መከላከያ አላማጣን ጨምሮ 13 ስልታዊ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር ታጣቂው በሁሉም ግንባሮች እየተበተነ ነው
አስገራሚ ወታደራዊ ስምምነቶችን በመፍጠርና ንጹሃንን ለጦርነት በመማገድ የሚታወቀው የትህነግ የጥፋት ቡድን፣ በራያ አላማጣ፣ በላሊበላና በተለያዩ የምሥራቅ ግንባሮች በከፈተው ትንኮሳ ታይቶ የማይታወቅ አይቀጡ ቅጣት እንደቀመሰና ፍጹም የመፍረስ አደጋ ላይ መውደቁን የጎልጉል የውስጥ ምንጮች አረጋገጡ።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከተከላካይነት ወደ ማጥቃት በመሸጋገር ባደረገው መብረቃዊ ጉዞ የአላማጣ ከተማን፣ የአላማጣ ወረዳንና ዙሪያውን ጨምሮ 13 ስልታዊ ቀጠናዎችን ሙሉ በሙሉ ነጻ አውጥቷል።
የጎልጉል ምንጮች ከግንባር እንዳረጋገጡት፣ በመከላከያ ኃይለኛ የተጠናከረ ክንድ ሙሉ በሙሉ ነፃ የወጡት 13ቱ አካባቢዎች፦ ዋጃ፣ ጥሙጋ፣ አየር ማረፊያ፣ ቢትሞ፣ ኩቢ ቀረንሳ፣ ኩቢ ድርባ፣ በደና ለኮ፣ ትግሬ መንደር፣ ጉበና መንደር፣ ራያ መንደር፣ ባይባዎ፣ መሓጎ እና ቀይ አፈር ናቸው።
የአመራሩ መፈርጠጥና የሎጂስቲክስ ውድመት
የመከላከያ ሠራዊት ወደ ፊት በከፍተኛ ግስጋሴ መግፋቱን ተከትሎ፣ በአላማጣ የነበሩ የትህነግ ከፍተኛ አመራሮች ወደ ኋላ እየሸሹ መሆኑ ታውቋል። በተለይም የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳዳሪ የነበረው አቶ ዝናቡ ገብረመድህን ከነሙሉ አጃቢዎቹና ተባባሪዎቹ ወደ መቀለ አቅጣጫ መፈርጠጡን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
የትህነግ ታጣቂዎች በሁሉም አቅጣጫ እየተበተኑ ሲሆን፣ የደቡብ ግንባር አዛዥ ጆን መዲድን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አዛዦች “አልቻልንም፤ ሠራዊታችን እየተበተነብን ነው” በማለት ተስፋ መቁረጣቸውን በምሥጢር ግንኙነታቸው መናገራቸው ተሰምቷል።
በሌላ በኩል፣ በአላማጣ ተከማችቶ የነበረው የትህነግ ጉጅሌ ካምፕ እና የጥይትና ተተኳሽ ማከማቻ መጋዘን በኢትዮጵያ አየር ኃይል በተሰነዘረ ድንገተኛ ጥቃት ሙሉ በሙሉ ወድሟል። በተጨማሪም የጥፋት ቡድኑ በደቡብ ግንባርና በዋግኸምራ ዞን ያስቀመጣቸው 5 ታላላቅ መድፎች (በድብርሳኤ 1 መድፍ፣ በ02 ቲያ 2 መድፎች እና በፋጫ 2 መድፎች) በድሮን ጥቃት ተመትተው ከነሜካናይዝድ ኃይላቸው ፍርክስክሳቸው ወጥቷል።







የታጣቂው ማመጽ፦ “አይበቃችሁም ወይ?”
የጎልጉል የውስጥ ምንጮች እንዳመለከቱት፣ በኮሎኔል ልጅዓለም የሚመራው አርሚ 11 ሙሉ በሙሉ በመበተኑ ከፍተኛ ቀውስ ተፈጥሯል። ከፍተኛ የጦር አመራሮች የተበተኑትን የሰቲት ክፍለጦር አባላት በድጋሚ ለማሰባሰብና ወደ ጦርነት ለመክተት ቢሞክሩም፣ ታጣቂዎቹ “እስካሁን አስበላችሁን፣ አይበቃችሁም ወይ?” በማለት በአለቆቻቸው ላይ ቃታ እስከመሳብ የደረሰ ከፍተኛ አመጽ አስነስተዋል።
በተመሳሳይ በራያ አላማጣ ግንባር በትህነግ አርሚ 31 አመራሮች እና አብረዋቸው በነበሩ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል “ጥቃት ሲመጣ ጥላችሁ ትሸሻላችሁ” በሚል እርስ በርስ የመካሰስና የመጋጨት ሁኔታ መፈጠሩ የቡድኑን ማክተም አፋጥኖታል። በአሁኑ ወቅት በአላማጣ፣ በሰቆጣ፣ በላስታ፣ በራያ ዓዘቦና ራያ ጨርጨር፣ በወጀራትና በአብዓላ መስመር የነበሩ ሁሉም አርሚዎች ፈርሰዋል።
በተኩለሽ፣ ድልድይና ላሊበላ ግንባር የደረሰው ምት
በተኩለሽ፣ ድልድይና ቀይ አፈር ግንባር የትህነግ ኃይሎች የከፈቱትን ጥቃት በቀጠናው የሚገኘው የሀገር መከላከያ ኮር በፍጹም ሀገራዊ ጀግንነት መክቶታል። የኮሩ አዛዥ እንደገለጹት፣ የታጣቂው ምኞት የከሸፈ ሲሆን ከመሞትና ከመቁሰል የተረፉት በርካታ ታጣቂዎች “አንዋጋም” በማለት እጃቸውን በሰላም ለመከላከያ እየሰጡ ይገኛሉ።
የቆሰሉት ምርኮኞች በመከላከያ ሠራዊት ሰብዓዊ ሕክምና እየተደረገላቸው ነው። በላሊበላ ግንባርም የተረፉትን አሰባስበው ለመከላከል ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው እየሞቱና እየሸሹ መሆኑ ታውቋል።
የቡድኑ የጭካኔ ማሳያ ንጹሃንን መፍጀት
የመጨረሻ ሽንፈት የገጠመው የትህነግ ስብስብ ከአላማጣ ከተማ ወጥቶ ሲሸሽ፣ የደረሰበትን የሞራል ስብራት ለመበቀል በአላማጣ ወረዳ ጣቢያ 04 ላይ በፈጸመው የመድፍ ድብደባ አንዲት ነፍሰ ጡር እናት በጭካኔ ተገድላለች። ይባስ ብሎም በአላማጣ ከተማ 01 ቀበሌ ውስጥ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ወጣቶች “ትህነግን ደግፋችኋል” በሚል በአሰቃቂ ሁኔታ በቡድኑ ተጨፍጭፈው መጣላቸው ታውቋል።
በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከተማዋንና ዙሪያዋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የመታደግ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply