በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖችን (ትህነግ፣ ፋኖ፣ ኦነግ-ኦነሠ እና ሌሎችንም) በገንዘብ፣ በማኅበራዊ ሚዲያና በተለያዩ መንገዶች የሚደግፉ የዲያስፖራ አባላት ላይ ከባድ የሕግና የኢሚግሬሽን ስጋት መደቀኑን የጎልጉል ምንጮች አስጠነቀቁ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የጦር መሣሪያ ያነሱትንና በቅርቡ ጥምረት የፈጠሩትን የታጠቁ ቡድኖች እንቅስቃሴ “የመገንጠል እና የሽብርተኝነት” ተግባር ሲሉ ፈርጀውታል። ይህንን ተከትሎ ዋሽንግተን ለእነዚህ ቡድኖች የገንዘብና የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ የሚያደርጉ የዲያስፖራ አባላትን መከታተልና መመርመር ወደሚችልበት ቀጣይ እርምጃ ልትሸጋገር እንደምትችል ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኙ ምንጭ ለጎልጉል እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ መንግሥት በሕገወጥ ስደትና በብሔራዊ ደኅንነት ዙሪያ እጅግ ጠንከር ያለና አስገዳጅ አቋም እየያዘ መጥቷል። ምንጩ እንዳሉት፣ “እንደ ምክር ቤት አባል ኢልሃን ዑመር ያሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንኳ ሳይቀሩ በኢሚግሬሽንና የጋብቻ ማጭበርበር ጥርጣሬዎች ሳቢያ ቤታቸው ተበርብሮ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው ባሉበት በዚህ ወቅት፣ ማንኛውም ተራ ዜጋ ወይም ነዋሪ ምርመራ ሊመጣበት እንደማይችል ማሰብ የለበትም” ብለዋል።
ምርመራው አንዴ ከተጀመረ ወዴት አቅጣጫና እስከ ምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችል መቆጣጠር የማይቻል በመሆኑ በቤተሰብና ኑሮ ላይ እጅግ ከፍተኛ ቀውስ እንደሚያስከትል የገለጹት የሕግ ባለሙያዎች፣ በተለይም የታጠቁ ቡድኖችን የሚደግፉ ግለሰቦች መረጃቸው በቀላሉ ሊመረመርና ቀደም ሲል የፈጸሟቸው የሕግ ጥሰቶች ሊጋለጡ እንደሚችሉ ያመለክታሉ። ከእነዚህም መካከል፦
- የታክስ ማጭበርበር እና ገቢን መደበቅ፦ በርካታ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ ለታክስ መሥሪያ ቤቱ (IRS) የሚያቀርቡት የገቢ ሪፖርት እጅግ አነስተኛ መሆኑ የሚታወቅ ነው። በተለይም እንደ ታክሲ አሽከርካሪነት ወይም እንደ ፓርኪንግ ሥራ መሠረታዊ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ነገር ግን በተለያዩ መንገዶች ያገኙትን ገቢ ደብቀው የትላልቅ ዘመናዊ ቤቶችና የከፍተኛ የገንዘብ ክምችት ባለቤት የሆኑ በርካታ የዲያስፖራ አባላት አሉ። የታጠቁ ቡድኖች ድጋፋቸው ሳቢያ የኢሚግሬሽን ምርመራ መረብ ውስጥ ሲገቡ፣ የፋይናንስና የታክስ ስወራ ወንጀላቸው በቀላሉ አብሮ የሚበረበር ሲሆን ይህ ደግሞ ሕይወታቸውን መሰቃቅሎ ወደ ከፋ ችግር ያስገባቸዋል።
- የውሸት ጋብቻ እና የቤተሰብ ማጭበርበር፦ ለኢሚግሬሽንና ለዜግነት ጥቅማጥቅም ሲሉ ከሥጋ ዘመዶቻቸው (ለምሳሌ ከወንድም፣ እኅት ወይም የአክስት/የአጎት ልጆች) ጋር በሐሰት ተጋብተው የመኖሪያ ፈቃድና ዜግነት ያገኙ ግለሰቦች፣ አሁን ባለው የጠበቀ የምርመራ መዋቅር መሠረት የዲኤንኤ (DNA) ምርመራን ጨምሮ በሰፊው ሊፈተሹ፣ ዜግነታቸው ተሰርዞ ከአገር ሊባረሩ ይችላሉ።
በተጨማሪም ለእነዚህ የታጠቁ ቡድኖች የሚደረጉ ማናቸውም የገንዘብ ድጋፎች በአሜሪካ የፋይናንስ መከታተያ መረብ (FinCEN) እና በስለላ ተቋማት በቀላሉ የሚታዩ መሆናቸው ታውቋል። በጥሬ ገንዘብ የሚደረጉ መዋጮዎችም ቢሆኑ ከገንዘብ ማጠብና (money laundering) ሕገወጥ ዝውውር ወንጀል ጋር ተያይዞ የሚያስጠይቁ በመሆናቸው፣ አክቲቪስቶችና ደጋፊዎች “ምንም አንሆንም” በሚል ጀብደኝነት ውስጥ ከመግባት ይልቅ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከአደጋ እንዲጠብቁ የሕግ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ይህ ካልሆነ ግን፣ አሁን ባለው አዲስና ጥብቅ አሠራር መሠረት፣ የሐሰት መረጃ ሰጥተው የተገኙ ወገኖች ዜግነታቸው ተሰርዞ ወደ ትውልድ አገራቸው ሊባረሩ፣ አልያም አገራቸው ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆነች በአሜሪካ እስር ቤቶች ውስጥ ላልተወሰነ ጊዜ ሊታሰሩ ወይም ወደ ሦስተኛ አገራት (እንደ ኤልሳልቫዶር ያሉ) አደገኛ ወንጀለኞች የሚታሰሩበት እስር ቤቶች ሊላኩ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መሆኑ ተጠቁሟል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply