* የትግራይ ሕዝብ መከላከያ ሠራዊትንና የትግራይ የሰላም ኃይልን ለመቀበል እየተዘጋጀ ነው
በሰሜን ወሎ በኩል ከትህነግ ታጣቂዎች ጋር በጥቅም ተጣጥሞ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፀረ-ሰላም ቡድን፣ ገና ከጅምሩ በደረሰበት የመዋቅር መበታተን እና ሽንፈት ምክንያት በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደሚገኝ ታወቀ።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል እና የሕግ ማስከበር ሥራውን ለማጠናቀቅ ፈጣን እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
ከጎልጉል ከምንጮች በተገኘው መረጃ መሠረት፣ በሰሜን ወሎ ዞን የሚንቀሳቀሰው ፀረ-ሰላም ቡድን ከትህነግ (TPLF) ታጣቂዎች ጋር ተጣጥሞ በግዳን ወረዳ (ሙጃ እና ወንዳች)፣ በላስታ ወረዳ (እንጃፋት)፣ በላሊበላ እና በሹምሽሃ ስፍራዎች ተስፋፍቶ ወደ መቄት እና ጋሸና የማስፋፋት እቅድ ነበረው።
ነገር ግን ግጭቱ በተቀሰቀሰበት የመጀመሪያ ወቅት የትህነግ ታጣቂዎች በመደናገጥ ወደኋላ በመሸሻቸውና በመበታተናቸው ምክንያት የታሰበው እቅድ መክሸፉን የቡድኑ አመራሮች ገልጸዋል። በሁኔታው የተበሳጩት የቡድኑ አመራሮች “ህወሓት ጉድ ሠራን” በማለት የምሬት አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የፋኖው ቡድን በደረሰበት ሙሉ ወታደራዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጫና ጫና ምክንያት በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደሚገኝ ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል፣ የመከላከያ ሠራዊት የሚያደርገው ፈጣን ግስጋሴ ተጠናክሮ በቀጠለበት ሁኔታ፣ የትግራይ ሕዝብ በአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ ከመንግሥት እና ከተቋቋመው የትግራይ የሰላም ኃይል ጎን በመሰለፍ ሠራዊቱን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
ጎልጉል ከትግራይ አንዳንድ አካባዎች ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ሕዝቡ በአሁኑ ሰዓት መከላከያ መቼ ነው የሚመጣው፤ መቼ ነው ልጆቻችንን የሚታደግልን፤ መቼ ነው የትግራይ የሰላም ኃይሎች ወደ ትግራይ ገብተው የመረጋጋት ሥራ የሚሠሩት፤ መቼ ነው ከትህነግ ግፈኛና ጨቋኝ ሥርዓት ነጻ የምንወጣው በማለት በከፍተኛ ተነሳሽነት እየጠበቀ መሆኑን መረጃው ይጠቁማል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply