በኦሬገን ግዛት ጠቅላይ ግዛት የዋሺንግተን አውራጃ ኮሚሽነር ሆና ለመመረጥ የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ የምትገኘው ትውልደ ሶማሊያዊቷ ናፊሳ ፋይ፣ በሚኒሶታ ግዛት ውስጥ ባደረገችው የቅስቀሳ መድረክ ላይ በተዘቀዘቀ የአሜሪካ ሠንደቅ ፊት ሙሉ ንግግሯን በሶማሊኛ ቋንቋ ብቻ በማድረጓ በአሜሪካ ከፍተኛ ቁጣንና ውዝግብን ቀስቅሳለች።
ይህ ድርጊት በአሁኑ ወቅት የዜግነት ስረዛ ምርመራ እየተካሄደባት ከምትገኘው ሌላኛዋ ትውልደ ሶማሊያዊ የኮንግረስ አባል ኢልሃን ዑመር ጋር በተመሳሳይ መልኩ፣ በአሜሪካ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሶማሊያ ተወላጆች ለሀገሪቱ ያላቸውን ታማኝነት እና ክብር ጥያቄ ውስጥ የጣለ አዲስ የውይይት አጀንዳ ሆኗል።
በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በኤክስ (X) እና በዋና ዋና የሚዲያ አውታሮች ላይ በስፋት የተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው፣ ናፊሳ ፋይ ከጀርባዋ የአሜሪካ ባንዲራ ተዘቅዝቆ በተሰቀለበት መድረክ ላይ ለተሰበሰቡት የሶማሊያ ማህበረሰብ አባላት ሙሉ በሙሉ በገዛ ቋንቋቸው ስትቀሰቅስ ታይታለች።
የአሜሪካ የሠንደቅ ዓላማ ሕግ እንደሚደነግገው፣ ሠንደቅን ዘቅዝቆ መስቀል እጅግ አስቸኳይና ለሕይወት የሚያሰጋ አደጋ (Distress Signal) ሲኖር ብቻ የሚደረግ ቢሆንም፣ በፖለቲካ መድረክ ላይ እንዲህ መደረጉ የሀገሪቱን ብሔራዊ ክብርና ሉዓላዊነት ያዋረደ፣ እንዲሁም ለሀገሪቱ ነጻነት ሲሉ ሕይወታቸውን ለሰጡት አሜሪካውያን ወታደሮች ታላቅ የውርደት መግለጫ ተደርጎ ተወስዷል።
ይሁን እንጂ፣ በአሜሪካ የሚገኙ የፖለቲካ ተንታኞችና ሚዲያ እንደገለጹት፣ ይህ ድርጊት በአጋጣሚ የተፈጠረ ስህተት ላይሆን ይችላል። በርካታ አሜሪካውያን ወታደሮች በሶማሊያ ምድር ሕይወታቸውን የገበሩ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ የሶማሊያ ተወላጆች አሜሪካ ሀገራቸውን እንዳጠፋችባት አድርገው ያስባሉ። በዚህም ምክንያት አንዳንዶች በስደት መጥተው የአሜሪካን ዜግነትና ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ካገኙ በኋላም፣ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሠንደቁን በመዘቅዘቅና አሜሪካን በማዋረድ የውስጥ በቀላቸውን ለመወጣት እንደሚሞክሩ ታዛቢዎች በምሬት ይናገራሉ።
ሌላው ከፍተኛ ትችት ያስከተለው ጉዳይ፣ በአሜሪካ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የእንግሊዘኛ ቋንቋን ወደ ጎን በመተው በሌላ ቋንቋ ብቻ መገልገሏ ነው። የአንድ ሀገራዊ የጋራ እሴት መገለጫ የሆነውን ዋና ቋንቋ ትቶ፣ በስደተኞች ቋንቋ ብቻ የፖለቲካ ቅስቀሳ ማድረግ ፍጹም ያለመዋሃድ (assimilate ያለማድረግ) እና ለሀገሪቱ ባሕልና ሕዝብ ክብር ያለመስጠት ተደርጎ ተወስዷል። ይህ አካሄድ አሁን በአሜሪካ ላይ እየተነሳ ካለው የኢልሃን ዑመር የስደትና የዜግነት ስረዛ ምርመራ ጋር ተዳምሮ፣ በስደት የመጡ የፖለቲካ መሪዎች አጀንዳቸው የአሜሪካን ሕዝብ ማገልገል ሳይሆን የራሳቸውን ብሔረሰባዊ ጥቅምና ስሜት ማስቀደም ነው የሚለውን ስጋት ይበልጥ አጋግሎታል።
ሠንደቅ የመዘቅዘቁን ክስተት ተከትሎ የተሠሩ ሐሰተኛ ቪዲዮዎች የበለጠ የጥላቻ መንፈስ እንዲፈጠር እያደረጉ ነው። የሐሰት ቪዲዮዎቹን የተመለከቱም ናፊሳን ፊትለፊት ተጋፍጠዋት እንደነበር የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ናፊሳም ሆነች በቦታው የተገኙ ሠንደቁ ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ እንደነበር ያምናሉ። በተለይ ናፊሳ ስትናገር “ሠንደቁ መዘቅዘቁን ልብ ኣላልኩም” ብላለች። ስትቀጥልም “የሚቻለኝ ከሆነ ለዚህች ሀገር እዋጋለሁ፤ ጦር ሜዳ መሔድ ካለብኝም እሄዳለሁ” በማለት ለአሜሪካ ያላትን የአርበኝነት ስሜት ገልጻለች። ይህንን ስትል ግን አሜሪካ ደግማ ሶማሊያን ብታጠቃ ትውልድ ሀገሯን ለመውጋት ጭምር መሆኑን አልጠቀሰችም።
ይሁንና ናፊሳ ክስተቱን በዚህ መልኩ ብታስረዳም ጎልጉል የሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተነሳው ተቃውሞ አሁንም አልበረደም። ናፊሳም ሆነች ኢልሃን ዑመር ዜግነታቸው ተሰርዞ ወደ ትውልድ ሀገራቸው መመለስ አለባቸው የሚለው አስተያየት አሁንም ጠንክሮ እየተስተጋባ ይገኛል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply