ዜናውን “መገጣጠም” ሲሉ በቁጭት ይገልጹታል። የትግራይ “ባለሃብቶች” በጋምቤላ መበደላቸውን ለውጭ አገርና ለአገር ውስጥ መገናኛዎች ያስታወቁበት ዕለትና የአኙዋክ ምስኪኖች በምድራቸው በግፍ የተጨፈጨፉበት ቀን ተሳሳመ። ደም እንደጎርፈ በፈሰሰበት፣ ንጹሃን እንደ እንስሳ የተቀሉብት ቀን ተዘንግቶ በሙታን ዱካ ተተክተው “ተበደልን” ያሉ የብሶት ዜና ተሰማበት – ታህሳስ 4፤ 2009 (ዲሴምበር 13 ቀን 2016)።
ታህሳስ 3፤ 1996 ዓ.ም በጋምቤላ ለተጨፈጨፉት ንጹሃኖች ፍትህና ርትዕ የሚሰጥ አካል እስካሁን አልተገኘም። በስደት ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያና የተለያዩ አገራት የሚኖሩ የአኙዋክ ተወላጆች ያንን ቀን ሲያስቡት አሁን ድረስ ያነባሉ። በመለስ አመራር ሌሎች በፌዴራል መንግሥት ስም የሚታወቁ የህወሃት ሰዎች ትዕዛዝ ከ400 በላይ አኙዋኮች ተረሽነዋል። አሁን እነሱ አፈር ውስጥ ሆነው ደማቸው ከላይ ይጮሃል።
በእነሱ ደምና አጽም ላይ ንግድ ጦፏል። ከያቅጣጫው ከተፈጥሮ ዛፎቿ ጀምሮ ጋምቤላ እየታለበች ነው። ካሩቱሪ፣ ሳውዲ ስታር እና 1000 የሚሆኑ የትግራይ “ባለሃብቶች” /ነባር ታጋዮች ናቸው/ በዚሁ የደም መሬት ላይ ሰፍረው ይበደራሉ፣ የክልሉን ህዝብ ጭሰኛ አድርገው ያመርታሉ፣ ይነግዳሉ፣ ይለውጣሉ፣ …
ታህሳስ 4፤ 2009 (ዲሴምበር 13 ቀን 2016) የቪኦኤ የትግራይ ዘጋቢ “የጋምቤላ እርሻ ባለሐብቶች የሕብረት ሥራ ማኅበር” በሚል ስያሜ የሚጠራውን የቀድሞ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ታጋዮች “በደል” ይፋ አድርጓል። የማህበሩን ሊቀ መንበር አቶ የማነ ሰይፉን አነጋግሯል።
ማህበሩ ያሰማው ቅሬታ የትግራይ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ በደል እንደደረሰባቸው ነው። አንድ ሺህ የሚሆኑት የትግራይ ባለሃብቶች ያመረቱት ማሳ ላይ እያለ ብድር መከልከላቸው ሆን ተብሎ የተደረገና በማንነታቸው የደረሰባቸው በደል ነው። ከ2001 ጀምሮ ወደ ጋምቤላ ባለሃብት ሆነው የገቡት የትግራይ ተወላጆች፣ የባንክ ብድር ማግኘት የጀመሩት ከ2005 ጀምሮ ሲሆን በያዝነው ዓመት ተቋርጦባቸዋል። ይህም የሆነው እነሱን አክስሮ ከጫወታ ውጪ ለማስገባት ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል በሄክታር 30 ብር ግብር ይከፍሉ ነበር አሁን በቅጽበት ወደ 111 ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል። የባንክ ብድር ወለድም ከ8.5 ወደ 12.5 ከፍ እንደተደረገባቸው ያስረዱት ሊቀመንበሩ፣ ደጋግመው የተናገሩት ድርጊቱ ሆን ተብሎ እነሱ ላይ በተነጣጠረ ሴራ መሆኑን ነው።
አበዳሪው ባንክ በበኩሉ ድራቢ የተወሰደ መሬት ስላለ ማጣራት እየተደረገ መሆኑንና ማጣራቱ ሲያልቅ ብድሩ እንደሚፈቀድ ተናግሯል። እንደ ባንኩ አባባል ውስብስብ ነገር ያለ አይመስልም። ባንኩ እንዲህ ያለ አቋም ካለው “በማንነታችን ሳቢያ /ትግሬ ስለሆን ተበደለን/” የሚለው አቤቱታ ለምን አስፈለገ? ሲሉ በርካቶች ይጠይቃሉ። ጉዳዩን ለተለያዩ ዓለም አቀፋዊ መገናኛዎች ማሳወቁስ “ለምን ይሆን” ሲሉ ዜናውን የሚመረምሩ አሉ። ዜናው ሲጠናቀርስ የተወገዘው የክልሉ ሃሳብ ለምን አልተካተተም? ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው? (ይህም ቢሆን አልተገለጸም) ወይስ ሌላ ምክንያት አለው? ግብር የሚጥል፣ ቀረጥ የሚሰበስብ፣ መሬቱን ሰፍሮ የሚሰጠው አካል ለምን ተዘለለ?
የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) ነባር ታጋዮቼ የሚላቸውን በፖለቲካ ጉዳዩ፣ በአካል ጉዳትና በእድሜ ሲቀንስ አቅም እያስጨበጠ ወደ ባለሃብትነት ከፍ እንዳደረጋቸው ራሳቸው ታጋዮች በተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል። እነሱ ባይናገሩም በርካታ ማሳበቂያ ማስረጃዎች ስላሉ ጉዳዩ ለክርከር የሚቀርብ እንዳልሆነ የበርካቶች እምነት ነው፤ የጸረ ሙስና ኮሚሽንን ጨምሮ!!
በጎንደር የተነሳውን ተቃውሞ አቅጣጫ ለማስቀየር “ትግሬ በመሆናችን ተፈናቀልን” የሚለውን ስባሪ ዜና በዓለምአቀፍ ደረጃ ያጎላው ህወሃት፣ ዓላማው ለሚወሰደውና እየወሰደ ላለው እርምጃ ዓለምአቀፋዊ ድጋፍ ለማግኘት እንደሆነ መዘገቡን ያስታወሱ፣ “በጋምቤላ ካሩቱሪ ወስዶት የነበረውን መሬት ለትግራይ ባለሃብቶች እና ለሳዑዲ ለመሸጥ በመታሰቡ ቅድመ ሁኔታ ለማመቻቸት ነው” የሚሉ እየተሰሙ ነው።
የክልሉን የመከራከርና “ለምን” ብሎ የመጠየቅ፣ ከህወሃት ተጽዕኖ ውጪ በራሳቸው ተደራጅተውና ከባንክ ተበድረው መስራት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው የመጠየቅና ቀደም ሲል በተፈጸመው ግፍ የመቆጨት ስሜት ያላቸውን ሃላፊዎች ለማራገፍ ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሆነ እነዚሁ ክፍሎች ይናገራሉ። ለዚህም ተግባራዊነት ሃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራ አንድ ቡድን መቋቋሙን እንደ ማስረጃ ያስቀምጣሉ።
በጋምቤላ በልማት ስም ሊተካ የማይችል የተፈጥሮ ደን ወድሟል። ተጨፍጭፎ ተቸብችቧል። ተወላጆች ተፈናቅለዋል። ከሁሉም በላይ ምስኪኖች ታርደዋል። በሦስት ቀን ውስጥ ከ400 በላይ ንጹሃን እንደ ተባይ ተረፍርፈዋል። በብሔር ብሔረሰቦች ስም ይምል የነበረው መለስ ጉዳዩን ወደ ሌላ አካል ለማዞር የሠራው ድራማ በክልሉ መሪዎች ተጋልጧል። ዓለምአቀፉ የወንጀለኛ ፍርድቤት (አይ.ሲ.ሲ.) የመለስን ፋይል ገምዶ ክስ ሊመሰርትበት በዝግጅት ላይ እንዳለ ሞት እንደ ቡሽ ክዳን አስፈንጥሮት ሌሎች የቀመሱትን አፈር ልሷል። ከዚህ በፊት ግን “እኛን የሚያሳስበን በሊዝ ያልሸጥነው መሬት ነው” በማለት መለስ መናገሩ ይታወሳል፡፡
“ትግሬዎቹ ለገንዘብ፤ አኙዋክ ግን ለደሙ ያለቅሳል” ኦባንግ ሜቶ
የአኙዋኮች በግፍ ከተጨፈጨፉበት ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩን የሚከታተሉት አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጎልጉል በሰጡት አጭር የስልክ ቃለምልልስ የትግራይ ተወላጆች ያነሱትን ጥያቄ “ፍጹም ሰብዓዊነት የሌለበት በሙታን ደም መቀለድ” ይሉታል፡፡
የአኙዋክ ሕዝብ ከህወሃት ጋር ገና ከጅምሩ ስምምነት እንደሌለው ያወሱት ኦባንግ የጥሉ ዋንኛ መነሻ ህወሃት የጋምቤላን ለም ምድር የራሱ ለማድረግ ከመፈለጉ ጋር ያያይዙታል፡፡ ህወሃት ሥልጣን ላይ እንደተቆናጠጠ የጋምቤላን ብቸኛ ጄኔሬተር በመንቀል ከመውሰድ አልፎ በአሎሮ ግድብ ላይ የነበሩትን ወደ 400 የሚሆኑ ማሽነሪዎች እና የእርሻ መሣሪዎች በምሽት ወደ ትግራይ ነቅሎ ወስዷል ይላሉ ኦባንግ፡፡ በመቀጠልም ተዝቆ የማያልቀውን የጋምቤላን ድንቅ ሃብት በረኸኞቹ ህወሃቶች ለመዝረፍ ውሳኔያቸው አደረጉ፡፡
መሬቴን አላስነካም በሚለው አኙዋክና ህወሃት መካከል ያለውን መቃቃር አንድ “ዕልባት” ላይ ለማድረስ በሚል አኙዋክን ማጥፋት የህወሃት ቀዳሚ ሃሳብ ሆነ እንደ አቶ ኦባንግ ሜቶ ገለጻ፡፡ ጉዳዩን አቅጣጫ ለማስቀየርም ከዚህ በፊት ተነስተው የማያውቁ የጎሣ ግጭቶችን ህወሃት መቆስቆስ ጀመረ፡፡ ሸመጋይ መስሎም የመከላከያ ሠራዊት በቦታው ማስፈር ተግባሩ አደረገ፡፡ በመጨረሻም “እንጨርሳቸው፤ አንድም አኙዋክ መትረፍ የለበትም የሚለው” ትዕዛዝ ወጣ፡፡ መለስ በመራው ስብሰባ ላይ አዲሱ ለገሰ፣ ስብሃት ነጋ፣ በረከት ስምዖን፣ ኦሞት ኡባንግ ኡሎም (ያኔ የጋምቤላ ደኅንነት ኃላፊ)፣ አባይ ጸሃዬ፣ ሳሞራ ዩኑስ፣ ዮሐንስ ገብረመስቀል (ያኔ የወታደራዊ ስለላ ኃላፊ)፣ አባዱላ ገመዳ ተገኝተዋል፡፡ የዕቅዱ አፈጻጸም ላይ አኙዋኮች እንዲጨፈጨፉ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሰጠው ጸጋይ በየነ (በጋምቤላ የሠራዊቱ ኃላፊ) ሲሆን ፈቃዱ ያገኘው ያኔ የፌዴራል ጉዳይ ኃላፊ ከነበረው ገብረአብ በርናባስ ነበር፡፡ የፖሊስ ኃላፊው ታደሰ ኃይለሥላሴም አኙዋኮችን የማስገደል ትዕዛዝ በመስጠቱ ውስጥ ነበረበት፡፡ ይህ ሁሉ በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን አቶ ኦባንግ ያስረዳሉ፡፡
“እንግዲህ ይህ ዘር የማጽዳት ዘመቻ በ1996 ከተካሄደ በኋላ የጋምቤላ መሬት እንደ ካሩቱሪና ሳውዲ ስታር ላሉ ባለሃብቶች በአንድ ዶላር ሒሳብ የተቸበቸበው፡፡ ብዙ ጊዜ ለውጭ ባለሃብት ተሰጠ ይባላል እንጂ ከጋምቤላ መሬት 78 በመቶውን የተቀራመቱት ትግሬዎች ሲሆኑ 12 በመቶው ብቻ ነው ለውጭ ባለሃብቶች የተሰጠው፡፡ ከዚህ ሌላ ይህ ሁሉ መሬትና ብድር ለትግራይ ተወላጆች ተሰጥቶ የእርሻ ልማት ባለቤቶች ሲሆኑ አንድም አኙዋክ ይህንን ዕድል አላገኘም፤ ይልቁንም ለውሃ ቅርብ የነበሩና በአባቶቻቸው መሬት ላይ የሚገኙትን አኙዋኮች በልማት ሰበብ በህወሃት ተፈናቅለው ወደ ሌላ ቦታ ሰፍረዋል” በማለት ኦባንግ ይናገራሉ፡፡
በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ስለተዘገበው ዜና ከጎልጉል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ሰምቼዋለሁ፣ እጅግ በጣም አዝኛለሁ፤ በተለይ የአኙዋክ ሕዝብ ፍትሕ ሳያገኝ ደሙ እየጮኸ 13 ዓመታት ማለፉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በሐዘን እየታሰበ ሳለ የትግራይ ተወላጆች ይህንን ዓይነት ነገር በዚያኑ ቀን ማሰማታቸው የአኙዋክን ሕዝብ እንደገና እንደገደሉት የሚቆጠር ነው፤ ዜናውን የሰማ አንዱ ወዳጄ ልቤን እንደገና ቀድደው አወጡት ነው ያለኝ፤ ሰብዓዊነት ያስፈልጋል፤ እነርሱ እያለቀሱ ያሉት ለገንዘባቸው ነው ያውም በብድር ለዘረፉት ገንዘብ ነው፤ የአኙዋክ ህዝብ ደም እያነባ ያለው ለፈሰሰበት ደም ነው” ያሉት ኦባንግ ሜቶ በሌላ በኩል እነዚሁ የትግራይ ተወላጆች ይህንን ዓይነት አቤቱታ ማሰማታቸው የአኙዋክ ደም የፈሰሰውና መሬቱን የተዘረፈው እነርሱን ለማበልጸግ ነው ሲባል የነበረውን ያለጥርጥር ያረጋግጣል ብለዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በዚህ “በደል ደረሰብን” በሚል ሰበብ የካሩቱሪን መሬት ለትግራይ ልጆች ለመስጠት የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ተብሎ ሊታይ ይችላል በማለት ኦባንግ ያስረዳሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኦባንግ ሜቶ ይህንን የህወሃት አሠራር በዘር ላይ የተመሠረተ የአፓርታይድ ሥርዓት ይሉታል፡፡ “ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች አገር ብትሆንም በጣሊያን ጊዜ የነበሩት ባንዳዎች የልጅ ልጆች አሁን አገሪቱን በዘር ላይ ባተኮረ አፓርታዳዊ ስልት እየዘረፉ፤ ራሳቸውን እየጠቀሙ ነው” በማለት በግልጽ ያስረዳሉ፡፡
ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ አንድን ዘር ለማበልጸግ ሲባል ጉራጌው ከመርካቶ ተፈናቅሎ መርካቶ የትግራይ ተወላጆች ሆናለች፤ ወልቃይት ከህዝቡ ተወስዶ ለትግራይ ተሰጥቷል፤ ተራራም ሳቀር ተሰርቋል፤ በማስተር ፕላን ስም የኦሮሞ ወገኖች መሬት ተወስዶ ለትግራይ ተወላጆች ማበልጸጊ እንዲሆን ተደርጓል፤ በደቡብ ኦሞ ሱርማዎችና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች በኢሰብዓዊነት መሬታቸው ተነጥቋል፤ ኮንሶ የግፍ ምድር ሆኗል፤ “ዝም የተባለው ዳርፉር” – ኦጋዴን ሕዝቡ “አናስተርፋችሁም” ተብለው ተጨፍጭፈዋል፤ ዝርዝሩ አያቆምም፡፡ ለዚህ ሁሉ ዋንኛ መፍትሔው ህወሃት በቀደደው የዘር ቱቦ መፍሰስ ሳይሆን “ከዘር ይልቅ ሰብዓዊነትን ማስቀደም” ነው ይላሉ “ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ሜቶ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በዕርቅ ላይ የተመሠረተ ርትዓዊ ፍትሕ ለኢትዮጵያ የሚበጅ መፍትሔ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply