ፖለቲከኞችን አስሮ ድርድር፤ ካድሬ አሰልፎ እርቅ – “አዙረኝ አታዙረኝ” እንዳይሆን

 • ከውጭ ያለው ችግር ከተፋዘዘ ብሄራዊ ስሜት ጋር!!

ኢህአዴግ በከፋ ቀውስ ውስጥ ይገኛል። ቀውሱ ከውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭም ነው። ሰሞኑን ይፋ የሆኑ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ውጥረቱ በውስጥ ካለው ብሄራዊ አንድነትና ኅብረት መደብዘዝ፣ ህዝብ እያደር ስርዓቱን መጠየፉ፣ የራሱ የፓርቲው መበስበስና በሙስና መርከስ፣ የውስጥ የእርስ በእርስ መከዳዳታን በአይነ ቁራኛ መጠባበቅና ከአቻ ፓርቲዎች መንሸራተት ጋር ተዳምሮ አስጊ ሆኗል።

ከውጭ – የሚደገስልን ቀውስ

በጨረፍታ ለማንሳት ያህል ግብጽ ዑጋንዳን ይዛ በደቡብ ሱዳን ውስጥ እያቦኩ ያሉት ጉዳይና ደቡብ ሱዳን በማስታውቂያ ሚኒስትሯ አማካሪ በኩል አቋሟን ይፋ ማድረጓ ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያበረክተው የቀውስ ፍም ተደርጎ እየተወሰደ ነው። ከኢህአዴግ የቅርብ ሰዎች እንደሚሰማው ዑጋንዳ በደቡብ ሱዳን ድንበሯ አካባቢ ኃይል አሰባስባለች።

ኢህአዴግ እትብታቸው ከተቀበረበት ያባረራቸው የጋምቤላ ተወላጆች ከቋጠሩት ቂም ጋር ደቡብ ሱዳን አሉ። የቤኒሻንጉል አኩራፊዎችም የሚንደረደሩት ከዚያው ነው። የራሱ የጋምቤላ አማጺዎችም እዛው አሉ። የደም ትሥሥርም አለ፤ አኙዋክና ኑዌር በሁለቱም አገራት ይገኛሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሳል ቫኪርን መንግስት ለመጣል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ኢህአዴግ እንደሚረዳ መረጃ አለ። ጉዳዩ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ ቆይቶ ደቡብ ሱዳን ግብጽን በገሃድ ማሞገስና “የሰላሜ ባለውለታ” እስከማለት ደርሳለች። በቅርቡ ከግብጽ ጋር ያደረገችውንና በተቃዋሚዎች “ቆሻሻ” ስለተባለው ስምምነት “ለኢትዮጵያ መንግስት የማሳወቅ ግዴታ የለብንም” ሲሉ ወደ ግብጽ ማዘንበላቸውን አውጀዋል።

“እናፈናጥረዋለን። ውጊያ ከተጀመረ የሚቆመው አስመራ ነው” እያሉ አፋቸውን የሚወለውሉበት ሻዕቢያ በቀይ ባህር ላይ ከአረብ አገራት ጋር እየገነባ ያለው ኃይል፣ እየታጠቀ ያለው መሳሪያና እያደረገ ያለው የጦር ስምምነት ሌላው ርዕደተ ህወሃት ሆኗል። ስጋቱ ከላይ ከተገለጸው የውስጥ ችግር ጋር ተዳምሮ ፖለቲካዊ መርበትበት ውስጥ ከቷቸዋል። ችግሩና ቀውሱ ውጫዊ ነውና “በጥልቅ ታድሼ” የሚባልለት አይሆንም። ሊሆንም አይችልምና ስጋቱ እንደተፈራው አገርና ሕዝብንም የሚያስጨንቅ እንዳይሆን ባለሙያዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተላላኪነት ሶማሊያ ዘልቆ በመግባት የፈጸመው ወንጀል የቋጠረልን በቀል አለ።

ከውስጥ – የቀረበልን የአሳር ቡፌ

ህወሃት እና እገዛዋለሁ የሚለው ሕዝብ የመጨረሻ ውላቸው /ውሉ የጉልበት ቢሆንም/ ላይታደስ የፈረሰው ባለፉት ሁለት ዓመታት መቶ በመቶ መመረጡን ሲያውጅ ነበር። በወቅቱ ጎልጉልን ጨምሮ የተለያዩ የሚዲያ ክፍሎች ባለሙያዎችን፣ ፖለቲከኞችን፣ ልምድ ያላቸውን፣ ወንጀል የተፈጸምበትን ህዝብ በመጠቀስ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ አመላክተዋል። አሁን በእስር ላይ ያሉት ዶ/ር መረራ ጉዲና እንደሚሉት አፍ እንጂ ጆሮ የሌለው ህወሃት ሊሰማ አልፈቀደም። ይልቁኑም በጠቅላይነቱ ሰክሮ “አውራ ነኝ” በሚል ያቀራራ ነበር። ከትምክህቱ ጋር ተዳምሮ በሙስና የገለማው መቀመጫው ልቡናውን ስለነሳው ሰው “እመጤፍ” ብሎ ነበር። ጥጋብና ትምክህት፣ ብሔራዊ ስሜትን ከመበታተን ዘመቻው ጋር አንድ ላይ ተንተክትከውበት የሚሆነውን አሳጥቶት ነበር። በወጉ አስበው የማይከተሉትን ደጋፊዎቹን ጭምር ሰክሮ አሰከራቸውና ከወገናቸው ለያቸው። ቂም እንደ ጭብጦ እየጨበጠ አዋጣቸው።

በራሱ አምሳልና ፕሮግራም የፈጠራቸውን የሚዲያ ቡድኖች ፖለቲካዊ ትፋቱን እየተፋባቸው ራሱን ዞሮ የሚበላውን ዘር አመረተ። በሃሰት እንደ ጋጋኖ እየጮኸ በቁጥር ወደፊት፣ በተግባር ወደ ኋላ ሮጠ። ጥቂቶች ሌብነቱ የፈላባቸው ገንቢዎች፣ አስመጪዎች፣ ላኪዎች፣ ኢንቬስተሮች፣ ተበዳሪዎች፣ አበዳሪዎች፣ ፈቃጆች፣ አስፈቃጆች፣ ቆጣሪ ተቆጣጣሪዎች፣ አሰሪዎች፣ … ሲሆኑ የራባቸው በዙ። በራሳቸው መሬት ላይ ዘበኛ የሆኑ ፈሉ። በተወለዱበት ቀዬ ለማይረባ ጉዳይ የሚፈናቀሉ ተበራከቱ። ከድሆች በአነስተኛ ዋጋ እየገዙ በሚሊዮን የሚያተርፉ ፈሉ። ዜጎች በራሳቸው መሬት ላይ የሰው እርሻ ተንከባካቢ ተደርገው ኬሚካልና መርዝ ጨረሳቸው። በቅጡ ዕዳቸውን የማይከፈሉ ማፍያዎች ድሆችን አመከኑ። በኬሚካል ቆዳቸውን አነደዱ፤ አጥንታቸውን አጎበጡ። ይህ ሁሉ ሲሆን ህወሃት ሌብነት ልቡን ነስቶት ለህዝብ ጥሪ ምላሽ የለውም ነበር። ከሥራ የተባረሩ፣ ቤተሰባቸው የተበተነ፣ ከኖሩበት ቀዬ የተፈናቀሉ፣ የሞቱ፣ የተጎዱ፣ … ስፍር ቁጥር የላቸውም።

ለዓመታት የተጠራቀመው በደል ድንገት ፈነዳ። እንድ ተስቦ አገሪቱን ወረረ። ኦሮሚያና አማራ ህዝብ አመጸ። ደቡብ ሙሉ በሙሉ ባይባልም ህዝብ ተቆጣ። የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ጥይት ተመረጠ። ህጻናት፣ አዋቂ፣ አባት እናትና አያት ሳይባል ጥይት ተረጨባቸው። ሃዘን ቤቱን አዳረሰ። የደረሰው ጉዳት ቀላል አልነበረምና ህዝብ ጥላቻውን ወደ ቂም ቀየረ። ዛሬ የአሜሪካው ባለሥልጣን እንዳሉት አገሪቱ የሚንተከተክ ማሰሮ ሆነች። በኦጋዴን፣ በጋምቤላበኦሞ ሸለቆኮንሶ፣ … ግፍ ተንሰራፋ። አሰቃቂ ግድያና የግድያ ታሪክ እንደ ፊልም ተተረከልን። በሚገርም ሁኔታ አገሪቱ ደምንና እምባ ፈሰሰባት። የዚያኑ ያህል ልብ ደማ። እስር ቤት እስኪጠፋ ድረስ ዜጎች በየስርቻው ታጎሩ። ስቃዩንና መከራውን የደረሰባቸው ይግለጹት

ጥቂት ስለ ዝርፊያ – የሃይለማርያም ምስክርነት

ከዚህ ሁሉ ክስረት በኋላ፤ መልካም አስተዳደር፣ ሥራአጥነት፣ እኩል ተጠቃሚ አለመሆን የሚባሉት የፕሮፓጋንዳ አባባሎች ተጠያቂ ሆኑ። በእነዚሁ የተለመዱ አባባሎ ላይ “ጥልቅ ተሃድሶ” የሚባል ዜማ ታከለበትና የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ቃል ተገባ። ሙስናን እንዘምትበታለን ተባለ። ሥራ እናመቻቻለን በሚል መቀደድ፣ መቦጥረቅ ተጀመረ። ሁሉም መፍትሄ አላመጣ ሲል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ። አገርና ህዝብ እግር ከወርች ታሰሩ።

የሙስና ዘመቻ ጆሮ ባደነቆረበት አፍላ ጊዜ ፖሊስ “ሰው ቤት ገብቶ ማር የላሰ ሌባ 2 ዓመት ተፈረደበት” ተባለ። ከዋኖቹ “የመንግሥት ሌቦች” መመሪያ የሚቀበለው ሃይለማርያም ደሳለኝ “ማስረጃና መርጃ” እያለ የተጠናበረ መግለጫ ሰጠ።

ሙስና!

በመላው ኢትዮጵያ የተፈጸመውን ሙስና ህዝብ ያውቀዋል። ለፌደራሉ የጸረ ሙስና ኮሚሽን ከበቂ በላይ ማስረጃና ጥቆማ ደርሷል። የኢኮኖሚ ደኅንነት ክፍሉ በጥልቀት ያውቀዋል። የማያውቁት በደርግ ጊዜ የሞቱ ዜጎች ብቻ ናቸው። ሃይለማርያም ገሃዱን የሚያውቀው ህዝብ ፊት ወጥቶ ከሚዘባርቅ ዝም ቢል እንደሚሻል በርካቶች ስድብ እያከሉ የማህበራዊ ገጾች መቀለጃ አድርገውታል።

በኤፍ.ቢ.አይ. ቅርጽ አዲስ የሙስና ወንጀልን የሚከላከል መመሪያ በፌደራል ፖሊስ ውስጥ መቋቋሙን ሲናገር ሰዎች ተሳልቀውበታል። ምክንያቱም ዋናዎቹ ሌቦች ደህንነቱን የሚያዙና የታጠቀውን ክፍል የሚመሩ፣ አለያም በታጠቀው ክፍል ሽፋን የሚሰጣቸው እንደሆነ እየታወቀ “ራሳችሁን መርምሩና እሰሩ” እንደ ማለት ነውና። በጥቅሉ አሁን እየተወሰደ ነው የሚባለው ርምጃ ዋና ሌቦችን ያላካተተ፣ ያኮረፉ የአቻ ፓርቲዎችን መስተጋብር (ኔትዎርክ) ለመበጣጠስ የተያዘ ፖለቲካዊ ርምጃ ነው።

ድርድርና እርቅ – ከመተማመን በፊት እንዴት?

ህወሃት የሚሰማው ካጣ ከርሟል። ብቻውን እንደሚጮህና ፕሮፓጋንዳው ሁሉ የዜሮ ድምር ስለመሆኑ ማህበራዊ ገጾች ምስክር ናቸው። የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ መርከል “መተንፈሻ ያጡ ዜጎች ያላቸው አንድ መንገድ ማኅበራዊ ሚዲያ ነው” በማለት አዲስ አበባ በነበሩበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።

ሰሞኑንን የዕርቀና የድርድር ወሬ አለ። ድርድሩ ገና ለመደራደር ስምምነት ላይ ስለመድረስ ከተባለው ውጪ ፍሬው አልታየም። እንዲያውም አብዛኞች የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን፣ አባላትን እንዲሁም ደጋፊዎችን አስሮ ምን አይነት ድርድር አለ? ሲሉ ይጠይቃሉ። አባላቶቻቸውን፣ ደጋፊዎቻቸውንና መሪዎቻቸውን ያጡ የፖለቲካ ድርጅቶች ወገኖቻቸውን አሳስረው ስለ ምን ጉዳይስ ሊደራደሩ ነው? በማለት ቅድሚያ ድርድሩ እስረኞች በሚፈቱበት ሁኔታ ሊሆን እንደሚገባው ይጠቁማሉ።

ገለልተኛ መሆናቸው ትልቅ ጥያቄ ውስጥ የሚገባው የሃይማኖት መሪዎችም የህወሃትን የዕርቅ ምልጃ ሰሞኑን ሲያስተጋቡ ተስተውለዋል፡፡ እንደ እምነት መሪነታቸው በቅድሚያ ለፈጣሪቸው በመታዘዝ ህወሃትን ከእውነት ጋር ማጋጨት ሲገባቸው ዕርቅ ያስፈልጋል፤ መስማማት ለልማት ወሳኝ ነው፤ ተግባብተን መኖር አለብን፤ … የሚሉ “ልማታዊ” ንግግሮች አድርገው በህወሃት ሹሞች ቡራኬ የተጀመረውንና የተዘጋውን ስብሰባ እነርሱም አጠናቀዋል፡፡

“ሕዝብህን መግደል አቁም፤ ማሰቃየት አቁም፤ መንግሥት ሕዝብን ይሰማል እንጂ ሕዝብ በመንግሥት እየተሸበረ አይኖርም፤ አደብ ግዙ፤ ሥራችሁን ፈጣሪ ያየዋል፤ የምታሰቃዩት ሕዝብ ለቅሶ ወደ ፈጣሪ ይደርሳል፤ ይፈርዳል፤ ከስተት መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ኧረ ሰከን በሉ የሚል የሃይማኖት አባት በሌለበት ምድር በህወሃት/ኢህአዴግ የሚቀመመው ዕርቅ ሳይሆን ዳግም ግፍ እና ሰቆቃ ብቻ ነው፤ ይህ ቀልድ ነው” በማለት ጉዳዩን የሚከታተሉ ለጎልጉል ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ህወሃት/ኢህአዴግ ጨንቆታልምዕራባዊ ጌቶቹ ደግሞ ሰላም ፍጠር ብለውታል፤ ሰላም መፍጠር በራሱ ህልውናውን አደጋ ላይ ይጥለዋል፡፡ ስለዚህም ነው የ“ጥልቁ ተሃድሶ” ውጤት እንደሆነ የተነገረለት ዕቅርና ድርድር የሰሞኑ አጀንዳ የሆነው፡፡ ሃሳባችሁን ተናገራችሁ ያላቸውን ሁሉ አስሮ ድርድር፤ እውነት የሌለበት፣ ፍትሕ ያልሰፈነበት፣ ካድሬ የተሰለፈበት ዕርቅ “አዙረኝ አታዙረኝ” ጨዋታ እንዳይሆን ከበፊቱ ያሁኑ እጅግ ያሰጋል፡፡


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

Comments

 1. ጐልጉሎች ያቀረባችሁት ትንተና አመርቂ ነው። የትንተናችሁ ይዘት ተጨባጭና በመርሬት ላይ የሚታይና ያለ እዉነታ ነው።
  ህወሓት/ኢህአዴግ ማለት የደነዘዘ የድንጋይ ሐውልት ነው – ያውም ዉሃ አይገባው ድንጋይ ማለት ነው። ስለዚህ የህወሓት ዋና ራስ/ጭንቅላት የነበረው መለስ ዜናዊ በጭንቅላት ነቀርሳ ከ 2006 -እስከ 2013 (አውሮፓውያን አቆጣጣተር) ሲሰቃይ ከርሞ የያዘውው ነቀርሳ ላይመለስ ይዞት ሄዷል። ልብ በሉ በ 1997/2005 ምርጫ ወቅት በካርዱ ወያኔ/ኢህዴግን አንፈልግህም ብሎ የነገረውን የኢትዮጵያ ህዝብ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአጋዚ እንዲገዴል ያዘዘው መለስ ዜናዊ ከምርጫ 97 በኋላ ማለትም በ1998 /2006 ዓ.ም በዓመቱ ነበር በግል ሐኪሙ “የጭንቅላት ነቀርሳ” አለብህ እናም ለሂወትህም አደገኛ ነው ተብሎ የተነገረው። በግል ሃኪሙ ብዙኡ አትቆይም እድሜህም አጭር ነው ተብሎ ከተነገረው በኋላ 8 ዓመት ብበዚሁ የጭንቅላት ነቀርሳ ሲሰቃይ ኖሮ በመጨረሻም የኢትዮጵጵያ ህዝብ አምላክ የህዝቡን እንባ ቆጥሮ አሰቃይቶ በሞት ነቀለው። 8 ዓመት ግን በከባድ ስቃይ ላይ ነበር። አመላክ ምንጊዜም ቢሆን ትክክለኛ ፌራጅ ነው። አሁንም በዚህ ዓይነት በሽታ የሚሰቃዪ የወያኔ ሰዎች አሉ ከነዚህ ውስጥ አንድ ሁለቱን ልጠቁም። አረከበ እና ደብረጺዮን ዋነኞቹ ና ጥቂቶቹ ናቸው። አባይ ጸሃዬም በሚጥል በሽታ የሚሰቃይ አጋሠሥ ነው። አምላክ የሚዘገይ የምስላል እንጅ ለሁሉም የእጁን ሲሰጥ በጊዜ ነው። አመላክ የተመሠገን ይሁን ። አሜን

 2. Honestly, my eyes were could with tears, while I was reading this particular page. The way it is written and presented is very figurative and real. My emotion was stirred, that was why my eyes were clouded and wet.
  Being a mother with two close to teenage, feels hopeless about the future of the kinds is the most horrible and devastating experience. There are millions Moms out there in the same circumstances even worse.
  The citizens are in a deplorable condition. The cost of living is out of control. No one for sure knows where the country and everything is heading. The only thing one can be sure of is he/ she can miss lunch or dinner or both the next day.
  All these problems are artificial. Had somebody said ” government itself is the problem ” He was absolutely right. We see it every day. We need to do something about it.

Speak Your Mind

*