* ውሳኔው ከዜግነት መነጠቅ እስከ ከአገር ማባረር ይደርሳል
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ በ“ሽብርተኝነት እና በመገንጠል” ተግባር ላይ የተሰማሩ ትህነግ፣ ኦነግ ሸኔ፣ ፋኖ እና ሌሎችንም ያካተተውን የትብብር ለሕልውና ታጣቂ ቡድኖች ስብስብ አስመልክቶ ካስተላለፉት ጠንከር ያለ መልእክት በመቀጠል፣ ዋሽንግተን እነዚህን ቡድኖች በሚደግፉ አካላት ላይ የማያወላዳ እርምጃ መውሰድ እንደምትጀምር ጎልጉል ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ያገኘው መረጃ አመለከተ።
በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ መንግሥት ሕገወጥ ስደተኞችን ከማጽዳት ባለፈ፣ በማንኛውም ሕገወጥ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙና በመወለድ ሳይሆን በመሃላ (naturalized citizenship) ዜግነት ያላቸውን ጭምር ዜግነታቸውን በመሰረዝ ከአገር እስከማባረር የሚደርስ ከባድ አካሄድ ላይ እንዳለ የሚታወቅ ነው። ይህ አዲስ አካሄድ እንደ ኢልሃን ዑመር ያሉ ትውልደ ሶማሊያዊ ግን የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን የምክር ቤት አባል ጭምር ዜግነት የመንጠቅ እና የማባረር ሂደት ውስጥ ሊያካትት እንደሚችል ምንጮች ይጠቁማሉ።
ወደ ዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ የሚኖሩና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሁለት ግለሰቦችን ጎልጉል ያነጋገረ ሲሆን እነርሱም በመረጃው እንደማያምኑ ተናግረዋል። አንድኛው ግለሰብ ዜግነት የወሰዱና የታጣቂ ቡድኖች ደጋፊ መሆናቸውን የገለጹ ናቸው። ሌላኛው ወደ አሜሪካ ከመጡ ሦስት ዓመት የሆናቸውና ገና መኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት በቀጠሮ ላይ ያሉ ለዚሁ ሲሉ ታጣቂ ቡድኖችን የሚደግፉ ናቸው። ዜጋ የሆኑት ሲናገሩ ይህ ሊሆን የማይችልና ለማስፈራራት የወጣ ነው እንጂ ዜግነቴን ማንም አይወስድብኝም ብለዋል። መናገር ያልፈለጉትን ታጣቂ ቡድን ደግሞ በሚችሉት ሁሉ መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ጉዳያቸው በመታየት ላይ ያሉት ግን ሁኔታው ያሳሰባቸው መሆኑን አልሸሸጉም። በፊት በዜጋ ላይ ምንም እርምጃ እንደማይወሰድና የሕግ ከለላ እንዳላቸው ነበር የሚታወቀው አሁን ግን ሕግ መጠቀስና መከራከር የማይቻልበት ሁኔታ ላይ መደረሱ እጅግ እንደሚያሳስብ ተናግረዋል። የሚያውቋቸውና ዜግነት የወሰዱ ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳን እንዳልፈሩ በጀብደኝነት የሚናገሩ ቢሆኑም በቅርበት ሲያነጋግሯቸው ግን ሁኔታው አስፈርቷቸው ሁሉም ከፖለቲካ መራቅ እንደሚፈልጉ ነው የጠቀሱላቸው።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉና ለአገሪቱ ሕግ ቅርበት ያላቸው አንድ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ለጎልጉል እንደገለጹት፣ በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በዋና ዋና መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል። ባለሙያው አክሎም፣ እነዚህ አካላት የአክቲቪዝም ተግባራቸውን በተቻለ መጠን ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ሲሉ መፍትሔ ሊፈልጉለትና በሙያዊ የሚዲያ ሥራ ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለባቸው አስገንዝቧል።
ይህ ካልሆነ ግን የሚሰሩት ሥራ የታጠቁ ቡድኖችን የመደገፍ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልና ዜግነታቸው ከተሰረዘ በኋላ የትውልድ አገራቸው ኢትዮጵያ እነሱን ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆነች፣ በአሜሪካ እስር ቤቶች ውስጥ ላልተወሰነ ጊዜ ሊታሰሩ እንደሚችሉ፤ ወይም እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ወደሚያስተናግዱ እንደ ኤልሳልቫዶር ያሉ ሶስተኛ አገራት ሊላኩ እንደሚችሉ ባለሙያው አስጠንቅቋል።
አንዳንዶች ግን ምንም አይደርስብንም፣ በዜግነታችን ነጻነት አለን፣ ይኼ ከዚህ በፊትም ሲነገር የኖረ ተራ ፕሮፓጋንዳ ነው ይላሉ ለሚለው የሕግ ባለሙያ አጭር መልስ ሰጥቷል። ኢትዮጵያውያን እንደ አለመታደል ሆኖ ይህንን መሰል ጭፍን አለመለካከት አለን፤ አሁን በአሜሪካ ላይ እየሆነ ያለው አገሪቱ ከተመሠረተች ሆኖ የማያውቅ ሊባል የሚችል አሠራር ነው። ሕግ አውጪውና አስፈጻሚውና ተርጓሚው የነበራቸው በጉልህ የሚታይ መስመር ደብዝዘው ጉዳዮች ከነጩ ቤተ መንግሥት በሚሰጥ ትዕዛዝ ብቻ እየተፈጸሙ ነው ያሉት። ወገኖቼን የምመክረው የማርኮ ሩቢዮ ንግግር ተራ የእግረመንገድ ወሬ ሳይሆን ፖሊሲ ነው ብሏል።
በተመሳሳይ መልኩ ለእነዚህ ቡድኖች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎችን በተመለከተ፣ የሚንቀሳቀሰው ማንኛውም የገንዘብ ፍሰት በአሜሪካ የስለላ እና የፋይናንስ መዋቅር በቀላሉ ሊከታተል እንደሚችል ተገልጿል። ብቸኛው የድጋፍ መንገድ በጥሬ ገንዘብ መስጠት ብቻ ሲሆን፣ ይህም ራሱ ከፍተኛ የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ሌላው ትልቅ ችግር መሆኑ ተመልክቷል። በዚህም ምክንያት ለእነዚህ የታጠቁ ቡድኖች ድጋፍ በማሳየት ብቻ የቋሚ ነዋሪነት ወይም የስደት ፈቃድ ጉዳያቸውን ለማስፈጸም የሚሞክሩ ወገኖች ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገልጿል። ይህ ተግባራቸው የስደት ሂደታቸውን የሚረዳ ሳይሆን፣ አሁን ያላቸውን ሕጋዊ የነዋሪነት ደረጃ ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ የታጠቁ ቡድኖች ደጋፊዎች ላይ አዲስ እና ከባድ ስጋት ደቅኗል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply