የቀድሞው የፋኖ አመራር የነበረው ማርሸት ፀሐዩ ከኤን.ቢ.ሲ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረገውና በቅርቡ ሙሉው ክፍል ይፋ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው ቃለ ምልልስ ቅንጫቢ ላይ፣ በፋኖ አመራሮች ውስጥ ስለሚፈጸመው ከፍተኛ የገንዘብ ዝርፊያ፣ ባለሀብቶችን ስለማስፈራራት እና በውጭ ሀገራት ባንኮች ስለተከማቹ ሚሊዮን ዶላሮች አስደንጋጭ መረጃዎችን ይፋ አድርጓል።
ማርሸት በንግግሩ እነዚህን አመራሮች “የጫካ ቱጃሮች” ሲል የጠራቸው ሲሆን፣ ትግሉ ከሕዝባዊ ዓላማ ይልቅ የግል ሀብት ማካበቻ እና የሥልጣን መወጣጫ መሆኑን በዝርዝር አስረድቷል።
እንደ ማርሸት ገለጻ፣ የፋኖ አመራሮች ለባለሀብቶች የማስፈራሪያ ደብዳቤዎችን በመጻፍ ከፍተኛ ገንዘብ ይቀበላሉ። “ስልኬ ላይ የተጻፉ ደብዳቤዎች አሉ” ያለው ማርሸት፣ ለባለሀብቶች “ይህን ያህል ገንዘብ ካላመጣህ ተሽከርካሪህ በዚህ አያልፍም፤ አንተም በሕይወት አትኖርም” የሚል ማስፈራሪያ እየተላከላቸው ከአንዳንድ ባለሀብቶች ብቻ 20 እና 30 ሚሊዮን ብር እንደተቀበሉ አጋልጧል።

በቃለ ምልልሱ ላይ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል እጅግ አስደንጋጭ የሆነው፣ በአንድ የጎጃም የፋኖ አመራር ስልክ ላይ ተገኘ የተባለው መረጃ ነው። የዚህ አመራር ስልክ ተይዞ በተደረገ ፍተሻ፣ በአሜሪካን ሀገር በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ተቀማጭ ገንዘብ እንዳለው የሚያሳይ መረጃ መገኘቱን ማርሸት ተናግሯል።
በተጨማሪም በእስክንድር ነጋ እና በዘመነ ካሴ ቡድኖች (ኤክስትሪሞች) መካከል ስላለው ልዩነት ሲያብራራ፣ የእስክንድር ቡድን በፋይናንስ አቅም የሚንቀሳቀስና በአካውንቱ ውስጥ ሚሊዮን ዶላር ያለው፣ ለፈለገው ሰውም የፈለገውን ያህል ሚሊዮን ብር የሚሰጥ ኃይል መሆኑን ጠቅሷል። በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነትም የርዕዮተ ዓለም ሳይሆን የሥልጣን ፉክክር መሆኑን አስምሮበታል።
ማርሸት አክሎም፣ በውጭ ሀገር (በተለይም በካሊፎርኒያ ከሚገኙ ግለሰቦች) የሚላኩ የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄዎች በአመራሩ ዘንድ ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጣቸው ሲገልጽ፣ ሁለት ቄሶች ድጋፍ እናደርጋለን ብለው የላኩትን ደብዳቤ ተከትሎ 16 የፖሊስ ቢሮ አባላት ለሶስት ሰዓት ተኩል ያህል ሲወያዩበት እንደነበር በምሳሌነት አንስቷል።
በመጨረሻም እነዚህ አመራሮች በዘረፋና በአምባገነንነት የጀመሩት ተግባር የፈለጉት ሥልጣን ላይ ካላደረሳቸው፣ ትናንት ከህወሓትና ከሻዕቢያ ጋር እንደተገናኙት ሁሉ፣ ነገም ከየትኛውም ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን ጋር በመተባበር ሽብርተኝነትን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት በሕዝብና በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አስጠንቅቋል።
የሚገርመው ጉዳይ፣ ማርሸት ዛሬ ከውስጥ ሆኖ ያረጋገጣቸው እነዚህ አስደንጋጭ ዝርፊያዎች ከዚህ ቀደምም በተለያዩ መድረኮች ሲዘገቡ ነበር። ሆኖም እውነቱን የተናገሩ ሁሉ በፋኖ ደጋፊዎች ዘንድ “ካድሬ” እና መሰል አጸያፊ ስሞች እየተሰጧቸው ሲወገዙና ሲሸማቀቁ ቆይተዋል። ዛሬ ግን መረጃው ከራሳቸው ከአመራሮቹ አንደበት ወጥቶ እውነቱን አፍጥጦ አሳይቷል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply