የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን) በፎርት ሁድ ቴክሳስ ወታደራዊ ጣቢያ 13 ሰዎችን በመግደል እና 32 ሰዎችን በማቁሰል ጥፋተኛ የተባለው የቀድሞው የጦር ሠራዊት የሥነ-አእምሮ ሐኪም ሻለቃ ኒዳል ሀሰን የሞት ፍርድ በርሸና (Firing squad) ሲፈጸምበት በቀጥታ በቪዲዮ ሥርጭት (Livestream) ለሕዝብ እንዲታይ መወሰኑን አስታውቋል።
ኒዳል ሀሰን ይህንን አሰቃቂ ጥቃት የፈጸመው በጥቅምት 26 ቀን 2002 ዓ.ም. (በአውሮጳውያኑ አቆጣጠር ህዳር 5 ቀን 2009) ሲሆን፣ ጥቃቱን ያደረሰበት ዋና ምክንያት የአሜሪካ ጦር በኢራቅ እና በአፍጋኒስታን የሚያደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ በመቃወም እና በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የሚደረግ ውጊያ አድርጎ በመመልከቱ እንደነበር በፍርድ ሂደት ወቅት ተገልጿል።
ይህ የፔንታጎን ውሳኔ በአሜሪካ የፖለቲካ እና የሕግ ባለሙያዎች መካከል ከፍተኛ ክርክር እና ውዝግብ አስነስቷል።
ውሳኔውን የሚደግፉ ወገኖች እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት እንደሚሉት፣ ድርጊቱ ለተጎጂ ቤተሰቦች ፍትሕ መስጠቱን የሚያሳይ ሲሆን፣ የቅጣቱን ሁኔታ በይፋ ማሳየቱ ለወደፊቱ መሰል አሰቃቂ ጥቃቶችን ለመግታት ትልቅ የማስጠንቀቂያ መልእክት ያስተላልፋል ብለዋል።
በተጨማሪም መንግሥት በከባድ ወንጀለኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃ ሕዝብ በቀጥታ ስርጭት እንዲመለከተው ማድረግ ግልጽነትን እና የተጠያቂነት መርህን ይፈጥራል የሚል እምነት አላቸው።
በአንፃሩ ውሳኔውን የሚቃወሙ ወገኖች እርምጃውን አጥብቀው ያኮንኑታል።
እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ የሰብዓዊ መብትና የሥነ-ምግባር ተሟጋቾች የሞት ፍርድን በሕዝብ ፊት በቀጥታ ማሳየት ጨካኝ፣ ኢሰብዓዊ እና በደልን የሚያባብስ ድርጊት ነው ሲሉ ይገልጹታል።
በርካታ የሕግ ባለሙያዎች፣ የፖለቲካ ተቺዎች እና በቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን እንደገለጹት፣ የሞት ፍርድን በሕዝብ ፊት በቀጥታ ማስተላለፍ አሜሪካ ከዚህ ቀደም የተሸጋገረችውን የመካከለኛው ዘመን፣ የሰሜን ኮሪያ ወይም የሌሎች አምባገነን ሀገራትን የኋላቀርነት አካሄድ የሚያስታውስ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።
ይህ የሕግ የበላይነትን ወደ “ትዕይንት” (spectacle) የሚቀይር አደገኛ አካሄድ መሆኑን ያመላክታሉ። በተመሳሳይ የሥነ-አእምሮ ባለሙያዎች ፍርድን በቀጥታ ስርጭት ማሳየት በተመልካቾች ላይ ከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀትና የሥነ-አእምሮ ጉዳት (PTSD) ሊያስከትል ይችላል በሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
እንደ መከላከያ ሚኒስቴሩ መግለጫ ከሆነ የሞት ፍርዱ የሚፈጸመው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 3 ቀን 2026 (Dec. 3, 2026) በፎርት ሁድ ወታደራዊ ጣቢያ ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply