ከትህነግ (ህወሃት) ታጣቂዎች ከመቐሌ መውጣት በኋላ በምስጢር ተዋቅሮ የነበረው አዲሱ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ዕዝ (ሴንተራል ኮማንድ) እየፈረሰ መሆኑ ተነገረ። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዚሁ ድብቅ የጦር መዋቅር ቁልፍ መሪ የነበረው ታጋይ ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ (ጆን መዲድ) የመፈራረሱ ዋና ምክንያት የጆን መዲድ መማረክ ሲሆን እርሱም ከምርኮ በኋላ ትናንት ከአክሱም ተነስቶ አዲስ አበባ መግባቱ ታውቋል።
ሌሎችም አዛዦች እንዲሁ ይማረካሉ በሚል የተፈጠረው ፍርሃት ትህነግ በምሥጢር ያቀናበረው ስትራቴጂክ ዕዝ ላይ ከፍተኛ መነቃነቅና ፈጥሯል፤ እንፈርሳለን የሚለው ስጋት አይሏል።
ለጎልጉል የደረሰው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የትህነግ አመራር ከመቐሌ ከወጣ በኋላ በፖለቲካውና በታጣቂው ክንፍ የተዋቀረ አምስት አምስት አባላት ያሉት አዲስ ‘ሴንተራል ኮማንድ’ (ማዕከላዊ ዕዝ) መስርቶ ነበር።
የማዕከላዊ ዕዙ (ሴንተራል ኮማንድ) አደረጃጀት የሚከተለው ነው፦
ሀ) ከፖለቲካው (ከትህነግ) ክንፍ፦
- ደብረፅዮን ገብረሚካኤል
- ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ)
- አማኑኤል አሰፋ
- ጌታቸው አሰፋ
- አብርሃም ተከስተ
ለ) የታጣቂው ክንፍ አመራሮች፦
- ጆን መዲድ (ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ) — አሁን የተማረከ
- ፍስሃ መነን
- ኃይለሥላሴ (ወዲ እምበይተይ)
- ምግበይ ኃይለ
- ብርሃነ (ወዲ መድህን) ነበሩ።
ይህ አስኳል የታጣቂ ዕዝ በቀጥታ የሚመራቸውና ተጠሪነታቸው ከላይ ለተጠቀሱት ዕዞች የሆኑ አምስት ንዑስ ግንባሮችን ያዋቀረ ሲሆን፣ ግንባሮቹን እንዲመሩ የተመደቡት አምስት የታጣቂ አዛዦች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፦
- ዘነበ
- ህንፃ ወልደጊዮርጊስ
- አብርሃ (ድንኩል)
- ወልደጂዎርጊስ (ሸሪፎ)
- ሙዘይ
ከእነዚህ በተጨማሪ በይፋ ያልተመደበውና በተለዋዋጭ ግዳጅ ላይ እንዲሰማራ ተደርጎ የነበረው ማሾ በየነ እንደሆነ ጎልጉል የደረሰው መረጃ ያረጋግጣል።
ይህ በትህነግ በኩል እንደ ትልቅ ስትራቴጂክ ምሽግ ተወስዶ የነበረው አዲስ መዋቅር፣ ገና ከመሬት ሳይረግጥ ተስፋ በተጣለበት በከፍተኛ መሪው ጆን መዲድ መማረክ ክፉኛ ተመትቷል።
የታጣቂው ክንፍ ግንባር ቀደም መሪ የነበረው ጆን መዲድ መማረክና አዲስ አበባ መግባት፣ በትህነግ ታጣቂዎችና ቀሪ አመራሮች መካከል ከፍተኛ አለመረጋጋትና የመበታተን ስጋት መፍጠሩን የጎልጉል ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።
ጆን መዲድ ሲማረክ በርካታ የትህነግ ዲጂታል ሠራዊትና ባንዳዎች መዲድ አስቀድሞም ምንም ታጣቂ ሳይመደብለት ብቻውን የነበረ እንጂ አመራር አልነበረም በማለት ኪሣራውን ለመጠገን እየሞከሩ ይገኛሉ።
የትግራይ የሰላም ኃይል (TPF) አባል የሆኑ ለጎልጉል እንደተናገሩት ከሁሉም ታጣቂ መሪ በላይ ጆን መዲድ ነበር ብዙ ተስፋ የተደረገበት፤ እርሱ ማለት የትግራይን አንድ ትውልድ ጨርሰንም ቢሆን ይህንን ጦርነት እንቀጥላለን እያለ ሲፎክር የነበረ ጀብደኛ ነው ብለዋል።
የጆን መዲድን መማረክ ተከትሎ ሌሎቹም የትህነግ ታጣቂ አመራሮች በቅርቡ ወይ ይማረካሉ ወይም ለመከላከያ እጅ ይሰጣሉ የሚለው ፍርሃቻ ቡድኑን ወደ መፈረካከስ እየመራው እንደሆነ ተሰምቷል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply