
ሰፊው በቀለ ናደው ይባላል። በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ቀበሌ 03 ነዋሪ ሲሆን፤ ውልደትና እድገቱ ምንጭ ውሃ በሚባል አካባቢ ነው። ጁንታው ከነ ጀሌዎቹ ወደ ሥፍራው በመጣ ጊዜ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ለአማራ ልዩ ኃይሉ ስንቅና ትጥቅ በማቀበል ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ብዙ ተጋድሎም ፈጽሟል።
አባቱ ሻምበል በቀለ ናደው የቀድሞ ሰራዊት አባል ሲሆኑ፣ አያቱም ታሪክ እንዳላቸውና የእነርሱን ታሪክ ለመድገም ቆርጦ መነሳቱን ያስታውሳል። በዚህም ያለ ጥይትና ያለ ክላሽ በያዛት ስልክ ብቻ ጠላቱን እንደተዋጋ ይናገራል። ኦፕሬሽኑን ለሚመሩት አካላት ጠላትን እየተከታተለ መረጃ በመስጠት ትልቅ ጀብዱ ፈጽሟል።
ሰፊው የሹፍርና ሙያ ያለው ሲሆን፣ ጁንታዎች በመንገድ ቢያገኙት መታወቂያውን አይተው መኪና ሊያስነዱት እንደሚችሉ በማመኑ በመታወቂያው ላይ “ሹፌር” የሚለውን ሰርዞ “ሽመና” ብሎ አስተካክሎታል። እንዳለውም አንድ ቀን አግኝተውት መታወቂያውን አይተው ሽመና የሚለውን ምን እንደሆነ ጠይቀውታል። እርሱም የሽመና ሙያ ላይ ተሰማርቶ እንደሚሰራ አስረድቷቸው አለፉት።
የእርሱ ተልዕኮ ግን ሸውዶ ማለፍ ብቻ ሳይሆን እነርሱን ተከታትሎ ማስያዝ ስለሆነ በቅርብ ርቀት እንቅስቃሴያቸውን ይከታተላል። ከዚያም ለሠራዊቱ አመራሮች መረጃ በመስጠት እንዲለቀሙ አድርጓል።
ሠፊው የሚዋጋበት መሳሪያ ስለሌለው የእጅ ስልኩን እንደ መሳሪያ ተጠቅሞ የጠላት ተዋጊዎች የት እንደገቡ፤ ምን እንደሚሰሩና እንደሚያቅዱ እየተከታተለ ለመከላከያ ሠራዊቱ መረጃ ስለሚያቀብል የሚሰወር አንድም ጁንታ የለም።
እመጫት ሚስቱን ለዘመዶቹ አስረክቦ ጁንታን በባዶ እጁ ለመፋለም የወጣው ሰፊው፤ ጣራ በምትባል ቦታ ላይ በርካታ የጁንታ ታጣቂዎችን በመጠቆም እንዲደመሰሱ አድርጓል።
ከጋይንት እስከ ሳሊ ድረስ ተከታትሎ ብዙዎች እንዲደመሰሱ በማድረግ ጠላት ሲመታለት ወኔ እየተሰማው መረጃ ማቀበሉን ቀጠለ። የጁንታው ታጣቂዎች በአካባቢው በምትገኘው የኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በኩል ቆርጠው በመግባት ጥበቃውን ነጭ ጋቢ አልብሰው ወደ ሳሊ ደን ሲያመሩ በጥብቅ ሲከታተላቸው የነበረው ሰፊው መረጃውን ሲያቀብል ከ40 በላይ የጠላት ኃይል ተደምስሷል።
ሥራው ውጤታማ እየሆነለት ሲመጣም ወደ ኋላ ሳይል ግድም ጭርቆስ በምትባል አካባቢ ጎጥ ሥር ተቀምጦ ጁንታ ደብቀሃል አልደበቅኩም እየተባበሉ ሲከራከሩ የነበሩ ሰዎችን ሰምቶ በድብቅ ተከታትሎ በአንድ ቤት ውስጥ የተደበቀውን የጁንታ አባል በመያዝ ለሚመለከተው አካል አስረክቧል።
ሳሊ በምትባል አካባቢ ተደብቀው የነበሩትን ዘጠኝ የጁንታ ታጣቂዎችን ከነ መሳሪያቸው እንዲሁም ቁስለኛን አብሮ በመያዝ ታሪክ የሰራ ጀግና ነው። እስካሁን በሠራው የጀብድ ሥራ አንድ ቁስለኛን ጨምሮ ከማረካቸው 15 ጁንታዎች 11 አንዱን ከነ መሳሪያቸው በግምባሩ ላሉ የመከላከያ አመራሮች አስረክቧል።
እስካሁን የሰራውን ጀብድ ወደ ፊትም እንደሚቀጥል ሰፊው ተናግሯል። ጁንታው እስከሚያልቅ ድረስ በሁሉም መንገድ ፍልሚያውን እንደሚቀጥል ቃል ገብቷል።
የሰፊውን ሥራ ሲከታተሉ የቆዩት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎችም ይህን ጀብድ የተመለከተው በግምባሩ ያለው የመከላከያ ሠራዊት አመራር በሚመለከተው አካል በኩል ህጋዊ የሆነ ክላሽ ሲሸልመው መመልከት ችሏል። ትላንት በባዶ እጁ ሲማርክ የነበረው ሰፊውም ክላሹን አንግቦ ወደ ውግያው ቦታ በመሄድ ጠላትን እየተፋለመ ይገኛል። (አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply