን ጉዳይ ይፋ አድርጎ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ማድረግ እንደሚገባው የሚናገሩ አካላት፣ ዕቅዱ ኢትዮጵያዊያንን በእምነት ሰይፍ አማዝዞ አገሪቱን የማፍረስ አካሄድ እንደሆነ በይፋ መነገር እንዳለበት እያስታወቁን ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በኃይማኖት ስም ያንዲት ቤተ ክርስቲያን መምህር እንደሆኑ በግልጽ እየጠቀሱ የዓመፅ ተግባርን የሚቀሰቅሱ ግለሰብ የቤተ ክርስቲያኗ አመራር ዝም ሊለው እንደማይገባ ለቤተ ክህነት ቅርብ የሆኑ ይናገራሉ። ቤተ ክርስቲያኗ በስሟ ለሚደረጉ ነገሮች ኃላፊነት አለባት የሚሉ፤ ረጅም ዘመናትን ባስቆጠረው አስተዳደራዊ አመራሯ መሰል ጉዳዮች ላይ ለመወሰን የዳበረ ልምድ አላት። ማስጠንቀቂያ ከመስጠት እስከ ማውገዝ መሄድ እንደምትችል የጠቆሙ ወገኖች በዝምታ ማለፍ ግን አለሁበት ከማለት ጀምሮ ተባባሪም ነኝ የሚል ስም ሊያሰጥ ስለሚችል፤ በኋላም በኃላፊነት ስለሚያስጠይቅ ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ።
ፋንታሁን ዋቄ አሸባሪ ናቸው፤ የሚሄዱበት መንገድ ሁልጊዜ የሽብርና ሕዝብን የሚያጫርስ፣ ደም የሚያፋስስ ነው። መምህሩን በተመለከተ አሜሪካ ናቸው የሚለው ትክክለኛ እስከሆነ ድረስ በዚህ ልክ የደም መፋሰስ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ለአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት ማድረግ ተገቢ እንደሆነ የሚመጣው ጉዳት የታያቸው እየመከሩ ነው።
በተለይ አሁን ባለው የትራምፕ አስተዳደር ዓለምአቀፋዊ የእግር ኳስ ዳኛና ቡድን ቪዛ እስከ መከልከል የደረሰ በመሆኑ ከአሸባሪነት ጋር የተዛመደ የኢሚግሬሽን ጉዳይ በዚህ ስልክ ቁጥር (1-866-DHS-2-ICE) ጥቆማ ከተሰጠው እርምጃ ለመውሰድ ጥቂት ጊዜ እንኳን ወስዶ አያስብም። እንደ መምህር ፋንታሁን ዋቄ ያሉትን አሸባሪዎች ለአሜሪካ መንግሥት በመጠቆም ደም መፋሰስን ማስወገድ ይቻላል፤ መጠቆሚያ ቁጥሮቹም እነዚህ ናቸው፤ ለመደወል 999፤ ቴክስት ለማድረግ 70999 በመጠቀም ሕዝብን መታደግ በፈጣሪም የሚያስመሰግን ሰው የመሆን አንዱ ግዴታ ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ



Leave a Reply