በቅርቡ እጃቸውን የሰጡ የቀድሞ የትህነግ ጀነራሎችና ኮሎኔሎች፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከፍተኛ ማዕረግ የነበራቸው ሰዎች፤ ያደረጉት የትጥቅ ትግል ትርጉም የለሽና የሞኝነት እንደነበር “ከሃዲዎቹ ምርኮኞች” በሚል ርዕስ በመከላከያ ሠራዊት በተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም ላይ መናገራቸው በዲያስፖራው የሚገኙ የትህነግ ደጋፊዎችን ክፉኛ አስቆጥቷል። ለሃምሳ ዓመታት ያህል ትህነግ ታጋዮቹ ሞትን የማይፈሩ፣ “ኮሎኔል ማራኪ”፣ የማይበገሩና “ተራሮችን ያንቀጠቀጡ” እንደሆኑ አድርጎ የገነባው ትርክት በራሱ የቀድሞ አዛዦች አንደበት መፈራረሱ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል።
ይህንን የፈራረሰ ትርክት ለመጠገንና የደረሰውን ጉዳት ለመቆጣጠር የኢትዮ ሚዲያ ፎረሙ (EMF) ያየሰው ሽመልስ ባቀረበው ዘገባ፣ እጃቸውን የሰጡትን ጀነራሎች ከመለስ ዜናዊ ለመነጠልና የመለስን ስም ለማዳን ሞክሯል። ይሁን እንጂ ያየሰው መለስ ዜናዊን “ድንቅ አሳቢ” አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር፣ ሳያውቀው የመለስ ዜናዊን ባዶነት፣ የአመራር ድክመትና በጥላቻ የታወረ ማንነት በአደባባይ ራቁቱን አስቀርቶታል።
ራሱን ያጠፋው የማስተባበያ ሙከራ
ያየሰው እነዚህ ከፍተኛ አዛዦች ለምን እጃቸውን እንደሰጡና ትግላቸውን እንደካዱ ለማስረዳት ሲሞክር፣ ሰዎቹ ከመጀመሪያውም እውነተኛ ታጋዮችም ሆኑ አሳቢዎች እንዳልነበሩ ገልጿል። በያየሰው ባቀረበው ጥንቅር ላይ እነዚህ “ጀነራሎች” “በመለስ ዜናዊ አእምሮ እና ትከሻ ላይ ተንጠላጥለው አዲስ አበባ የገቡ”፣ “ትንሽ ፊደል ቆጥረው” በመለስ ዙሪያ የተሸሸጉና “የገበሬ ልጆች እየሞቱላቸው” ከጦር ግንባር ርቀው የኖሩ በማለት ገልጾዋቸዋል።
ያየሰው በዚህም አላበቃም፤ “መለስ ዜናዊ የሚባል ሰው ባይኖር ኖሮ ወላጆቻቸው ብቻ የሚያውቋቸው ሰዎች ይሆኑ ነበር” ሲል ተናግሯል። አክሎም መለስ እያሰበ፣ መለስ እየሰራና “መለስ ጽፎ የሰጣቸውን እያነበቡ” አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ጀነራል አድርጎ እንደመደባቸው፣ እነዚህ ሰዎች ግን “አንድ ገጽ ጽፈው ፖለቲካ እና ውትድርና መስራት የማይችሉ” እና “የሚቆሙለት መርህና አቋም የሌላቸው” መሆናቸውን በአደባባይ መስክሯል።

መለስ ዜናዊ: ባዶና በጥላቻ የታወረ፣ ከተከታዮቹ የባሰ አላዋቂና የወረደ “መሪ”
ያየሰው ይህንን የተናገረው እጃቸውን የሰጡትን ጀነራሎች ለማዋረድና መለስ ዜናዊን ብቸኛ ሊቅ አድርጎ ለማጉላት ቢሆንም፣ ንግግሩ በቀላል አመክንዮ ሲመዘን መለስ ዜናዊን ራሱን እጅግ ከንቱና አላዋቂ መሪ መሆኑን አረጋግጧል። የያየሰውን ንግግር እውነት ነው ብለን ከተቀበልን፤ ማለትም እነዚህ ጀነራሎች መርህ የሌላቸው፣ አንድ ገጽ መጻፍ የማይችሉና የማይረቡ ስብስቦች ከነበሩ፤ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ይነሳል፤ እነዚህን ሁሉ ከንቱ፣ ደካማና የማይረቡ ሰዎች በዙሪያው ሰብስቦ የሀገርን መከላከያ ሰራዊት እንዲመሩ ጀነራል አድርጎ የሾመው መለስ ዜናዊ ምን ያህል የወረደ፣ ፈሪ፣ ከጥላቻ በስተቀር ማሰብ የማይችልና ደካማ መሪ ነበር ማለት ነው?
በያየሰው የራሱ ምስክርነት መሰረት፣ መለስ ዜናዊ ነገሮችን አርቆ መተንተን የማይችል፣ ራዕይ የሌለውና በጥላቻና በበቀል ስሜት ብቻ የሚነዳ ግለሰብ ነበር። አንድን ሀገር በብቃት ከመምራት ይልቅ፣ በዙሪያው የሰበሰበው የራሳቸው ሀሳብ የሌላቸውን፣ አንድ ገጽ እንኳን መጻፍ የማይችሉ ደካሞችን ነበር፤ ምክንያቱም ብቁና አዋቂ ሰዎች ቢኖሩ ኖሮ የእሱን ባዶነትና አምባገነንነት ስለሚገዳደሩት ነበር። የማይረቡ ሰዎችን በዙሪያው መሰብሰቡ የመለስን ሊቅነት ሳይሆን፣ የራሱን አቅመ ቢስነት፣ የስልጣን ጥማትና ለሀገር የነበረውን ጥላቻ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
የሃምሳ ዓመት ተረት ፍጻሜ
ለአስርት ዓመታት ሕዝቡ ሲነገረው የኖረው የትህነግ ወታደራዊ አመራሮች ድንቅ ስትራቴጂስቶችና የማይበገሩ ጀግኖች እንደሆኑ ነበር። ለዚህም ትልቁ ማሳያ የአውራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ ከተማራኪዎቹ አንዱ የሆነውን ዮሐንስ መዲድን “ማገዶ ቆጣቢ” ብሎ ሲያደንቀው የነበረበት የውሸት ፕሮፓጋንዳ ነው፤ እዚህ ላይ “ማገዶ” የተባለው ምስኪኑን ተዋጊ ወጣት መሆኑን ልብ ይሏል። ይሁን እንጂ ራሱ ዮሐንስ መዲድ በዶክመንተሪው ላይ ቀርቦ ሲናገር “አይተነው የማናውቀው መከላከያ ነው የገጠመን፤ ያላሰብነው ጦርነት ነበር” ብሎ መማረኩንና ሽንፈቱን በአደባባይ አምኗል።
ዛሬ ላይ ግን የእነዚህን አዛዦች እጅ መስጠት ለማስተባበል ትህነግ ባደረገው የድንጋጤ ሩጫ፣ በትግርኛ የተጻፈለትን ባማርኛ ተርጉሞ በሚያነበው ያየሰውና በራሱ የትህነግ ሚዲያ እነዚያ ጀነራሎች ከመጀመሪያውም ከንቱ እንደነበሩና መለስ ዜናዊ ጽፎ እየሰጣቸው ኮከብ የደረደረላቸው መሆኑን በአደባባይ አረጋግጧል።
ያየሰው ሽመልስ የመለስ ዜናዊን ስም ለማዳን ሲል የመላውን የትህነግ አመራርና የመለስን ጭንብል ገፍፎታል። መለስ ዜናዊ ሀገርን ሲያምስና ሕዝብን ሲከፋፍል ኖሮ፣ ትቶት ያለፈው ውርስ (ሌጋሲ) የማይረቡ ሰዎችን ስብስብ ብቻ መሆኑን የራሱ ሚዲያ በአደባባይ መስክሯል። ይህም መለስ ሲሞት በስድስት ዓመት ውስጥ እንደ እንቧይ ካብ የተናደ የውሸትና የጥላቻ ግንብ መሆኑን በራሳቸው አንደበት አሳይተዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply