• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

አዲሱ የቴድሮስ ካሳሁን 888 ኮድ፤ እንደ 666?!

April 15, 2026 05:53 am by Editor Leave a Comment

* ለመሆኑ የቴዲ ኢትዮጵያ የት ትሆን ያለችው?

ታዋቂው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አዲሱን አልበሙን በስምንተኛው ወር፣ በስምንተኛው ቀን፣ በስምንተኛዋ ሰዓት ለመልቀቅ መወሰኑ በቁጥር ስሌት (Gematria) ዙሪያ መነጋጋሪያ አጀንዳ ፈጥሯል። ይህ “888” የተሰኘው ቁጥር በአጋጣሚ የተመረጠ እንዳልሆነና አርቲስቱ ሆን ብሎ መልዕክት ለማስተላለፍ የተጠቀመበት ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ። በክርስትና እምነት 777 የመለኮት ቁጥር ሲሆን፣ 666 ደግሞ የባቢሎን፣ የአውሬው ወይም የክርስቶስ ተቃዋሚ ቁጥር ተደርጎ እንደሚወሰድ ሁሉ፣ 888 ምንን ሊወክል ይችላል የሚለው ጥያቄ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።

ከመንፈሳዊ ትርጓሜ አንፃር፣ 888 በግሪክ ቋንቋ የኢየሱስ (Ιησούς) ስም መጠሪያ ሆኖ የሚያገለግልና ከፍጽምና በላይ የሆነን መለኮታዊ ኃይል ወይም አዲስ ጅማሮን የሚያመለክት ቁጥር ነው። ቁጥር 7 የፍጹምነት ምልክት እንደሆነ ሁሉ፣ 888 ደግሞ ከዚያም የላቀውን ሰማያዊ ኃይል ይወክላል። ቁጥሩ የሀብት፣ የስኬት እና በመንፈሳዊና ቁሳዊ ነገሮች መካከል ያለን ሚዛን የሚያመላክት ሲሆን፣ አንድ የሕይወት ምዕራፍ አብቅቶ የተሻለ ምዕራፍ መጀመሩን እንደሚያበስር ይገለጻል።

ቴዲ አፍሮም ይህን ቁጥር መጠቀሙ አሁን ካለው የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማያያዝ፣ አዲስ የተስፋ ምዕራፍ መጀመሩን ለማብሰር ካለው ፍላጎት ሊመነጭ እንደሚችል ግምቶች አሉ። ሌሎች ደግሞ “ብልጽግና ስምንት ዓመት ገዝቷል፤ ይበቃዋል” ነው ቴዲ እያለ ያለው ሲሉ ጉዳዩን ከብሔር አኳያ ለማያያዝ የሚፈልጉ ደግሞ በገዳ ሥርዓት አባ ገዳ የሚመረጠው በየስምንት ዓመቱ ስለሆነ የዐቢይ ኦሮሙማ አገዛዝ ይብቃህ ሊባል ይገባዋል የሚል የነውጥ/ለውጥ ኮድ መልዕክት አለው ይላሉ። በማስረጃነትም ቴዲ የዓድዋ በዓልን አስመልክቶ ይህንን “ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቃ ልንለው” ይገባል በማለት በማኅበራዊ ድረገጹ ያስተላለፈውን መልዕክት ይጠቅሳሉ።

በሌላ በኩል፣ 888 በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ ከአሉታዊና ከምሥጢራዊ ማኅበራት (ኢሉሚናቲ) ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚገልጹ መረጃዎች አሉ። አንዳንዶች ቁጥሩ ሰዎችን ለማታለል፣ አዲስ የዓለም ሥርዓትን (New World Order) ለማስተዋወቅ ወይም በገንዘብና በቁሳዊ ስኬት ላይ ብቻ ያተኮረ የስግብግብነት ምልክት እንደሆነ ይተረጉሙታል። በተጨማሪም ቁጥሩን ለጥንቆላና ሰዎችን በሐሳብ ለመቆጣጠር (Mind Control) እንደሚጠቀሙበት የሚገልጹ ወገኖች፣ በታዋቂ ሰዎች ዘንድ ሲጠቀስ “በማር የተለወሰ መርዝ” ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

እንዲህ ያሉ ምሥጢራዊ ቁጥሮችን መጠቀም የሰዎችን የማወቅ ጉጉት በመቀስቀስ ለዝናና ለገበያ ማሟሟቂያ የሚውል “Mystery Marketing” ሊሆን እንደሚችልም ይገመታል። አርቲስቶች ራሳቸውን እንደ መንፈሳዊ መሪና አዳኝ አድርገው ለማቅረብና ደጋፊዎቻቸው እንደ ደቀ መዝሙር እንዲከተሏቸው ለማድረግ እንዲህ ያሉ ኮዶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ይህ አካሄድ አድናቂዎች ከአድናቆት ባለፈ የ”ደቀ መዝሙርነት” ስሜት እንዲያድርባቸውና አርቲስቱን እንደ ንጉሥ ወይም ጥበበኛ መሪ እንዲመለከቱት ለማድረግ የታለመ ስልታዊ የምስል ግንባታ እንደሆነም ይገለጻል።

በአጠቃላይ፣ የ888 ምርጫ በቴዲ አፍሮና በደጋፊዎቹ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ መንፈሳዊ ከፍታ የሚወስድና አርቲስቱ “እኔ ከብርሃኑ ወገን ነኝ” የሚል ምስል ለመፍጠር የተጠቀመበት መንገድ እንደሆነ ይነገራል። ቁጥሩ የብልጽግና ምልክት በመሆኑም፣ ቴዲ የደረሰበት የዝናና የሀብት ከፍታ ከመለኮታዊ ድጋፍ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማሳየት ያስችለዋል። ይህ በምሥጢራዊነት የተሞላ የአልበም መግለጫ አየሩን እንዲቆጣጠርና በኢንዱስትሪው ውስጥ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ ብልጽግና በመደመር ሳይሆን የሚመጣው በኢቶሪካ ነው፤ ለዚህም ደግሞ መለኮታዊ ድጋፍ አለን የሚል የአጸፋ ምላሽ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።

ዓመጽን፣ ለውጥን ማነሳሳት እና 888

በሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ቁጥሮች ሰዎችን ለአንድ ዓላማ ለማንቀሳቀስ ይውላሉ። ከዚህ አኳያ ከታሰበበት 888 ለለውጥ ማቀጣጠያ፣ ለውስጥ አብዮት ማነሳሻ፣ ለዓመጽ ማቀጣጠያ ማገለገሉ ከብዙ በጥቂቱ ነው።

ከሥርዓት ለውጥ ጥሪ አንጻር 888 “አዲስ ጅምርን” ይወክላል። በመሆኑም 888ን ዘፋኞች በአገራቸው ውስጥ ያለውን ነባሩን ፖለቲካዊ ወይም ማኅበራዊ ሥርዓት በመቃወም “አዲስ ዓለም” ለመፍጠር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ እንደ መፈክር ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ይህ በአድናቂዎች ዘንድ “አሮጌውን ሥርዓት አፍርሱ” የሚል የዓመጽ መንፈስ መቀስቀሻ ተደርጎ ይወሰዳል።

እንግዲህ ቴዲ ከየትኛው ጎን ሆኖ ይህን መለያ እንደመረጠ ይፋ ስላላደረገ አፍ ሞልቶ መናገር ባይቻልም፣ በቅርቡ እነ አቶ ነዓምን፣ “ታዋቂ ሰዎችን፣ የኪነት ሰዎችን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን፣ ወዘተ እንጠቀማለን” በማለት በኢትዮጵያ ምርጫውን ተቀባይነት እንዳይኖረው (በእርሱ ቋንቋ delegitimize) ለማድረግ በተጀመረው የዓመጽ አደራጅ ቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ከተናገሩት ጋር ይገጥማል በሚል ስጋት የገባቸው ጥቂት አይደሉም።

የዚሁ የእነ አቶ ነዓምን እና አቶ ልደቱ ድርጅት የፕሮፓጋንዳ ክንፎች “እንጠብቅሃለን” በማለት በቴዲ አፍሮ አልበም ስም የተሸለመ ጥብቆ ደምቀው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ዘመቻ መጀመራቸው ባለቤቱ አምለሰት “ጥቁር ልበሱ” በሚል ስታቀጣጥለው የነበረውን የውክልና ዘመቻ የሚያስታውስ መሆኑን የሚጠቅሱ አሉ። በዚህ በከሸፈው “ጥቁር ልበሱ፤ ወደ አራት ኪሎ ገስግሱ” ዘመቻ ወቅት “ከአራት ኪሎ ለዙፋኑ ቅርብ ከሆኑ መመሪያ እየጠበቅን ነው” ሲሉ የተሰሙ መኖራቸው የሚታወስ ነው። ይህ ጊዜው ሲደርስ የሚዘረገፍ የአራት ኪሎ ስብስብ ገድል ነው።

የውስጥ አብዮት ለማስነሳት የሚውለው 888ን “እንደ ምልክት የሚጠቀሙ አድናቂዎች ራሳቸውን እንደ አንድ ልዩ ሠራዊት እንዲቆጥሩ በማድረግ፣ ዘፋኙ የሚሰጠውን ማንኛውንም ትዕዛዝ ወይም ዓቋም ያለ ጥርጣሬ እንዲቀበሉ ሊያደርጋቸው ይችላል” የሚሉት ወገኖች “ይህቺን ካንጠለጠልህ ጥይት አይመታህም” ልክ እንደሚባለው ዓይነት የድግምት ተጽዕኖ እንደሚመለከቱት ይገልጻሉ።

ወቅቱን ጠብቆ የተለቀቀው “ናዕት”

ቴዲ አፍሮ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ የሙዚቃ ሥራዎቹ የሚታወቅ ነው፤ ሁኔታዎችን ዓይቶ የሚወስደው እርምጃና የሚለቀው ነጠላ ዘፈን በአንዳንዶች ዘንድ “ጥቅመኛ” የሚል ስያሜ የሚያሰጠው ቢሆንም ድፍረቱ ግን አሁንም አየሩን እንዲቆጣጠር አድርጎታል። ከበርካታ ዓመታት በፊት አንድ የትግራይ ተወላጅ ሙስሊም ወጣት በሶማሊያ የተበየነበትን ፍርድ ቴዲ በሺዎች ብር ከፍሎ፣ ነጻ አስወጥቶ፣ ከቤተሰቡ እንዲቀላል ያደረገበት የሚረሳ አይደለም።

በዚህ ልክ ታላቅ ሥራ የሠራው ቴዲ ሌላም የማይታወቅ ወይም ብዙም የሚይጠረጠርበት ምሥጢራዊ ማንነትም አለው። በትህነግ ዳግም ወረራ አማራ ክልል ወደ ዓመድነት ሲቀየር፣ በቃላት ሊገለጽ የማይችል አስደንጋጭ፣ ሊታመን የማይችል ግፍ፣ ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈጸም፣ አፋር ክልል ሲወደም፤ ቤተ እምነቶች ሲረክሱ፣ መነኮሳት ሲደፈሩ፣ የምነና ቆባቸውን ጥለው ማቅ ሲለብሱ፣ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ተምሳሌቶች ሲገደሉ፣ ገዳዮቹና ጨፍጫፊዎቹ በገሃድ እየታወቁ የቴዲ ዝምታ ሌላው ጥያቄን የጫረ ጉዳይ ሆኖ ያለፈና እስካሁን መልስ ያልተገኘለት ጉዳይ ነው። አሁን ላይ የሕዝብ ሰቆቃ ድምፅ ነኝ በማለት በጽሑፍና በዘፈን እንደሚያደርገው ያኔም ተመሳሳይ ነገር አለማድረጉ ምን ይሆን ምሥጢሩ የሚያሰኝ ሆኖ ቀርቷል።

ወረራውን ለመመከት ከልሒቅ እስከ ደቂቅ፤ ከምሑር እስከ ተማሪ፤ የሕክምና ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች፣ በግምባር ለመፋለም ብቻ ሳይሆን ሠራዊቱን ለማነቃቃት በግምባር እየተገኙ ስለ ኢትዮጵያ ሲያዜሙ፣ ወታደሩን ሲያደፋፍሩ፣ ደሙን ሲጠርጉ፣ ቁስሉን ሲያጥቡ፣ ቀለቡን ሲያዘጋጁ፣ ቴዲ “ፍቅር ያሸንፋል” ብሎ ይመስላል ዝምታን ነበር የመረጠው። የብልጽግና ሹመኛ የነበረው ዮናስ ዘውዴ “ቴዲን በአካል አውቀዋለሁ፤ ለህልውና ዘመቻው እንዲቀሰቅስ ብዙ ተለምኖ፤ ብዙ ተጎትጉቶ ነበር እርሱ ግን ወይ ፍንክች” ብሎ እንደነበር ሰሞኑን ባጋራው መረጃ መግለጹን ልብ ይሏል። 

ከወረራው በኋላም የግፍ ገፈት ቀማሾችን መልሶ ለማቋቋም ርብርብ ሲደረግ፣ ገንዘብ ሲሰበሰብ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ሕዝብ ሲረዳዳ፣ … ሠንደቋን የሙጥኝ ብሎ በየመድረኩ የሚታየው ቴዲ አንዲት ኮንሰርት አድርጎ ለተፈናቃዮች መርጃ የሚውል ገንዘብ ሲያሰባስብ አለመታየቱ የቴዲ “ኢትዮጵያ” በነጠላ ዘፈኑና በመድረክ ላይ ብቻ ትሆን ያለችው የሚያስብል ሆኖ አልፏል።

በዚያን ወቅት (የዛሬ አራት ዓመት) “ናዕት” በሚል ርዕስ ያወጣው ዘፈኑ ሲያልቅ “መታሰቢያነቱ ላለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አለአግባብ በግፍ ለተገደሉ፣ አካላቸው ለጎደለ እና ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ንጹሐን ዜጎች በሙሉ ይሁን” ይላል። “መታሰቢያነቱ” ነው የሚለው እንጂ “ገቢው” አላለም!!

ሌላው የሚጠቀሰው ጉዳይ “ናዕት” የሕዝብ ጩኸት ነው፤ የሕዝብ ድምፅ ነው የተባለለትን ያህል የወጣበት ጊዜ ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም። እንደ አርቲስትና እንደ ኢትዮጵያዊ ቴዲ የሕዝብን ድምፅ በ“ናዕት” በዚህ መልኩ ማሰማቱ ችግር የለውም። ጥያቄ የሚፈጥረው ግን የተለቀቀበት ቀን ነው – ቴዲ የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ “ሳር ያለመልማል ዛሬም በእልፍ አእላፍ ሬሳ” የሚል ስንኝ ያለበትን “ናዕት” የለቀቀው “አረንጓዴው አሻራ” የችግኝ ተከላ በሚጀመርበት ዕለት ነበር። በርግጥ የዘፈኑ ዓላማና የተለቀቀበት ቀን የሕዝብ ድምፅ መሆን ነው ወይስ በሕዝብ ድምፅ ስም ሌላ ዓላማ ይኖረው ይሆን ብሎ የሚያስጠይቅ ነው። የአሁኗ 888ስ እንዲሁ በጥናት የተከሰተች ኮድ ናት ወይስ የኪነ ጥበብ ብቻ ውጤት ነች? 

ወደኋላ መለስ ብለን ትህነግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕዝብ በሚያሰቃይበት ጊዜ እና በጅምላ በሚጨፈጭፍበት ጊዜ፤ የወልቃይት ሕዝብ መግቢያ አጥቶ በጅምላ ሲታረድ በነበረበት ዘመን በቴዲ ሚስት አምለሰት መሪነት “አረንጓዴ መሬት” የሚል ችግኝ መትከል ፕሮጀክት ነድፋ ታስተዋውቅ ነበር (ጎልጉል የሠራው ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል)። ፕሮጀክቱ በሒልተን ሆቴል ሲተዋወቅም ቴዲ የመጀመሪያ ልጁ ሚካኤል ያለበትን ፎቶ በትልቁ አሠርቶ ለሚስቱ መድረክ ላይ ሲያበረክት እንዲህ ነበር ያለው፤ “ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል”።

“ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል” ቴዲ አፍሮ

የባለቤቱን የችግኝ መትከል ፕሮጀክት በመደገፍ ይህንን በአደባባይ የተናገረው ቴዲ በናዕት ዘፈኑ “ሳር ያለመልማል ዛሬም በእልፍ አእላፍ ሬሳ” ብሎ ቀን ጠብቆ በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ዕለት ነጠላ ዜማ መልቀቁን፤ በደጋፊዎቹ “ንጉሡ” እየተባለ የሚጠራው ቴዲ የሚሠራው ለማን ነው የሚል ጥያቄ ይጭራል። ለጎረቤትና ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ነው እንዳይባል “ኢትዮጵያ” እያለ የሚያዜምላት አገሩን በዚህ ልክ አሳልፎ ሊሸጥ ይችላል ብሎ እንዴት ማሰብ ይቻላል?  

ኢቶሪካ ሌላ ጊዜውን ጠብቆ የወጣ “ናዕት”?

“ጦርነት ሁሉ በማስመሰልና በማታለል ላይ የተመሠረተ ነው” ይላል ሱን ዙ ስለ ጦርነት ጥበብ ሲናገር፤ “ማጥቃት በምንችልበት ጊዜ ዓቅም የለሽና የማንችል ሆነን እንታያለን፤ ኃይል መጠቀም በምንችልበት ጊዜ ምንም የማናደርግ ሥራፈት መስለን መታየት አለብን፤ ስንቀርብ ጠላታችን በጣም የራቁ ናቸው ብሎ እንዲያስብ ማሳመን አለብን፤ ስንርቅ ደግሞ የቀረብን እንዲመስለው አድርገን ማሳመን አለብን”።

ሐሙስ የሚለቀቀው የቴዲ አፍሮ አልበም ታቅዶበት ይሁን ወይም እየሆኑ ባሉ አጋጣሚዎች ትኩረት እየሳበ ነው። ከላይ እንደገለጸነው የ888 “ምሥጢርም” ሆነ የኢቶሪካ አልበም ምንነት ጊዜውን ጠብቆ የሚታወቅ ነው የሚሆነው። በቁጥሩ ምን ድብቅ መልዕክት እያስተላለፈ ይሆን? ወይስ እንዲሁ የሀበሻ ሤራ ነው? ወይስ እንዲሁ ደስ ብሎትና ነገሩ ተገጣጥሞበት ነው?

“ዘፈንና ዘፋኝነት ኃጢአት ነው”፤ “ዘፋኞች መንግሥተ ሰማያትን አይወርሱም” በሚለው አስተምህሮ የሚታወቁ የቤተ ክህነት ሰዎች፤ ማለትም ሰባኪያንና መምህራን “ኢቶሪካ” ዘፈን ሳይሆን ከሰማይ የተላከ የመላእክት ዝማሬ አድርገው እየመሰከሩለት ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ በርካታ ተከታይ ያላቸውና በትምህርታቸው የሚታወቁት መምህር ዶ/ር አረጋ አባተ “ኢቶሪካ”ን በተመለከተ አጭር ጽሑፍ ለቅቀዋል። ብልጽግናን አምርረው የሚቃወሙትና የሞዐ ተዋህዶ ግምባር ቀደም ደጋፊና ቀስቃሽ የሆኑት መምህር አረጋ ስለ ቴዲና ስለ አልበሙ ሲናገሩ እንዲህ በማለት ይጀምራሉ “እንኳን ዘፈን መዝሙሩም ማድመጥ የምወድ ሰው አይደለሁም። ኤዲት ማድረግ ካልሆነ ትኩረት የሚፈልግ ሥራ ስሠራ ጸጥ ያለ ቦታ ነው የምመርጠው። ሕይወቴ እንዲያ ስለሆነ መዝሙርም ቢሆን የማድመጥ ልምድ የለኝም። የቴዲን ግን ብዙዎቹም ሙዚቃዎቹን ሰምቻለሁ። … ሙዚቃው ሲወጣ ቢሮ እየሠራሁ እሰማዋለሁ” በማለት መዝሙር መስማት ብዙም የማይወዱት የሃይማኖት መምህሩ ለኢቶሪካ ቅስቀሳ አድርገዋል።  

ሞዐ ተዋሕዶ “ነጻ አውጪ ግምባር” – ሞነግ

ከላይ እንደጠቀስነው ከሻዕቢያ ተልዕኮና ገንዘብ ተቀብለው “ሕዝባዊ ዓመፅ” በመቀስቀስ ምርጫውን “ሕገወጥ” ለማድረግ ከሚንቀሳቀሱት እነ አቶ ነዓምን ጀምሮ ከላይ እስከተጠቀሱት የሃይማኖት መምህር አረጋ ድረስ ኢቶሪካን ወደ አራት ኪሎ የሚያደርስ ተስፋቸው አድርገውታል። የሚያደርገውን ነገር፤ የሚመርጠውን ቀን፤ የሚናገርበትን ሚዲያ፤ ወዘተ በጥንቃቄ እንደሚያከናውን በቅርብ ወዳጆቹ የሚነገርለት ቴዲ ስምንተኛውን ወር፣ ስምንተኛውን ቀንና ስምንተኛው ሰዓት (888) አለምክንያት አልመረጠም። መሳካት አለመሳካቱ እንዳለ ሆኖ “ናዕት” በታቀደለት ቀንና ጊዜ እንደወጣ ሁሉ ኢቶሪካም እንዲሁ በዕቅድ የተደረገ ለመሆኑ ብዙ ጠቋሚ ነገሮች አሉ። ውጤቱና ሌላው ጉዳይ ሰሞኑን በሀገራችን ከሚከሰተው የፖለቲካ አቅጣጫ አኳያ የሚታይ ይሆናል።

ማጠቃለያ፤ ቴዲ በዘፈን ሥራው የተካነ ነው፤ የሚያወጣቸው ዘፈኖች ተወዳጅ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያ የሚናገረው ልብን ይነካል፤ ስሜትን ይኮረኩራል፤ በዚህ ዓይነት የልዕልና ማማ ላይ ያለው ቴዲ በዚሁ ልክ ስለ ሀገር፤ ስለ ኢትዮጵያ ብሎ ጥቂት ርቀት ሲሄድ ግን አይታይም። እርሱ በሙዚቃው የሚያወድሳትንና ከልጆቹ ጋር በሰላም እንዲኖሩ  የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ፤ ደሙን እያፈሰሰ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለሚያስጠብቀው ወታደር ቴዲ ያደረገው ምን ነገር አለ? እንደ ቀደምት አርቲስቶች ለሠራዊቱ ሲያዜም ወይም ግምባር ሄዶ ሲያነቃቃ አይታይም። የፍቅር መልዕክተኛ ስለሆነ ነው ከተባለም ዕውቅናውንና ሃብቱን ተጠቅሞ ለሀገር የሚጠቅም፤ ሥራ የሚፈጥር መሠረተ ልማት ሲገነባ አይታይም። በመድረክ እንደሚታየው ትህትናው ለአረጋውንም ሆነ ለችግረኞች የሚሆን ይኼ ነው የሚባል የሠራው ተጠቃሽ የማኅበራዊ ጉዳይ ሥራ የለም፤ ቢያንስ ዝናውን ተጠቅሞ ሕዝብን አስተባብሮ በላብ ተነክሮና በእንባ ታጅቦ ለሚያዜምላት ኢትዮጵያ የሚሆን ስሙ የሚጠራበት መሠረተ ልማት ሠርቶ አይታወቅም። ታዲያ የቴዲ ማንነት የትኛው ነው? የቴዲስ ኢትዮጵያ የት ይሆን ያለችው?

በመጨረሻም ደራሲው አንድሬ ማልሩ በተናገረው እናብቃ፤ “የሰው ልጅ ማንነቱ፣ ነኝ ብሎ የሚያስበው ወይም በገሃድ የሚታየውና የሚያሳየው ሳይሆን እውነተኛ ማንነቱ የደበቀው ነው”።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Left Column, Politics Tagged With: etorika, teddy afro

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ሪፖርተር፡ “ስውር ተልዕኮ” – በከባድ ወንጀል ሊከሰስ May 6, 2026 11:55 pm
  • የፋኖ ኃይል በደረሰበት ጉዳት ሃምሳ ሺህ የሚጠጋ ትጥቅ ጥሎ ጠፋ April 29, 2026 02:27 pm
  • አዲሱ የቴድሮስ ካሳሁን 888 ኮድ፤ እንደ 666?! April 15, 2026 05:53 am
  • ምኑ ነው ያሳቃችሁ፤ ያስደሰታችሁ? April 2, 2026 10:52 am
  • የጀዋር መሃመድ የፖለቲካ ማንነት እና የባዕዳን ተልዕኮ April 2, 2026 10:16 am
  • ከግብፅ በዳያስፖራ ትርምስ ጠማቂዎች በኩል ፋኖ ወደ አዲስ አበባ የላከው “ስጦታ” March 27, 2026 09:14 am
  • “ሰላማዊ ታጋዮቹ” እነ ልደቱ ከአራጁ ሸኔ ጋር ተጣምረዋል March 25, 2026 01:04 pm
  • ጸረ-ኢትዮጵያዊ የሆነው የሪፖርተር አዘጋገብ March 19, 2026 11:54 am
  • የአውሬው ሪፖርተር ቀላቢዎች፡ የኦሮሚያ የልማት ድርጅቶች March 18, 2026 10:48 am
  • የጃኖ ስጦታና የዶሮ ፖለቲካ በጎንደር March 10, 2026 09:24 am
  • “አዲሷ” ኢህአፓ፤ ከንፈሯን ቀለም የተቀባች አሳማ February 25, 2026 11:24 am
  • የተንጋደደው የገዱ መልስ February 6, 2026 03:05 pm
  • ሻዕቢያ “አክሱም ገብቶ ወጣቶች በጅምላ ሲረሽን ጸብ ተፋፍሟል …” February 4, 2026 01:15 pm
  • አደራ ጠባቂው የኢሉአባቦር ሕዝብ February 4, 2026 12:14 pm
  • የአውሬው ሪፖርተር ቀላቢዎች፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን January 28, 2026 09:56 am
  • በአሜሪካ ጥምር ዜግነት እንዲቀር ጥያቄ ቀረበ January 27, 2026 03:05 pm
  • “ከህወሓት፣ ከሻዕቢያ፣ ከግብፅ ሰዎች ጋር ሆኖ እንዴት የአማራን ጥያቄ ማስመለስ ይቻላል?” ኮሎኔል ፈንታው January 25, 2026 04:23 am
  • የኢትዮጵያ አየር ኃይል: ለአፍሪካ ሀገራት የመጀመሪያዎቹን የአየር ኃይል አብራሪዎች ያሰለጠነ ተቋም January 25, 2026 03:50 am
  • የአማረ ሪፖርተር እያደረሰ ያለው የብሔራዊ ደኅንነት አደጋ January 22, 2026 01:56 am
  • የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማርያምን ማዕረግ ዝቅ አደረገች December 12, 2025 09:27 pm
  • ኢህአፓ: ከነጭ ሽብር ወደ “አዲስ አበባ ትናገር” የጎዳና ሽብር? December 12, 2025 09:11 pm
  • EOC Bans Haile Gebrselassie Over Are­qie Comments Linked to Doping November 21, 2025 07:47 pm
  • በሥራ ማቆም አድማ ጥሪ ዘርፍ ባለሙያው ጃዋር ሌላ ጥሪ አቀረበ November 17, 2025 09:25 am
  • የ-አብሮነት ማኅበር የመረጠው ሕቡዕ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፋ ሆነ November 5, 2025 12:06 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2026 · Goolgule