ጎልጉል ከታመኑ የውስጥ ምንጮቹ ባገኘው ሰበር መረጃ መሠረት፣ በሽብርተኛውና በውድቀት ዋዜማ ላይ በሚገኘው የትህነግ ቡድን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ላይ በተሰነዘረ የተቀናጀ የከባድ መሳሪያና የድሮን ጥቃት በርካታ አዛዦች ተደምስሰዋል።
መስከረም 20 እና 21 ቀን 2019 ዓ.ም. በተካሄደው በዚህ የከረረ ምት የተገደሉት የትህነግ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፦
- ኮሎኔል ትንሱ ብርሃነ — የአርሚ 43 አዛዥ፣
- ኮሎኔል አፅበሃ — የአርሚ 15፣ የ151ኛ ኮር አዛዥ፣ እና
- ስሙ እስካሁን ያልተገለጸ ሌላ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር መሆናቸው ተረጋግጧል።
የእነዚህ ከፍተኛ አዛዦች መደመስስ በቡድኑ ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና ተስፋ መቁረጥን የፈጠረ ሲሆን፣ የቀብር ስነ-ስርዓታቸውም ዛሬ መስከረም 21 ቀን በመቀሌ ከተማ “እንዳ ገብርኤል” በሚባለውና በተለምዶ የታጋዮች መቃብር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በምስጢርና በሀዘን ድባብ ተፈጽሟል።
በተፈናቃይ መጠለያዎች የተነሳው ተቃውሞ እና የትህነግ የጭካኔ አቅጣጫ
በሌላ በኩል፣ ቡድኑ በየግንባሩ እየደረሰበት ካለው የህልውና አደጋ ጎን ለጎን፣ በቁጥጥሩ ስር ባሉ ተፈናቃዮች ዘንድ የሕዝብ ዓመፅ እየተቀሰቀሰበት ይገኛል።
ጎልጉል የደረሰው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በህንፃፅ፣ በዓዲመሓመዳይ እና በማይሓንሴ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብላቸው ከማስጨነቅ ባለፈ፣ በፅንፈኛው የትህነግ ቡድን ላይ ሕዝባዊ ተቃውሞ የመቀስቀስ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
ይህንን የተፈናቃዮች እንቅስቃሴ የተመለከተው በማይሓንሴ የሚገኝ የቡድኑ ፖለቲካዊ አመራር፣ ደደቢት ለሚገኘው የአርሚ 42 የመረጃ አመራር “ሓየሎም” አጣዳፊ ጥቆማ አድርሷል።
ይህን ተከተሎ የትህነግ የመረጃ አዛዥ ሓየሎም ያስተላለፈው መመሪያ የቡድኑን ጨካኝ ባህርይ የበለጠ ያጋለጠ ሆኗል። ሓየሎም ባስተላለፈው አቅጣጫ፦ “ቡድኑ የገጠመውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ እየታገለ ባለበት ወቅት፣ እርዳታ ጠባቂው ተፈናቃይ ስርአት ሊይዝ ይገባል” በማለት፣ መሰል የፍትህና የእርዳታ ጥያቄ የሚያነሱ ተፈናቃዮችን “ከለውጥ ኃይሎችና ከመንግሥት ጋር ግንኙነት አላችሁ” በሚል ሀሰተኛ ሽፋን በመስጠት በቁጥጥር ስር እንዲያውሏቸውና እንዲያፍኗቸው ጥብቅ አቅጣጫ ሰጥቷል።
ይህ እንቅስቃሴ የሚያሳየው፣ የትህነግ ቡድን በየግንባሩ እየደረሰበት ካለው ወታደራዊ ሽንፈት በተጨማሪ፣ በገዛ ወገኑ ላይ በሚፈጽመው በደል ሳቢያ ከሕዝብ ተነጥሎ የመጨረሻው የውድቀት ምዕራፍ ላይ መድረሱን ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply