• አንድ ሺ 564 ሰዎች በጭካኔ ተገድለዋል።
• 81 ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
• ድርጊቱን የፈጸመው አሸባሪው ሕወሓት ያደራጀው ሳምሪ የሚባል ገዳይ ቡድን ነው።
የዛሬ ዓመት በማይካድራ በተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ አንድ ሺ 564 ሰዎች በጭካኔ መገደላቸውን፤ 81 ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ድርጊቱን የፈጸመው አሸባሪው ሕወሓት ያደራጀው ሳምሪ የሚባል ገዳይ ቡድን መሆኑን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህርና ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት የጥናት ቡድን መሪ ገለጹ።
የጥናት ቡድኑ መሪ አቶ ጌታ አስራደ አለማየሁ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የዛሬ አመት በማይካድራ ጭፍጨፋውን ያካሄዱት ሳምሪ የተባለ አሸባሪው ሕወሓት ያደራጃቸው ገዳይ ቡድን ነው። ይህ ቡድን አንድ ሺ 564 ሰዎችን መጥረቢያ፣ ቆንጨራና፣ ቢለዋ፣ ማጭድና መሰል መሳሪያዎችን ተጠቅሞ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ አካሂዷል።
ገዳይ ቡድኑ በአሸባሪው ሕወሓት የጦር መኮንኖችና በልዩ ኃይል አባላት ሥልጠና የተሰጠው መሆኑን አመልክተው፤አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ በተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ሽንፈት መከናነቡን ሲረዳ በወልቃይት፣ በጠገዴና በማይካድራ በጭካኔ የተሞላ የዘር ጭፍጨፋ ለማካሄድ አደረጃጀት መፍጠሩን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ጌታ አስራደ ገለጻ፤ የትግራይ ተወላጅ የሆነ ሳምሪ የተባለው የወጣቶች ቡድን የዘር ጭፍጨፋ እንዲካሄድ አሸባሪው ሕወሓት የጦር መኮንኖችና የልዩ ኃይል አባላቶች ሥልጠና ሰጥቷል። ሥልጠናው ከትግራይ ብሔር ውጪ ያሉ የአማራ ተወላጆችን እንዴት ለይቶ በጭካኔ መግደል እንዳለባቸው በተግባር የታገዘ ሥልጣና ያገኙ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ከትግራይ ተወላጆች ውጪ ያሉ ነዋሪዎችን መታወቂያና ሲም ካርዳቸውን በመሰብሰብ መዝግበዋቸው እንደነበር ያወሱት አቶ ጌታ አስራደ፤ በስም ዝርዝራቸው መሠረትም ገዳይ ቡድኑ ቤት ለቤት በመሄድ በመጥረቢያ፣ በቆንጨራና፣ በቢላዋ፣ በማጭድና በመሰል መሣሪያዎች ጭፍጨፋ ማካሄዳቸውን አስረድተዋል።
ድምጽ አልባ መሣሪያዎችን የመረጡበት ምክንያትም ወደ ከተማው የሚገቡ ሰዎች የመሳሪያ ድምጽ ሰምተው እንዳይመለሱና በማይካድራ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች የማምለጥ ሙከራ እንዳያደርጉ ታስቦ መሆኑንም ገልጸዋል። ለማምለጥ የሚሞክሩ ካሉ በከተማዋ መውጫና መግቢያ በሮች ላይ መሳሪያ የታጠቁ አልሞ ገዳዮች ተዘጋጅተው እንደነበር ጠቁመዋል።
ስለ ማይካድራ የዘር ጭፍጨፋ አብዛኛውን መረጃ የተገኘው በወቅቱ ከተጎዱ ሰዎች መሆኑን ቡድን መሪው አመልክተው፤ በ24 ሰአት ውስጥ አንድ ሺ 564 ሰዎች ተገድለዋል፤ 81 ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎችም አሉ ብለዋል።
ከተገደሉት መካከልም በልጁና በሚስቱ ፊት በጩቤ አርደው ከገደሉት በኋላ በእሳት ያቃጠሉት ጎልማሳ ግለሰብ ይገኝበታል። ይህ ደግሞ ምን ያህል ጨካኝና አረመኔ መሆናቸውን የሚያሳይ ድርጊት መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል። (ኢፕድ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
ሲጀመር ወያኔ አማራ ጠል ነው። አሁንም ወደፊትም በአማራ ላይ ያለው የትርክት ጥላቻ ይቀጥላል። ድርጅቱ በውሸት የተካነ፤ ለውጭ ሃይሎች ያደረ ለሃገርና ለወገን ግድ የማይሰጠው የማፊያ ጥርቅም ነው። አሁን እንሆ በአሜሪካና በተከታዪቿ እየተመራ በፈጠራ ሽብር በወሬ አናፋሾቹ በኩል ህዝባችን የሚያናውጡት ለኢትዮጵያ ህዝብ አዝነው የሚመስለው ካለ ስቷል። እነ አየርላንድ፤ ኖርዌ እና ሌሎችም አሁን የሚያናፍሱት የትግራይ ህዝብ አለቀ ጩኽት ባለፈ ትርክት ስለተለከፉ ነው። የሚገርመው ግን ነጩ ህዝብ ለጥቁር ህዝብ ያዝናል በማለት መታሰቡ ነው። በጭራሽ። አሁን የትግራይ ህዝብ ተራበ፤ ኡ ኡ የሚሉት ጎዶች ወያኔ በስልጣን ላይ እያለ ያደርስ የነበረውን ግፍ ሁሉ እንዳላየ አይተው ያለፉ ናቸው፡፡ አንባቢ ወይም የጊዜውን የሃገራችን የሚዲያ ሽፋን የሚከታተል ለምን ይሆን ይህን ያህል ትኩረት የተሰጠው ይል ይሆናል። አንደኛው ምክንያት የሚያወሩት የተሻለ ወሬ የለም። ሁለተኛው ተከፋዪችና ብላቢ የተገዙ የመንግስታት ጉዳይ አስፈጻሚዎችን ትዕዛዝ ለመፈጸም ነው። የእንግሊዙ ቢቢሲ ኦንላይነ በቀን ከሶስት ዜና በላይ በትግራይ ብቻ ያተኮረ ያወጣል። ሌላው ሽርፍራፊ ሳንቲም ለመሰብሰብ በተለያዪ ሶሻል ሚድያ ላይ የሆነ ያልሆነውን ይለጥፋል። የዚህ ሁሉ ወሬ ድምር ግን የውሸት ክምር ነው። ለምሳሌ – ወያኔ ተወቃ፤ ተደመሰሰ፤ ፈረጠጠ፤ ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር አለቁ እየተባልን ወያኔ ግን ከትግራይ ምድር ርቆ በአፋርና በአማራ ክልል ላይ ያደረሰው የመከራ ዝናብ ከጣሊያኑ ወረራ የከፋ ነው። ታዲያ ሽለላው፤ ፉከራው፤ የጦር ሃይሉ ገድል፤ የአየር ሃይሉ ድብደባ ወዘተ ያመጣው ለውጥ የለም። እንዲያውም በጦርነቱ ለመካፈል ወደ ውጊያው ቀጠና የገቡ ገበሬዎች፤ ፋኖዎችና ሌሎችም ቆዪ ጠብቁ ት ዕዛዝ እየተባሉ በጎን በኩል ደግሞ ወያኔ ሰሜን ሸዋ ድረስ ገብቶ ህዝብ እየጨረሰ ነው። ወደ ኋላ እየሮጡ የት ሊደረስ ነው? አሁን እንሆ የምዕራባዊያንና የወያኔን ፕሮፓጋንዳ ወደ ጎን አርገን በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ስናይ የሚነግረን ይዋጋል የሚባለው ሰራዊት እያፈገፈገ እንዳለ ነው። ውጊያ ከጊዜ ጋር የሚፈጸም ጉዳይ ነው። ሰው በሰላ ጭንቅላትና በተቀናጀ መልኩ በአንድ በኩል ድል ሲቀናጅ በሌላ በኩል ያለው ሃይሉ ጉልበት ያገኛል። አሁን የምናየው የፓለቲካ አሻጥር ግን ለወያኔም ሆነ ለቀሪዋ ሃገራችን የሚጠቅም አይሆንም። ወያኔ በባድሜ በኩል ከኤርትራ ሰራዊት ጋር ፍልሚያ ቢገጥም ማንም ወያኔን ደግፎ ውጊያ የሚገባ አይኖርም። የትግራይን ህዝብ ከሌላው ህዝብ ጋር ደም አቃብተውታል። የሰሜኑን ጦር በተኛበት ሲረሽኑ የገደሉት አማራ ወታደሮችን ብቻ አይደለም። የብሄር ብሄር ስብስብ ወታደሮችን እንጂ። በእያንዳንድ ቤት ሃዘን ገብቷል። ይህ የሆነውም በወያኔ አርነት (ባርነት) ትግራይ ነው።
እንግዲህ ጉዳዪ እንዲህ ከሆነ የወያኔ ወደ አዲስ አበባ እየተጠጋ መሄድ ለሽብር እንጂ እንደገና መንግስት የመሆን አላማ የለውም። እንዲያውም አሁን የትግራይ ሚዲያዎችን ለተመለከተ ተገንጥለዋል ለማለት ይደፍራል። ደብረጽዪንን የትግራይ ፕሬዚደንት ሲሉት አፍራሽ ሃይላቸውን የትግራይ ሰራዊት ነው የሚሉት። እኔ በትግራይ መገንጠል ችግር የለብኝም። ግን በመሃል ሃገር ተደላድለውና ሃብታም ሆነው የሚኖሩት ሁሉ እቃቸውን ጠቅለው መቀሌ መግባት አለባቸው። ያ ካልሆነ በመካከላችን በመሆን ሁልጊዜ ሸፍጥና መከራ እንደዘሩብን ይኖራሉ። ባጭሩ ወያኔ ሃብት አካፍሉን ማለቱ ፍቺ እንደሚፈልግ ያሳያል። የፍቺው ወረቀት ይሰጣቸውና ሃገር ይሁኑ። ግን ያቺ ምድር የመከራ ዝናብ ከአሁን በባሰ ይዘንብባታል። ወያኔዎች ያለ ጦርነት ሌላ ነገር ማምረት አይችሉም።
በማጠቃለያው ሰላም ሰላም እርቅ እርቅ የሚባለው ሁሉ ቱልቱላ ነው። እርቅ ከወያኔ ጋር የሚታሰብ አይደለም። እነርሱም አይፈልጉትም። እየገደሉ መሞት ነው የሚፈልጉት። የኢትዮጵያ መንግስት በምርኮ የያዛቸውን ሁሉ ቆጥሮና መዝግቦ ይዞ ወያኔ ከያዛቸው ጋር የእስረኛ ልውውጥ በማድረግ ለቀይ መስቀል አስረክቦ የወያኔን ምርኮኞች መቀሌ መስደድ አለበት። በምንም ሂሳብ እነዚህ ሰዎች ከትግራይ የበላይነት ውጭ ምንም ነገር አይቀበሉም። ውሸትን ተግተዋል። ወያኔ መልሶ ጦርነት ውስጥ ሲማግዳቸው ያኔ ሁሉን ነገር ማገናዘብ ይችላሉ። ዝም ብሎ እነዚህን ሰዎች እያጠራቀሙ መቀለቡ አስቸጋሪና በህዋላ ጉዳት የሚያመጣ ነው የሚሆነው።
በመዝጊያ እናተርፋለን ብለው ከሱዳን፤ ከግብጽ፤ ከአሜሪካና ከሌሎች ሃገር በቀል የወያኔ ቅጥያ ሙታኖች ጋር ቁጭ ብድግ የሚሉ ሁሉ ትርፋቸው ሞትና ውድመት ነው የሚሆነው። ሃገሩን አፍርሶ ሃገር የሰራ ሃገር የለም። የተከመረ የእህል ክምር የሚያቃጥል የእብድ ሃገር ተራብኩ ቢል ማን ይሰማዋል? አሁን የተመድ የእርዳታ ድርጅቶች ዋይታ ለሃገራችን ህዝብ አዝነው ሳይሆን በዚሁ ግርግር የሚበላ ብዙ ገንዘብ ስላለ ነው። ዝርፊያው ስር ሰደድ ነው። ገዢው ይሰርቃል። ጭኖ ስፍራው የሚያደርሰው ይሰርቃል። ስፍራው ከደረሰ በህዋላ ይሰረቃል ኸረ ስንቱ ብቻ ይህን ለማወቅ የፈለገ ሱዳን ባሉ የመጠለያ ጣቢያዎች ሂዶ ከጎበኘ በህዋላ ገቢያ ወጥቶ የሚቸበቸበውን የእርዳታ ቁሳቁስና ምግብ ማየት ይቻላል። በስደተኞች ስም የሚያተርፉት ብዙ ናቸው። ለስደተኛው የሚደርሰው ኢምንት ብቻ የሆነ ነገር ነው። መጠቅለያው ስላማረ ምግቡ የጤና ነው፤ መድሃኒቱ ፈዋሽ ነው የሚሉ ጅሎች ረጋ ብለው ሁሉን ሊመረምሩ ይገባል። በተሎ የወያኔ መስፋፋት ካልቆመ ምድሪቱ ዶጋ አመድ ስትሆን ይታየኛል። በቃኝ!