የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሱዳን በኩል ተገዝተው ለትህነግ የተላለፉ የUAV M6 ድሮኖችን፣ የላቁ የስለላና የወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ከነግዢ ሰነዶቻቸው ማረከ።
የተገኙት የቴክኒክ ርክክብ ሰነዶች እና የግዢ ውሎች እንደሚያረጋግጡት፤ በPFI ቁጥር 071749749-02 (ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም / እ.ኤ.አ ፌብሩዋሪ 3 ቀን 2025) እንዲሁም በሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 11 ጁን 2025) የተመዘገቡት እነዚህ ወታደራዊ ቁሳቁሶች በገዢው ሕጋዊ ተወካይ አማካይነት ጥልቅ የቴክኒክ ምርመራ ተደርጎላቸውና ብቃታቸው ተረጋግጦ ጸድቀዋል።
በፍተሻው ሂደት ከተካተቱት ሶስት የUAV M6 ድሮኖች መካከል አንደኛው የቪዲዮና የበረራ ሙከራ እንዲያደርግ የተመረጠ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ በመሬት ላይ ዝርዝር የቴክኒክ ምርመራ ተካሂዶባቸዋል። ሁሉም ክፍሎች ያለ ምንም ችግር መስራታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ግዢው ተጽድቋል። በተመሳሳይ መልኩ ከስለላ መሳሪያዎች (surveillance payloads) አንዱ ለሙከራ ተመርጦ ሲፈተሽ፣ ሌሎቹ በመሬት ላይ ተመርምረው የመጨረሻ የቴክኒክ ተቀባይነት አግኝተዋል። በሰነዱ የተዘረዘሩት UAV M6፣ FCU እና BRU መሳሪያዎች ሙሉ በሙሉ ትህነግ እጅ መድረሳቸው ተረጋግጧል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተገኘውና “ምሥጢር” የሚል የደህንነት ደረጃ በተሰጠው ደብዳቤ ላይ፣ በሱዳን ጦር ሠራዊት የተንቀሳቃሽ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ኢንጂነር አህመድ አደም አህመድ የተፈረመ መመሪያ ተገኝቷል። ይህ ደብዳቤ ለተጓዳኝ ኦፕሬሽኖችና ለሎጂስቲክስ አገልግሎት የተመደበውን መኪና ዝርዝር መረጃ፣ የሻንሲ ቁጥር እና ልዩ የይለፍ ፈቃድ የያዘ ሲሆን፣ ተሽከርካሪው በየፍተሻ ኬላዎች ላይ ያለ ምንም ጥያቄና እንግልት በነጻነት እንዲያልፍ የሚያስችል ነው።
ግዢውን በፈጸመው ሱዳናዊው ኤላሚን አህመድ አማካይነት ውል ተፈርሞ ትህነግ እጅ የገቡት እነዚህ ድሮኖችና የስለላ ካሜራዎች በመከላከያ እጅ መግባታቸውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችም ወጥተዋል። ይህም ትህነግ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ጀርባ ለጦርነት ሲዘጋጅ መኖሩን እንደሚያረጋግጥ ተመልክቷል።

































በተያያዙት ምስሎችና ሰነዶች መሠረት፣ ስሙ ባልተገለጸ አካል በወኪል አማካይነት ለትህነግ ከተገዙት ሶስት የM6 ወታደራዊ ድሮኖች መካከል አንዱ ድሮን ብቻ አራት ቦንቦችን የመሸከም አቅም አለው። በተጨማሪም 12 የቦንብ ማቀፊያ ዩኒቶች፣ የተለያዩ ካሜራዎች፣ ከመሬት ሆነው ድሮኖቹን ለማዘዝ የሚያስችሉ ኮምፒውተራይዝድ የመተኮሻና ማዘዣ መሳሪያዎች (የመሬት መቆጣጠሪያ ጣቢያ [GCS]፣ ፋየር ኮንትሮል ዩኒት [FCU] እና የሬዲዮ/መገናኛ መሳሪያዎች)፣ ሙሉ መለዋወጫዎችና የመጠገኛ ኪቶች ተገዝተው ትህነግ እጅ መግባታቸው ተረጋግጧል።
የUAV M6 (Mohajer-6) ድሮኖች መካከለኛ ከፍታ ላይ ለረጅም ሰዓታት መብረር የሚችሉ፣ ለስለላና ለታለሙ ወታደራዊ ጥቃቶች የሚያገለግሉ ዘመናዊ የታክቲካል ደረጃ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ናቸው። ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የቀንና የሌሊት ኦፕቲካል ካሜራዎች (Payloads) የታጠቁ በመሆናቸው የቀጥታ ምስልና የመረጃ ስርጭትን ወደ ምድር መቆጣጠሪያ ጣቢያ ያሻግራሉ። የውጊያ መቆጣጠሪያ (FCU) እና የቦምብ መልቀቂያ (BRU) ሲስተሞች ስላሏቸውም የታለሙ ኢላማዎችን በትክክለኛነት የመታት ከፍተኛ አቅም አላቸው።
የእነዚህ ድሮኖች ጥራት የሚገለጸው በሲግናል ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂያቸውና የጂፒኤስ ማወክን በሚከላከሉ (GPS Anti-Jamming) ክፍሎቻቸው ነው። በድንገተኛ አደጋ ወቅት አውሮፕላኑን የሚያድን የፓራሹት ደህንነት ሲስተም ያላቸው ሲሆን፣ በሜዳ ላይ በቀላሉ ሊጠገኑ የሚችሉ አጠቃላይ የመለዋወጫና የጥገና ቁሳቁሶች ስብስብ (Integrated Logistic Support) አሏቸው።
በዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያዎች ገበያ ዋጋ መሠረት፣ የተጠቀሱትን 3 የM-6 ድሮኖች፣ 4 የካሜራ ፔይሎዶች፣ 12 የቦምብ ማቀፊያዎች፣ የመቆጣጠሪያ ኮምፒውተሮችና የመለዋወጫ ዕቃዎችን ያካተተው ይህ ሙሉ ፓኬጅ አጠቃላይ ዋጋው ከ5 ሚሊዮን እስከ 10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር (እስከ 2 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር) ይገመታል። አንድ ሙሉ የM-6 ድሮን ሲስተም ከነመቆጣጠሪያው ከ1.5 እስከ 2.5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሲሆን፣ ቀሪው ወጪ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ መለዋወጫዎችና የጥገና ዕቃዎች የሚውል ነው።
እነዚህን መሳሪያዎች ሙሉ በሙሉ የማረከው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባለሙያዎች እስካሁን ይፋዊ መግለጫ አልሰጡም። ሆኖም የተማረኩት መሣሪያዎች ትህነግ ባለው አቅም ሁሉ ለጦርነት ሲዘጋጅ እንደነበር የሚያረጋግጡ መሆናቸውን መረጃውን ያቀበሉት አካላት አስታውቀዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply