“መግደልም መድፈርም መብታችን ነው” – “ተገድደነው የዘመትነው” የሚሉት የትህነግ ታጣቂዎች
ዕድሜያቸው 50ዎቹን ያለፈው የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪዋ አዛውንት በአሸባሪው የህወሓት ታጣቂዎች በቡድን ከተደፈሩ በኋላ ራሳቸውን አጥፍተዋል።
ፖሊስና የአካባቢው የዓይን እማኞች በሥፍራው ለሚገኙት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች እንደገለጹት፤ ዕድሜያቸው 50ዎቹን የተሻገረውና የሸዋሮቢት ከተማ ቀበሌ 02 ነዋሪ የነበሩት ወይዘሮ ሞሚና አህመድ (ስማቸው የተቀየረ) በአሸባሪው የህወሓት ታጣቂዎች በመደፈራቸው የልጄን ዓይን ከማይ ብለው ራሳቸውን አጥፍተዋል።
ወ/ሮ ሞሚና የማገዶ እንጨት በመሸጥና እንጀራ በመጋገር የሚተዳደሩ ሲሆን፤ የ15 ዓመት ታዳጊ ልጅ እንዳላቸው የሸዋሮቢት ከተማ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሀላፊ ኮማንደር አህመድ መሐመድ ለኢፕድ ገልጸዋል።
ኮማንደሩ እንዳሉት፤ ግፈኛው ቡድን ልጃቸው ላይ በር ቆልፎ እናቱን ወደ ሌላ ቤት በመውሰድ አስነዋሪውን ግፍ ፈጽሟል።
በተመሳሳይ ከወ/ሮ ሞሚና ጋር በአንድ ቤት በአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች አብረው የተደፈሩት ወይዘሮ አለምሸት አሸብር (ስማቸው የተቀየረ) ከሟች ጋር አንድ ቤት እንደነበሩ እና እየተፈራሩቁ በሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል በደል እንዳደረሱባቸው ይናገራሉ።
ዛሬም በሳቸውና በጓደኛቸው ላይ የተፈጸመው በደል ያንገበግባቸዋል። እሳቸው በህይወት ተርፈው ጓደኛቸውን የነጠቃቸውን ግፍም በሲቃ ተሞልተው ይናገራሉ።
ጓደኛየ በደሉ ከደረሰባት በኋላ “ከዚህ በኋላ የልጄን አይን የማይበት ዐይን የለኝም’ ብላ ራሷን አጠፋች” ሲሉ ተናግረዋል።
እርሳቸውም በታጣቂዎቸ የተደፈሩት በቡድን መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ አለምሸት፤ ከሞራል ስብራቱና በደሉ ባሻገር አከላዊ ህመም እየተሰማቸው እንደሆነ ለኢፕድ ገልጸዋል።
የራስ ጸጉራቸውን በመንጨት ብዙ እንግልት በማድረስ ሁለቱን አዛውንት አየተፈራረቁ ድርጊቱን እንደፈጸሙባቸው ወይዘሮዋ የነገሩን ሀዘንና ሲቃ በተሞላበት አንደበታቸው ነው።
እነዚህ አረመኔዎች ግፉን ከመፈጸማቸው በፊት “እንጀራ አምጡ” ብለው ጠይቀው በእጃቸው ከበሉ በኋላ እንደሆነና፤ “መግደልም መድፈርም መብታችን ነው” እያሉ በመሳሪያ አስፈርርተው ድርጊቱን እንደፈጸሙ ተጎጂዋ ተናግረዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች ንጹሃንን በጅምላ መግደል፣ ህጻናትና አዛውንት ሴቶችን መድፈርና ንብረት ማውደም መፈጸሙን የሰብአዊ መብት ተቋማት ጭምር እየገለጹ ይገኛሉ። (ኢፕድ፣ አዲሱ ገረመው፣ ሸዋሮቢት)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
በምድራችን አረምና አራሙቻ እየበቀለ ህዝባችን በዚህም በዚያም ማወክ ከጀመረ ረጅም ዘመን ቆጥረናል። አብሮ መክሮ ወገኑን ያስገደለ፤ ምንም ባልሰራው (ችው) በጥይት ተደብድበው የሞቱ፤ አካለ ጎድሎ የሆኑ፤ ይህን ያዪ ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ጎረቤት ሃገሮችና ወደ አውሮፓና ሌሎችም የነጭና የዓረብ ሃገሮች ሲያፈተልኩ እንደ ወጡ ቀርተዋል። አሁን ወያኔ የከተማ ሰው ከሆነ ወዲህ የተሰራውና የሚሰራው ግን ከሰውነት ደረጃ የወረደ ፍጽም አውሬነት ነው። አሁን በምንፋተግበት የእብዶች ጦርነት የውሸት ጋጋታና የማጋነን ወሬዎች ውስጥ ስንት ሃሰትና የፕሮፓጋንዳ ጡሩንባ እንደሚነፋ ልብ ላለ ይታየዋል። ታዲያ ከመቀሌ ዶ/ር ደብረጽዪንና አንድ የወያኔ ጄኔራል ጦርነቱ አልቋል ከማን ጋር ነው የምንደራደረው ሲሉን አሁን ደግሞ ዶ/ር አብይ ጦርነቱ አልቋል፤ ወያኔ ተበትኗል ተብለናል። በዚህ መካከል ግን ህዝባችን በዚህም በዚያም እንደ ቅጠል ይረግፋል። የዶ/ር ደብረጽዪንን የቅርብ ቀን መግለጫ ላዳመጠ የወያኔን እብደት ማቆሚያ እንደለሌው ማየት ይቻላል። ትላንትም ውሸት፤ ዛሬም ውሸት፤ ትላንትም የትግራይ ህዝብ ዛሬም በትግራይ ህዝብ ላይ ቁማር መጫወት። አሁን ማን ይሙት ወያኔዎች ስፍራ ለቀው የወጡት ወደው ነው? ጭራሽ? እየገደሉ፤ እያፈረሱ፤ እየዘረፉ፤ በደቦ ሴቶችን እየደፈሩ ነው በጦርነት ተሸንፈውና እየተሸነፉ እንጂ። ይህ ትውልድ ከዚህ ፍትጊያ እንኳን ተርፎ መኖር ቢችል የህሊና ችግር እንደሚኖርበት ምንም አያጠራጥርም። ታላቋ ትግራይን እንመሰርታለን የሚለው የወያኔ ጡሩንባ ያቺ ታላቅ ትግራይ ለማን እና በእነማን ነው የምትመሰረተው? ሰው ሁሉ ካለቀና አካለ ጎደሎ ከሆነ በህዋላ ለማን ነው ያቺ የህልሟ ትግራይ የምትቆመው?
ልቤ እጅግ ያዝናል በደረሰባት በደል የተነሳ ደጋፊ አጥታ ራሷን ያጠፋቸው እህታችን ሳስብ። አይ ሃገር እንዲህ ሆንን ብለን ብለን ዘርና ቋንቋ እየቆጠርን ሰውን ብቻ ሳይሆን እንስሳትንና የተከመረ እህልን ሁሉ የምናቃጥል የሙታን ጥርቅም። ወያኔ ጉድጓድ መግባት ያለበት ድርጅት ነው። በሚሊዪን የሚቆጠሩ ሰቆቃዎችን ያደረሰና በማድረስ ላይ ያለ ድርጅት ምህረት ሊደረግለት አይገባም። እኔን የሚያናድኝ የወያኔ የጭፍን ደጋፊዎች የትግራይ ተወላጆች ናቸው። እውነቱንና ፕሮፓጋንዳውን እንዴት ሰው መለየት ይሳነዋል? በወያኔ ስንት የትግራይ ልጆች ነው የተገደሉት? አሁንስ በዚህ ግጭት የሚረግፉት? ደብረጽዪን አሁንም ጥሉ ከአማራ ህዝብ ጋር ነው። ልብ ይሰብራል። አማራ የትግራይ ህዝብ ላይ ምን በደል ፈጸመ? ወያኔ ግን ለዘመናት የአማራን ህዝብ ሲያተራምስና አምካኝ መርፌ ሁሉ ሲወጋ የኖረ ለመሆኑ አሊ የማይባል መረጃ አለ። ያው ግን የሽፍጠት ፓለቲካ ጠላትህ መጣ፤ ተወረርክ፤ ተያዝክ፤ እናትህ ሚስትህ እህትህ ልትደፈር ነው በማለት ነው ሰውን ወደ እሳት የሚማግደው። ዶ/ር አብይ የውጭ ሃይሎች ከወያኔ ጋር ሆነው እየተዋጉ ነው እንዳለው ሁሉ አሁን ደግሞ የወያኔ ጭፍን መሪ የውጭ ሰዎች ገብተው እየተዋጉን ነው በማለት አላዝኗል። በሁለቱም ጎን ግን የቀረበልን መረጃ የለም። ይህ ደግሞ እንደተባለው የጦርነትን ቀዳሚ ሰለባ እውነት ራሷ መሆኗን ያሳየናል።
አርቲ ቡርቲውን የሃበሻ ፓለቲካ ወደ ኋላ ጥሎ ነገሮችን በረጋ መንገድ ለተመለከተ የዓለም መሳቂያ መሆናችን ያሳያል። እኛው የቆመን ሁሉ አፍርሰን፤ አቃጥለን አሁን ተመልሰን ተራብን፤ በሽታ ገባ፤ እንዲህና እንዲያ ሆንን ብንል ሰሚ የለም። የሰሙን ከመሰለንም እኛኑ የሚያናኩር ነገር ቋጥረው እንጂ በቅንነት ሃገርን አይረድም። ይህ አሁን በድህረ ገጾች ላይ የምናየውና የምንሰማው የቀድሞ የአውሮፓና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በዶላር ከተገዙ ሃገር ሽያጭ ሃበሾች ጋር በመሆን የሚሸርቡት ሴራ ከአንድ ምንጭ መቀዳቱን ያሳያል። ያስገርማል። It is rehearsed play. በተናጠልም ሆነ በህብረት የሚሰጧቸውን ቃለ መጠይቆች፤ ማስጠንቀቂያዎች፤ የድጋፍ ሃሳቦች ላጤነ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ፓሊሲ የተቀዳ ሁሉም የፈረሙበት ለመሆኑ አያጠራጥርም። እነዚህ ናቸው ሰለ ሰላምና ዲሞክራሲ ዓለም ሊያስተምሩ የሚሹት። የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች እንዲሉ። ዛሬ በአውሮፓ፤ በአሜሪካ በራችው ድረስ የተኮለኮሉት ጥገኝነት ጥያቄዎች የመጡት ነጩ ዓለም ተባብረው ከደረመሷቸው ሃገሮች ነው። ገና ብዙ ይነጉዳል። ግን ያልታበሱ እንባዎች አይዞሽ አዞህ ብሎ የሚያጽናናቸው ወገን ሳያገኙ በተስፋ መቁረጥ ራሳቸውን ሲያጠፉ ምንኛ ያሳዝናል። ዘሩን ጎሳውን፤ ቋንቋውንና ሃይማኖቱን ወግድልኝ ብሎ በሰውኛ ልብ ላሰበ እየየው ያሰኛል። ግን ሁሉ አልቃሽና አስለቃሽ በሆነበት የሃበሻ ምድር መሰማማት የት አለና። ግን መቼ ይሆን መገዳደላችን የሚያበቃው? ጊዜ ይመጣ ይሆን? አላውቅም።
እውቁ አሜሪካዊ የህዋ ተመራማሪ Carl Sagan ከዘመናት በፊት “Pale Blue Dot” እንዲህ ይለናል። ፈልጋችሁ ራሱ ሲናገር ብትሰሙት የበለጠ የሃሳቡ ጥልቀት ይገባቹሃል። ያም ሆነ ይህ ቅንጫቢ ሃሳቡ እንሆ።
The Earth is a very small stage in a vast cosmic arena. Think of the rivers of blood spilled by all those generals and emperors so that, in glory and triumph, they could become the momentary masters of a fraction of a dot. Think of the endless cruelties visited by the inhabitants of one corner of this pixel on the scarcely distinguishable inhabitants of some other corner, how frequent their misunderstandings, how eager they are to kill one another, how fervent their hatreds.
አምናለሁ በዚህም በዚያም ለሰው ልጅ ህሊናው ይመሰክርለታል። ግን ምንም ያልሰራ ሰው ዝቅዝቆ የሚሰቅል፤ ይህ መሬት ላይ ያንቺ ልጅ አይወለድም በማለት የነፍሰጡር ሴት ሆድ ቀዶ ልጅ የሚያወጣ፤ እናቱን፤ እህቱን ወንድሙን አባቱን ገድሎ የሚፎክር፤ ያለምንም ሃፍረት ሴት ልጆችን በደቦ የሚደፍር የአውሬ ስብስብና መሪዎችሁ በመዘዙት ሰይፍ ይወድቃሉ። በታሪክ ያየነው ያን ነው። እስከዚያው ግን በዚህም በዚያም መገዳደሉ ይቀጥላል። በቃኝ!