
በ1930ዎቹ የጀርመን ወግ አጥባቂ ልሒቃን በሀገራቸው እያቆጠቆጠ ያለው ኮሙኒዝም አስፈራቸውና አንድ “መላ” ዘየዱ። በሕዝብ ዘንድ ዝና እያገኘ የመጣውን አዶልፍ ሒትለርን ወደ ሥልጣን ማምጣትና ኮሙኒዝምን ድባቅ መምታት። ውሳኔ ተላለፈ፤ ሒትለርም የፓርቲው ካዝና፣ ቁልፍ፣ ወንበር፣ … ሁሉም ተሰጠው። አጅሬውም ወዲያውኑ የራሱን መስተጋብር በመፍጠር ያበላውን ፓርቲ መልሶ መውጋት ጀመረ። የናትዚው “አውሬ” ሒትለር የዴሞክራሲ መዋቅሮችን አፈራረሰ፣ የተቃዋሚ እንቅስቃሴዎችን አገደ፣ የቀድሞ አጋሮቹን በሙሉ አጸዳና ሥልጣኑን በኪሱ አስገባ። ነፍሰበላ አውሬ እየቀለቡ መሆናቸውን ያልተገነዘቡት ወግ አጥባቂዎቹ ባሳደጉት “ውሻ” ተበሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ሒትለር እየተቀለቡ ያሉና አንድ ቀን ሊበሉን ያሰፈሰፉ፤ የበሉበትን ወጭት ሰባሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ያበላቸውን የሚበሉ ወይም ሊበሉ እያደቡ ያሉ ጥቂት አይደሉም። ከነዚህ መካከል ዋነኛ ተጠቃሹ አማረ አረጋዊና አጀንዳ ተካዩ ሚዲያው “ሪፖርተር” ነው። ለዚህም በጣም ጥቂት የቅርብ ጊዜ ሦስት ማሳያዎችን እንጥቀስና በማስከተልም ሰሞኑን ከወልቃይት ጋር በተያያዘ የተናፈሰውን ዋና መረጃ እናቅርብ።
ሪፖርተር የፓርላማ ወንበር አስልቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፓርላማ እንዳይደገፍ ያደረገው
የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ የትህነግ ልዩ ዓላማ እየተተገበረ ያለበትን የአማራ ክልል ቀውስ ለማስታገስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ የድምጽ ስሌት አቅርቦ የአማራ ብልጽግና ከዋናው ብልጽግና የተለየ አቋም እንዲይዝ የቢሆን ስሌትና ምኞት ያለበት ዜና አሰራጭቶ ነበር። አብንና ኢዜማንም በዚህ ስሌት ውስጥ ደምሯቸው ነበር።
“… በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክር ቤቱ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማፅደቅ ይኖርበታል” በሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊፀና የሚችለው ከአጠቃላይ የምክር ቤቱ አባላት ማለትም በስድስተኛው ዙር ተመርጠው በምክር ቤቱ መቀመጫ ከያዙት 427 ተወካዮች መካከል 285 የሚሆኑት የድጋፍ ድምፅ ከሰጡ ነው። ከተጠቀሱት 427 ተመራጮች ውስጥ 142 የምክር ቤት አባላት የተቃውሞ ድምፅ ከሰጡ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀሪ ሊሆን ይችላል” ይላል ስሌቱን አመላክቶ ሪፖርተር ምን ያህል ድጋፍ ቢያገኝ አዋጁ ውድቅ ሊደረግ እንደሚችል ባመላከተበት ዜና።
ሪፖርተር አክሎም “በምክር ቤቱ ወንበር ካገኙ አጠቃላይ 427 አባላት ወስጥ 410 የሚሆኑት በብልፅግና ፓርቲ አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 125 ያህሉ በአማራ ብልፅግና ፓርቲ አቅራቢነት የተወዳደሩና የክልሉን ሕዝብ የሚወክሉ ናቸው” ሲል አማራ ብልጽግናን ከዋና አገራዊ ፓርቲ ብልጽግና የተገነጠለ አድርጎ ዘራቸውን ቆጥረው ምርጫውን እንዲያሰሉ አቅጣጫ አሳይቷል።
አጀንዳ ተካዩ ሪፖርተር ሲቀጥልም፤ “ከብልፅግና ፓርቲ ውጪ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ አምስት የሕዝብ ተወካዮች ሲኖሩ፣ በኢዜማ አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ ሌሎች አራት የሕዝብ ተወካዮች እንደሚገኙም ይታወቃል” ሲል ከአማራ ብልጽግና ወኪሎች ጋር ሊዳመሩ እንደሚችል በዜና መልክ “ተባበሩ” ብሏል። በሌላ አነጋገር ተባበሩና የትህነግን ዓላማ አሳኩ በማለት የአማራ ክልል በጥብጥ ዋናው ባለቤት ማን እንደሆነ አሳብቋል።
ነገርግን በሪፖርተር ላይ የተወሰደ ምንም እርምጃ የለም።
ሪፖርተር፡ “መንግሥት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረው አንድ ትሪሊዮን ዕዳ እንዳለበት ተገለጸ” በማለት የዘገበው
መጋቢት 28 ቀን 2017ዓም የታተመው የሪፖርተር ጋዜጣ በፊት ገጹ በገዢ ዜናነት ያወጣው መረጃ ከላይ በርዕሱ የተጠቀሰው ነበር። ይህንን በአገር ኢኮኖሚ፣ በዋጋ መረጋጋት፣ በፋይናንስና ባንክ አሠራር፣ ወዘተ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያመጣ የሐሰት መረጃ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአጽዕኖት በመቃወም “የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመንግሥት አንድም ብር አበድሮ አያውቅም!” በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ምላሽ ሰጥቷል። መግለጫውን እዚህ ላይ ማንበብ ይቻላል።

የባንኩ መግለጫ ሲያጠቃልል ይህንን ብሎ ነበር፤ “በመጨረሻም ባንካችን ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው በግልጽ ካቀረበው እውነታ ባፈነገጠና በተዛባ መልኩ የሪፖርተር ጋዜጣ በዜና አርዕስቱ “መንግሥት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረው አንድ ትሪሊዮን ዕዳ እንዳለበት ተገለጸ” በሚል እንዲሁም በሌሎች ጥቂት ሚዲያዎችም የመንግሥት ዕዳ ብር 1.3 ትሪሊዮን እንደተሻገረና አሁናዊ የመንግሥት የብድር ዕዳ ዕድገትን የሚያሳይ በሚመስል መልኩ ተቀናብሮ የቀረበው ዘገባ ሀሰተኛ ከመሆኑም ባሻገር ከላይ በዝርዝር በተመላከቱት እውነተኛ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ በባንካችን በኩል የቀረበውን ትክክለኛ ሪፖርት የማያንጸባርቅ እና እነዚህን ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተሰጡትን ብድር ለባንካችን ለመክፈል መንግሥት እያደረገ ያለውን ቁርጠኝነት ታሳቢ ያላደረገ በመሆኑ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሚዲያዎች የተላለፈው የተዛባና የተሳሳተ ዘገባ እንዲታረም እናሳስባለን”።
ነገርግን በሪፖርተር ላይ የተወሰደ ምንም እርምጃ የለም።
ሦስተኛው ሪፖርተር ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በኃላፊነት የተጠየቀበት ነው፤
አዲስ አበባ አስተዳደር የሪፖርተርን የተዛባ መረጃ ኮነነ፤ ሕጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ አለ
የአማረ አረጋዊ ሪፖርተር፤ የአንድ ትሪሊዮን ሐሰተኛ ዕዳ ዘገባ ባወጣ በማግስቱ ሌላ ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በኃላፊነት ተጠይቆ ነበር። ይህንን የጠየቀው የአዲስ አበባ አስተዳደር ሲሆን ሰኞ መጋቢት 29/ 2017 ዓ.ም “የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የኑሮ ውድነቱ አናታቸው ላይ ወጥቷል” በሚል ርዕስ ሪፖርተር ያወጣውን የአጀንዳ መትከያ መረጃ በመቃወም ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት በመጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም “በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤና ተሳትፎ ማሳደግን” አላማው ያደረገ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። መድረኩ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካም በዕለቱ የውይይት መድረኩን እንዲዘግቡ በጽ/ቤቱ ከተጠሩት ከ15 በላይ የሚሆኑ የመደበኛና የዲጂታል ሚዲያዎች ተገኝተው ዘገባቸውን ማሰራጨታቸው የገለጸው የምክር ቤቱ መግለጫ 14ቱ የተነገረውን ሲዘግቡ ሪፖርተር ግን ዓላማ አድርጎ የያዘውን አጀንዳ የመትከል ዘገባውን አሰራጭቷል። ምክር ቤቱ በወቅቱ ያወጣው መግለጫ እዚህ ላይ ይገኛል።

በመጨረሻም ጽ/ቤቱ “ሪፖርተር ጋዜጣ ይህንኑ በአስቸኳይ እንዲያርምና ማስተባበያ እንዲያወጣ እያሳሰብን ይህ ካልሆነ ግን ጽ/ቤታችን ሕጋዊና አስተዳደራዊ መንገዶችን በመከተል ተጠያቂነትን እንደሚያረጋግጥ በጥብቅ እናሳውቃለን” ብሏል።
ነገርግን በሪፖርተር ላይ የተወሰደ ምንም እርምጃ የለም።
ወደሰሞኑ የሪፖርተር የአጀንዳ ተከላ እንሂድ …፤
ከወልቃይት “አስተዳደር መፍረስ” ዜና ጀርባ ያለው የሪፖርተር የሤራ ፖለቲካ
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ጉዳይ እጅግ ስሱና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ አገራዊ አጀንዳ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን፣ በተለይም በሪፖርተር ጋዜጣ አማካኝነት የሚሰራጩ ዘገባዎች በአካባቢው የተጀመረውን አንጻራዊ ሰላምና የተፈናቃዮችን የመመለስ ተስፋ አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው። እነዚህ መረጃዎች ከተራ የጋዜጠኝነት ስህተትነት ባለፈ በትህነግ ፊት አውራሪነት በተለያዩ የፖለቲካ ተዋናዮችና የታጣቂ አመራሮች የተቀነባበሩ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች አካል መሆናቸው ለመረዳት ጠንቋይ ቀላቢ መሆን አይጠብቅም።
ከነዚህ መረጃዎች መካከል ሪፖርተር ጋዜጣ ከጥቂት ቀናት በፊት የአሜሪካ አምባሳደር ወደ ወልቃይት በመሄድ ጉብኝት አድርገው ከተመልሱ በኋላ “የወልቃይት አስተዳደር እንደሚፈርስ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የምስራቅ አፍሪካ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ” በማለት የዘገበው ይገኝበታል። ይህ ዘገባ በዋናነት በፌደራል መንግሥቱና በአካባቢው አስተዳደር መካከል የጥርጣሬና ያለመተማመን መንፈስ ለመዝራት የታለመ ነው። በተለይም ከፍተኛ የመንግሥት የኃላፊነት ቦታ ያላቸውን ግለሰቦች ንግግር ከዐውዱ ውጭ በመጥቀስና ቦታና ጊዜን በመቀየር የሚቀርቡ ዘገባዎች፣ ሕዝቡንና የጸጥታ መዋቅሩን ለከፋ የስነ ልቦና ጉዳት የሚዳርጉ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ ስልታዊ የመረጃ ማዛባት ዓላማው በአካባቢው የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ከሕዝቡ መነጠልና ለዳግም ወታደራዊ ትንኮሳ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መሆኑን መረዳት ይቻላል።
የመረጃ ግራ መጋባትን እንደ ስትራቴጂ
በሪፖርተር ዘገባ ላይ አቶ ጌታቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ተደርገው መጠቀሳቸው የንግግሩን ሚዛን ከክልላዊ ጉዳይ ወደ ፌደራል ውሳኔ ከፍ ያደርገዋል። ይህ ስያሜ ንግግሩን “የመንግሥት የመጨረሻ ዓቋም” አስመስሎ በማቅረብ፣ በአማራ ክልል ሕዝብና አመራር ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና ስጋት እንዲሁም የክህደት ስሜት (Sense of Betrayal) እንዲነግሥ በማድረግ፣ ሕዝቡ በፌደራል መንግሥቱ ላይ ያለው አመኔታ እንዲሸረሸርና በመካከላቸው የጥቅም መጋጨት እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ያመቻቻል።
ከዚህም በላይ፣ ሪፖርተር የአቶ ጌታቸውን የድምፅ ቅንጫቢ ቦታ ለይቶ ሳይጠቅስ ማሰማቱ፣ መረጃው ለማንኛውም አወዛጋቢ ጉዳይ ሊሰራ እንደሚችል በማስመሰል ከፍተኛ የትርክት ብዥታ ይፈጥራል። ይህ ደግሞ በአካባቢው የሚገኘውን አመራርና የጸጥታ መዋቅር ለተሳሳተ እርምጃና ለከረረ ምላሽ በመገፋፋት፣ በክልሉና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት ለማበላሸት ሆን ተብሎ የተነደፈ የስነ-ልቦና ጦርነት ስልት ነው።
መከላከያ ሠራዊቱንና ሕዝቡን መነጠል
የጄነራል ምግበይ ወታደራዊ ዝግጅት እና የ”ሪፖርተር” ጋዜጣ ዘገባ በአንድ ወቅት መገጣጠማቸው እንደ ድንገት የሚታይ ሳይሆን፣ የተቀናጀ የስነ-ልቦና ጦርነት (PSYWAR/PSYOP) አካል መሆኑን ያሳያል። ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ ከመጀመሩ በፊት የጠላትን የውስጥ አንድነት ማዳከም የጦርነት ስልት ነው። በዚህ ረገድ፣ “አስተዳደሩ ሊፈርስ ነው” የሚለው ወሬ ሆን ተብሎ እንዲሰራጭ የተደረገው፣ በአካባቢው ባለው የጸጥታ መዋቅርና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የእርስ በርስ መጠራጠርን ለመዝራት ያለመ ነው። ይህ ስሌት ሠራዊቱና የአካባቢው ታጣቂዎች እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩ በማድረግ፣ የጋራ ጠላታቸውን በአንድነት ለመከላከል ያላቸውን አቅምና ዝግጁነት እንዲላላ ያደርገዋል። በሕዝቡ ዘንድ ደግሞ “መከላከያ ሠራዊቱ እኛን ጥሎ ሊወጣ ነው ወይም አሳልፎ ሊሰጠን ነው” የሚል ስጋት እንዲነግስ በማድረግ፣ ሕዝቡ በሠራዊቱ ላይ ተቃውሞ እንዲያነሳና ድጋፉን እንዲነፍግ ይገፋፋዋል። ይህ የሕዝብና የሠራዊት መለያየት (Decoupling)፣ ሠራዊቱ ያለ ሕዝብ ድጋፍ እንዲቀርና ለጥቃት ተጋላጭ እንዲሆን ያደርገዋል።
ይህ ሤራ የመጨረሻ ግቡ የእርስ በእርስ ግጭት መፍጠር ነው። በሕዝቡ ዘንድ የሚፈጠረው የ”ተከዳን” ስሜት ወደ ዓመፅ ካመራ፣ ሠራዊቱ ሰላም ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከሕዝቡ ጋር እንዲጋጭ በማድረግ በትግራይና በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች ትርምስ መፍጠር ይፈለጋል። እንዲህ ያለው ትርምስ ደግሞ ለጄነራል ምግበይና ለሚመራው ታጣቂ ኃይል “ወደ አካባቢው በኃይል ለመግባት” ወርቃማ አጋጣሚን ይፈጥርለታል። ሠራዊቱ የውስጥ አመጽን ለመቆጣጠር በሚወጠርበት ወቅት፣ ውጫዊ ጥቃትን የመከላከል አቅሙ ስለሚቀንስ ሤራው ወታደራዊ ድልን በትንሽ መስዋዕትነት ለመቀዳጀት የታለመ መሆኑን ያሳያል።
የአምባሳደሩን ጉብኝት ለፖለቲካ ትርፍ ማዋል
የአሜሪካው አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ያደረጉት ጉብኝትና በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሰጡት አስተያየት፣ ሆን ተብሎ አውዱን በሳተ መልኩ ለፖለቲካ ትርፍ እንዲውል ተደርጓል። አምባሳደሩ “ሰውነት ይቀደም” በሚል መሪ ቃል ያስተላለፉት መልዕክት፣ በመከራ ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮችን ሰብዓዊ መብት ማክበርና ወደ ቀዬያቸው መመለስ ላይ ያተኮረ እንጂ ስለ አካባቢው አስተዳደራዊ መዋቅር መፍረስ ወይም መለወጥ የተናገሩት አንዳችም ይፋዊ ቃል አልነበረም። ሆኖም የትህነግ ደጋፊ ሚዲያዎችና “ሪፖርተር” ጋዜጣ ይህን ሰብዓዊ ጥሪ በማጣመም፣ አምባሳደሩ የአሁኑን አስተዳደር መፍረስ የደገፉ አስመስለው ማቅረባቸው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እንደ ፖለቲካዊ ሽፋን የመጠቀም ፍላጎታቸውን ያሳያል።
ይህ ስልታዊ የመረጃ ማዛባት ዋና ግቡ፣ የትህነግን ወታደራዊ ፍላጎት በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ድጋፍ የታጀበ ለማስመስል መሞከር ነው። አምባሳደሩ ያልተናገሩትን አጀንዳ አያይዞ ማቅረብ፣ በአካባቢው ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም ወታደራዊ ትንኮሳ “ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያለው ህጋዊ እርምጃ” ለማስመስል የሚደረግ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው። በዚህም የትግራይ ታጣቂዎች ወደ አካባቢው ለመግባት ለሚያደርጉት ዝግጅት ሞራላዊና ፖለቲካዊ ቅቡልነትን ለመፍጠር ሞክረዋል።
በተጨማሪም፣ ይህ አካሄድ በአካባቢው አስተዳደርና በሕዝቡ ላይ “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አግልሎናል” የሚል የተሳሳተ ስሜት በመፍጠር የስነ-ልቦና ጫና ለማሳደር የታለመ የዲፕሎማሲ ሤራ ነው። አምባሳደሩ ከአካባቢው አመራሮች ጋር በነበራቸው ቆይታ የነበረውን የመግባባት መንፈስ ወደ ጎን በመተው፣ አስተዳደሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንደሌለውና መፍረስ እንዳለበት አምባሳደሩ እንደጠቆሙ ተደርጎ መዘገቡ፣ በአካባቢው አመራሮች ላይ የብቸኝነትና የከበባ ስሜት (Siege Mentality) ለመፍጠር የተወጠነ ነው።
ፋኖንና የሌሎች ኃይሎችን ወደ ሰላም መምጣት ማደናቀፍ
በቅርቡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የፋኖና የኦነግ ሸኔ አመራሮች እንዲሁም ሰፊ ቁጥር ያለው ሠራዊት የትጥቅ ትግሉን ትተው ወደ ሰላማዊ መንገድ መመለሳቸው፣ ለሻዕቢያና ትህነግ የፖለቲካና የወታደራዊ ስትራቴጂ ትልቅ ስጋት ደቅኗል። ይህ በሀገሪቱ እየታየ ያለው የሰላም ፍንጭና የኃይሎች ወደ ማዕከላዊ መንግሥቱ መጠጋት፣ ትህነግ ለብቻው ተነጥሎ እንዲቀርና ለሚቀጥለው ዙር የጦርነት ዕቅዱ የሚሆን የአጋር ኃይል እንዲያጣ ያደርገዋል። በመሆኑም፣ ይህንን የሰላም ሂደት ለማኮላሸት “መንግሥት ወልቃይትን ለትህነግ አሳልፎ ሊሰጥ ነው” የሚል እጅግ ስሜት ቀስቃሽና የሃሰት ትርክት በማሰራጨት፣ ወደ ሰላም እየመጡ ያሉ ኃይሎች በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት እንዲናጋ ማድረግ የሤራው ዋነኛ ግብ ነው።
ይህ ትርክት በተለይ በፋኖ አመራሮች ዘንድ “መንግሥት ከጀርባ ከትህነግ ጋር ተደራድሮ መሬታችንን ሊሸጥ ነው” የሚል የክህደት ስሜት እንዲፈጠር በማድረግ፣ የጀመሩትን የሰላም መንገድ አቋርጠው ወደ ጫካ እንዲመለሱ ይገፋፋቸዋል። “መንግሥት ከዳን” የሚለው የስነ-ልቦና ጫና፣ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን እንዳይፈቱና ዳግም ወደ ጦርነት አዙሪት እንዲገቡ በማድረግ ሀገሪቱ በቋሚ ትርምስ ውስጥ እንድትቆይ ይፈልጋል። እንዲህ ያለው አለመረጋጋት ደግሞ ትህነግ ለሚያቅደው አዲስ ግንባር ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል፤ ምክንያቱም መንግሥት በሌሎች አካባቢዎች በሚነሱ ግጭቶች ሲወጠር፣ ትህነግ ወልቃይትን በኃይል ለመያዝ የሚያደርገው ጥረት ተቃውሞ አይገጥመውም የሚል ስሌት ስላለው ነው።
ከዚህም በላይ፣ ይህ ሤራ ትህነግ የሚከፍተውን አዲስ ጦርነት ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር ለማቀናጀትና የጋራ ግንባር ለመፍጠር የሚጠቀምበት ስልት ነው። የሰላም ሂደቱን በማደናቀፍ ታጣቂዎች ከመንግሥት ጋር እንዲጋጩ ማድረግ፣ በተዘዋዋሪ ታጣቂዎቹ ከትህነግ ጋር እንዲተባበሩ ወይም ቢያንስ ለመንግሥት እንቅፋት እንዲሆኑ በር ይከፍታል። ሪፖርተርና መሰል ሚዲያዎች ይህንን “የአስተዳደር መፍረስ” ዜና ሲያመርቱ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎች ወደ ሰላም መመለሳቸውን ችላ ማለታቸው፣ የሤራው ዓላማ ሰላምን ማደብዘዝ እና ጦርነትን በናፋቂ ኃይሎች መካከል አዲስ የትብብር መድረክ መፍጠር መሆኑን በግልጽ ያሳያል።
“አውሬውን” 30 ዓመት ለምን እንመግባለን?
ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርነው ሪፖርተር አጀንዳ ተካይ ሚዲያ ነው። ሚዲያው አፍቃሪ ትህነግ ብቻ ሳይሆን ባለቤቱ አማረ አረጋዊ በራሱ አንደበት ሲናገር እንደሚደመጠው ትህነግ ለዘላለም እንዲኖር የሚፈልግ፣ ተግቶም የሚሠራ ግለሰብ ነው። ይህንንም በ1997ቱ ምርጫ ወቅት በግልፅ አሳይቷል። እንደሚዲያ ተገቢውን የሙያ ሥራ ከመሥራት ይልቅ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ከትህነግ በላይ መመሪያና ትዕዛዝ ሲሰጥ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።
ላለፉት 30 ዓመታት በነጻ ሚዲያ ስም በቀዳሚነት ሀገርን የማፍረስ ሥራ የሚሠራ ሚዲያ ማነው ተብሎ ቢጠየቅ ሪፖርተር በአውራነት የሚጠቀስ ነው፤ ሌሎችም አሉ። በፕሬስ ነጻነት ስም በመቆመር የሀገርን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ የሚዲያ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ መንግሥት ጥብቅ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል። ነጻነት ኃላፊነትን እንደሚጠይቅ ሁሉ፣ የሕዝብን ስነ-ልቦና የሚሰባብሩና ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ የተዛቡ ዘገባዎችን የሚያሰራጩ አካላት በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበት አግባብ ሊመቻች ይገባል። የሚዲያ ተቋማት የሰላም ግንባታ አካል መሆን ሲገባቸው፣ የጦርነት አጋፋሪና የሤራ ጠማቂ ሆነው ሲገኙ መንግሥት ብሔራዊ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ሲባል ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ መነሳት የሚገባው ዐቢይ ጉዳይ ሪፖርተር ይህንን ሁሉ የሚያደርገው በሀገር ሃብት መሆኑ ነው። የሪፖርተር ጋዜጣን ገለጥ አድርጎ የተመለከተ ሰው የሚያገኘው አጀንዳና ፕሮፓጋንዳ ብቻ ሳይሆን እጅግ በርካታ ማስታወቂያዎችን ነው። ማስታወቂያ ከፋዮቹ ደግሞ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚባሉት ናቸው። “ምስጋና ለታማኝ ከፋዮቹ ይሁንና” ከጨረታና ሌሎች ማስታወቂዎች ሌላ በክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያዎች ጭምር የትህነጉ አማረ አረጋዊ ኪስ ካበጠ በጣም ቆየ። መረሳት የሌለበት ግን ትህነግ ሀገራችንን ወደ ጦርነት በከተታት ወቅት ሪፖርተር በአፋርና አማራ ክልል በትህነግ የደረሱትን የግፍ ጭፍጨፋዎችና ውድመቶች ከመዘገብ ይልቅ ትህነግ እንዴት ጦርነቱን አሸንፎ ወደ አራት ኪሎ እንደሚገባ አቅጣጫ የሚሰጡ ዘገባዎችን ሲያጠናክር የነበረ መሆኑ ነው። በዚህ ላይ ሌላው መዘንጋት የሌለበት የሪፖርተር አሠራር በአማርኛ አንድ አጀንዳ የያዘ ዘገባ ካወጣ በኋላ በእንግሊዝኛው ሪፖርተር ወይም በቲቪ/ዩትዩብ ዜና ደግሞ ሌላ ዓይነት የማደናገሪያ ዘገባ የማውጣቱ ጉዳይ ነው – የአጀንዳ ሸማው እንደሚፈለገው ለሚፈለገው ወገን ይዘጋጅለታል።
“አውሬው” ለ30 ዓመት ሲቀለብ ኖሯል። አሁንም የበቃው አይመስልም። ከዚሁ ከ30 ዓመቱ ጋር በተያያዘ እየሰበሰበ ያለውንና የከፋዮቹን ማንነት ለውሳኔ የሚጠቅም ከሆነ እንጠቁም። የፕላቲኒየም፣ የወርቅ፣ የብር ስፖንሰሮች በማለት ከሚያቆለጳጵሳቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና መ/ቤቶች መካከል ጥቂቶቹ፤ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጠቃሾች ናቸው።
ወግ አጥባቂዎቹ የጀርመን ልሒቃን ኮሙኒዝምን እንከላከላለን ብለው ነበር ሒትለርን ሲያደልቡ የነበረው። የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ልክ ለብሔራዊ ደኅንነት አደጋ የሆነን እንደ ሪፖርተር ያለ በ“ሚዲያ” ስም ሀገርን አደጋ ላይ ለመጣል ቀን ተሌት ራሱን እያደለበ ለሚገኝ “አውሬ” በራሱ ሕዝብ ገንዘብ ለምን እንደሚቀልብ ብዙም ግልጽ አይደለም። አያውቅም እንዳይባል እኛ እዚህ ዘገባ ላይ ካቀረብነው እጅግ በጣም ጥቂት ከሆነው መረጃ በላይ ስለ ሪፖርተር በቂ ክምችት አለው። ይህንንም ጠቅላዩ የዛሬ ዓመት አካባቢ ከሚዲያ ሰዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ጠቅሰው ነበር። በወቅቱ ሪፖርተርን ወክሎ ስብሰባው ላይ ለተገኘው ሰው ያሉትም፤ “የማናውቅ እንዳይመስለው፤ ሰውየውን ምከሩት፣ ንገሩት” ነበር ያሉት።
ታዋቂው የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ሞሼ ዳያን በተናገሩት አባባል እናብቃ፤ “አሜሪካውያን ወዳጆቻችን ገንዘብ፣ ጦር መሣሪያና ምክር ሰጡን፤ ገንዘቡን ወሰድን፣ የጦር መሣሪያውን ወሰድን፤ ምክሩን ግን አልተቀበልንም”።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ


Leave a Reply