* “የጌታቸው አሰፋ ኢትዮጵያ ከዐቢይ አሕመዷ ተሽላለች” በማለቱ አነጋጋሪ ሆኗል
በተቃውሞው ጎራ የተመሠረተው “ትብብር” በአፈጻጸም ድክመት፣ በአመራር ብቃት ማነስ፣ በግል ታይታና በመንደር ሽኩቻ ተተብትቦ ትግሉን እያዳከመና ጦርነቱን እያራዘመ መሆኑን ስደተኛው ይልቃል ጌትነት በብርቱ ተቸ። በተለይ በፋኖ አመራር ውስጥ ያሉት በዚህ ረገድ የሚፈጽሙት ተግባር “የድንቁርና ነው” በማለት አምርሮ ተናግሯል።
ይልቃል ጌትነት ከመዓዛ መሐመድ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ በትብብሩ ውስጥ የተሰባሰቡ አካላት በጥቃቅን ጉዳዮች መጠመዳቸው ትግሉን ውጤት አልባ እያደረገው መሆኑን ገልጿል።
መዓዛ ትብብሩ ምንም ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሳያደርግ በሕዝብ ግንኙነት ብቻ መወሰኑንና ከኦነግ ሠራዊት (ኦላ) ጋር በመጣመሩ በአማራው ማኅበረሰብ ዘንድ የተነሳውን ቁጣ በአግባቡ አለመያዙን በመጥቀስ “ትብብሩ ምን አሳክቷል?” ስትል ጠይቃዋለች።
ይልቃል ለዚህ በሰጠው ምላሽ፣ ትብብሩ በአመራርና በአፈጻጸም ረገድ ሙሉ በሙሉ መድከሙን በግልጽ ተናግሯል። “ከፍተኛ የአፈጻጸም ድክመት አለ። ቴክኒካል፣ ኦፕሬሽናል በሆነ ጉዳይ ውስጥ የሚያደርጉት ነገር ትግሉን እያዳከመና በታሰበው ፍጥነት እንዳይሄድ እያደረገው ነው” ሲል የትብብሩን ውጤታማ አለመሆን አስረድቷል።
የትብብሩ አመራሮች ሀገር ለመምራት እየተንቀሳቀሱ በአካባቢያዊ ንትርክ መጠመዳቸውን የኮነነው ይልቃል፣ “አንድ ጎጥ ያለ የጎጃም እና አንድ መንደር ያለ የጎጃም አመራር መጣላት እኮ የአፈጻጸምን እና ጠንከር አድርጎ እርምጃ ያለመውሰድ ችግር እኮ ነው። በቃ ሀገር እመራለሁ እያልክ እዛ ማዶና እዚሁ ያለ ሰው ካልተስማማህ አንተ መጀመሪያ የምትሰራውንም ነገር አታውቅም” ሲል በትብብሩ ውስጥ ያሉትን በተለይ የጎጃም ፋኖ አመራሮችን በስም ሳይጠቅስ በከፍተኛ ወርፏቸዋል።
በትብብሩ ውስጥ ብቃትና ችሎታ (ሜሪት) መጥፋቱንና በምትኩ የግል ፍላጎት መንገሡንም አሜሪካ በስደት የሚገኘው ይልቃል አልሸሸገም። ለትግሉ መጓተት ዋነኛ ምክንያቶቹ “ኦፕሬሽናል የሆነ የራስ ታይታ፣ የመንደር ጉዳይ፣ የሥልጣን ጥማት፣ ‘እገሌ ይቀየመኛል’” የሚሉ ጉዳዮች ናቸው” ሲል አጋልጧል።
ይህ የአመራር ድክመትና መጓተት ጦርነቱን በማራዘም በንጹሐን ዜጎች ሕይወት ላይ ከባድ ዋጋ እያስከፈለ ነው ያለው ይልቃል፣ በትብብሩ ዙሪያ የሚርመሰመሱ ብቃት የሌላቸው ሰዎች ለሕዝብ እልቂት መባባስ ተጠያቂ መሆናቸውን ገልጿል።
“በዚህ ዙሪያም የተተበተቡ ሰዎች አወቅን ብለው በማያውቁት ነገር የሚያማስሉ ሰዎች ለትግላችን እንቅፋት ሆነው በሚሞቱ ሰዎች ውስጥ ዕዳ እየጨመሩብን ነው” ሲልም ትግሉን እየጎተቱ ያሉ አካላትን በጽኑ አውግዟል።
በሌላ በኩል በዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ ይልቃል ጌትነት አሁን በሀገሪቱ ያለውን ቀውስ ከቀድሞው ሥርዓት ጋር በማነጻጸር፣ “የጌታቸው አሰፋ ኢትዮጵያ ከዐቢይ አሕመዷ ተሽላለች” ሲል የሰጠው አስተያየት አነጋጋሪ ሆኗል።
ጌታቸው አሰፋ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ በነበረበት ወቅት፣ ኢትዮጵያውያን በጨለማ እስር ቤቶች እየታጎሩ፣ ጥፍራቸው እየተነቀለ፣ በብልታቸው ላይ የውኃ ኮዳ እየተንጠለጠለና ዘግናኝ ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው መኖራቸው በይፋ የተጋለጠና የቅርብ ጊዜ መራራ ትዝታ ሆኖ ሳለ፣ ያንን የጭካኔ ዘመን ከአሁኑ ጋር አነጻጽሮ የተሻለ ነው ማለቱ በብዙዎች ዘንድ ትዝብትን አጭሯል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply