በትህነግ (ህወሓት) ከፍተኛ አመራር፣ በበታች መኮንኖችና በተራው ታጣቂ መካከል የተፈጠረው እምነት ማጣትና የርስ በርስ መቧጨቅ፣ ድርጅቱን ከባድና የለየለት የውስጥ ትርምስ ውስጥ እንደከተተው ታማኝ ምንጮች አረጋገጡ።
ጎልጉል ባገኘው አስተማማኝ መረጃ መሠረት፣ ትህነግ ለበርካታ ዓመታት እዋጋበታለሁ ብሎ የተማመነበት ታጣቂ ኃይል ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መበታተኑ በአመራሩ ዘንድ ትልቅ ድንጋጤን ፈጥሯል። በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ አመራሩና በታጣቂው መካከል አንዱ ሌላኛውን ለሽንፈት ተጠያቂ የማድረግና አልፎ ተርፎም እርስ በርስ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ የመታቀድ ሒደት ላይ መሆኑ ታውቋል።
ከውስጥ አዋቂ ምንጮች የተገኘው ዝርዝር መረጃየ ውጥረቱን መነሻና መዳረሻ እንደሚከተለው ያሳያል፦
“ማንን ተማምነን ቅርቃር ውስጥ ገባን?” — የከፍተኛ አመራሩ ስጋትና የተደገሰው የርሸና ሴራ
በከፍተኛ አመራሩ ደረጃ በተደረገ ግምገማ፣ ታጣቂውናየበታች አመራሩ የሞራልና የመዋጋት ፍላጎት ሙሉ በሙሉ እንደሌላቸው ተገልጿል። ታጣቂው በቀላሉ መሣሪያ ጥሎ የሚፈረጥጥ፣ ትእዛዝ የማይሰማ እና ስለ ሕይወቱ መትረፍ ብቻ የሚጨነቅ መሆኑ ተጠቅሷል።
እንዲያውም በተደጋጋሚ ለአመራሩ “እራሳችሁ ግቡና ተዋጉ” የሚል የድፍረት መልስ እየሰጠ መሆኑ ለአመራሩ ትልቅ ራስ ምታት ሆኗል።
በዚህም የተነሳ “ማንን ተማምነን ነው እዚህ ቅርቃር ውስጥ የገባነው?” በሚል ከፍተኛ ስጋት ላይ የወደቁት የትህነግ አመራሮች፣ ታጣቂውና የበታች አመራሩ ያምፁብናል በሚል ስጋት የኤርትራ ገዳይ ስኳድ (Hit Squad) ወደ ትግራይ ክልል ማስገባቸው ታውቋል። ይህ የገዳይ ቡድን መሣሪያ ጥሎ የሸሸውንና ትእዛዝ ያላከበረውን ታጣቂ ከጀርባ ሆኖ እንዲረሽን ዝግጅቱ መጠናቀቁን የጎልጉል ምንጮች አረጋግጠዋል።












“ምላጫችንን በአመራሩና በኤርትራ ላይ እንስባለን” —የታጣቂው ቁጣና ክህደት
በሌላ በኩል ታጣቂውና የበታች አመራሩ ከፍተኛውን አመራር “የመምራት ሞራልና ችሎታ የሌለው ፈሪ” ሲሉ ይወርፉታል። አመራሩ በተሳሳተ ውሳኔና በስሜት ተገፋፍቶ ታጣቂውን ለእልቂት እንደዳረገ፣ እሱ ግን የራሱን ምቾት ብቻ እያየ በታጣቂው ደም ሕይወቱን ማሰንበት እንደሚፈልግ እየተናገሩ ይገኛሉ።
“ለማን ብለን ዋጋ እንከፍላለን?” በሚል ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የገባው አብዛኛው ታጣቂ መሣሪያውን እየጣለ ወደ ቤተሰቦቹ፣ እድሉን ያገኘው ደግሞ ወደ መከላከያ ሠራዊትና ወደ ሰላም ኃይሉ እየተቀላቀለ መሆኑ ታውቋል። ከዚህም በላይ በትህነግ አመራርና በኤርትራ ገዳይ ስኳድ የተደገሰላቸውን የጀርባ ርሸና ሴራ የተረዱ በርካታታጣቂዎች፣ “አፈሙዛችንንና ምላጫችንን ወደ አመራሩና ወደ ገዳዩ ቡድን እናዞራለን” በማለት ከባድ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ተሰምቷል።
ይህ በትህነግ መዋቅር ውስጥ የተፈጠረው ከፍተኛ የውስጥ መከፋፈልና እርስ በርስ የመጠፋፋት ስጋት፣ የድርጅቱን የቁልቁለት ጉዞ ይበልጥ እያፋጠነው እንደሚገኝ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply