ቴዲ አፍሮን የሚወዱት ሰዎች እጅግ በርካታ የመሆናቸውን ያህል ጥቂት የማይባሉ ደግሞ አምርረው ይጠሉታል። ደጋፊዎቹ በተለይ በዘመነ ትህነግ በድፍረት የሚያዜማቸውን እያነሱ “የአንድ ሰው ሠራዊት” ይሉታል። የሚጠሉት ደግሞ ቴዲ “ሰላም፤ እንደምን አደራችሁ?” ቢል እንኳን “ይሄ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ፣ …” በማለት የስድብ ናዳ ያወርዱበታል።
ቴዲ በትህነግ ዘመን ግልጽ ግፎች ደርሰውበታል። የሙዚቃ ኮንሰርቶቹ ያለ ምንም ካሣና ቅድመ ማስታወቂያ ቲኬት ከተሸጠ በኋላ በተደጋጋሚ ተሰርዘውበታል። የጎዳና ተዳዳሪ ገድለሃል በሚል ክስ ለእስር በተዳረገበት ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረበ ቁጥር ያለማቋረጥ እያለቀሰ ንጹሕ መሆኑን ለማሳመን ሞክሯል። ከእስር የተለቀቀበት አግባብም በራሱ ብዙ ሊያስብል የሚችል ነው።
በአገራችን የለውጥ መዓበል በተነሳበት ወቅት ጃዋርን ጨምሮ አክራሪና ጽንፈኛ ኦሮሞዎች ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ የተጠናከረ የቢራ ፖለቲካዊ ዘመቻ በከፈቱበት ጊዜ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ እንደሚዲያ ተግባሩን በማውገዝ ተሟግተናል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ቴዲ “ምኒልክ ጥቁር ሰው” በሚለው ሙዚቃው በድፍረት የሄደበትን መንገድ፤ ያውም በዘመነ ትህነግ፤ አድንቀናል፤ አወድሰናል። የሚቃወሙትም እስከ ጥግ ሄደው ብዙ ብለዋል።
ቴዲ አፍሮ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ የሙዚቃ ሥራዎቹ የሚታወቅ ነው፤ ሁኔታዎችን ዓይቶ የሚወስደው እርምጃና የሚለቀው ነጠላ ዘፈን በአንዳንዶች ዘንድ “ጥቅመኛ” የሚል ስያሜ የሚያሰጠው ቢሆንም ድፍረቱ ግን ታዋቂነቱንና የደጋፊውን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምርለት ያደረገ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ የትግራይ ተወላጅ ሙስሊም ወጣት በሶማሊያ የተበየነበትን ፍርድ ቴዲ በሺዎች ብር ከፍሎ፣ ነጻ አስወጥቶ፣ ከቤተሰቡ እንዲቀላል ያደረገበት የሚረሳ አይደለም።
ታላቁ የአደባባይ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ከሚታወቁባቸው መለያዎች ዋነኛው እውነትን ቁልጭ አድርገው በመናገራቸው ወይም በመጻፋቸው ነው፤ ለዚህም በርካታ እንግልት ደርሶባቸዋል። በቅርብ ጓደኞቻቸው ተከድተው ብቸኛ ሆነዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ሲመረጡ ሕዝቡ የመጀመሪያ ሴት የአገራችን መሪ ሆነው ሲያይ ደስ አለው። የኔታ መስፍን ግን የተቃውሞ ድምጻቸውን ካሰሙት ቀዳሚው ሆነው ሲታወሱ ይኖራል።
ግን ደግሞ ፕሮፍ ጭፍን ተቃዋሚ ብቻ አልነበሩም። ባህርያቸው የፈለገ ክፉ ቢሆን መንግሥትንም ሆነ ግለሰብ የቱንም ያህል የሚቃወሙት ቢሆን መልካሙን ሥራውን ግን ይጠቅሳሉ። ለምሳሌ የፓርቲ ፖለቲካና ውይይትን በአገራችን ያስጀመረው ወያኔ ነው በማለት ፕሮፍ ተገቢውን ምስጋና ይቸራሉ። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን በንቁ አድማጭነቱ ያደንቁታል፤ ለሌሎችም እንዲሁ ተግባራቸውን ቢጸየፉ እንኳን በጭፍንና በጅምላ ወይም እንደ መድረክ ሰው የሕዝብን ጭብጨባ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ሰውን አይነቅፉም፤ በመንጋ አስተሳሰብ አይመሩም። እንዲያውም “ጭብጨባ ሲበዛ ጭንቅላት ያብጣል” ይሉ ነበር።
ትህነግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕዝብን ጠፍንጎ በያዘበትና በተለይም የአማራን ሕዝብ ለማጥቃት ብሎ ግፉንና መከራውን ባከረረው ጊዜ፤ የወልቃይት ሕዝብ መግቢያ አጥቶ በጅምላ ሲጨፈጨፍ በነበረበት ጊዜ፤ ለአገር የሚያስቡ ሰዎች አልጠፉም ነበር። የአገራችን የወደፊት በረሃነትና የሕዝቧ መከራ ያሳሰባት አምለሰት ሙጬ ከባለቤቷ ጋር “አረንጓዴ መሬት” ብላ ችግኝ የመትከልን ተግባር በወጣቱ ዘንድ እንዲስፋፋ ፕሮጀክት ነድፋ ነበር። ዘጋቢ ፊልም ሠርታ ተሸልማበታለች፣ ተሞግሳበታለች። ቴዲም ለዚሁ ፕሮጀክቷ ዘፍኖላታል። በፊልሙ ላይ መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ (የቀድሞ የኢህአዴግ ፕሬዚዳንት)፣ የ“ለም ኢትዮጵያ” መሥራች የሚባለውና የትህነግ ተሟጋች ቆስጠንጢኖስ በርኼ (ዶ/ር ነኝ የሚል ግን ዲግሪዎቹ በሙሉ የሐሰት የሆኑ)፣ አዜብ ግርማይ ከENDA ግብረሰናይ ድርጅት፤ እና ሌሎችም ታዋቂ ሰዎችና የሙያው ባለቤቶች ተሳትፈውበታል።
የዛሬ ሰባት ዓመት አካባቢ የዞን ዘጠኝ ልጆች በትህነግ እስር ቤት ሲማቅቁና በካንጋሮ ፍርድ ቤት ሲንገላቱ፤ የእስር ቤቱ ቋንቋ ኦሮምኛ በነበረበት ጊዜ፣ ቀይ ባሕርን አቋርጠው ወደ አረብ አገር ከተሳካላቸውም ወደ አውሮጳ ሲሰደዱ የአዞ ምሳ ሆነው ሲቀሩና በአንድ ቀን ብቻ 70 የሚሆኑ ሲሞቱ፤ ትህነግ በባሕር ዳር አማራዎችን ሲያርድና መነኮሳትን ሲገድል፣ ቤተእምነትን ሲያረክስ፤ በጉራ ፈርዳ አማሮች ለዓመታት ሲያርሱት የነበረውን መሬታቸውን ተነጥቀው አቤት የሚልላቸው ጠፍቶ አንገታቸውን ሲደፉና ያለ ጥሪት ሲቀሩ፤ ወዘተ በዚያኑ ጊዜ የአገርን ወደፊት ያሰቡና የተጉ ለሠሩት ተግባር በሒልተን ሆቴል ሽልማት ሲደረግላቸው ነበር።
በታኅሳስ 2007ዓም በሒልተን ሆቴል በተካሄደው ሥነሥርዓት ላይ ቴዲ አፍሮ ይናገራል፤ ያመሰግናል። ተሸላሚዋና ተመስጋኟ ሚስቱ አምለሰት ነች። “አረንጓዴ መሬት” ዘጋቢ ፊልም የሠራችውና ያዘጋጀችው ባለቤቱ አምለሰት ሙጬ ወደ መድረክ ተጠርታ ባሏ ያዘጋጀላትን ግን ያላሰበችውን ሥጦታ እንድትቀበል ቴዲ ይጠራታል። ትልቅ ፎቶ ነው ሽልማቱ። አላሰበችውምና ተደነቀች፣ እጅግ ተደሰተች። ሚካኤል ቴዎድሮስ ገና ጨቅላ ሕጻን ነበር፤ የስድስት ወር ልጅ። በፎቶው ላይ ችግኝ ሲተክል ይታያል። ቴዲም ሽልማቱን ለሚስቱ ሲሰጥ ይህንን አለ፤ “ሚካኤል ራሱ ችግኝ ነው፤ የስድስት ወር ልጅ ነው። ችግኝ እየተከለ ነው”።
በደርግ ጊዜ የአካባቢ ጥበቃና የደን ልማት በሰፊው ይካሄድ ነበር። በወቅቱ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ የነበሩት ከዚህ በፊት ለጎልጉል የተናገሩት የማይረሳ ነው። በእርሳቸው አመራር 1 ሚሊዮን ችግኝ ከአዲስ አበባ እንጦጦ እስከ ሰሜን ሸዋ ባለው እንዲተከል አድርገው ነበር። “አረንጓዴ አሻራ” ከመተግበሩ በፊት እንጦጦ ላይ የምናያቸው ዛፎች በእርሳቸው አመራር የተተከሉ ነበሩ። ያኔ በመተከላቸው ዘመናትንና ትውልድን ተሻግረው በርካታዎችን ጠቀሙ፤ አገርን አለሙ፤ አካባቢን ጠበቁ።
ደርግን ይጠሉና ይቃወሙ የነበሩ ኢህአፓዎች ግን ጸረ ችግኝ ነበሩ። ደርግን የጎዱ ይመስል በወዶ ፈቃደኝነት ለችግኝ ተከላ ሲዘምቱ ወይ ቀድሞ የተተከሉትን ወይም ራሳቸው የሚተክሉትን ችግኞች እየገለበጡ ይተክሉና በአገር ላይ ኪራሣ ያስከትሉ ነበር ብለው ኃላፊው ነግረውናል። ችግን ተከላን መቃወም ጤና ቢስነት ነው።
ትህነግ ሠሜን ዕዝ ላይ በራሱ ቃል “መብረቃዊ ጥቃት” አድርሶ ወታደሮቻችንን ሲያርድና የአገር መከላከያን ሲያፈርስ ሁላችንም ተቆጣን። ታዋቂ የኪነጥበብ ሰዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከዳር እስከ ዳር ቁጣቸውን ገለጹ። ዝምታን የመረጡም ነበሩ። የአገር ተቆርቋሪነቱ ጥያቄ ውስጥ የማይገባው ቴዲን ብዙዎች ነጠላ ይለቅና የወታደሩን ሞራል ያነሳሳል ብለው ጠብቀውት ነበር። ተስፋ እንዲያደርጉ ምክንያት የሆናቸው “ጥቅመኛ” ነው ተብሎ እስኪወቀስ ድረስ ልዩ ክስተት ሲፈጠር በፍጥነት ዘፈን በማውጣት ቴዲን የሚስተካከለው ባለመኖሩ ነበር። ግን አልሆነም።
በትህነግ ዳግም ወረራ አማራ ክልል ወደ ዓመድነት ሲቀየር፣ በቃላት ሊገለጽ የማይችል አስደንጋጭ፣ ሊታመን የማይችል ግፍ፣ ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈጸም፣ አፋር ክልል ሲወደም፤ ቤተ እምነቶች ሲረክሱ፣ መነኮሳት ሲደፈሩ፣ የምነና ቆባቸውን ጥለው ማቅ ሲለብሱ፣ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ተምሳሌቶች ሲገደሉ፣ ገዳዮቹና ጨፍጫፊዎቹ በገሃድ እየታወቁ የቴዲ ዝምታ ሌላው ጥያቄን የጫረ ጉዳይ ነው።
ወረራውን ለመመከት ከልሒቅ እስከ ደቂቅ፤ ከምሑር እስከ ተማሪ፤ የሕክምና ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች፣ በግምባር ለመፋለም ብቻ ሳይሆን ሠራዊቱን ለማነቃቃት በግምባር እየተገኙ ስለ ኢትዮጵያ ሲያዜሙ፣ ወታደሩን ሲያደፋፍሩ፣ ደሙን ሲጠርጉ፣ ቁስሉን ሲያጥቡ፣ ቀለቡን ሲያዘጋጁ፣ ቴዲ “ፍቅር ያሸንፋል” ብሎ ይመስላል ዝምታን ነበር የመረጠው።
ከወረራው በኋላም የግፍ ገፈት ቀማሾችን መልሶ ለማቋቋም ርብርብ ሲደረግ፣ ገንዘብ ሲሰበሰብ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ሕዝብ ሲረዳዳ፣ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ሳይቀሩ በነጻ ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው እንመልሳለን ብለው ወገናዊነታቸውን ሲያሳዩ ሠንደቋን የሙጥኝ ብሎ በየመድረኩ የሚታየው ቴዲ አንዲት ኮንሰርት አድርጎ ለተፈናቃዮች መርጃ የሚውል ገንዘብ ሲያሰባስብ አለመታየቱ የቴዲ “ኢትዮጵያ” በነጠላ ዘፈኑና በመድረክ ላይ ብቻ ትሆን ያለችው አስብሎናል። አዲስ ያወጣው ዘፈን “ናዕት” ሲያልቅ “መታሰቢያነቱ ላለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አለአግባብ በግፍ ለተገደሉ፣ አካላቸው ለጎደለ እና ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ንጹሐን ዜጎች በሙሉ ይሁን” ይላል። “መታሰቢያነቱ” ነው የሚለው እንጂ “ገቢው” አላለም!!
“ናዕት” የሕዝብ ጩኸት ነው፤ የሕዝብ ድምፅ ነው የሚሉ እጅግ ብዙዎች ናቸው። እንደ አርቲስትና እንደ ኢትዮጵያዊ ቴዲ የሕዝብን ድምፅ በዚህ መልኩ ማሰማቱ ችግር የለውም። አረንጓዴው አሻራ በሚጀመርበት ቀን መለቀቁና በተለይ ችግኝ ተከላን በግልጽ በመቃወም የተሰነቀረው “ሳር ያለመልማል ዛሬም በእልፍ አእላፍ ሬሳ” የሚለው ስንኝ ግን በርግጥ ዓላማው የሕዝብ ድምፅ መሆን ነው ወይስ በሕዝብ ድምፅ ስም ሌላ ዓላማ ይኖረው ይሆን ብሎ የሚያስጠይቅ ነው። የንጹሐንን በግፍ መገደል መቃወምና መንግሥትንም ተጠያቂ ማድረግ ፍጹም ትክክል ቢሆንም በዚያ ሰበብ ችግኝ ተከላን መቃወም “ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል” ተብሎ በአደባባይ የተወሳውን ጨቅላ ህጻን ከንቱ የመድረክ መጠቀሚያ ማድረግ አይሆንም?
በደርግ ጊዜ ከተከናወኑና እጅግ ከሚያስመሰግኑ ተግባራት ቁንጮውና ዘመን የማይረሳው ድንቅ ተግባር በመሃይመነት ላይ የታወጀው ጦርነት ነው። “መሃይምነት ጥቁር መጋረጃ ነው” በማለት ከገጠር እስከ ከተማ የተሠራው ድንቅ ሥራ ጥቂት የማይባሉ ዜጎችን ለኮሌጅ ሲያበቃ በጣት ይፈርሙ የነበሩ ሚሊዮኖች ግን ስማቸውን በብዕር እንዲጽፉ ያስቻለና ሰብዓዊ ክብራቸውን የመለሰ ነው። ይህ የተደረገው ሕዝብ በጦርነትና በረሃብ እንደ ቅጠል በሚረግፍበት ጊዜ ነው። ቴዲ ለዓቅመ ዘፋኝነት በዚያን ጊዜ ቢደርስ ኖሮ “መሃይምነት ይጥፋ ይላል ዛሬም በሕዝብ ሬሣ” ብሎ ይዘፍን ይሆን? በማለት የሚያስጠይቅ ነው። እንኳንም ያኔ ህጻን ሆነ ያስብላል።
በመጨረሻም፤ “የአረንጓዴው መሬት” ሃሳብ ባለቤትና የሃሳቡ አቀንቃኝ እስካሁን በተካሄዱት “የአረንጓዴ አሻራ” ችግኝ ተከላዎች በአንዱም እንኳን ሲሳተፍ አለመታየቱ የጤና ነው? ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል። ቴዲ “ሳር ያለመልማል” በማለት በናዕት ውስጥ የሰነቀራትን ስንኝ ከላይ ከጠቀስነው የኢህአፓ ተግባር ጋር በንጽጽር እንድናየው አስገድዶናል። ይህንን የእርሱን አንዲት ስንኝ ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ የተጀመረውን የችግኝ ተከላ ተቃውሞ ተናብቦ የመሥራት የሰኔ ፕሮጀክት ይሆን ብለን እንድንጠይቅ ገፋፍቶናል? እርሱ ከባለቤቱ ጋር “የአረንጓዴው መሬት” ሃሳብን ሲያራምዱና ችግኝ ሲተክሉ፣ ችግኙ ሚካኤልም እንዲሁ ችግኝ ሲተክል ሕዝብ ይጨፈጨፍ ነበር። የቴዲን የዚያን ጊዜውን ሃሳብ ማንም አልተቃወመም። “ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል” ያለው ቴዲ የሕዝብ ሰቆቃ ድምፅ ነኝ በሚል “ሳር ያለመልማል ዛሬም በእልፍ አእላፍ ሬሳ” ብሎ ቀን ጠብቆ በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ዕለት ነጠላ ዜማ መልቀቁን ግን ሚዛን ደፊውን ቴዲ ሚዛን ተደፋብህ አስብሎናል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ™” አቋም ነው።
Getahun says
ለምንድነው ብዙ ጊዜ ዕውነት ሲነገር የማይወደደው፣ ክቡር (ዶ/ር) ቴዲ አርቲስት ነው ሙያውን ተጠቅሞ ሃሳቡን ጊዜውን በጠበቀ፣ ሁኔታውን ባገናዘበ አማርኛ አዋዝቶ ገልጸዋል፡፡ በዘፈኑ ብዙ ወቅቱን የሚያመለክት ንግግር አድርጓል፣ እውነት እውነቱን፡፡ ማንነቱ ነው፣ ኢትዮጵያዊ የቋንቋ ችሎታውም ታይቶበታል፡፡ በምንም መንገድ ችግኝ አትትከሉ የሚል መልዕክት አያስተላልፍም፡፡ የምንተክልበት አፈር ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የሰው ደም ጠጥቷል ፡፡ አሁንም በየቀኑ እየጠጣ ነው፡፡ በየሙያችን በየቀኑ እውነት እውነቱን እተናገርን ደም መፍሰስ እንዲቆም መስራት አለብን፡፡ እንደዜጋ መንግስትንም ማሳሰብ ማስጠንቀቅ በአግባቡም መደገፍ መብታችን ነው፡፡ ዘፈኑን ችግኝ ተከላው አልፎ ቢያወጣው ኖሮ ልክ ይሆን ነበር!
Abebe Tegegne says
መጻፍ ትችላለህ!
አመስግኖ ለመናድ የተሞከረ ሰለክላካ ውጥን መሆኑ እንደ ጥቁርና ነጭ ውዳሴና ዕርግማኑ ቁልጭ ያለ ነው:: ነገር ግን እሕአፓ ችግኝ ያወድም ነበር ብለህ ጥላቻን በጥላጫ ልትለቀልቅ መሞከርህ ልፋትህን ታሪክን በሚያውቀውና ስሌትን ሳይንሳዊ ባረገው (ጥቂት ቢሆኑም) ያና ይሄ ትውልድ መሃል መጻፍ በመቻል ዕውነታን ማደብዘዝ አያስችልምና…. ሰለክላካ የብዕር ቀለምህ እንዳደፈ ውሃ ወደ ቦዩ ተደፍቶብሃል!!
Editor says
ሰላም Abebe Tegegne
በቅድሚያ መጣጥፉን አንብበው አስተያየት ስለሰጡን የአክብሮት ምስጋናችንን እናቀርባለን።
ኢህአፓን በተመለከተ ያገኘነው መረጃ በስሚ ስሚ ወይም በመሰለኝ ሳይሆን፤ በእንግሊዝኛ ከፈረሱ አፍ እንደሚባለው፤ በወቅቱ መሥሪያቤቱን ሲመሩ ከነበሩ ከራሳቸው የሰማነውን ነው። የችግኝ ተከላውን ሲያስተባብሩና ሲመሩ የነበሩት የነገሩንን ነው ማስረጃ አድርገን ያወጣነው እንጂ ኢህአፓን ባልተፈጠረ ታሪክ ለመውቀስ አይደለም።
ምናልባት ኢህአፓ እንደ ፓርቲ ይህንን አላደረገም ይሆናል። ነገር ግን የኢህአፓ አባላት በራሳቸው አነሳሽነት በግል ይህንን እኩይ ተግባር ፈጽመው ይሆናል። ሲያዙ ደግሞ ኢህአፓ መሆናቸው መረጋገጡና ሌሎች ግን በእንደዚህ ዓይነት ተግባር ላይ አለመሠማራታቸው ኢህአፓዎች ይህንን አደረጉ ሊያስብል ይችላል።
እንደ ማስረጃ ለምሳሌ በደርግ ጊዜ ከሶማሊያ ጋር አገራችን ጦርነት በገባችበት ጊዜ ኢህአፓዎች ሶማሊያን ይደግፉ እንደነበር፤ ስቴዲየም ውስጥ ይህንኑ ድጋፋቸውን ሲገልጹ እንደነበር፤ ለጦር ሠራዊት ይላክ የነበረው ስንቅ ውስጥ የተፈጨ ብርጭቆና አሸዋ ይጨምሩ እንደነበር በርካታ የቀድሞ አባሎቹ ተናግረዋል። ይህ ግን ፓርቲው በመርህ ደረጃ ይህ እንዲደረግ መመሪያ ሰጥቷል ወይም አልሰጠም ለማለት ሳይሆን ድርጊቱን የፈጸሙት አብዛኛዎቹ እነሱ በመሆናቸው ኢህአፓዎች ይህንን ፈጸሙ ሊያስብል ችሏል።
የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ኢህአፓ ላይ ትኩረት ማድረግ ስላልሆነ ጉዳዩን በዚህ ብንዘጋው ጥሩ ነው። ምክንያቱም ከጽሁፉ ዋና ዓላማ ያስወጣናል።
ሆኖም የተጻፈው ጉዳይ ስህተት ነው የሚሉ ከሆነ በጨዋ ደንብ በማስረጃ የተደገፈ የአጸፋ ጽሁፍ ቢልኩልን አክብረን በኤዲቶሪያል ፖሊሲያችን መሠረት ልናትመው እንደምንችል እንገልጻለን።
አርታኢው
2nd editor says
Look at your statement
“የኢህአፓ አባላት በራሳቸው አነሳሽነት በግል ይህንን እኩይ ተግባር ፈጽመው ይሆናል”
“ይሆናል” isn’t this far fetched guess without evidence?
Then you say prove us wrong. Editor – do read what you write?
Editor says
No, it is NOT far-fetched!!
Editor
Tesfa says
ቴዲ አፍሮ በሰው ተጠላ ተወደደ ምን ትርፍ አለው? ለዚያውም የሃበሻ ፍቅር። ወረተኛና ዘረኛ በሆነው። ራሱ የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ባንድ እጅ እየገረፈ በሌላ እጅ አይዞህ የሚል ቅጥ ያጣ ነው። ህይወት አጭር ናት። ሰው ሊያስረዝማት ቢቃጣም ዝም ብሎ መለጣጠፍ ብቻ እንጂ ጥራት ያለው ኑሮ ተፈጥሮ እንዳደለን አይኖርም። አሁን ይህን ከማንበቤ በፊት ገጣሚው ወንድማችን በቀለ ወያ በአፋኙ መንግስት እንደተጠለፈ ይወራል። ወሬውን ሁሉ እንዳለ መሰልቀጥ ባይመቸኝም ሆኖ ከሆነ እጅግ ያሳዝናል። መቼ ነው ያዘው ጥለፈውን ትተን በጠራ እይታ ተሟግተን የምንለያየው? የኢትዮጵያ መንግስት ዞሮበታል። ሰራዊቱን ከጨረሱና ሃገር ከናድ ሃይሎች ጋር ስለ ሰላም ሲያወራ ስለ ሃገራቸው የሚጽፉና የሚያስቡትን አልፎ ተርፎም የጦር አውድ ላይ ገብተው የተፋለሙትን እያፈሰ ዘብጥያ ማውረድ ምን ለማለት ተፈልጎ እንደሆነ ጭራሽ አይገባኝም።
የትግራዪ የጦር አበጋዝ ጄ/ታደሰ ወረደ የትግራይ ሰራዊትና የኢትዮጵያ ሰራዊት ሲገጥሙ እያለ ለሁለት እንስት ጋዜጠኞች የሰጠውን መግለጫ ለተመለከተ አብደናል፤ ምንም የቀረን ነገር የለም ያስብላል። የሚያሳዝነው ስለሚጠይቁት ነገር እንኳን ጭብጥ መልስ አይሰጥም ነበር። ደመሰስናቸው፤ ደረስንባቸው አመለጡን ወዘተ እንጂ። በድካም ወይም በመጠጥ አልፎ ተርፎም በሰው ደም የተነከረ ሰው ቅብዝብዝ ነው። በግልጽ የሚታየውም ያ ነበር። ግን ከብዙ ድንፋታውና ጉራው ባሻገር እውነት ተረግጣ ጠረጴዛው ሥር ነበረች። የእናቶች ዘመቻ እያለ ሲቀልድ መስማት ደምን ያፈላል። እናቶችም እማ ልጆቻችን የት ናቸው እያሉ ነው። ግን ሁሌ እሳት በመቆስቆስ እድሜ ልኩን ያሳለፈ ዘረኛ ተው ቢሉት የሚሰማ አይሆንም። መተው ነገሬን ከተተው የሚለው የሃገራችን ህዝብ እንዲህ ላለው ፍሬ ፈርሲኪ ነገር ነው። መጨራረሱ ይቀጥላል እንደ ጄኔራሉ ድንፋታ!
ወደ ዋናው ነጥባችን ወደ ቴዲ አፍሮ ስንመለስ ያለውን ቁርጠኛ አቋምና የሰላም ሰው መሆኑን አደንቃለሁ። ግን ከተከታዪችም ከሚዘልፉትም ወገን አይደለሁም። ከያኔና ደራሲ የሚመዘኑት በስራቸው በመሆኑ አንድ ቢጠላው አንድ ቢወደው ሰው መሆናችን ያሳያል እንጂ ሌላ ማረጋገጫ ነገር አይደለም። ሲቸመር ኢትዮጵያ እኮ የዶ/ር ጥላሁን ገሰሰን አንገት ለመቁረጥ የሞከሩ ሰዎች ያሉባት ምድር ናት? ይህን ሁሉ ክርፋት የሚያመነጨው ደግሞ የዘርና የቋንቋ ፓለቲካ ነው። ከቀደመው ታሪካችንም እውቁ ደራሲ አቤ ጉበኛ፤ በዓሉ ግርማን አፈር የመለሱባቸው ኢትዮጵያ ትቅደም ያሉ መለዪ ለባሾች ነበሩ። ሌሎችም በወያኔ ሴራ ግባዕተ መሬታቸው የተፈጸመ እልፍ ናቸው። ወንጀላቸው ሃገርን ህዝብን አትከፋፍሉ ተው በህዋላ የባሰ ነገር ይከተላል በማለታቸው ነው። በመሰረቱ የቅርብ ቀኑ የቴዲ አፍሮ ዘፈንና ግጥም ከእርሱ በፊት ሰለ ሃገርም ሆነ በሃገሪቱ ስላለው ችግር ተገጥመው ከተዘፈኑ ወይም ከተዘመሩ የተለዬ ነገር የለውም። ያው ሃበሻው ማሽቃበጥና ሆይ ሆይ ማለት ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ አይነት ሆኖ እንጂ። እንዴት ቢባል ኮፒ በማድረግ በየድህረ ገጽ በመለጣጠፍ ሳንቲም ለመልቀም እንዲያመቻቸው እንጂ።
ደግሞ አንድ መንግስት ችግኝ መትከሉ ወንጀል አይደለም። ለነገሩ ጦርነት ሆኖ እንዴት የስንዴ ማሳ ይጎበኛል የሚሉ የፓለቲካ ሸውራራዎች ያሉበት ሃገር አደለች እንዴ። ጦርነት ስላለ ሳይበላ ይታደራል? ሁሉ ነገር ያዘው ጥለፈው ብቻ ከሆነ እኮ የሚያዝም የሚጠለፍም ሊጠፋ ነው። የፓለቲካውንና የኢኮኖሚውን ሁኔታ አስማምቶ መጓዙ ያለ መሆን የሚገባው ነገር ነው። የኢትዮጵያ ችግር መሪዎቿ ብቻ አይደሉም። ሰውም እንጂ። ሰው ከመቆራቆስ ሌላ ነገርን ለማርገብ፤ ለሚመስለው ድጋፍ ሰጥቶ ሌላውን የማግለል ባህሪው እንደ እስስት ቀለም ተለዋዋጭ ነው። ስለሆነም እንደ ጲላጦስ ውሃ አቅርቦ ከዚህ ደም የለሁበትም ብሎ መታጠቡ ራሱን ለመሸንገል እንጂ ንጽህናውን አያሳይም። ቴዲ አፍሮ ራሱን መጠበቅ አለበት። ሊያጠፉት የሚሹ ሃይሎች ዛሬም አልተኙም። እውቁ ወንድማችን ሃጫሉ ሁንዴሳን በሴራ ያስገደሉት ሃይሎች ዛሬም አልተኙ። ቆፍጠን በል እላለሁ። በቃኝ!
ገብርዬ : says
በመጀመሪያ ሰለ ድረ ገፁና አዘጋጁ ያለኝን አክብሮትና ምስጋን ለመቅረብ እወዳለሁ:::: ለረጅም ጊዜ በድረ ገፁ የሚወጡ ጽሑፎችን የፕለቲካ ትንተናዎችን እንደ(reference) ብዙ ስወችን (share) ሳደርግ ነበር ::በ Editor በኩል የሚወጡ ርዕፅ አንቀጾች ጊዜውን የጠበቀ ትምህርታዊ (fare & balance ) ትንታዎችን ታደርጋለህ :: በአሁኑ ርዕፅ እንቀስህ ላይ በብዙ መንገድ በእጣቀስካቸው ምሣሌዎች በተለይ በፅረ ችግኝ ተከላ ኢህአፓን የደርግ አባል እንዲህ ብለው ነብር ብለህ የደመደክበት ውሳኔ ከእውነት የራቀ ሀስት ነው በዘመኑ ደርግም ወያኔም አሸናፍዎች ስለነበሩ የተሳሳተ ታሪክ መዝግበዋል:: ሰለ Teddy Afro (Editor) በኔ አስተያየት ሊደነቅ የሚገባው አርቲስት ነው በአጭር ቀን ውስጥ ግጥምና ሙዚቃን እ ውቀናብሮ ማውጽጣት በጣም ጥሩ ችሎታ ነው ሌሎችም ከዚህ ሊማሩ ይገባል Teddy አገር ወዳድ ነው period.
Editor says
ሰላም ገብርዬ
በቅድሚያ የድረገጻችን ተከታታይ ስለሆኑና ጽሁፎቻችንም ለሌሎች ስለሚያጋሩ የአክብሮት ምስጋናችንን እናቀርባለን።
ኢህአፓን በተመለከተ ያገኘነው መረጃ በስሚ ስሚ ወይም በመሰለኝ ሳይሆን፤ በእንግሊዝኛ ከፈረሱ አፍ እንደሚባለው፤ በወቅቱ መሥሪያቤቱን ሲመሩ ከነበሩ ከራሳቸው የሰማነውን ነው። የችግኝ ተከላውን ሲያስተባብሩና ሲመሩ የነበሩት የነገሩንን ነው ማስረጃ አድርገን ያወጣነው እንጂ ኢህአፓን ባልተፈጠረ ታሪክ ለመውቀስ አይደለም።
ምናልባት ኢህአፓ እንደ ፓርቲ ይህንን አላደረገም ይሆናል። ነገር ግን የኢህአፓ አባላት በራሳቸው አነሳሽነት በግል ይህንን እኩይ ተግባር ፈጽመው ይሆናል። ሲያዙ ደግሞ ኢህአፓ መሆናቸው መረጋገጡና ሌሎች ግን በእንደዚህ ዓይነት ተግባር ላይ አለመሠማራታቸው ኢህአፓዎች ይህንን አደረጉ ሊያስብል ይችላል።
እንደ ማስረጃ ለምሳሌ በደርግ ጊዜ ከሶማሊያ ጋር አገራችን ጦርነት በገባችበት ጊዜ ኢህአፓዎች ሶማሊያን ይደግፉ እንደነበር፤ ስቴዲየም ውስጥ ይህንኑ ድጋፋቸውን ሲገልጹ እንደነበር፤ ለጦር ሠራዊት ይላክ የነበረው ስንቅ ውስጥ የተፈጨ ብርጭቆና አሸዋ ይጨምሩ እንደነበር በርካታ የቀድሞ አባሎቹ ተናግረዋል። ይህ ግን ፓርቲው በመርህ ደረጃ ይህ እንዲደረግ መመሪያ ሰጥቷል ወይም አልሰጠም ለማለት ሳይሆን ድርጊቱን የፈጸሙት አብዛኛዎቹ እነሱ በመሆናቸው ኢህአፓዎች ይህንን ፈጸሙ ሊያስብል ችሏል።
የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ኢህአፓ ላይ ትኩረት ማድረግ ስላልሆነ ጉዳዩን በዚህ ብንዘጋው ጥሩ ነው። ምክንያቱም ከጽሁፉ ዋና ዓላማ ያስወጣናል።
ሆኖም የተጻፈው ጉዳይ ስህተት ነው የሚሉ ከሆነ በጨዋ ደንብ በማስረጃ የተደገፈ የአጸፋ ጽሁፍ ቢልኩልን አክብረን በኤዲቶሪያል ፖሊሲያችን መሠረት ልናትመው እንደምንችል እንገልጻለን።
አርታኢው
ሙሴ says
የሴራ ፖለቲካችሁ፡ መቼም ቢሆን ማለቅያ የለቅም። በትግራይ ሕዝብ ላይ ያላችሁ ጥላቻ ዓይኑ ያፈጠጠ ነው።
ምን ዋጋ ኣለው። እንዲህ እንዲህ እያላችሁ ኣገሪቱ ሙሉ በሙሉ ፈረሰች።
Tesfa says
በትግራይ ህዝብ ላይ ማንም ጥላቻ የለውም። በወያኔ ግፍና መከራ የተጠበሰው የሃገራችን ህዝብ ግን ከወያኔዎች መስማትም ሆና እነርሱን ማየት ቋቅ ብሎታል። ዛሬ ላለው መተላለቅና ግፍ መንስኤው የወያኔ ባርነት ትግራይ የክልል ፓለቲካ ፓሊሲ ነው። የትግራይ ህዝብ ክቡር ነው። እንዳንተ ያሉ ወስላቶች እየነገድበት እንሆ 50 ዓመት ሙሉ በጨለማ ውስጥ አለ። ዝም በለህ የፈጠራ ወሬ እያናፈሱ ህዝብን ከማጨራረስ ህዝባችን እርስ በራሱ መናቆሩን ትቶ በሰላም እንዲኖር የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። በቅርቡ በወዲ ወረደና ለፍልፎ በማይደክመው በጌታቸው ረዳ የተሰጡ መግለጫዎችን ረጋ ብሎ ላዳመጠ የእብደት እንጂ የጤና እንዳልሆነ መገንዘብ ይችላል። እስከ መቼ ነው የምንገዳደለው? ማን ተረትቶ ማን ትጥቅ ይፈታል? ሱዳን በውስጥ ፓለቲካ እየነደደች ነው። በዚህ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ውዝግብ ላይ ነች። ደቡብ ሱዳን ከካርቱም መንግስት ከተፋታች ወዲህ ያተረፈችው ምንድን ነው? እንዳውም በቅርቡ የወጣ የተመድ ዘገባ በደቡብ ሱዳን ሰዎች በረሃብ እየሞቱ ነው ይላል። የነጻነትና የመገንጠል ቱሩፋቱ የቱ ላይ ነው? አንድን አፋኝ መንግስት አባሮ ሌላ አፋኝና ገዳይ መንግስት በቦታው ለእድሜ ልክ ማስቀመጥ ከሆነ እንዲህም ብሎ ነጻነት የለም።
በሴራ ፓለቲካው የተካነው የራሱን የትግራይን ልጆችን እንደ ቄራ ከብት የሚቆራርጠው ወያኔ ነው። ዛሬ በአማራው ላይ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ነን በሚሉ ስንኩላን የሚፈጸመው ግፍ ከዚሁ ከመቀሌ የተሽረበ ሴራ ነው። ሰው ግን እንዴት አብሮ መኖርን ረሳ? እንዴትስ ይህ የእኔ ክልል ያ ያንተ አጥር መባባል ጀመረ? ምድሪቱ ሰፊ ናት። ለሁላችንም ትበቃለች። የኦሮሚያ ክልል፤ የአማራ ክልል፤ የደቡብ ገለ መሌ እያልን ለፓለቲካ ፍጆታ ምድሪቱን ቆራርጠን አሁን ልትፈርስ ነው አትፈርስም ማለቱ ቧልት ነው። አሁን ባለን አካሄድ ፍርክርኳ እንደሚወጣ ለመገመት ጠንቋይ መጠየቅ አያስፈልግም። ትላንት ጠንካራ የነበሩት ሃገሮች ዛሬ የሮም አወዳደቅን ወድቀው እንሆ በዓለም ዙሪያ እናያለን። ሰውን በመግደል፤ በማፈን፤ በማስፈራራት ምንም አይነት ሰላም አይመጣም። ቆም ብለን ለሃገሪቱ ሰላም የራሴ ድርሻ ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ አዋቂነት ነው። በሶሻል ሚዲያ ላይ የሚለጠፉ ሃገር ነክም ሆነ ክልል እያጣቀሱ የሚለጠፉ የፓለቲካም ሆነ ሌሎች ወሬዎች ሁሉ አሻሮዎችና የፈጠራ ወሬዎች ናቸው። ሰው ደሙን ለማፍላት ፈልጎ ካልሆነ በሶሻል ሚዲያ ቀኑን ሁሉ መጣድ ለአሁንም ለወደፊትም የአዕምሮ በሽታ ለመሸመት ብቻ ነው። ስለሆንም ልጅ ሙሴ የሴራ ፓለቲካ አናፈሳችሁ የትግራይን ህዝብ አጥላላችሁ ከማለት ራስህን ጠይቀህ በጎነት የተላበሰ ተግባር ፈጽም። የትግራይህ ህዝብ ያ ወደደው ይህ አጥላላው ማንነቱን የሚቀይረው የለም። ሃገርና ወገኑን፤ ሃይማኖቱን አክባሪ ህዝብ ነው። ዛሬም ትላንትም በጠበንጃ አፈሙዝ እኛን ምሰሉ እያሉት እንሆ አንድ ለአምስት በተባለ የወያኔ የፓለቲካ ገመድ ተተብትቦ ይገኛል። ያን ነው ለመቁረጥ መታገል። ሌላው ሁሉ የፓለቲካ አተካራ ለከብቶች የተጣለ የአተላ ክምር ነው። እንርሳው!
2ኛ አርታኢ says
ጎላጉል – አመም ያደርጋችኋል – አሁን ይሄ መረጃና ማስረጀና ብምንጭ ስም የሚደርግ አሉባልታ ምን ይባላል? – ለመሆኑ ሰውዬው እንዲህ ሲሉ በምን አረጋግጠው ይሆን?
“ደርግን ይጠሉና ይቃወሙ የነበሩ ኢህአፓዎች ግን ጸረ ችግኝ ነበሩ። ደርግን የጎዱ ይመስል በወዶ ፈቃደኝነት ለችግኝ ተከላ ሲዘምቱ ወይ ቀድሞ የተተከሉትን ወይም ራሳቸው የሚተክሉትን ችግኞች እየገለበጡ ይተክሉና በአገር ላይ ኪራሣ ያስከትሉ ነበር ብለው ኃላፊው ነግረውናል። ችግን ተከላን መቃወም ጤና ቢስነት ነው”
Editor says
First – please learn how to write better in Amharic. Then come and comment here.
Editor