
ቴድሮስ አድሃኖም አዲስ አበባ አልመጣም!
መሠረተቢሱ መሠረት ሚዲያ!
ራሱን “ዓለምአቀፋዊ ጋዜጠኛ” ብሎ በመሰየም ለፈረንጅ ሚዲያ መሥራት እና አገርን መሸጥ፣ ባንዳ መሆንን ጌጡ ያደረገው ኤሊያስ መሠረት ህወሃት/ትህነግ ከመንበሯ ከተነቀለች ጊዜ ጀምሮ በዋንኛነት የያዘው አጀንዳ መርዘኛ ፕሮፓጋንዳውን በ“መረጃ” ስም መትፋት ነው።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፋኖ ትግል መሪ የሆነውን እስክንድር ነጋን ፊት ለፊት በማድረግ “ከመንግሥት ጋር በውጪ ድርድር እንዲደረግ የፋኖ ክንፍ ጠየቀ” ብሎ የሐሰት ወሬ በትኖ ነበር። ይህ ሆን ብሎ የፋኖ ኃይሎችን ለመበታተን እና አንድነት በመካከላቸው እንዳፈጠር ያስወራው ተራ አሉባልታ እንደሆነ ራሱ እስክንድር ወጥቶ ተናግሯል። መሠረተ ቢሱ ኤሊያስ ይህንን መረጃ ካወጣ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ “ይህ ሰው ያኔ ለወያኔ እንደሠራ አሁንም ለብልፅግና መሥራት ጀመረንዴ” ብለው አስተያየት የሰጡ ተስተውለዋል።
ከዚህ በፊት ኤሊያስ ከወያኔዎች ጋር በተለይም አየር መንገዱን የግል ቤቱ ካደረገው ተወልደ ገብረመድኅን ጋር በቅርበት ይሠራ እንደነበር ብዙ ሲባልበት ነበር። ተወልደም ለውለታው ኤሊያስን ለጫጉላው ሞሪሺየስ የነጻ ደርሶ መልስ የአውሮፕላን ቲኬት እንደሰጠው ስዩም ተሾመ ማስረጃዎቹን በማሳየት በገሃድ የተናገረው እውነታ ነው። የመረጃ ተዓማኒነትን እመዝናለሁ (ፋክት ቼክ) የሚለው ኤሊያስ፤ ተወልደ ቦሌ ኤርፖርት እስር ቤት እንደነበረው አንድም ጊዜ ሳይነግረን ለመቅረቱ ምንም ያለው ነገር የለም። መቼም አያፍርም “አላውቅም ነበር” ነው የሚለው።
ኤሊያስ ግን ሌላ የሚያውቀው መረጃ አለ፤ ያውም ከማንም በፊት የሚሰማው መረጃ። ያው እንደተመለደው “ምንጮቻችን” ነው የሚላቸው። ተወልደ አየር መንገዱን ዘርፎ ከአገር ሲኮበልል ቀድሞ ያወቀው ኤሊያስ ነበር። ከዚያም አሜሪካ ሲገባ፤ ከዚያም ዴልታ አየር መንገድ ሲቀጥረው ከተወልደ ቤተሰቦች ቀድሞ መረጃውን የሰበረው ኤሊያስ ነበር። ማን ይሆን የነገረው?
ኤሊያስ ለአሶሺየትድ ፕሬስ ሲዘግብ በነበረበት ዘመን ወያኔ /ትህነግ ሰዎች በየእስር ቤቱ እጅግ ሰቅጣጭ በሆነ መንገድ ያሰቃይ እንደነበር አንዴም ተናግሮ አያውቅም። ያው “አላውቅም ነበር” ነው የሚለው። እውነት ነው ሞሪሺየስ ሲዝናና ስለነበር አያውቅም።
ትህነግ/ህወሃት በየቀኑ ሚዲያ በሚባለው በሙሉ ሙልጭ ያለ የሐሰት ዜና ሲያቀርብ፤ በጋምቤላ 424 ንጹሐንን ከመሬታቸው ለማፈናቀል ብሎ ሲጨፈጭፋቸው አንዴም ለየትኛውም የውጪ ዜና አገልግሎት ዘግቦ አያውቅም። ያው “አላውቅም ነበር” ነው የሚለው። ግን የጋምቤላ ጭፍጨፋ በየዓመቱ ታኅሳስ ወር ሲከበር አንዴም ሰምቶ አያውቅም? ወያኔ በሚሰፍርለት ዳረጎት ከርሱን እየሞላ ስለነበር አይታየውም ነበር።
ሰሞኑን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ከመጀመሩ 15 ቀናት በፊት ኤሊያስ የትህነጉን ሰው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አዲስ አበባ ይመጣል ብሎ በእርግጠኛነት አወራ። ዜና ብሎ አወጣ፤ በዜናው ላይም “ለመሠረት ሚዲያ የደረሰው መረጃ” ብሎ የቴድሮስን መምጣት አስረግጦ ተናገረ። ይህም ሳያንሰው በዚሁ “ዜናው” ላይ ቴድሮስ ዳግም እንዳይመረጥ “የመንግሥት ሚዲያዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ዘመቻ ከፍተውባቸው” ነበር ብሎ አስተዛዘነለት። ግን ለምን እንዳይመረጥ እንደዘመቱበት ትንፍሽ አላለም። ለምን ይሆን?
ቴድሮስ አድሃኖም ገብረኢየሱስ ድጋሚ እንዳይመረጥ ከመንግሥት ይልቅ በርትተው የሠሩት የማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎች ናቸው። ወይም በሌላ አነጋገር የዓለም ሕዝብ ነው። ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ ከኮሮና ጋር በተያያዘ ቴድሮስ ከሥልጣኑ እንዲለቅቅ ዘመቻ የከፈተበት የዓለም ሕዝብ ነው። ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ቴድሮስ ይልቀቅ ብሎ ፔቲሽን የፈረመበት ወንጀለኛ ነው። ይህንን ባንዳው ኤሊያስ አይጽፍም። ለምን ይሆን?
እኔ እንደ ኤሊያስ ስላልሆንሁ ሌላውንም መረጃ ልንገራችሁ፤ ቴድሮስ ከሥልጣን መልቀቅ የለበትም ብለው “ኤሊያስና ጓደኞቹ” የድጋፍ ፊርማ አሰባስበውለታል። ፔቲሽኑን የጀመረለት ሚካኤል ገብረኢየሱስ ነው ይላል፤ 18ሺ ያልሞላ ፊርማ ተሰብስቦለታል፤ ያው ኤሊያስ ካለው የጥቅም ትሥሥርና ዝምድ አኳያ አልፈረምም ትላላችሁ?
ወደ ጉዳዩ ስመለስ ቴድሮስ አድሃኖም ገብረኢየሱስ፤ ኤሊያስ መሠረት አዲስ አበባ ይመጣል ብሎ እንዳወራለት ሳይመጣ ቀርቷል። ለምን ቀረ? ማን ጠየቀ? ደጋፊዎቹ ብቻ “መረጃ” እያለ የሚለቅላቸውን እያጋበሱ “ኤላ አንተ ትለያለህ” እያሉ ሳክስ ይነፉታል፤ እሱም እንደ ፊኛ ዝም ብሎ ይነፋል፤ ያብጣል።
ቴድሮስ ያልመጣው ግን በብዙ ምክንያቶች ነው። አንዳንዶቹ አስቂኝ ሌሎቹ ደግሞ አዛኝና አሳፋሪ ስለሆኑ እዚህ ላይ ለመናገር ስለማይመጥኑ ትቼዋለሁ። ሌላው ግን የወያኔ/ትህነግ (የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር) ዓለምአቀፍ አሸባሪ የወንበዴ ቡድን የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት ለማክበር በአስመራጭ ኮሚቴነት እያገለገለ ስለነበር ሥራ በዝቶበት ነው ብለው “ምንጮቼ ነግረውኛል” ልበል እንደ ኤሊያስ? ምን ያንሰኛል?
ኤሊያስ “ፋክት ቼክ” አድራጊ ነኝ ብሎ ራሱን ሾሞ በዚህ በገነባው ስም አሁን ደግሞ ትክክለኛ መረጃ አቅራቢ ነኝ ብሎ ዓይኑን በጨው አጥቦ የመጣ ድንቁርናው በረከት የሆነለት የተሸጠ ባንዳ ነው። እውነተኛ ፋክት ቼክ አድራጊ ቢሆን የቴድሮስን አለመምጣት በተመለከተ ማስተካከያ መስጠት ነበረበት። ይህንን ካነበብህ በኋላ ቀኑን ወደኋላ አድርገህ ከሰጠህ በዚህ ዲጂታል ዘመን አታመልጥም፤ ትያዛለህ።
ቴድሮስ ይመጣል ብሎ ማን ነገረህ? መረጃህ ትክክል ከነበረና ከቀረ ለምንድነው የቀረበትን ምክንያት ያልተናገርኸው? እኔው ልመልስልህ፤ አንተ ዓላማህ አጀንዳ መስጠት፤ ሕዝብን የሚጠቅም ሥራና አሠራር ማንቋሸሽ፣ ማራከስ ነው። ይህንን ደግሞ ለከፋዮችህ ተጠንቅቀህ የምትሠራው ነው። እነሱ ደግሞ ለባንዳነትህ ዳረጎት ይወረውሩልሃል፤ በዚያች ከርስህን ትሞላና አገር ላይ ትተፋለህ። አቤት ውርደት! አቤት ዝቅጠት!
ከመጨረሴ በፊት አንድ ነገር ልጠይቅህና ላብቃ፤ “ዓለምአቀፉ ጋዜጠኛ እያለ የሚያሞካሽህ” ቲክቫህ ለምንድነው “የመሠረት ሚዲያን” ዜና የማያትመው? ወይም ጠቅሶ የማይጽፈው? መሠረተቢስ ሆኖበት ይሆን? ኤላ ፋክት ቼክ ላድርግልንዴ?
ወዳጆቼ፤ ስለ ኤሊያስ የባንዳነት ተግባር፤ አሁን የት እንዳለ፤ ኬኒያ ከነማን ጋር እንደሚሠራ፤ መረጃ የሚጽፉለት እነማን እንደሆኑ የምመለስበት ጉዳይ ነው።
አሁንም ግን ደግሜ እላለሁ፤ ቴድሮስ አድሃኖም አዲስ አበባ አልመጣም፤ ኤሊያስ መሠረት “መረጃ አለኝ” ብሎ ያወራው ውሸት ነው፤ መሠረት ሚዲያ የዘገበው መሠረተ ቢስ መረጃ ነው። (ሁሉም ፎቶዎች በጸሐፊው የተላኩ ናቸው)
መሠረት አታላይ ነኝ ከዴንቨር
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣበ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply