የካቢኔ ተሿሚዎቻቸውን ለፓርላማ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ስለ ተሿሚዎቹ ከፓርላማ አባላት አስተያየት ተሰጥቷቸው ነበር። አንዲት የፓርላማ አባል ሴቶች ላይ መሠራት እንዳለበት በመጥቀስ ባሁኑ የተደረገው ሹመት ቢያንስ 30 በመቶ ቢደርስ ጥሩ ነበር፤ የበለጠ መሥራት አለብን ሲሉ ተደምጠዋል።
የተከበሩ የፓርላማ አባሏ የዘነጉት የሒሳብ ስሌት አለ። ባሁኑ ከተሾሙት 23 ሚኒስትሮች ዘጠኙ ሴቶች ናቸው። ግማሽ ለመሆን ሁለት ወይም ሦስት የቀረው ነው። በሌላ አነጋገር ወደ 40 በመቶው ሴቶች ናቸው። የሴቶች ውክልና ከ30% በደንብ ያለፈ ነው።
አስተያየቱ ያልጣማመቸው ዐቢይ ለዚህ ሲመልሱ ይህንን አሉ፤ “በዚህ ጉዳይ እኛ ለዓለም ምሳሌ ስለሆንን ሌሎች ሀገራት ከኛ መማር አለባቸው ብዬ ነው የማስበው። ከ23 ሚኒስትሮች ዘጠኝ ሴት ሚኒስትር ያደረገ አንድ ሀገር መጥራት አትችሉም፤ አንድ ሀገር። አደግሁ፣ ሰለጠንሁ የሚልም ቢሆን ማለት ነው። ስለ ሴቶች መብት ከኛ በላይ የሚያወራውም ቢሆን ሁለት ወይም ሦስት ሴት ብታገኙ ነው። በዚህ ረገድ ጥሩ ሥራ ተሠርቷል። ነገርግን ሴት ስለተኮነ ብቻ አንሾምም። የምንኮራበት ነው። ይህንን በየትኛውም የአፍሪካ ሀገር ማግኘት አትችሉም”።
በዓለም ላይ ኒካራጓ፣ ፊንላንድ፣ አይስላንድ፣ ሌክተንስታይን፣ ከስድሳ በመቶ በላይ ሴቶች የካቢኔ አባል ያሉባቸው ሀገራት ናቸው። ወደ አፍሪካም መለስ ስንል ደግሞ እንደ ሩዋንዳ ያሉ ሀገራትን መጥቀስ ይቻላል።
የጠቅላዩን ንግግር ከዐውዱ አንጻር እንመልከተው። ኢትዮጵያ ሴቶችን ለካቢኔ በማብቃት ፈር ቀዳጅ የሆነችባቸው ነጥቦች አሉ። ጥቂት ምሳሌዎችን እንጥቀስ።
በቀድሞው ዘመናት የሴቶች የካቢኔ ተዋጽዖ ከ15 በመቶ አልፎ አያውቅም ነበር፤ ብዙዎቹ ሀገራትም ወደ 50 በመቶ የደረሱት በአዝጋሚ ለውጥ ነው። ኢትዮጵያ ግን ባንዴ ነው ይህንን አስደናቂ እመርታ ያደረገችው። በዚህ ዓለም ሊደነቅ ይገባዋል።
ሌላው በካቢኔ ውስጥ የሴቶች ሥልጣን በአብዛኛው ማኅበራዊ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ነው። ጤና ሚኒስቴር፣ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ወዘተ። ኢትዮጵያ ግን የሰላምና የመከላከያ ሚኒስቴር ቦታዎችን ለሴቶች በመስጠት የድፍረት እርምጃ የወሰደች ሀገር ናት።
ከላይ እንደተጠቀሰው አብዛኛዎቹ ሀገራት በጣም አዝጋሚ በሆነ ለውጥ ነው አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ የደረሱት። ደፍረው ባንድ ጊዜ በግማሽ አልደረሱም። ብዙ ውዝግቦችና ክርክሮች ከተካሄዱ በኋላ ነው እድገቱ የታየው። የኢትዮጵያ በዚህ ፍጥነት ማደግ ከእንግዲህ ወዲህ ሴቶች የማይሾሙበት የካቢኔ ሥልጣን የሌለ መሆኑን ያረጋገጠ ነው። ሌላው ተመልሶ ወደ 15 በመቶ እና ከዚያ በታች እንደማይወርድ ያረጋገጠ ነው።
ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታና የባሕል ተጽዕኖ አኳያ በዚህ ፍጥነት ሴቶችን ማብቃታቸው ሊያስመሰግናቸው የሚገባ ነው። የርሳቸውም ምላሽ በዚህ መልኩ ሊታይ ይገባዋል። ለወደፊት ደግሞ እንዲህ ያለ ምላሽ ሲሰጡ አሁን ከተናገሩበት መንገድ በተለየ ቢያቀርቡት የተሻለ ነው። ፋክት ቼክ እናደርጋለን እያሉ ስሕተትን ብቻ እያጎሉ ለሚያወሩ ጋዜጠኛ ነን ባዮች የወሬ ቀለብ ላለመስጠት። የሚገርመው እነዚህ በጋዜጠኛነት ስም የሚንቀሳቀሱ በትህነግ ዘመን ለምን ፋክት ቼክ ሳያደርጉ ለ30 ዓመት ዝም ብለው እንደኖሩ ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply