
ሪፖርተር በሌላ ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በኃላፊነት ተጠየቀ፤ ይህንን የጠየቀው የአዲስ አበባ አስተዳደር ሲሆን ሪፖርተር መረጃውን ካላስተካከለ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል። መግለጫው ከዚህ በታች ይገኛል:-
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ፣
የተዛባና ሚዛናዊነት የጎደለው መረጃን ግልፅ ስለማድረግ፣
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት በመጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም “በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤና ተሳትፎ ማሳደግን” አላማው ያደረገ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ ይታወሳል። መድረኩ የታለመለትን አላማ እንዲያሳካም በእለቱ የውይይት መድረኩን እንዲዘግቡ በጽ/ ቤታችን ከተጠሩት ከ15 በላይ የሚሆኑ የመደበኛና የዲጂታል ሚዲያዎች ተገኝተው ዘገባቸውን አሰራጭተዋዋል።
ተቋማችን ከመድረኩ መጠናቀቅ በሁዋላ ባካሄደው የሚዲያ ዳሰሳና ቅኝት ላይ ግን ሪፖርተር ጋዜጣ በትናንትናው እለት ሰኞ መጋቢት 29/ 2017 ዓ.ም “የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የኑሮ ውድነቱ አናታቸው ላይ ወጥቷል” የሚል ርአስ የያዘ ዘገባ ማውጣቱን ተመልክተናል።
በመሠረቱ በጽ/ ቤታችን በተጠራው መድረክ ላይ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የመወያያ ርእሰ ጉዳዪ ” የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ላይ የህዝብ ተሳትፎን ማሳደግ” እንጅ የንግድ አሊያም የገቢ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ አልነበረም።
ሆኖም ግን በወቅቱ በመድረኩ ላይ ከተሳተፉት ከ200 በላይ ታዳሚዎች በርካቶች መድረኩ የተዘጋጀበትን ርእሰ ጉዳይ መሠረት በማድረግ ሃሳባቸውን እና አስተያዬታቸውን በነፃነት ያንሸራሸሩበት ሁኔታ ተስተውሏል።
ይሁንና በወቅቱ በመድረኩ ላይ ተገኝቶ ዘገባውን ያወጣው ሪፖርተር ጋዜጠኛ ከመድረኩ አውድ ውጭ በርእሰጉዳይነት ያልተካተ፣ የመድረኩን ሙሉ ስእል የማያሳይ፣ ቁንፅል፣ ስሜት ቀስቃሽ፣ ተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ እና ከጋዜጠኝነት የሙያ ስነምግባር ያፈነገጠ ዘገባ ማሰራጨቱ ተቋማችን በህዝብ ዘንድ ያለውን አመኔታ ሆን ተብሎ ለማሳጣት የተፈፀመ እኩይ ተግባር መሆኑን ተገንዝበናል።
በተለይም ደግሞ የሪፖርተር ጋዜጣ ዋነኛ የዜና ርእስ የሆነው አስተያዬት የዜናው ቀዳሚ ርእስ (Headline) በማድረግ ማውጣቱ ስሜታዊነት የተንፀባረቀበት፣ ሃላፊነት የጎደለው እና በምንም አይነት መስፈርት ተቀባይነት የሌለው እንዲሁም የጽ/ቤታችን የህዝብ ቅቡልነትና ተአማኒነት ሆን ተብሎ ለመሸርሸር የተፈፀመ በመሆኑ ሪፖርተር ጋዜጣ ይህንኑ በአስቸኳይ እንዲያርምና ማስተባበያ እንዲያወጣ እያሳሰብን ይህ ካልሆነ ግን ጽ/ቤታችን ህጋዊና አስተዳደራዊ መንገዶችን በመከተል ተጠያቂነትን እንደሚያረጋግጥ በጥብቅ እናሳውቃለን ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply