
የመሠረት ሚዲያ ባለቤት አቶ ኤሊያስ መሠረትን በስም ጠቅሶ የመንግሥት ተከፋይ እንደሆነ የፋኖ አንድ ክንፍ መሪ እስክንድር ነጋ በይፋ ተናገረ። እስክንድር “ጭምብሉ ዛሬ ወለቀ” ሲል አመልክቷል።
እስክንድር ይህን ያለው ከEMS ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ሲሆን፣ መነሻው አቶ ኤሊያስ መሠረት በአባቱ ስም እንደሰየመው በሚገልጸው የግሉ ሚዲያ ላይ እስክንድርን ጠቅሶ “ከመንግሥት ጋር ለመደራደር የተዘጋጀው የፋኖ ክንፍ ንግግሩ በአሜሪካ ወይም በአውሮፓ እንዲሆን ጠየቀ” በማለት ሪፖርት ማድረጉን ተከትሎ ነው።
አቶ ኤሊያስ “መሠረት ሚዲያ ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ሚዲያ ውስጥ በሠሩ እና አሁንም እየሠሩ ባሉ ጋዜጠኞች ሚዛናዊ፣ አዳዲስ እና ፈጣን መረጃዎችን ለአንባቢዎች ያደርሳል” በሚል መሪ እሳቤ እንደሚሠራ በማኅበራዊ ገጹ ላይ አስፍረዋል።
እስክንድር ነጋ በቃለ ምልልሱ “ኤሊያስ ስሙን የተከለው ፋክት ቼክ በሚባል የማኅበራዊ ሚዲያ የሐሰት ልጥፎችን አጋልጣለሁ” በሚል መሆኑን ደጋግሞ አመልክቷል። ይህን ካለ በኋላ “እሱ ጋር ሲደርስ ፋክት ቼክ አይሰራም ወይ?” በማለት ጠይቋል።
የቀድሞው የባልደራስ መሪና የአሁኑ የትጥቅ ትግል መሪ እስክንድር ነጋ “የኤሊያስ መሠረት ጭንብል ወልቋል” ሲል አጋጣሚው ማንነቱን ይፋ እንዲሆን ያስቻለ መሆኑን አመልክቷል። ዓላማውም ፋኖን ከሕዝብ ለማጣላትና ተቀባይነቱ ላይ ጥላ ለማጥላት መሆኑ ግልጽ እንደሆነ በዜናው ውስጥ የተሰገሰጉትን ጉዳዮች ተንተርሶ አመልክቷል።
አቶ ኤሊያስ መሠረት በዘገበው መረጃ “… በእስክንድር ነጋ የሚመራው የፋኖ ክንፍ ድርድሩ በውጭ ሀገራት እንዲሆን እየጠየቀ መሆኑ ታውቋል” ብሏል።
“የመሠረት ሚድያ ምንጮች እንደተናገሩት ታጣቂ ክንፉ ድርድሩ በአውሮፓ አልያም በአሜሪካ እንዲደረግ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል” ይላል በዜናው መግቢያ።
እስክንድር ራሱ የኢጋድ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የአሜሪካ ተወካዮች መገኘታቸውን ገልፆ እንደነበር የሚያስታውሰው የአቶ ኤሊያስ ዘገባ፣ ምንጮቹ እንደተናገሩ በመግለጽ ከሁለቱም ወገን ቀረቡ የተባሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ጠቁሟል።
ከየትኛው ወገን ያሉ ምንጮች እንደነገሩት ምንም ሳይጠቅስ መረጃውን ያወጣው አቶ ኤሊያስ፤ ከነእስክንድር በኩል ለመንግሥት የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች ብሎ ከዘረዘረው “ክልሉን ማስተዳደር፣ በፌደራል መንግሥቱ በሥልጣን መወከል” የሚል ይገኝበታል።
“በመንግሥት ዝግ ስብሰባ ላይ ሲያጨቃጭቅ የነበረው የነእስክንድር ክንፍ ዓቅም ጉዳይ ሲሆን ግምገማውም በሀገር ውስጥና በውጭ ተቀባይነትን ለማግኘት መነጋገሩ እንደ አማራጭ ተወስዷል” ያሉን ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ምንጫችን ሸዋ ላይ ድርጅቱ የተሻለ አቅም እንዳለው፣ ነገር ግን ጎጃም ላይ የለም የሚባል ደረጃ ላይ እንደደረሰ መረጃ ቀርቦ ንግግር ተደርጎበታል ብለዋል” ይላል የአቶ ኤሊያስ መረጃ።
አንዳንዶችም ይህ የመንግሥት መረጃ በቀጥታ ከመንግሥት ሰዎች ይሁን ወይም እስክንድርን ከሚቃወሙ የፋኖ ታጣቂዎች ወይም ከዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ተወካዮች ማግኘቱን መጠነኛ ፍንጭ አለመስጠቱ አቶ ኤሊያስ ከነማን ጋር ነው የሚሠራው? የዜናውስ ዓላማ ምንድነው? ብለው እንዲይቁ አድርጓቸዋል።
አቶ ኤሊያስ ይህን ጽሁፍ ባሰራጨበት የፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስተያየት ከሰጡ በርካታ ተከታዮች መካከል Menbere Kassaye የተባሉ “ቆይ ሁሉም ይሁን እሺ ። እስክንድር ላይ የተተኮረው ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ቀደም ሲል ግኑኝነት ስለነበረው። የጎጃሙ ተዳክሟል። ጠንከር ያለው የሸዋው ነውን ምን አመጣው? በመንግሥት በኩል እነ እስክንድር ተጠያቂዎችን አሳልፈው እንዲሰጡ ተጠይቀዋል ይላል። እነዛ ፀጉራቸውን አንዠርግገው በሱፍ ተሸፍነው፣ አዲስ አበባ የደረሰችበትን ሲጎበኙ የነበሩት እነ ጃል ሰኚ ማንን አሳልፈው ሰጥተዋል?” ሲሉ ለአቶ ኤሊያስ ዘገባ ጥያቄ አስፍረዋል።
አቶ ኤሊያስ በጻፈው ዜና መንግሥት “ተጠያቂ የሚሆኑ አባላቱን አሳልፎ መስጠት” የሚል ቅድመ ሁኔታ ማቅረቡ፣ እስክንድር የፋኖን ታጋዮች አሳልፎ ለመስጠት ሊስማማ እንደሚችል አድርጎ በውስጥ አዋቂዎች ስም ዜናው ውስጥ የተካተተ መርዝ እንደሆነም በርካቶች አመላክተዋል።
ዜናው መለስ ብሎ “ቢያንስ ሸዋን ማ(ጠ)ቃለሉ እንደ ጥሩ ዕድል በመታየቱ እና የድርድር ዝርዝር መረጃም የሚቀበሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትም በመንግሥት የንግግሩ ቦታ ስለተጓጓዙ ውይይቱ ተደርጓል” ሲል ድርድር ስለመደረጉ በርግጠኛነት ያወራል። እስክንድር ግን “አንድም የመንግሥት ሰው ድርሽ አላለም፤ የተነጋገርነው ዕርዳታ በሚገባበት አግባብ ነው። ረሃብ አለ። ሕዝብ ድጋፍ ማግኘት አለበት። … ” በማለት የንግግሩን ዋና ነጥብ ያለውን ይገልጻል።
ሌላ Bitania Alula የተባሉ አስተያየት ሰጪ ስለ ሚዲያዎች አመሠራረት ካብራሩ በኋላ “… እራሱን [መሠረት ሚዲያ] ብሎ የሚጠራ ተቃዋሚ ዘመም ሚዲያ የፃፈውን ካያችሁት በተመሳሳይ መልኩ ከላይ የፃፍኩትን የውጭ ሚዲያዎች ዓይነት ነው። “መሠረት ሚዲያ” የፃፈው የውሸት ዘገባና ፍጹም ጎጃም ዘመም ዘገባ ነው። ከዚያ ይልቅ አስረስ ማረ ለፕሮፓጋንዳ ብሎ የፃፈውን ዘገባ እንደወረደ ያቀረበ ነው። ዘገባው በአጠቃላይ የተፃፈው በእነ [አስረስ ማረ] ነው። አጠቃላይ ምንም ድርድር በሌለበት ሁኔታ “የእስክንድር ቡድን ተደራደረ” በሚል የውሸት ዘገባ ሽፋን የሰጠው የእነ አስረስ ማረ ዘመም ደጋፊ ሚዲያ ነው” ብለው በጽሁፉ ግርጌ ጽፈዋል።
አቶ ኤሊያስ በዘገባው “ተንታኝ” ያለውን ሰው ጠቅሶ “… አሳሳቢው ጉዳይ አሁንም ልክ እንደነ ጃል ሰኚ እንዳይሆን ነው፣ ሙሉ ሰላም ለማምጣት የተወሰነ ቡድን ሳይሆን ሁሉንም አካታች መሆን አለበት” ሲሉ “ተንታኙ” ለአቶ ኤሊያስ መናገራቸውን መረጃው ጠቅሷል። ይህንን እስክንድርን ከጃል ሰኚ ጋር የማነጻጸሩን አካሄድ ያወገዙ ግን እጅግ ብዙ ናቸው። ጃል ሰኚ በአሥር ሺህ የሚቆጠር ሠራዊት ይዞ መግባቱ አይዘነጋም።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች አቶ ኤሊያስ መሠረትን በቀድመው የህወሃት/ትህነግ አፋኝ አገዛዝ ዘመን የነበረውን የ“ጋዜጠኛነት” ሚና በማንሳት ይከሱት እንደነበር ያስታወሱ “የኤሊያስ መሠረት ጭምብል ዛሬ ወልቋል” በማለት እስክንድር የተናገረውን ያጠናክራሉ። ድጋፋቸውንም ይሰጣሉ።
ስዩም ተሾመ በአቶ ኤሊያስ ላይ በተደጋጋሚ በማስረጃ ማቅረቡን ጠቅሰው በዘመነ ትህነግ፤ የውጭ ሚዲያዎች ለትህነግ ጥሩ ሽፋን እንዲሰጡ የማመቻቸት፣ ትህነግን የሚደግፍ ሪፓርት በማዘጋጀት እሱ ራሱ ይሠራበት በነበረ የውጪ ሚዲያ በማሳተም፣ በወቅቱ ሕዝብ ላይ በደል ሲፈጸም፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ተቋማዊ ዘረፋ ሲፈጸም በውጭ ሚዲያዎች ከለላ በመስጠት አቶ ኤሊያስ ለሚሠራው ሥራ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ዳጎስ ክፍያ ይፈጸምለት እንደነበር ለማስታወስ የተገደዱ ተቃውሞ እያሰሙ ነው።
እስክንድር ድርድር ባያደርግም ንግግር መደረጉን፣ ንግግር መደረጉ ወደ ቀጣይ ድርድር እንደሚያመራ የጠቆሙ ክፍሎች፣ አቶ ኤሊያስ አየር መንገድ ውስጥ እስር ቤት እንደነበር እያወቁ ከተወልደ ገብረመድኅን ጋር በነበረው የጥቅም ግንኙነት ምክንያት ዝም በማለት፣ ለዚህም ውለታው በአየር መንገዱ በጀት ሞሪሺየስ የጫጉላ ሽርሽር ማድረጉን ያስታውሳሉ። ተወልደ ወደ አሜሪካ ሲኮበልልና በዴልታ አየር መንገድ ውስጥ ሥራ ማግኘቱን ከተወልደ ቤተሰብ ቀድሞ መረጃውን ይፋ ያደረገው አቶ ኤሊያስ መሆኑን እንደ መረጃ ያቀርባሉ።
ከለውጡ በኋላ በርካታ ድርጅታዊ ጥቅም በማጣቱ ወደ ተቃዋሚነት ማደጉን የሚገልጹና በርካታ መረጃዎች ከአየር መንገዱ ሲወጣና በስዩም ተሾመ በኩል ሲሰራጭ እንደነበር የሚገልጹ “አቶ ኤሊያስ ከፓርቲና መንግሥት ጋር ተሰናስሎ በምሥጢር በመሥራት በዘርፉ በቂ ልምድና የዳበረ ኔትዎርክ ያለው፣ እርቅና ሰላም ፍጹም የማይመቸው የሚዲያ ታጋይ ነው” ይሉታል።
ይህንኑ ልምድ አሁን በተቃዋሚ ስም ግን በድብቅና ረቂቅ በሆነ መንገድ በሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር እየሠራበት እንደሆነ ጠቋሚ ነገሮች አሉ የሚሉ ወገኖች፤ አቶ ኤሊያስ በእስክንድር ላይ ያወጣው ይህ መረጃ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ውጤቱም ሸኔን ከፋፍሎ እንደተሠራው ሥራ በቋፍ ላይ ያለውን የፋኖን አደረጃጀት ከፋፍሎ መንግሥትን የመጥቀም አደገኛና መሠሪ ዜና ነው አቶ ኤሊያስ የሠራው በማለት ይከስሳሉ።
በእስክንድር ሥር ያለው ታጣቂ እጁን ከሰጠ ሌሎቹ ፋኖዎች እጅ አንሰጥም የሚሉበትን ምክንያት ያሳጣል፤ በዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ዘንድም ዕርቅን አለመቀበል ተቀባይነት ስለሌለው በጎጃም፣ በጎንደርና በወሎ የሚገኙ የፋኖ አደረጃጀቶችን ለከፋ መከፋፈል የሚዳርግ መርዝ የተቀላቀለበት ዜና ነው አቶ ኤሊያስ የዘገበው ይላሉ።
አቶ ኤሊያስ ግን ለራሱ የሚሰጠው ግምትና የጋዜጠኛነት ማዕረግ ሰሞኑን በራሱ ገጽ “በጀት = 0 ብር፤ የሰራተኛ ብዛት = 1፤ በጎ ፈቃደኞች = 3፤ ተፅእኖ = 100 ፐርሰንት፤ ሁሌ እኮራለሁ!” በማለት ነው። ይህን የገጽታ ግንባታ ራሱ የሰጠ ሲሆን በዚሁ ልጥፍ ሥር በርካቶች “አይተኬ፣ አይበገሬ፣ አንድ ለእናቱ…” በሚል አበባ በትነውለታል። አፋቸውን በጃቸው የጫኑም አሉ።
አቶ እስክንድር መሠረት ሚዲያንና አቶ ኤሊያስን በስም ይጠቀሱ እንጂ መረጃ ለማጣራት “እሁድ እስኪያልፍ ምን አጣደፋቸው” ሲል ሌሎች በተመሳሳይ የዲፕሎማቲክ ምንጮች እንደነገሯቸው ገልጸው የዘገቡትን “ሚዲያዎች” ወቅሷል። እሁድ ቢሮ ዝግ በመሆኑ ቢያንስ በድርድሩ ተገኙ የተባሉትን ዓለምአቀፍ ተቋማት ሰኞ ቢሮ እስኪከፈት ጠብቀውና እነርሱ ጠይቀው ለማጣራት አለመሞክራቸውን የገለጸው እስክንድር፣ “ይህ የጋዜጠኝነት ሀ፣ ሁ፣ ነው” ብሏል።
እስክንድርን ያናገሩት የEMS የተቃዋሚ ጎራ አባላት አቶ ፋሲልና አቶ ወንድማገኝ ዋናው ዓላማቸው እስክንድር “ድርድር አልተደረገም” እንዲል ስለነበር በመሠረት ሚዲያና በሌሎች ላይ ለቀረበው የተዓማኒነት ጥያቄ ብዙም ትኩረት እንዳልሰጡ ከውይይቱ ለመረዳት ይቻላል።
አቶ ኤሊያስን እናውቀዋለን የሚሉና ከህወሃት/ትህነግ ዘመን ጀምሮ በጋዜጠኛነት ስም ሸፍጥ ሲሠራ የኖረ ነው በማለት የሚከሱት፤ በኬኒያ የሚያደርገውን፤ በቀድሞ ጊዜ ግንኙነት ከመሠረተባቸው የውጪ ሚዲያ አካላትና የትህነግን ዓላማ በማስፈጸም ትልቅ ድጋፍ ሲሰጥ የነበረውን፤ ከቀድሞ የአየር መንገድ ኃላፊ ተወልደ ገብረመድህን ጋር አቶ ኤሊያስ የነበረውን ግንኙነት በመጥቀስ አሁን ደግሞ በተቃዋሚ፣ በ“ፋክት ቼክ” አድራጊነትና በ“ጋዜጠኝነት” ስም እንደ ቀድሞው በድብቅ ለመንግሥት የሚሠራ መሆኑን ይህ ስለ እስክንድር ድርድር ያወጣውን መንግሥት ዘመም መረጃ በዋቢነት ይጠቅሳሉ።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
መቼ ነው ከፓለቲካው ዓለም እርቀን ቆም ብለን ህይወትን የምናጣጥመው? መቼ ነው በጎሳና በብሄር ፓለቲካ መጠፈራችን ቀርቶ ፍጥረትን በማድነቅ ፓለቲካ ያልበረዘው ንጽህ አየር የምንስበው? ሃበሻ በደረሰበት ሲራኮት፤ ሲካሰስ፤ ሲደባደብ፤ በዚህም በዚያም ሲጠላለፍ እድሜ ልኩን መኖሩ እንደ ስልጣኔ ቆጥሮ በየዘመናቱ አንድ በአንድ ላይ አካኪ ዘራፍ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል። የምንኖረው የእድሜ ልክ ስንት ነው? ለዚህች አጭር ዘመን ይህ ሁሉ ገመና።
በቅርቡ በርሊን ከተማ የሚገኝ ሰው ደወለና ምነው ጠፋህ አለኝ። አይ አንተ እንጂ እኔ አልጠፋሁም ስል። አይ እኔማ ወደ ሃገር ቤት ሂጄ ነው አለኝ። እንዴ ሃገር ቤት ሄድኩ ካልከኝ እኮ 3 ወራት አልሞላም ስለው እየሳቀ አዎን እንዳንተ እንደ ደብተራ ደብተር ላይ ተደፍተን አንውልም የሚሰሩ እጆቻችን ይሰራሉ ሲለኝ ሃገር ቤት ምን እየሰራህ ነው አልኩት። እባክህ ቤት ጀምሬአለሁ አለኝ። አዲስ ቤት ገዛሁ ካልከኝ እኮ ዓመት አልሞላም ስለው አዎን ሌላ ነዋ ሲለኝ ተገረምኩና። እንዴት ባለ ሂሳብ ነው አንተ የጀርመን መንግስት ጥገኛ ሆነህ ያለሥራ የተቀመጥክ ሰው ባለ ሁለት ቤት የምትሆነው? ቀደም ብዬ እኮ እጃችን ይሰራል ብዬህ ነበር አልገባህም መሰል ሲለኝ። ወንድሜ እኔ ታክስ የማይከፈል ገቢና ሥራ ሌብነት እንጂ ሥራ ነው አልልም በማለት ትንሽ ተፏገርንና በመጨረሻም የህዝቡን መከራ የምታበዙት እናንተ ናችሁ አልኩት። እንዴት አለ። ሰርቃቹሁም፤ ተበድራችሁም እዚያ ሥፍራና ቤት እየገዛችሁ ኗሪውን የጎዳና ሰው ያደረጋችሁ። ነገርየውን ሁሉ ያስወደዳችሁት አንተና መሰሎችህ ናቸሁ። እኔ መንግስት ብሆን እንደ እናንተ ላለው 100% ታክስ ነበር የምጥለው ስለው ብዙ ከተነፈሰ በህዋላ እንዴት አለኝ። የምትገዛው ቤት 10 ሚሊዪን ብር ካወጣ 20 ሚሊዪን አስከፍልሃለሁ። በ 10 ሚሊዪን ለሁለትና ለሶስት ቤተሰቦች ቤት እሰራበታለሁ። ቆጣ አለና ይሄ ሶሻሊዝም ነው ኮሚኒዝም አለኝ። ሁለቱም አይደለም። ፍርድ ላጡ መቆም ይባላል ስለው ዘጋብኝና ጫወታችን አበቃ። ስንቱ የሃበሻ ሌባ ነው በካናዳ፤ በአሜሪካ፤ በአውሮፓና በሌሎችም የሃገሪቱ ክፍሎች በመንግስት ቤት እየኖረና እየተደጎመ ሙሉ ስራው ሃገር ቤት የሆነ? ህሊና የሌለው ትውልድ! ሃፍረት የማይሰማው የገፋፊ ስብስብ።
ዛሬ በሃገራችን ኑሮ ከመወደድ የተነሳ ህዝባችን ጾሙን እያደረ ነው። በዚያ ላይ በዚህም በዚያም የታጠቁ ሃይሎች ሲያዋክቡትና ሲገድሉት አልፎ ተርፎም እንደ ከብት አግደው ገንዘብ ክፈሉ ሲሉት ስሰማና ሳነብ ሰው እንስሳ መሆኑን ለመረዳት ጊዜ አይፈጅብኝም። በሰው እንባና ደም የእለት እንጀራን ማግኘት። አድነኝ ነው የሚያሰኝ። መንግስት ተብየው የሚያስረው የሚገርፈው ከአስከሬን ጋር አብሮ የሚያሳድረው ለሃገርና ለወገኑ ያደሩትና የሰላም ሰዎችን ነው። ለምን ይሆን በቅርቡ ከእናቷ ፊት ታፍና ዘብጥያ የወረደችው ምሥራቅ ተረፈ? በእውነት ለመንግስት ስልጣን አስግታ ወይስ ሌላ የጊዜው አለቆች ያልወደድላት ጉዳይ አለ? ከክፋት መሰላል ወደ ሌላ የከፋ መሰላል እየተሸጋገርን ኖረናል ብለን እንሞታለን። መኖር አይበለው። ሁሌ ኡ ኡታ ሁሌ ለእኔ ብቻ። ሃገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል ያሉት ለካ ለዚህ ነው። ምንም የሃብት ክምር ቢኖርህ ከሞት አያድንህም። የሰው መኖር የሚለካው ለሌላው በመኖሩ ነው። እንደ አሳማ የተገኘውን ሁሉ በልቶና ጠጥቶ መድለብ ለፍርድ ቀን ራስን ማዘጋጀት ይሆናል። ያች ቀን ስትመጣ ደግሞ የሚሽራት ምድራዊ ሃይል አይኖርም።
ማነው ለትግራይ ህዝብ የቆመ፤ ስቃዪን የተካፈለ? ጠበንጃ አንጋቾች? በጭራሽ? ማነው ለአማራ ህዝብ መከራ ምንጩ ፋኖና ተፋላሚው መንግስት አይደሉምን? ማነው ለኦሮሞ ህዝብ ችግርና መከራ ተጠያቂው? ኦነግና መሰሎቹ አይደሉም? ግን በየዘሩ ለተሰለፈ ተውሳክ ሰውን በሰውነት አቻ አድርጎ የማየት አይኑ ፈሷልና ሁሉም በየጎጡ ያቅራራል። በመሃል ለሰላም ለደስታ ለነጻነት ቃል የተገባለት ህዝብ ያልቃል። ለገባው ከጦርነት ሰላም ይመረጣል። ዝንተ ዓለም ጠበንጃ ይዞ እንዘጥ እንዘጥ ከማለት ጥቂትም ቢሆን በሰላም ሰርቶ መኖር ይመረጣል። መንግስት ታጣቂዎችን ሲኮንን እነርሱ ብልጽግናን ሲሞግቱ ይኸው ህዝባችን በመሃል አለቀ። ኸረ ተው ልብ ግዙ። የዘር ፓለቲካ ለማንም አይጠቅምም። በሉ በዚህች የእንግሊዘኛ ግጥም ልሰናበታችሁ። ለገባው ይግባው።
The fruits of labor, once so near,
Are swept away, replaced by fear.
Each coin we save, each note we hold,
The worth they have, in time, grows old.