በቅርቡ በሰሜኑ የሀገሪቱ ቀጠና አዲስ የጦርነት ትንኮሳ የጀመረው የትህነግ (ህወሓት) ታጣቂ ቡድን፤ በሰሜን ወሎ እና በራያ ግንባሮች በደረሰበት አይቀጡ ቅጣት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ አስተናግዶ ንብረቱን፣ ሙትና ቁስለኛውን እያዝረከረከ ወደ ትግራይ መሸሹን ለጎልጉል የደረሰው መረጃ አመለከተ።
ጎልጉል ያነጋገራቸው በሰቆጣና በአላማጣ አካባቢ የሚገኙ የዓይን እማኞች እንዳረጋገጡት፤ ሰሞኑን ትህነግ (ወያኔ) እና አጋሮቿ ያስረከቡትና በመከላከያ ሠራዊቱ የተማረከው የጦር መሣሪያና የተተኳሽ ብዛት እጅግ ከፍተኛና ለማመን የሚከብድ ነው።
ቡድኑ በግብፅ አስተባባሪነትና በሻዕቢያ ጋሻ አጃግሬነት የፈለፈላቸውን አጋሮቹን ተማምኖ፤ “በመስቀል ሰቆጣ ላይ ችቦ አበራለሁ” በሚል እብሪት ለአንድ ሳምንት ቀንና ማታ ሲዋጋ እንደነበር ምንጮች ለጎልጉል ጠቁመዋል።
ሆኖም ግን የቡድኑ የተሳሳተ ግምገማ ከእውነታው ጋር የተጋጨ ሲሆን፤ በሰሜን ወሎ ተራሮች፣ በወለህ ሰንሰለታማ ተራራማ ቦታዎች እና በአቡነ ዮሴፍ ከፍተኛ መሬቶች ላይ ሲለማመድ በነበረው 13ኛ ዕዝ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ራሱ “ሻማ ሆኖ መቅለጡን” እማኞች ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ጠላት ሙትና ቁስለኛውን ጥሎ የኋልዮሽ በመሸሽ ላይ ሲሆን፤ የዋግ ሕዝብ ደግሞ የአስክሬን መቅበር ሰብአዊ ግዴታውን እየተወጣ እንደሚገኝ ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ያረጋግጣል።












በተለይም በራያ ግንባር — ዋጃ፣ ጥሙጋ፣ አላማጣ አየር ኃይልና ቤተ ማሪያም በተባሉ ቦታዎች የመከላከያ ሠራዊቱ በሰነዘረው ፀረ-ማጥቃት ግንባሩን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ላይ ይገኛል።
ከመስከረም 17 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ/ም በራያ አላማጣ ወረዳ ልዩ ስሙ አሞራ ቀጠያ፣ አዛዥ አምባ እና ጀመዶ ማሪያም በተባሉ አካባቢዎች በተደረገ ውጊያ ከትህነግ ታጣቂዎች የተማረኩት መሣሪያዎች ዝርዝር ለጎልጉል የደረሰው መረጃ እንደሚከተለው ያሳያል፦
ከባድ መሣሪያዎችና ተሽከርካሪዎች፦ 2 የ122mm መድፎች፣ 3 ባለ 107 ሮኬቶች፣ 7 ፓትሮል፣ 2 ኦራል እና 2 አምቡላንስ ተሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም 1 ዶዘር።
የቴክኖሎጂና የመገናኛ መሣሪያዎች፦ 18 ባለ 15 ኢንች አጥፊ ድሮኖች፣ 8 የድሮን ባትሪዎች፣ 4 ጄኔሬተሮች እና 1 የሬድዮ አንቴና።
ቀላልና መካከለኛ መሣሪያዎች፦ 7 መትረየሶች፣ 2 ዲሽቃዎች፣ 8 ባለ 81mm የድሮን ሞርታር ቅንቡላዎች፣ 1 ላውንቸር እና 4 የSPC የጦር መሣሪያዎች።
በርካታ ተተኳሾች፦ 4,250 የዲሽቃ ጥይቶች፣ 39 የመድፍ ጥይቶች፣ 19 የፀረ-ታንክ ጥይቶች፣ 82 የRPG ጥይቶች፣ 78 የ82mm ሞርታር ቅንቡላዎች እና 78 የRPG ቁንቡላዎች።
ጎልጉል ያነጋገራቸው እማኞች፤ በትህነግ መሪዎች የተሳሳተ ወታደራዊ ግምገማ ምክንያት አሁንም ዋጋው እየተከፈለ ያለው በወጣቶች ሕይወትና በዕንባ መሆኑን በከባድ ሐዘን ገልጸዋል። በግድ ልጆቻቸው ተገደው ወደ ጦርነት የተማገዱባቸው እናቶች “ልጄ የት አለ?” ብለው ለሚያቀርቡት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ያለባቸው እነዚህ መሪዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
“ወቅት ሲከዳህ አይጣል ነው። ሰላምን የመረጠ ተሸነፈ አይባልም” ያሉት እማኞቹ፤ በየሰፈሩ ያሉ የቡድኑ አጋሮች አሁንም ቢሆን የሕዝቡን እረፍት አስበው ራሳቸውን ከማታለል ወጥተው ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply