የሰባተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ተከትሎ፣ የቀድሞው የአብን ተመራጭና የአሁኑ የኢህአፓ/ትብብር እጩ ተወዳዳሪ የነበሩት ዶ/ር አበባው ደሳለው በሰጡት ቃለ መጠይቅ በምርጫው ማሸነፍ ባለመቻላቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ብስጭትና ንዴት ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ተወዳድረው ከትብብሩ እና ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሕዝብ የተመረጡትንም በብልጽግና ችሮታና ድጋፍ የተመረጡ፣ በምርጫ ሳይሆን በቅርጫ ያሸነፉ በማለት ወርፈዋል። ወደ ፓርላማ አለመግባት ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነም ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ኢንሳይደር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የተከበሩ አቶ አበባው ብሔር ተኮር ከሆነው አብን ወጥተው ወደ ኢህአፓ የገቡበትን ምክንያት አስረድተዋል። “ኢህፓን የመረጥኩበት ምክንያት ደግሞ እንደሚታወቀው ጠንካራ ታጋዮች የወጡበት ፓርቲ ነው። ለተራ ጥቅም ብለው ለተራ ኢኮኖሚ ጉዳይ ብለው ህሊናቸውን የማይሸጡ ለመስዋዕትነት ዝግጁ የሆኑ አባላት የነበሩበት ፓርቲ ስለሆነ ነው” ብለዋል። በዚህ አነጋገራቸው በአሁኑ ጊዜ በአብን የሚገኙትን የቀድሞ ጓዶቻቸውን ለጥቅም የተገዙና ህሊናቸውን የሸጡ ናቸው በማለት እንዳሸሞሩባቸው ለመረዳት ይቻላል።
ስለ ምርጫው በተለይም ትብብሩ ውጤቱን አልቀበልም ማለቱን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲናገሩ “የአማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ ሊቀመንበሩ የተለያየ መግለጫ ሲያወጣ ነበር፤ ይሄም የፓርቲ ኃላፊዎች ጋር ሳይነጋገር በራሱ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ነበሩ”። ካሉ በኋላ በትብብር ውስጥ ስለሚነገረው ክፍፍል ለተጠየቁት ሲመልሱ “ምናልባት ክፍፍል ያልከው ከዚህ አኳያ ነው እንጂ ሌሎች ሶስቱ ፓርቲዎች አሁንም በጥሩ ጥንካሬ በጥሩ ውህደት እየሠሩ ይገኛሉ” ብለዋል። ሆኖም ግን ምርጫ ቦርድ ለትብብሩ ዕውቅና የሰጠው ለምርጫ ብቻ እንደሆነ እና ምርጫው ሲጠናቀቅ ትብብሩ እንደሚፈርስና ሁሉም ወደየግል ፓርቲያቸው እንደሚመለሱ የታወቀ ነው። በመሆኑም ትብብሩ የሕይወት ዘመኑ የተጠናቀቀና ከዚህ በኋላ ፓርቲዎቹ ውህደት እስካልፈጸሙ በስተቀር የማይቀጥል ስብስብ ነው።
ከዚህ ሌላ ጎልጉል በተደጋጋሚ በሠራቸው ዘገባዎች በግልጽ ለማሳየት እንደሞከረው፤ ሚያዚያ 24 ቀን ማለትም ከምርጫው አንድ ወር በፊት የትብብሩ አመራሮች ተሰብስበው ወደ ምርጫ እንግባ ብለው በአብላጫ ድምፅ እንደወሰኑ ተገልጾዋል። ከዚህ ውሳኔ በኋ ከምርጫው መውጣት ብዙ ቅጣቶች የሚያስከትልና የተሰጣቸውንም ሁለት ሚሊዮን ብር መመለስ እንዳለባቸው፤ በቀጣይም እንደ ፓርቲ ኅልውናቸውን እንደሚያጡ የታወቀ እውነት ነው። ይህንንም የተከበሩ አቶ አበባው በቃለ ምልልሳቸው ሲናገሩ “ለፓርቲው ህልውናም ሲባል” ምርጫ ውድድር ውስጥ እንደሚገባ ከገለጹ በኋላ “አንድ ፓርቲ ሲቋቋም ዋና አላማው በምርጫ መሳተፍ እና ስልጣን መያዝ ነው፤ በምርጫ የማይሳተፍ ከሆነ የመሰረዝ ዕድል አለው፤ ከዚያ አኳያ ዋና ተግባሩን ካልፈጸመ ፓርቲ ፓርቲ አይባልም” ብለዋል። በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበው አንዱም ጥያቄያቸው ሳይመለስ ወደ ምርጫ ከገቡበት በርከት ያሉ ምክንያቶች አንዱ ይህ መሆኑ ነው።
ከዚህ በፊት ጎልጉል በሠራው ዘገባ ላይ የኢህአፓ ሊቀ መንበር የሆኑት መጋቤ ብሉይ አብርሃም ሲናገሩ በሚያዚያ 24 ወደ ምርጫ እንዲገባ በአብላጫው ከተወሰነ በኋላ ጉዳዩን የትብብሩ አባል ላልሆኑት ግን በዓላማው የሚያምኑትን የቀድሞ የአብን አባል ክርስቲን ታደለን እስር ቤት ድረስ ሄደው ማነጋገራቸውን ጠቅሰዋል። አቶ ክርስቲያንም የፓርቲውን ሕልውና ለመጠበቅ ወደ ምርጫ መግባቱ የተሸለ እንደሆነና ለፓርቲው ውሳኔ መገዛት እንዳለባቸው ምክር እንደሰጧቸው አቶ አብርሃም ተናግረዋል።
በሽሮ ሜዳና በአፍንጮ በር አካባቢ የምርጫ ጥሰቶችን ተመልክቼ ነበር ያሉት የተከበሩ የተሰናባቹ ፓርላማ አባል አቶ አበባው፤ ይህንን የምርጫውን ውጤት ሊያደናቅፍ ወይም ሊቀይር የሚችል ክስተት ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ እንዳላቀረቡ አልካዱም። ይልቁንም ስህተቱን ሲፈጽም የነበረውን ወጣት “ለፖሊስ ተናግረን ለጊዜው ዞር እንዲል ተደርጎ ነበር” ብለዋል። ሆኖም “ስፔሻል ኬዞች” ያሏቸውን ለምርጫ ቦርድ አቅርበው ቦርዱ እንዳልተቀበለው ተናግረዋል።
በምርጫ ክርክር ወቅት ኢትዮጵያ ሱዳንን አለአግባብ ወርራለች፤ ተገቢ አይደለም በማለት፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጦር በኤርትራ ድንበር ነው ያለው፤ ኤርትራን ሊያጠቃ ነው በማለት ለኤርትራ ሲከራከሩ የነበሩት የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት የተከበሩ አቶ አበባው “የተማሪው ኅብረተሰብ ክፍል በብዛት ካርድ እንዳላወጣ ነው ያለን መረጃ እና በጥቅማ ጥቅም እና በሴፍቲ ኔት የተደራጁ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ናቸው ካርድ በብዛት እንዲያወጣ መንግሥት ሠራተኛው ያው ተገድዶ ካርድ እንዳወጣ ግልጽ ነው ቤት ለቤት ቁጥራችሁን ንገሩኝ ተብለው ሁሉ የተመዘገቡበት ሁኔታ እንደነበረ መረጃው ማስረጃውም አለ። የተለያዩ ዜጎች እንደተናገሩት ምርጫው በጣም ሙሉ በሙሉ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ አልነበረም፤ እንዲያውም ቅርጫ ነበር” ብለዋል። ከምርጫ ቦርድ የተሰጠው መረጃ እንደሚጠቁመው 50 ሚሊዮን ሕዝብ ለመምረጥ ተመዝግቦ ከ40 ሚሊዮን በላይ እንደመረጠ ነው። ከዚህ ሌላ ሕዝቡ ማንም ሳያስገድደው እስከ እኩለ ሌሊትና ከዚያ ባለፈ ሰዓት ሁሉ ሲመርጥ የነበረው ለሴፍቲኔት ብሎ ወይም ጠብመንጃ ተደግኖበት በግድ አይደለም።
“በዚህ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አሸንፋለሁ የሚል ግምት ነበረዎት?” ተብለው ለተጠየቁት ክቡር አቶ አበባው ሲመልሱ “አዎ፤ አሸንፋለሁ ባልል ኖሮ አልወደደርም ነበር፤ እራሴን ከምርጫው አገልል ነበረ። ሙሉ እምነት ነበረኝ እንደማሸነፍ” በማለት በምርጫውና በሒደቱ በማመን በርግጠኝነት ወደ ምርቻ እንደገቡ ተናግረዋል። በመቀጠልም “ታዲያ ለምን ሳይሳካልዎት ቀረ?” ለሚለው ቀጣይ ጥያቄ ፋኖን፣ ሕዝቡን፣ ነጋዴዎችን ሰበብ አድርገዋል።
የተሳተፉበት ምርጫ ምንም ጠንካራ ጎኖች የሉትም ያሉት አቶ አበባው ፋኖ አትምረጡ፣ አትመረጡ፤ ይህንን ከተላለፋችሁ እገድላችኋለሁ ብሎ ያወጣው መግለጫ እንዳይመረጡ ምክንያት እንደሆናቸው በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ጽፈው ነበር። ከፋኖ ሌላ ነጋዴዎችም ሆኑ ህዝቡ እንዳልደገፋቸው አልካዱም። ሁኔታውን ሰፋ አድርገው ተንትነዋል፤
“በፋኖ መግለጫ ምክንያት ለምሳሌ ነጋዴዎች፣ ባለሃብቶች፣ ፓርቲዎችን ለመደገፍ ዝግጁ አልነበረም እኛን ለመደገፍ ዝግጁ አልነበረም። ደግሞ እንደሚታወቀው ምርጫ ፋይናንስ ነው ምርጫ ቦርድ የሚለቅቀው ገንዘብ በጣም ደካማ ነው በቂ አይደለም የግድ ባለሃብቶች ሊደግፉት ይገባል፤ ሌላው ደግሞ ምንድነው የፋኖ እንደዚህ አይነት መግለጫ ማውጣቱ ዲያስፖራው ሚዲያው ባጠቃላይ የምርጫው አስፈላጊ እንዳልሆነ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን ማግለል እንዳለባቸው በሰፊው ሠርተዋል። በዚያ ምክንያት እውነተኛ መራጮች ካርድ አላወጡም። እውነተኛ መራጮች፤ የኛን ሐሳብ የሚደግፉ መራጮች ካርድ አላወጡም። በዚያ ምክንያት ሊመርጡን አልቻሉም። … ሽማግሌዎችን አሮጊቶችን በሴፍቲ ኔት የተደራጁትን ወጣቶችም ሆነው ከመንግስት ጋር የጥቅም ትስስር ያላቸው ሰዎች ብቻ ካርድ እንዲያወጡ አደረጉ፤ ብዛት ሲመረጥም እነዚህን ጠርንፎ አሰልፈው እንዲመጡ አደረጓቸው፤ ይሄንን ሪፖርት አድርገናል፤ ይሄ ፋክት ነው በዚህ ላይ የሚከራከረኝ ካለ ዝግጁ ነኝ ምንም ይሄ የሚካድ ነገር አይደለም” ያሉ ሲሆን ይህንን ማስረጃ አለኝ ያሉበትን ጉዳይ ምርጫ ቦርድ ለምን እንዳልተቀበለው አልተናገሩም።
“ታዲያ እርስዎ ቢያሸንፉ ኖሮ ምርጫው ፍትሐዊ አይደለም ገለልተኛ አይደለም ወይም ደግሞ ነጻና ፍትሐዊ አይደለም ካሉ ምርጫውን ውጤቱን ትቀበሉት ነበር ማለት ነው?” በሚል ለቀረበላቸው ቀጥተኛ ጥያቄ ይህንን ብለዋል። “እኔ በግሌ ባሸንፍ ኑሮ፤ አይ ማለት እኔ አሸነፊያለሁ ስለዚህ ይሰረዝን ልል አልችልም፤ ግልጽ ነው፤ ነገር ግን ምርጫው ነጻ እና ፍትሐዊ አለመሆኑን ከመናገር ወደኋላ አልልም” በማለት “ቅርጫ ነው፤ ኮታ ነው፤ ችሮታ ነው” ባሉት ምርጫ ቢያሸንፉ ኖሮ ወደለመዱት ፓርላማ በቀጣይ አምስት ዓመታት ገብተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የተከበሩ አቶ አበባው የሰጡትን ቃለ ምልልስ ያዳመጡ አስተያየት ሰጪዎች እዚያው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዩትዩብ ገጽ ላይ የተለያየ አስተያየት ሰጥተዋል። Amir Reshid የተባሉ አስተያየት ሰጪ፤ “ዶ/ር አበባው ኢትዮጵያ የአረብ ኤሚሬት ተላላኪ በመሆን ሱዳንን እየተነኮሰች ናት ያሉ ቀን ነው የተሸነፉት። ሀገሬው ሀገሩን ሲያዋርዱበት አይወድም” ብለዋል። henocksY የተባሉ ደግሞ “ልክ ነው ለኢትዮጵያ እና ለብሔራዊ ጥቅሟ እንደመከራከር ለኤርትራ ዋስ ጠበቃ ሆነው የተከራከሩ ቀን ነው የተሸነፉት… የዛን ቀን ነው ሕዝብ እንደማይመርጦት እርግጠኛ የሆነው” በማለት የኤርትራ ተላላኪ በመሆናቸው ሕዝቡ እንደተቀየማቸው ተናግረዋል። ሌላ Tofik Adem የተባሉ ደግሞ፤ “እርስዎ እኮ በክርክር ሰዓት ይወዳደሩ የሚመስሉት ለሱዳንና ለኤርትራ ነበር፤ ኢትዮጵያ ሱዳንን ወራለች ኤርትራንም ልትወር ነው… ሲሉ ነበር…” በማለት ያልተመረጡበትን ምክንያት እርሳቸው የተናገሩት እንዳልሆነ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
በቃለ መጠይቁ ላይ “በሴፍቲ ኔት የተደራጁ፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው ካርድ ያወጡት” በማለት የተከበሩ አቶ አበባው ለተናገሩት አስተያየት የሰጡ ደግሞ ይህንን ብለዋል። “በንግግርህ ንቀት አለብህ” ያሉ አስተያየተ ሰጪ “… አሮጊቶች ሴቶች ሴፍቲ ኔት የሚሠሩ ድሀዎች ሽማግሌዎች ወጣቶች የኢትዮጵያ ህዝቦች አይደሉም? ላንተ መምረጥ መብት ያላቸው እና ሕጋዊ መራጮች ሀብታሞች ብቻ ናቸው?” በማለት በራሳቸው ንግግር ሞግተዋቸዋል። “እውነተኛ መራጮች ካርድ አላወጡም ማለት ራሱ ሕዝብ መናቅ ነው። ሃምሳ አራት ሚሊዮን ሕዝብን እውነተኛ መራጭ አይደለም ማለት ምን ማለት ነው?” ሲሉ ሌላኛው ጠይቀዋል። Hibbaba የተባሉ ደግሞ “ኧረ ሀዝቡን አትናቁ!! እኔ አልተገደድኩም” በማለት በነጻነት ድምፃቸውን እንደሰጡ ተናግረዋል።
“በቀጣይ እንግዲህ መንግሥት የፓርላማ ዘመን ሲያልቅ የስራ ምደባ አለ” ያሉት የተከበሩ አቶ አበባው በፓርላማ አባልነታቸው የሚያገኙትን ጥቅም አልሸሸጉም። የፓርላማ አባል ሆነው በመሥራታቸው አሁን ባለመመረጣቸው መንግሥት በአንድ ቦታ ላይ መድቦ በደመወዝ እንደሚሠራቸው፤ ይህም በሕጉ የተቀመጠ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ በኋላ “የተከበሩ” መባል ቢቀርባቸውም አበባው ደሳለው፤ “በምደብበት ቦታ ላይ በቅንነት ሕዝቤን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply