ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደውን የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ተከትሎ “ትብብር” የተሰኘው ቡድን ያወጣው መግለጫ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው። የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) እና የእናት ፓርቲ አመራሮች “ትብብር” የተባለውን ስብስብ ወክለው ኢኤምኤስ ለተባለው ዩትዩብ የተናገሩት በሀገር ውስጥና በዲያስፖራው ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ አስነሳ።
ሚስጥረሥላሴ ከኢህአፓና ጌትነት ከእናት ፓርቲ ሆነው “ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ ያልሆነ የጨረባ ምርጫ ነው” በማለት ውድቅ ለማድረግ ቢሞክሩም፣ ሕዝቡ ግን “ቀድሞውኑ ለገዢው ፓርቲ አጃቢና ድራማ አድማቂ ለመሆን የገባችሁ የፖለቲካ ድንኮችና ሆዳሞች ናችሁ” በማለት በብርቱ እያወገዛቸው ይገኛል።
የፖለቲካ ተንታኞችና የውስጥ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ የኢህአፓ እና የ“ትብብር” ጥምረት መሪዎች ቀድሞ የነደፉት ስልት በምርጫው ሂደት ውስጥ ተሳታፊ መስለው በመቆየት፣ ሂደቱ ሊጠናቀቅ ሲል “ምርጫው ፍትሐዊ ስላልሆነ ራሳችንን አግልለናል” በማለት ምርጫውን እና በቀጣይ የሚደረገውን የመንግሥት ምሥረታ ቅቡልነት ለማሳጣት ነበር። ይሁን እንጂ አስቀድሞ የተነደፈላቸውን ስልት ሳይከተሉ በምርጫው ከተሳተፉ በኋላ፤ ምርጫው ተጠናቆ ውጤቱ ከመታወቁ በፊት የተሳተፉበትን ምርጫ “የጨረባ” በማለታቸው፣ በዲያስፖራውና በሀገር ውስጥ የነበራቸው ደጋፊ ሙሉ በሙሉ እምነት አጥቶባቸዋል።
“ኢህአፓ ከምርጫው በኋላ ይሰነጠቃል” – የጎልጉል ዘገባ
መሪዎቹ በዩቲዩብ ጥያቄ ላቀረበላቸው ወንድማገኝ ምላሽ በሰጡበት ወቅት፣ ከተመልካቾች የተሰጡት በመቶዎች የሚቆጠሩ አስተያየቶች ፓርቲውና ጥምረቱ ምን ያህል ሕዝብ እንደተጸየፈውና ከባድ ተቃውሞ እያቀረበ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ከተሰጡት መራራና እጅግ ከረር ያሉ የሕዝብ ትችቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
- “ለብልፅግና ጥቅም አገልግላችኋል”፦ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ትብብሩና ኢህአፓ “ለአጃቢነት የገቡ ማፈሪያዎች ናቸው፤ አስመሳይ በመሆናቸው ለብልፅግና ጠቅመውታል” ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ “የሙሽራ አጃቢዎች በሕዝብ መታመን ባይችሉም ባጋጣሚው መንገድ ያረጋገጡት ጥቅማቸው ለነሱ በቂያቸው ነው” በማለት መሪዎቹ የግል ጥቅማቸውን አሳደው የሕዝብን ድምጽ በቅርጫት መጣላቸውን ገልጸዋል።
- “አሁን መለፍለፉ ፋይዳ የለውም”፦ ሕዝቡ ምርጫው ገና ሳይጀመር እንዳይሳተፉ በተደጋጋሚ ሲማጸናቸው እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎች፣ “ወንበር ስታጡ ነው አሁን የምትቀባጥሩት፤ በክብር መጀመሪያውን ባትሳተፉ ኖሮ ትከበሩ ነበር። የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” በማለት ተሳልቀውባቸዋል።
- “የታሪክና የስም ክህደት”፦ የፓርቲውን ስም አስመልክቶ ከተሰጡት ትችቶች መካከል፣ “የኢህአፓ ስም በፅናት፣ በዕውነትና በፖለቲካ ትግል የተገነባ የሰማዕታት ታሪክ ሆኖ ሳለ፣ ዛሬ ለሆድ አደርነትና ለአጋጣሚ ፈላጊነት (Opportunism) መገልገያ ሲደረግ ማየት ያሳዝናል፤ ይህ የሞቱትን ወገኖች ታሪክ መሳደብ ነው” የሚሉ ጠንካራ ወቀሳዎች ቀርበዋል።
- “እንኳን ሲሸጡን ሲያስማሙን ይገባናል” እና ሌሎች ጠንካራ ስድቦች፦ በርካታ የዲያስፖራና የሀገር ውስጥ ተመልካቾች መሪዎቹን በቀጥታ “ባንዳዎች፣ ሆዳሞችና ዱቄቶች” ሲሉ ጠርተዋቸዋል። አንዱ ተመልካች “እንኳን ሲሸጡን ሲያስማሙን ይገባናል” በማለት መሪዎቹ ገና ከጅምሩ ሕዝብን አሳልፈው ለመስጠት እንደገቡ የገለጸ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ “ይህች ቀባጭ አይጥ የድመት አፍንጫ እያሸተተች ነው፤ ኢህአፓ የኮርማዎች ዘመን አይሆንሽም” በማለት የአመራሮቹን ድፍረት አውግዟል።
- በሚስጥረሥላሴ ላይ ያነጣጠሩ፡- በትችቶቹ ውስጥ የአመራሮቹን የግል ጥቅም አሳዳጅነት የሚኮንኑ አስተያየቶች በስፋት የታዩ ሲሆን፣ “እነዚህን ማሀይሞች ባታመጧቸውስ፤ እንዴት እንደጠላዋቸው በተለይ ይች ተንከሲስ አስመሳይ፤ ኢሕአፓ ከእንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ መቀጠል የለበትም፤ ብልፅግና አጋድሞ ቢግጣችሁ ደስ ባለኝ” የሚል መራር አስተያየት ተሰጥቷል፤ ሌላው ደግሞ “ኢህአፓ አስመሳይ አድርባይ ፓርቲነው” ያለ ሲሆን “ሚስጥረ ስላሴ ሳይሆን ምስጢረ ሴረኛ ነሽ መባል ያለብሽ” ብሏል፤ “ሚስጥረ ያራዳ ልጅ በአሜሪካ ኤምባሲ በኩል ከነ አቢይ ጋር ተደራድራ 200 ሚልየን ተቀባብላለች አሉ ቪላ አየሰራች ነው ኦልድ ኤርፓርት” በማለት አላግጦባታል።
በተለይ ሚስጥረ ሥላሴ ምርጫ ስታደርግ ፎቶዋ ወጥቶ እንደነበር በመጥቀስ ለቀረበላት ጥያቄ ስትመልስ፤ እኔ በዚያ ምርጫ ጣቢያ በዚያ ሰዓት እንደምገኝ ማን እንደነገራቸው አላውቅም፤ ያለ እኔ ፈቃድ ፎቶዬን አንስተው በሚዲያ ላይ መበተናቸው ሕገወጥ ተግባር ነው፤ በቀጣይ አስፈላጊውን አካሄድ የምከተል ይሆናል በማለት ተናግራለች። ሆኖም ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የውጪ አገር ታዛቢዎችን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በምርጫ ጣቢያ አካባቢ ፎቶ ሲነሱና ቪዲዮ ሲቀረጹ የዋሉ ሲሆን የትኞቹም ያለፈቃዳችን ፎቶ ተነሳን ብለው ሲሞግቱ አልተደመጡም። ከዚህ ይልቅ የሚስጥረ ምላሽ “ስመርጥ መታየት አልፈልግኹም ነበር” የሚል ይመስላል። ፎቶውም ያንኑ የሚመሰክር ይመስላል በማለት የጎልጉል አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል።
ኢህአፓም ሆነ እናት ፓርቲ ከምርጫው በፊት በትብብሩ ስም እንዲሁም በራሳቸው ፓርቲ ስም በምርጫው ሒደት ሲሳተፉ የቆዩ ነበር። በምርጫ ክርክሮች በአብዛኛዎቹ ተሳትፈዋል፤ ዕጩዎቻቸውንም አስመዝግበዋል። ምንም እንኳን መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ዕጩ እንደሌላቸው ራሳቸው በተደጋጋሚ ተናግረው የነበረ ቢሆንም በምርጫ ክርክሩ ወቅት ግን “በምርጫ አሸንፈን መንግሥት ስንመሠረት” እያሉ በድፍረት ሲናገሩ ነበር።
በተለይ ኢህአፓ በአስር ከተሞች ታላቅ ሰልፍ አደርጋለሁ ብሎ ከዚያም የምርጫ ቅስቀሳ አደርጋለሁ ብሎ ቃል ከገባና አንዳንዶች እንደሚሉትም ከዳያስፖራው ብር ከተሰጠው በኋላ ምንም ሳያደርግ መቅረቱ፤ እንዲሁም ለዚሁ ዓላማ የተሠራ የሚመስለውን የቴዲ አፍሮ “ዳስ ጣል” ሙዚቃ እያሰሙና ሕዝብ ያነሳሳልናል ብለው ያሰቡትን ሰንደቅ ዓላማ እያሳዩ አዲስ አበባ ላይ ያደረጉት “የምርጫ ቅስቀሳ” አስር ሰው ብቻ የወጣበት መሆኑ ከፍተኛ ትችትና ወቀሳ አስከትሎባቸዋል።
በአጠቃላይ፣ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት “ለምርጫው አስቻይ ሁኔታ ሊኖር ይገባል፣ ሕዝባዊ ሰልፍ እንጠራለን” እያሉ ሲቀጥፉ የነበሩት እነዚህ የ“ትብብር” እና የኢህአፓ መሪዎች፣ አሁን ላይ የደረሰባቸውን ውድቀትና የሕዝብ አመኔታ ማጣት ለመሸፈን “የጨረባ ምርጫ ነው፤ ምክር ቤት አንገባም” የሚል ወላዋይና ፋይዳ-ቢስ አቋም ይዘው ብቅ ማለታቸው ይበልጥ እንዳስናቃቸው ሕዝቡ በቁጣ በሰጣቸው ምላሽ አረጋግጧል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply