የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከተከላካይነት ወደ ማጥቃት እርምጃ ከተሸጋገረ የትግራይ ክልል የመጨረሻው መዳረሻ እንደማይሆንና ዋናው ግብ ቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ መትከል መሆኑን በይፋ አስታወቁ።
ጄኔራሉ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ በትዕግስትና በጥበብ የመከላከል ሥራ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። ይሁንና ወደ ማጥቃት በሚገባበት ወቅት ትኩረቱ ጥቃቅን አሸባሪዎችና ተላላኪዎች ላይ ሳይሆን፣ ቀጥታ ዕዝን መቀለ ላይ በማድረግ የቀይ ባህርን መውጫ መቆጣጠርና በአሰብ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ እንደሆነ በቁርጠኝነት ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፣ በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ በመከላከያ ሠራዊቱ የካሜራ እይታና ቁጥጥር ሥር ያለ በመሆኑ፣ የሠራዊቱ ዋና ዝግጅትና ስትራቴጂያዊ እቅድ ከቀይ ባህር ጋር የተያያዘ ነው።
“እኛን የሚገዛን የሀገር ፍቅር ብቻ ነው፤ ጥልቀት ያለው ውኃ ደግሞ ዝምተኛ ነው” ያሉት ጄኔራል አበባው፣ መከላከያ ሠራዊቱ ሙያውንና ብቃቱን በውስጡ አፍኖ ራሱን በከፍተኛ ደረጃ እያጠናከረ ለሚሰነዘሩ ትንኮሳዎች ሁሉ አጥጋቢና የማስተማሪያ ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል። ሠራዊቱ እንደ ትህነግ ፀረ-ሕዝብና የወንበዴ ስብስብ ሳይሆን፣ የሀገርና የሕዝብ ሉዓላዊነት ጠባቂ በመሆኑ በስሜት ሳይሆን በጥበብና በብስለት እንደሚመራ አረጋግጠዋል። “በደራሲያንና በፕሮፓጋንዳ ጩኸት አንጮኽም፤ ሲዘሉም አንዘልም” በማለት የሠራዊቱን ስክነትና ፕሮፌሽናሊዝም አስምረውበታል።
በተያያዘም፣ የሻዕብያ ተላላኪ የሆኑና ወደ 4 ኪሎ ቤተ-መንግሥት ለመግባት የሚንደፋደፉ ኃይሎች እንኳን 4 ኪሎን ሊረግጡ፣ 4 ኪሎ ሜትር እንኳ መጓዝ የማይችሉ ደካሞች መሆናቸውን ጄኔራሉ በጠንካራ ቃላት ገልጸዋል። የትግራይ ሕዝብም በትህነግ አምባገነናዊና አውዳሚ አካሄድ በመሰልቸቱ “መከላከያ መቼ ነው የሚገባው?” በማለት በጉጉት እየጠየቀ እንደሚገኝ በስፍራው ካሉ እናቶች የተገኘው የጎልጉል የመስክ መረጃ ያመለክታል።
በመጨረሻም፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተሸከመው አደራ የታላቋን ኢትዮጵያ ህልውና የማስከበር ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑን የገለጹት ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀብና ስነ-ልቦና ላይ የተገነባው ይኸው ሠራዊት ሀገሪቱን ወደ ፍጹም ድል እንደሚያሸጋግራት ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ እንደሌላቸው በልበ-ሙሉነት አስታውቀዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply