* ውሳኔው የኢትዮጵያን የወደብ ፖለቲካ ስትራቴጂካዊ ኃይል ሰጥቶታል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ እሑድ ጥቅምት 8 ቀን 2019 ዓ.ም. ባቀረቡት አዲስ ብሔራዊ የደኅንነት ዶክትሪን መግለጫ ላይ፥ ሶማሊላንድን ከቀሪዋ ሶማሊያ ነጥሎ ሉዓላዊት ሀገር አድርጎ የሚያሳይ አዲስ ጂኦ-ፖለቲካዊ ካርታ ይፋ አድርገዋል። ይህ እርምጃ ቀጣናዊ የኃይል ሚዛኑን በእጅጉ የሚቀይር ሲሆን፥ በተለይም ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ በኩል የባሕር በር ለማግኘት ለምታደርገው ብሔራዊ ጥረት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊና ስትራቴጂካዊ ግፊት እንደሚፈጥር ተነግሯል።
በእስራኤል መንግሥት የፕሬስ ቢሮ አርማ በታተመውና “በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ጂኦ-ፖለቲካዊ ጥምረቶች” በሚለው ካርታ ላይ ሶማሊላንድ ለእስራኤልና ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (UAE) ስትራቴጂካዊ ምሕዋር “ወዳጅ” ተብላ በልዩ ቀለም ተለይታለች። ይህ አሰላለፍ እስራኤል እ.ኤ.አ. በ2025 መገባደጃ ላይ ሶማሊላንድን እንደ ገለልተኛና ሉዓላዊት ሀገር በይፋ እውቅና የሰጠችበትን ታሪካዊ ውሳኔ በድጋሚ ያረጋገጠ ነው።
ኔታንያሁ ሶማሊላንድን እንደ ሉዓላዊ ሀገር መቁጠራቸው በበርበራ ወደብ በኩል በቀይ ባሕርና በኤደን ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የሚስተዋሉትን የደኅንነት ሥጋቶች ለመቆጣጠር ታስቦ የተደረገ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
ይህ የእስራኤል ይፋዊ አቋም ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን ከሶማሊላንድ ጋር ካደረገችው የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው። በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በጅቡቲ ላይ ያለውን ፍጹም ጥገኝነት ለመቀነስና ብሔራዊ ደኅንነቱን ለማስከበር በሶማሊላንድ በኩል የባሕር በር ማግኘት የህልውና ጉዳይ ካደረገው ሰነባብቷል። ይህ የኔታኒያሁ ውሳኔ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የወደብ ጥያቄ በር ከፋች ከመሆን ባለፈ ኢትዮጵያ በሰላጤው ላይ ሊኖራት የሚችለውን የጎላ ሚና ያሳየ ሆኗል።

እስራኤል ለሶማሊላንድ በሰጠችው የሉዓላዊነት እውቅና ጀርባ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (UAE) ቁልፍ ሚና የነበራት ሲሆን፥ ኤምሬትስ በበርበራ ወደብ ላይ እያደረገችው ያለው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎት የሚያግዝ ነው። የእስራኤልና የኤምሬትስ ጥምረት በሶማሊላንድ ላይ መጽናቱ፥ ቱርክና ግብፅ በሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት በኩል ቀጠናውን ለመቆጣጠር ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትልቅ ምላሽ እንደሆነም ተመልክቷል።
ኢትዮጵያና እስራኤል ለዘመናት የዘለቀ ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከሚስተዋለው ጽንፈኝነትና የቱርክ ወታደራዊ መስፋፋት አንጻር ሁለቱ ሀገራት ጥቅማቸው ይበልጥ ተሳስሯል። ኢትዮጵያ የውስጥ የጸጥታ ፈተናዎች ባሉባት በዚህ ወቅት፥ የወደብ ፍላጎቷን ለማስከበርና የቴክኖሎጂ አቅሟን ለማሳደግ እስራኤልን እንደ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ አጋር ትመለከታለች።
ይህ በኔታንያሁ ይፋ የተደረገው አዲሱ የካርታ አሰላለፍ፥ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር ካደረጉት የሁለትዮሽ የስልክ ውይይትና የቅርብ ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ማጠናከሪያ እርምጃዎች ጋር የተያያዘ እንደሆነ የዲፕሎማሲ ምንጮች ይጠቁማሉ። ካርታው አዲስ አበባን፣ ኢየሩሳሌምንና አቡዳቢን በአንድ የስትራቴጂክ ወዳጅነት ምሕዋር ውስጥ ማካተቱ፥ በመጪዎቹ ዓመታት በአፍሪካ ቀንድ የሚኖረውን የኃይል አሰላለፍ በግልጽ የሚያመላክት ሆኗል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply