
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “አሉኝ” የሚላቸውን መረጃዎች የሚያሰራጭበት ሚዲያ በመኖርና በመጥፋት መካከል እንደሆነ ጠቅሶ የተለያዩ አማራጮችን ሲያቀርብ የነበረው ኤሊያስ መሠረት በተቃውሞ ሽፋን ለብልጽግና እየሠራ እንደሆነ መቅመጫቸውን ኬኒያ ያደረጉ ክፍሎች ገልጸዋል። በአገር ቤት ያሉና ይህንኑ ዜና የሚደግፉ ተጨማሪ ማስረጃዎችን በመገጣጠም ዜናውን አጉልተዋል።
ኤሊያስ መሠረት በተቃውሞ ሽፋን ለብልጽግና እንደሚሠራ መረጃ የሰጡት ክፍሎች ኤሊያስ መሠረት ናይሮቢ በከተመበት ወቅት በቅርበት የሚያውቁት ናቸው።
ትህነግ በሥልጣን በነበረበት ዘመን በሥልት ዜናዎችን ሲያቀዛቅዝና ሲያድበሰብስ ጠንቀቀው የሚያውቁት ወዳጆቹ እንደሚሉት፣ ኤሊያስ መሠረት ወደ ብልጽግና የመሸጋገር ዝንባሌ የታየበት “ትህነግ ዳግም ይመለሳል” የሚለው ምኞቱ ሙሉ በሙሉ መክሰሙን ከተረዳ በኋላ ነው።
ለትህነግ ለሚሰጠው አገልግሎት በኢትዮጵያ አየር መንገድና በግል የንግድ ተቋም አማካይነት ክፍያ ይፈጸመለት የነበረው ኤሊያስ መሠረት ሜይ 29፤ 2021 “አቶ ጌታቸው አሰፋ ኤርፖርት ላይ ተያዙ” በሚል ለተሰራጨው ዜና የሰጠው ምላሽ አነጋጋሪ እንደነበር ይታወሳል።
“እስከማውቀው ድረስ አቶ ጌታቸው አሰፋ ቦሌ ኤርፖርት አይጠቀሙም” የሚል ልጥፍ በፌስቡክ ገጹ ያሠራጨው ኤሊያስ መሠረት፤ ራሱን ደብቆ ስለኖረው የደኅንነቱ መሪ ይህን ያህል መረጃ ማግኘቱ ራሱም የጌታቸው አሰፋ የሚዲያ ክንፍ ከመሆኑ የተነሳ እንደሆነ ትችት አስነስቶበት ነበር። ወቅቱ የትርምስና ጦርነት በመሆኑ ትኩረት አልተሰጠውም እንጂ “እንዴት ነው ነገሩ?” ያሉ ጥቂት አልነበሩም።
“ኤሊያስ መሠረት ሦስት ልጆቹን ይዞ ተሰደደ” በሚል ለተሰራጨው መረጃ “ኬኒያ ከገባ እኮ ቆየ፤ እዛ እኮ ድርጅት ከፍቷል” በሚል ወዳጆቹ ምላሽ መስጠታቸውን በማስታወስ አሁን ላይ አሜሪካ እንደሚኖር የሚጠቁሙ፣ ችግር ላይ መሆኑን እንደሚያውቁ አስታውቀዋል።
የኤሊያስ መሠረት የቅርብ ጊዜ አካሄድ ግራ እያጋባ መሆኑን እነዚሁ ወገኖች ይገልጻሉ። በተለይ ከዩስኤይድ በፋክት ቼክ ስም ያገኝ የነበረው ድጎማ ከቆመበት ጊዜ ወዲህ ለውጥ ማየታቸው የወዳጃቸውን ዙሪያ ገባ ለማየት መነሻ እንደሆናቸውን እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ።
የሚያወጣቸው የዜና ዘገባዎችና “መረጃ” እያለ የሚበትናቸው የራሱ ሪፖርቶች “ይህ ሰው በርግጥ ለማን ነው የሚሠራው?” የሚል ጥያቄም አጭሮባቸዋል። በዚሁ መነሻ የራሳቸውን ክትትል አድርገዋል። ከከትትላቸው በኋላ “ኤሊያስ በተቃዋሚ ስም የብልጽግናን አጀንዳ እያስፈጸመ ነው” ወደሚለው ድምዳሜ መዳረሳቸውን የሚገልጹት እነዚሁ ወገኖች፣ ኤሊያስ በተመሳሳይ ሥራ የቆየ በቂ ልምድ ስላለው ሊቸገር እንደማይችልም ይገልጻሉ።
ኤሊያስ ከዚህ በፊት በ“ጋዜጠኛነት” ስም ለትህነግ ይሠራ እንደነበር፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሹም የአቶ ተወልደ ገብረመድኅን ታማኝ የቀኝ እጅ እንደነበር፣ ማስረጃ በመጥቀስ አሁንም በተቃዋሚ ስም ለብልጽግና መሥራት እንደማያዳግተው በርካታ የቅርብ ሰዎቹ ዘንድ መግባባት አለ። ቅርቡ ከሆኑት መካከል አንዱ “በቅርብ የማውቀው ስላለ ያንን ተንተርሼ ጉዳዩን ላብራራ” ሲል ለጎልጉል የአዲስ አበባ ተባባሪ የሚያውቀውን አጫውቷል።
“ከቅርቡ ልጀምር … የቀድሞው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ትህነግ) ከሥልጣን መንበር ከተወገደ በኋላ ኤሊያስ፣ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ፣ Ethiopia Check የሚባል ድርጅት ከፈተ። በዚሁ ድርጅት የሃሰት መረጃዎችን እያጣራሁ ሕዝቡን ከተሳሳተ መረጃ እታደጋለሁ አለ። ይህን እየሠራ ዳጎስ ያለ ብር ከዩኤስኤይድ ይቀበልበት ነበር። እሱም ድረገጹ ላይ ከ“partners” ብር እንደሚቀበል አልካደምና ይህ እንደመንደርደሪያ ይሁነን” ይላል እማኙ።
“በወቅቱ አካሄዱ መጥፎ አልነበረም፤ ግን ኤሊያስ በዓላማ ይንቀሳቀስ ስለነበር ብዙም አልገፋበትም” የሚለው ይኸው መረጃ ሰጪ፤ “ኤሊያስ “ዓለምአቀፉ ጋዜጠኛና ኢትዮ ፋክት ቼክ መሥራች” የሚል ብራንድ” መትከሉን አጋጣሚ እንዳልሆነ ያስረዳል።
የአሶሺየትድ ፕሬስ ዘጋቢነቱን ለዚህኛው መስፈንጠሪያ እንዳደረገው ሁሉ ይህንን “ፋክት ቼክ” ብሎ የጀመረውንም ለቀጣዩ ሥራው መስፈንጠሪያ በማድረግ “በኦሮሚኛና በትግሪኛ ፋክት ቼክ አደርጋለሁ” እያለ ከዩስኤይድ በደንብ እንደሸቅለበት አመልክቷል።
“ፖለቲካው እየተጧጧፈ ሲሄድ የፋክት ቼክ ሥራውን ለድጎማ እየተጠቀመ ወዲያው በስሙ በከፈተው የማኅበራዊ ገጾች መረጃዎችን ማውጣት ጀመረ። ይህንንም ለመስፈንጠሪያ እያመቻቸው እንደነበር የምናውቅ እናውቃለን” የሚለው ወዳጁ፣ ይሄኛው አካሄዱ ወደ ብልጽግና ለመግባት ያቀዳው ሥልቱ ስለመሆኑ ያስረዳል። አክሎም ይህን ማድረግ ከጀመረ በኋላ በሚያወጣቸው መረጃዎች የመንግሥት ተቃዋሚ መስሎ ዙሩን አክርሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ዕውቅና፣ ከዩኤስኤይድ ጥቅም፣ ከተቃዋሚዎች ይሁንታን ሰበሰበበት።
“ብዙም ሳይቆይ በርካታ ሰዎች በስሜ የማወጣውን መረጃ ወደ ሚዲያ ቀይረው ስላሉኝ ሚዲያ ልከፍት ነው፤ የናንተው ሚዲያ ስለሚሆን ስም ስጡ፤ ሎጎ አውጡ፣ ሚዲያውን ምሩት” የሚል ጥያቄና ግብዣ ማቅረቡ እሱን ለሚያውቁት ጥርጣሬያችን አሰፋው።
ለጎልጉል ተባባሪ መረጃውን ያቀበለው ይኸው ወዳጁ ከናይሮቢና አዲስ አበባ ለእሱ ሲሠሩና መረጃ ሲያቀብሉ እንደሰማው አካሄዱና ግብዣው ተከታዮቹን ለማማለል እንጂ የሚዲያውን ስም ሆነ ሁሉንም ነገር ወስኖ ጨርሶ እንደ ነበር።
ኤሊያስ “መሠረት ሚዲያ” መሥርቻለሁ ባለ ባጭር ጊዜ ውስጥ የአሜሪካ ፖለቲካ ድብልቅልቁ ወጣና ለፋክት ቼክ የሚሰጠው ድጎማ ተቋረጠ። አሁን ኤሊያስ ጉዳዩን አቅጣጫ ማስያዝ ግድ ሆነበት። በተቃዋሚ ሚዲያ ስም የከፈተውን “መሠረት ሚዲያን” ለሚቀጥለው የብልጽግና ጉዞ መጠቀሚያ ማድረግ ብቸኛ አማራጩ ሆነ። ስለዚህ ያለው ብቸኛ አማራጭ በተቃዋሚ ስም መቀጠልና ከበስተጀርባ የብልጽግና ተከፋይ መሆን ነበር።
ኤሊያስ የሚጓዝባት መንገድ በፕሮፓጋንዳው ዓለም የታወቀ ተቃዋሚ መስሎ፣ በተመረጡ ጉዳዮች ላይ መንግሥት የሚቃወሙ መረጃዎችን በማውጣት አንዳንድ አካሄዶችን ማኮላሸት፣ ለሕዝቡ አጀንዳ መስጠት፣ የተፋፋሙ እንቅስቃሴዎችን በሌላ “ትኩስና ሰበር” መረጃ መበረዝ፣ ወዘተ ነው። ልክ በምዕራቡም ሆነ በምስራቁ ዓለም ሲሠራበት የኖረና ያለ የፕሮፓጋንዳ ሥልት ዓይነቱ መተጣጠፍ ለኤሊያስ እንግዳ ባለመሆኑ እንደሚሳካለት መረጃውን የሰጡን ይስማማሉ።
ኤሊያስ በዚህ መስመር እየሄደ እንደሆነ በተቃዋሚ ስም የመንግሥት ጉዳይ አስፈጻሚ የበለጸገ “ጋዜጠኛ” መሆኑን፤ ተከታዩችንም በዚሁ ረቂቅ ሥልት ያደነዘዘ ለመሆኑ ማሳያ ይሆን ዘንዳ እነዚሁ ወገኖች አንድ ሁለት መረጃዎችን ያጣቅሳሉ።
የመጀመሪያው፤ … “ለአማራን ሕዝብ እንታገል” ብለው ዱር ቤቴ ያሉ ፋኖዎች የመንግሥትን ኃይል በትጥቅ ትግል ሲፋለሙ ኤሊያስ እንዳይጠረጠር አንዳንድ አገር ያወቀውን፣ ፀሐይ የሞቀውን መረጃ ከማካፈል በስተቀር፤ ስለ ድሎቻቸውም ሆነ ስለ ሥራዎቻቸው ምንም ትንፍሽ ብሎ እንደማያውቅ መረጃውን ያካፈሉት ወገኖች ያስታውሳሉ።
“የተቃዋሚ ሚዲያ ከሆነ እና የመንግሥትን ግፍ የሚያጋልጥ ከሆነ ለፋኖ ታጋዮች እና ለገድሎቻቸው ሚዛናዊ መረጃዎችን ለአንባቢው ማጋራት ይጠበቅበታል። ኤሊያስ ግን ያደረገው የተገላቢጦሹን ነው” የሚሉት ወገኖች፣ “በተለያየ አመራርና ዕዝ ተደራጅቶ ያለው የፋኖ ሠራዊት ወደ አንድነት ለመማጣት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ኤሊያስ ያደረገው ነገር ቢኖር የፋኖ ኃይል የሚከፋፍል ለመንግሥት የወገነ መረጃ ማውጣት ነው” በሚል ሥልታዊ አካሄዱን ያጋልጣሉ።
በዚሁ ሥልታዊ አካሄዱ “የእስክንድር ነጋ ፋኖ ለድርድር እየተመቻቸ ነው” ሲል በፋኖ የአንድነት ጉዞ ላይ ስለት አነሳ። “… በእስክንድር ነጋ የሚመራው የፋኖ ክንፍ ድርድሩ በውጭ ሀገራት እንዲሆን እየጠየቀ መሆኑ ታውቋል” በሚል ያሰራጨው ዜና “የመሠረት ሚዲያ ምንጮች እንደተናገሩት ታጣቂ ክንፉ ድርድሩ በአውሮፓ አልያም በአሜሪካ እንዲደረግ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል” የሚል ማሰሪያ የተበጀለት ነበር።
ይህ ዘገባው አንዱ ወገን ተደብቆ ሌሎችን በመግፋት እያሤረ እንደሆነ ተደርጎ በመቅረቡ የፋኖን ኅብረት ክፉኛ ጎዳው። ወሬው ያስከተለው ጥፋት ከፍተኛ በመሆኑ እስክንድር ነጋ “ኤሊያስ ስሙን የተከለው ፋክት ቼክ በሚባል የማኅበራዊ ሚዲያ የሐሰት ልጥፎችን አጋልጣለሁ በሚል ነው። እሱ ጋር ሲደርስ ፋክት ቼክ አይሠራም ወይ?” ሲል ነቀፌታውን አሰማ። በወቅቱ ትኩረት አልተሰጠውም እንጂ እስክንድር “የኤሊያስ መሠረት ጭንብል ወልቋል” ብሎ ነበር። የምን “ጭምብል”?
ወደ አማራ ሕዝብ ትግል ከመግባቱ በፊት እስክንድር በጋዜጠኛነት ብዙ ዓመት የሠራ ነው፤ ሙያውን፣ በውስጡ የሚደረጉት አሻጥሮች፣ የሤራ ቅንብሮችና አካሄዶች ራሱም ያለፈበትና በደንብ የሚያውቀው ነው፤ ለዚህም ነው እስክንድር “የኤሊያስ መሠረት ጭምብል ወልቋል ያለው” ሲሉ በወቅቱ ሁለቱ በደንብ እንደሚተዋወቁ ጠቅሰው አስተያየት የሰጡ ነበሩ። “ችግሩ ግን በእስክንድርና በዘመነ መካከል ባለው የሃሳብ ልዩነት የደጋፊዎች ዕይታም እንዲሁ የተንሸዋረረ በመሆኑ ተድበሰበሰ። እስክንድር ለተናገረው ትኩረት ቢሰጥ ኖሮ ፍትሕና እውነት ፈላጊዎች የወለቀውን የኤሊያስ ጭምብል ባፈላለጉ ነበር” ሲሉ ጊዜው አሁንም እንዳልረፈደ የመረጃው ባለቤቶች ይገልጻሉ።
“ኤሊያስ መሠረት ግን በዚህ መረጃው በፋኖ ኅብረት ውስጥ ጥርጥር እንዲኖር አድርጓል። አለመተማመንን ፈጥሯል። እስክንድር በገሃድ ውይይት ማካሄዱን እየተናገረ ያንን ገልብጦ በማቅረብ የፋኖ ደጋፊዎች በጎራ ተከፋፍለው እንዲለያዩ አድርጓል። ታዲያ ይህ ማንን ነው የጠቀመው? የማን አጀንዳ ነው? ኤሊያስ እየሠራ ያለውስ ለማን ነው? ከፋዩስ ማነው?” ሲሉ ጥርጣሬያቸውን በአመክንዮ ደግፈው የቅርብ ሰዎቹ አንባቢ እንዲመረመር ያሳስባሉ።
ሁለተኛው፤ … ከሰሞኑ የሕክምና ባለሙያዎች ያነሱትን የሥራ ማቆም አድማ አልዘገበም እንዳይባል ኤሊያስ ትንሽ ቀባብቶ ወደ አጀንዳው መመለሱን እነዚሁ ወገኖች ይገልጻሉ። የሕክምና ባለሙያዎቹ ጥያቄያቸውን እያሰፉ ባለበት ወቅት ግን፣ ኤሊያስ እንደ ሚዲያ “ባለሙያ” ተከታትሎ መዘገብ ሲገባው፣ ያደረገው ሌላ ነው እንደሆነ ጠቅሰው ሌላውን ማሳያቸውን ያቀርባሉ።፡
በትዕዛዝና በአጀንዳ የሚንቀሳቀሰው ኤሊያስ የሐኪሞቹ እንቅስቃሴ ሞቅ እያለ ባለበትና ሁሉም በዚያ ላይ እየተረባረበ ባለበት ውቅት “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ጠፈር ሊጓዙ ነው፤ ጠፈር ላይ በመሆን ለአለም ህዝብ የሰላም መልዕክት ለማስተላለፍ መታቀዱን ሚድያችን አረጋግጧል” የሚል የማደንዘዣ መረጃ ረጨ።
ይህ መረጃ እውነት እንኳን ቢሆን ወጪያቸው የሚሸፈነው በጋባዡ አገር እንደሆነ እየታወቀ፣ ኤሊያስ ሆን ብሎ በትዕዛዝ ያሰራጨው መረጃ የማኅበራዊ ሚዲያ ቡፌ ሆነ፤ የሐኪሞቹ ተጋድሎ ተዘነጋና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስም የማኅበራዊው ሚዲያ ግለት ሆነ። ከልሒቅ እስከ ደቂቅ ወሬውን ተቧጨቀው። ከዚያች ሰዓት ጀምሮ አየሩን ይዞት የነበረው የሐኪሞቹ የ“ትግል ውሎ” አረጀ፤ ደነዘዘ። የሚዲያ ባለቤቶችና ዋና የድረገጽ ዐውዶች ወሬያቸው በሙሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠፈር ጉዞ ሆነ። መረጃቸውን በምክንያት የሚያስደግፉት አሁንም በድጋሚ “ታዲያ ይህ ማንን ነው የጠቀመው? የማን አጀንዳ ነው? ኤሊያስ እየሠራ ያለውስ ለማን ነው? ከፋዩስ ማነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
ሦስተኛ፤ … በቀደመው አገዛዝ በጋዜጠኛነት ስም የወያኔ ልሳን ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ሪፖርተር ጋዜጣ ከዳር ሆነው በሚያዙት የሤራ አምራቾች አማካይነት ባሁኑ ጊዜ በመንግሥት ላይ ዘመቻ መክፈቱን የሚገልጹት እነዚሁ ወገኖች፣ “አሁን ያለው የሪፖርተር ስብስብ በጥናት መንግሥት ላይ ጫና ማድረስ የሚችል አቅም እንደሌለው ጠቅሰው ከጀርባ የሚነዱት የሚታወቁ አኩራፊዎች አሉ” ሲሉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ እግረ መንገዳቸውን ያሳስባሉ። አክለው ግን ኤሊያስ መሠረት ለማን ነው የሚሠራው? የሚለውን ጥያቄ ለማጉላት ሪፖርተርን ለማሳያ ይጠቀማሉ።
ባለፈው ሳምንት የፊት ገጹ ላይ እያንዳንዱ ዜጋ ምን ያህል የመንግሥት ዕዳ እንዳለበት ሪፖርተር አኻዝ ሰፍሮ ማስቅመጡ ይታወሳል። “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ያለበት የውጭ ዕዳ መጠን ከ575 ዶላር በላይ መድረሱ ተነገረ” በማለት እየበለጸግን ነው የሚለውን መንግሥት ያበሳጨ መረጃ ፊት ለፊት ያተመው ሪፖርተር አስር ቢሊዮኑ ዕዳ ባይከፈል እያንዳንዱ ዜጋ ላይ የሚደርሰው ዕዳ ምን ያህል እንደሆነ የዘነጋው “የትህነግን ካባ ባለማውለቁ ነው” የሚሉ ቢሰሙም ኤሊያስ ግን ለዓላማው ተጠቅሞበታል።
የሪፖርተር አካሄድ ያልጣመው መንግሥት አሁን ላይ ዋና የዜና ምንጩ ፓርላማ በመሆኑ ከዚያው ከፓርላማ የሚያገኛቸውን ወሳኝ መረጃዎች እንዳያገኝ መከልከሉን ራሱ አስታውቋል። ሰሞኑን ሪፖርተርን ከ30 ዓመት በላይ ሲዘግብበት ከነበረው ፓርላማ እንዳይገባ መታገዱ እየተዘገበ ባለበት፤ በማክሸፍ እና አቅጣጫ በመስጠት ታላቅ አገልግሎት እየፈጸመ ያለው ኤሊያስ ሪፖርተርን የደገፈ መስሎ የለቀቀው አደገኛ መረጃ ብዙዎች የተረዱት እንደማይመስላቸው እንቅስቃሴውን የሚያውቁትና እያጠኑት ያሉት ገልጸውዋል።
ዴይሊ ኔሽን የተባለውን የኬኒያ ጋዜጣ የፊት ገጽ ፎቶ አንስቶ “ይህ የዛሬ የኬንያው ‘ዴይሊ ኔሽን’ ጋዜጣ እትም ነው፣ በፊት ገፁ ላይ ‘State Terror’ ወይም ‘መንግስታዊ ሽብር’ በማለት የሀገሪቱ መንግስት በአንዳንድ ፖለቲከኞች ላይ እየፈፀመ ነው ያለውን የወንጀል ድርጊት ያጋልጣል። ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ ሪፖርተር ጋዜጣ ፓርላማ ተገኝቶ በይፋ የተባለውን፣ የተነገረውን ለህዝብ ስላቀረበ ፓርላማ ተገኝቶ እንዳይዘግብ ይታገዳል” በማለት ነው ኤሊያስ መሠረት አሜሪካ ቁጭ ብሎ የዘገበው።
“ይህ የኤሊያስ መረጃ ላይ ላዩን ላየው የተቆርቋሪ ወይም የደጋፊ ነው የሚመስለው፤ ግን ሪፖርተርን በደንብ ሊያስመታውና ከጨዋታ ውጪ ሊያደርገው የታሰበ እንደሆነ ብዙም ትኩረት የተሰጠው አይመስልም” ይላሉ የመረጃው ሰዎች።
“ኤሊያስ ሪፖርተርን ፓርላማ እንዳትገባ የተደረገብህን ተጽዕኖ “መንግሥታዊ ሽብር” ብለህ ሰይመው፤ በሚቀጥለው ዕትምህ የፊት ገጽ አትመው። ግፋ በለው እያለ እየኮረኮረ ነው። ሪፖርተርን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እያደፋፈረ ለምትና ለክስ እያመቻቸው ነው። በነገራችን ላይ ኤሊያስ ሕግ ተምሯል በኢትዮጵያ የሽብር ክስ ስንት ዓመት እንደሚያስቀጣ ያውቃል፤ ሪፖርተርን በአሸባሪነት የሚያስከስሰውን ተግባር እንዲፈጽም አድርጎ ከጨዋታው ውጪ አድርጎ ከነ ስህተቱም ቢሆን በየሳምንቱ ጥቂትም መረጃ የሚያቃምሰንን ሚዲያ ከጥቅም ውጪ አድርጎ እሱ ብቻ ሊነግሥበት፣ ኪሱንም ሊያደረጅበት ነው። ታዲያ ይህ ማንን ነው የጠቀመው? የማን አጀንዳ ነው? ኤሊያስ እየሠራ ያለውስ ለማን ነው? ከፋዩስ ማነው?” ሲሉ ተጨማሪ አመክንዮ ያቀርባሉ።
“ይህ የኤሊያስ ድብቅ ሤራ እንዳይጋለጥበት አንድ የሚጠቀመው የተጠና ሥልት አለ። ይህም መሠረት ሚዲያ ነጻና የሕዝብ ነው፤ እኔ ገንዘብ የለኝም፤ ተረከቡኝ፤ ሚዲያው እንዲቀጥል የምትፈልጉ ከሆነ ደግሞ ከፍላችሁ መረጃዬን አግኙ፤ ሚዲያው እንዳይዘጋ ደግፉ፤ …” በማለት ተከታዮቹን ነጻ ሚዲያ የሚደግፉ እንዲመስላቸው፤ እሱም መንግሥት ተከፋይ አለመሆኑን የሚያደናግርበት አሪፍ ሥልት መሆኑን በናይሮቢ ያሉ ወዳጆቹን የሚያውቁ ይናገራሉ። አክለውም “ለዚህም ነው ኤሊያስ በየቀኑ እየወጣ ይህንን ያህል ደጋፊ ተገኝቷል፤ ቅናሽ አድርጌአለሁ፤ እኔ የስድስት ወር እከፍላለሁ እያለ ለማሳመን የሚጥረው እንጂ በበጀት የሚንቀሳቀስ እንደሆነ በረቀቀ ሥልት የሚያወጣቸው የማዘናጊያ መረጃዎች ማስረጃ ናቸው” ብለዋል።
“ኤሊያስን በግል አውቀዋለሁ፤ የግል ሕይወቱን ጨምሮ በቅርብ መረጃው አለኝ፤ ስለ እርሱ ማንነትና ድብቅ ስብዕና እንዲሁም ካገር ወጥቶ ለምን እንደሚኖር፣ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ማጋለጥ ፈልጌ ነበር፤ ግን ሚስቱን እንተዋት ቢባል እንኳ ልጆቹን ማሰብ ግድ ነው። ልጆቹ አሳዘኑኝ እንጂ ተግባሩ ለይቅርታ የሚያበቃው አልነበረም፤ ምናልባት እኔ ስለማጋልጠው መረጃ ቤተሰቡ ምንም ዕውቀት የሌለው ከሆነ ይጎዳል፤ ከምንም በላይ ኤሊያስ ይህን ይረዳል። ለጊዜው ልለፈው” ብለዋል።
“ጋዜጠኞች ይገዛሉ፣ ይሸጣሉ፤ ተቃዋሚ ነኝ ብሎ የሚያወራ ሁሉ ተቃዋሚ አይደለም። ሥራው ብዙ መልክ፣ ብዙ ፈርጅ አለው፤ ካላመናችሁ ብዙ መከራና ግፍ ደረሰበት ሲባል የነበረው ተመስገን ደሳለኝ የት ነው ያለው? ምነው ድምፁ ጠፋ? ያ ሁሉ የሚዲያ ግለት ምነው በረደ?” የሚል ጥያቄ በማንሳት መጠየቅ የኤሊያስ መሠረትን ቀጣይ መውደቂያ በገሃድ እንደሚያሳይ እነዚሁ ወገኖች አመላክተዋል። ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply