- የአውሮፓ ፓርላማ በኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ የጉዞ እገዳ እንዲጣልና የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥ ወሰነ
- ውሳኔው በ529 የድጋፍ ድምፅ የጸደቀ ሲሆን፣ የተቃወሙት ሁለት አባላት ብቻ ናቸው
የአውሮፓ ፓርላማ በኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የታለመ ማዕቀብ እንዲጣልና የአውሮፓ የገንዘብ ድጋፍ መስመሮች እንዲዘጉ በከፍተኛ ድምፅ ማሳለፉን ተከትሎ በአሥመራ መንግሥትና በውጭ በሚኖሩ ደጋፊዎቹ ላይ ከፍተኛ ድንጋጤና ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ተፈጥሯል።
ሐሙስ ኅዳር 17 ቀን 2019 ዓም (November 26, 2026) በስትራስበርግ በተካሄደው ስብሰባ፣ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የፓርላማው አባላት በአንድነት በመቆም በኤርትራ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያወግዝ ጠንካራ የውሳኔ ሐሳብ አጽድቀዋል።
የአውሮፓ ፓርላማ ይፋዊ መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ ውሳኔው በ529 የድጋፍ ድምፅ የጸደቀ ሲሆን፣ የተቃወሙት ሁለት አባላት ብቻ ናቸው፤ 25ቱ ደግሞ ድምፅ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ለዚህ ውሳኔ መነሻ የሆነው ለ25 ዓመታት ያለፍርድ የታሰረውና ደብዛው የጠፋው የኤርትራና ስዊድን ጥምር ዜግነት ያለው ጋዜጠኛ ዳዊት ኢሳቅ ጉዳይ ቢሆንም፣ እርምጃው ግን በቀጥታ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን መንግሥትና በአውሮፓ የሚገኙ የገንዘብ መረቦቹን የሚያንቀጠቅጥ ነው።
የፓርላማው አባላት ያጸደቁት የውሳኔ ሐሳብ በኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ ጠንካራ ክሶችን ያቀረበ ሲሆን፣ መንግሥቱ ስልታዊ ስቃይ፣ የዘፈቀደ እስርና በጋዜጠኞች፣ በሃይማኖት መሪዎችና በፖለቲካ ተቺዎች ላይ የማያባራ አፈና እየፈጸመ መሆኑን አስምሮበታል።
ፓርላማው የዳዊት ኢሳቅና የሌሎች የኅሊና እስረኞች በሕይወት መኖር በአስቸኳይ እንዲረጋገጥና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ከመጠየቁ ባሻገር፣ የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት በሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ በተሳተፉ ግለሰቦች፣ የፀጥታ አዛዦችና የመንግሥት ተቋማት ላይ በአውሮፓ ኅብረት የሰብአዊ መብት ማዕቀብ ሕግ መሠረት የጉዞ እገዳና የንብረት ማገድ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም የአውሮፓ ኮሚሽንና የኅብረቱ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማንኛውም የአውሮፓ የልማትም ሆነ የዲፕሎማሲ ገንዘብ ለኤርትራ መንግሥት መዋቅር እንዳይውል ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ይህ ውሳኔ ተግባራዊ ከሆነ በአሥመራ መንግሥትና በውጭ በሚገኙ ደጋፊዎቹ ላይ የሚያስከትለው መዘዝ እጅግ ከባድ ነው። ለዓመታት የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትችት ችላ በማለት በስዊድን፣ በጀርመን፣ በኔዘርላንድስና በጣሊያን በሚገኙ የዳያስፖራ መረቦች አማካኝነት ገንዘብ ሲሰበስብ የቆየው ሻዕቢያ አሁን ከፍተኛ ፈተና ተጋርጦበታል።
በማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ ከፍተኛ ወታደራዊ፣ የደኅንነትና የፓርቲ ባለሥልጣናት በአውሮፓ ያላቸው የባንክ ሒሳብ የሚታገድ ሲሆን፣ ወደ አውሮፓ የመግባት ፈቃዳቸውም ይሰረዛል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በአውሮፓ ኅብረት ሕግ መሠረት ማዕቀብ ለተጣለባቸው አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ገንዘብ ማስተላለፍ በሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል በመሆኑ፣ በአውሮፓ የሚኖሩ የመንግሥቱ ደጋፊዎች የሚያዘጋጇቸው ፌስቲቫሎች፣ የሚሰበስቡት የሁለት በመቶ የዳያስፖራ ግብርና ወደ አሥመራ የሚልኩት ገንዘብ ከፍተኛ የሕግ ተጠያቂነትን ያስከትልባቸዋል።
የአውሮፓ ባንኮችም ከፍተኛ ቅጣትን ለመሸሽ ሲሉ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸውን የገንዘብ ዝውውሮችና የባንክ ሒሳቦች በራሳቸው ተነሳሽነት መዝጋታቸው አይቀርም።
በፖለቲካዊ ረገድም ቢሆን፣ እንደ ብራሰልስ ታይምስ ዘገባ ውሳኔው በ529 ለ2 ድምፅ ማለፉ የአሥመራ መንግሥት “ጥቂት የምዕራባውያን ፖለቲከኞች ሴራ ነው” በማለት የሚያቀርበውን የተለመደ ሰበብ ሙሉ በሙሉ ዋጋ ያሳጣው ሲሆን፣ መንግሥቱን በአውሮፓ ዓይን የተገለለ አድርጎታል።
በአውሮፓ ኅብረት አሠራር መሠረት ፓርላማው በራሱ ማዕቀብ የመጣል ሥልጣን ባይኖረውም፣ ማዕቀብ የማጽደቅ ሥልጣን ያለው የ27ቱን አባል ሀገራት የሚወክለው የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ነው። በመሆኑም አሁን ኳሷ ያለችው በአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እጅ ላይ ነው።
የዜጋዋን የዳዊት ኢሳቅን ጉዳይ በግንባር ቀደምትነት የያዘችው ስዊድን በብራሰልስ የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፣ በቀጣይ ሳምንታት በማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ የኤርትራ ባለሥልጣናት ስም ዝርዝር የማዘጋጀት ሥራ ይጀመራል።
ውሳኔው በምክር ቤቱ እንዲጸድቅ የሁሉም 27 አባል ሀገራት ሙሉ ስምምነት የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ ከስትራስበርግ የተላለፈው መልዕክት ግን ግልጽ ነው፤ የዝምታ ዲፕሎማሲ ዘመን አብቅቶ በአሥመራ መንግሥትና በአውሮፓ መረቦቹ ዙሪያ የገንዘብና የሕግ አጥሮች እየጠበቡ መጥተዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ


Leave a Reply