አሸባሪው የህወሓት ቡድን በዛሪማና አካባቢው ሰርገው በገቡባቸው ቀናት የተለያዩ ግፍና በደሎች መፈፀማቸውን ተጎጂ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
በዛሪማ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ የተከራየውን ንብረትነቱ የኪዳነምህረት ገዳም የሆነ ህንፃ የሚቆጣጠሩት አባ ገብረማርያም ሳሙኤል እንደተናገሩት፣ አሸባሪ ቡድኑ እኔን እንኳ በአባትነት ሳያከብሩኝ ገፍትረው ጥለው የባንኩን ኤቲኤም ማሽን ሰብረው መዝረፋቸውንና ወደውስጥ በመግባትም የፈለጉትን አድርገው መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዛሪማ ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ባዬ አትክልት እና አቶ ዳግማዊ ገነነውም የሽብር ቡድኑ ዘራፊዎች የሞቀ ቤታቸውን በማዘጋት ሱቃቸውንና የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሳቸውን እንደዘረፏቸው ገልጸዋል፡፡
ቋንቋና ዘርን እየለዩ አሰቃይተውናል ያሉት አቶ ባዬ እና አቶ ዳግማዊ መሳሪያ ተደግኖባቸው እጃቸውን ወደላይ እንዲያነሱ ተደርገው ከኪሳቸው ብር እና ልብሶቻቸው ጭምር እንደተወሰዱባቸው አስረድተዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በዘር ፣ በብሄርና በሀይማኖት እየለየ መግደል፣ መዝረፍና ማሰቃየት መለያው እንደሆነ የሚያስረዱት መሃመድ ሱለይአደም የእምነቱ ሰዎች ሶላት ላይ በነበሩበት ሰዓት ወደ መስጊዱ በመግባት የሰጋጆቹን ኪስ በመፈተሽ የነበራቸውን ገንዘብ ሁሉ መቀማታቸውንና አውልቀውት የነበረውን ጫማ ሳይቀር መውሰዳቸውን ገልፀዋል፡፡
መከላከያ ሰራዊቱ፣ የአማራ ልዩ ሀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ዛሪማና አካባቢውን ከተቆጣጠረ በኋላ ከሰቀቀን ወጥተው እንቅልፍ መተኛት መቻላቸውን ከምስጋና ጋር ተናግረዋል ሲል የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply