አሁን የሚፈለገው የሚያሻገሩ መሪዎችን ማግኘት ብቻ ነው። ሕዝብ በፖለቲካ መሪዎች ሃፍረትን እየተግሞጠሞጠና ደሙ ደመ ከልብ እየሆነ የሚኖርበት ዘመን እንዲያከትምለት ይፈልጋል። የአንተ ደም የእኔ ደም ነው በማለት የችግሩ ጉያ ውስጥ ሆኖ አጋርነቱን፣ አንድነቱን ሲያሰማ ሩቅ ተቀምጦ እንደ ቅጥረኛ የወገንን ሞራል ማላመጥ አግባብ አይሆንም። ውሎ አድሮ ከገዳዮቹ በላይ ያስጠይቃል። በቅጥረኛነትም ያስመድባል።
ከአገራችንም ሆነ ከዓለም ዘመን የማይረሳቸው የውብ ስብእና ባለቤቶች ሕዝባቸውን አሻግረዋል። ክፉዎች የቀበሩትን የቂምና የጥላቻ ገመድ በጣጥሰው አገራቸው በልዕልና፣ ሕዝባቸው በሰላም እንዲኖር አስችለዋል። በቀናነት ጀምረው፣ በቀናነት ጨርሰዋል። በታማኝነት ሃላፊነትን ተረከበው በታማኝነት አለፈዋል። ዝርዝር ውስጥ ባንገባም በህይወት ያሉም አሉ። እንዲህ ያሉትን የሚያስቡ “እኛንስ ማን ያሻግረን ይሆን” ማለታቸው እውነት ነው። ሕዝብ ይህን ቢያስብና ቢመኝም በገሃድ የሚታየው ሌላ መሆኑ ጨለማውን ብርቱ፣ ገዳዮችን ጡንቸኛ፣ ተስፋን ኮሳሳ አድርጎብናል። ከሁሉም በላይ እራሳችንን በራሳችን እየበላን መሳቂያ ሆነናል። የጠላቶች እቅድ አስፈጻሚ ከመሆን በላይ የሚያሳፍር ነገር ባይኖርም፤ ለሆዳቸው ሲሉ እንደ ጭቃ ተቦክተው የተጠፈጠፉ ወንድሞቻችን ከውስጥም ከውጭም ከባዕድ ብሰውብናል። ለመነሻ ይህ ከተባል ወደ ዋናው ሃሳብ እንዝለቅ፤-
በዓለማችን የሚካሄደው የፖለቲካ ትንቅንቅ በአብዛኛው የሕዝብ ትግል ይዘትና ባህሪ እንዲይዝ ቢደረግም፣ የተወሰኑ ኃይላት ለግል ጥቅማቸው እንደተጠቀሙበት በበርካታ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች የታየ ሐቅ ነው። በአንድ ወቅት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሩዘቬልት “በፖለቲካ ዓለም በድንገት የሚከሰት ነገር የለም፤ ካለም የተከሰተው እንደዚያ እንዲሆን ታቅዶ ስለመሆኑ መወራረድ ይቻላል” ማለታቸው ይታወሳል።
የዓለማችን ፖለቲካዊ ንቅናቄዎች ከጥንስሣቸው የሕዝብ እንዲመስሉ ማድረግ የተለመደ ነው። መሃላውም በዚሁ ህዝብ ስም ይሆንና በቀጣይ ቅልበሳ ይካሄዳል። በቅልበሳው የሚማልበት ሕዝብ ምኞቱ እንደጉም ሲተንና ተስፋ ሲቆርጥ ታይቷል፤ አሁንም እየታየ ነው። አብዮት አቀጣጣዮቹም የራሳቸው ወይም የሚታዘዙት ዓላማ ቢኖራቸውም ያንን ግን በይፋ የሚያካሂዱት ጉዳይ ሳይሆን ቅጥረኛ ሆነው ነው “የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ” የሚያስበሉት!
ሌላው በዓለማችን በፖለቲካ ስም የሚካሄዱ ለውጦች የሕዝብ አብዮት ከመሆን ይልቅ የበቀል ፖለቲካ ማራመጃ የመሆናቸው ጉዳይ ነው። ሽንፈትን መቀበል ያቃታቸው ኃያላን ከመቶዎች ዓመታት በፊት የተፈጸሙ ነገሮችን ቆጥረው፣ መትረው፣ ቆርጠውና ቀጥለው ለፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ በሚያገኙት አጋጣሚ የበቀል ጥማታቸውን የሚወጡበት የፖለቲካ አካሄድ ሲከሰት ተስተውሏል። ብቀላው በራስ ወገን፤ በለውጥ ስም ወይም በመብት ጥበቃ ቅዱስ ሃሳብ ስር ተመሽጎ የሚከናወን መሆኑ ደግሞ እጅግ ያማል። እውነት እንነጋገር ከተባለ ይህ ሁኔታ ዛሬም ድረስ በአገራችን የህዝብን ትግል የሚያጨናግፍ የፖለቲካ ውርጃ ነው።
የጥቁሮች መብት ቅልበሳ በራሳቸው በጥቁሮች
በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ በአሜሪካ የጥቁሮችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር በተደረገው ንቅናቄ በርካታ መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል። ዓላማዎቹን በማራመድ ሕዝብን ሲደራጁ የነበሩ ጥቁርና ነጭ አሜሪካውያን ህይወታቸውን አጥተዋል። በተለይ ጥቁሮች የመምረጥ መብት እንዲኖራቸው ለማድረግ እጅግ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸውን ሰጥተዋል።
ይህ ብቻ አይደለም፤ በትምህርት ቤቶች፣ በሥራ ቦታዎች፣ በመዝናኛ እና በመመገቢያ ቦታዎች እንዲሁም በሕዝባዊ መገልገያዎችና ቦታዎች ያለው የዘረኝነት መድልዖ እንዲፈርስ እጅግ ብዙ ደም ፈሷል። በተለይ ጥቁር ተማሪዎች ነጮች በሚማሩባቸው ት/ቤቶች እንዳይማሩ ይከለክል የነበረው ሥርዓት እንዲፈርስ በፍርድ ቤት ሙግትና በህይወት ብዙ የተከፈለበት ነው።
የዛሬ 60ዓመት አካባቢ እነዚህ ሁሉ የጥቁሮች መብቶች እንዲከበሩ በሕግ ቢታወጅም በአሜሪካ የሚኖሩ ጥቁሮች አሁንም በአገራቸው የዜግነት መብታቸው አልተጠበቀላቸውም፤ መድልዖው አሁንም አላቆመም። በዚህ የሚቆጩ ጥቁሮች አሁንም ትግላቸውን አላቆሙም። ሆኖም በቅርብ ጊዜ ዕውቅናን እያገኘ የመጣው “የጥቁርም ሕይወት ይገባዋል” (Black Lives Matter – BLM) እንቅስቃሴ ታሪካዊውን የ60ዎቹን ነውጥ አልባ የሰብዓዊ መብቶች ትግል ወደሌላ አቅጣጫ እየወሰደው ይገኛል።
እጅግ አስደናቂ በተባለለትና የብዙዎችን (ነጮችን ጨምሮ) ቀልብ የሳበው ነውጥ አልባው የአሜሪካ ጥቁሮች ትግል በነውጠኛው BLM እየተቀየረ ነው። የእንቅስቃሴው አቀንቃኞች ነውጥን እንደ መብት ማስከበሪያ አድርገው በመውሰድ በርካታ ጥቃቶችን ሰንዝረዋል፤ ጉዳቶችንም አድርሰዋል። ይህ ብቻ አይደለም በዘመነ 60ዎቹ የሕይወት መስዋዕትነት የተከፈለባቸው መብቶች በBLM አራማጆች ወደ ነበሩበት ይመለሱ የሚያስብል ጥያቄዎችም እየቀረቡ ነው።
ምርጫን በተመለከተ በርካታ ጥቁር ወጣቶች ለመምረጥ ያላቸው ፍላጎት እየቀነሰ መጥቷል። በተለይ በ2008 (እኤአ) በርካታ ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በታች የሆኑ ጥቁር አሜሪካውያን በታሪካዊው የኦባማ ምርጫ የተሳተፉትን ያህል በመጪው ምርጫ ቁጥራቸው እንደሚቀንስ የዋሽንግተን ፖስት የዳሰሳ ጥናት ያመለክታል። በአንጻሩ ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑቱ በ2008 ከነበረው 12.3 በመቶ መጠን ወደ 16 በመቶ እንደሚያድግ ያሳያል። ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው ኦባማ ያወሩትን፣ ተስፋ የሰጡትን ያልፈጸሙ በመሆናቸው ጥቁር አሜሪካውያን በራሳቸው ወገን ጀርባቸውን በጩቤ እንደተመቱ ይቆጥሩታል።ይህም በዕቅድ የተደረገ አድርገው የሚወስዱት አሉ፤ ሩዝቬልት እንዳሉት!!
በአሜሪካ የሚገኘው ብሔራዊ የሕዝብ ሬዲዮ (NPR) ያነጋገራት የ36ዓመቷ ጥቁር አሜሪካዊት ኮያ ግራሃም (Koya Graham) በኦባማ ምርጫ ወቅት የምርጫ መፈክር የነበሩት “ለውጥ” እና “ይቻላል” ታላቅ ተስፋ የሚያሰንቁ መርሆዎች እንደነበሩ ትጠቅሳለች። በመጪው የኅዳር ወር ምርጫ ድምጽ እንደማትሰጥ ስታስረዳ “ምንም ተጨባጭ የሆነ ለውጥ አላየሁም፤ ፍትሕ የለም” ስትል በየቦታው ምንም መሣሪያ ሳይዙ ስለተገደሉ ጥቁሮች ቁጭቷን ትናገራለች። የእርሷም ሆነ የሌሎች ጥቁር አሜሪካውያን ስሜት “የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት” በሥልጣን ላይ ቢቀመጡም ለውጥ አለመምጣቱ ተስፋ አስቆርጧቸዋል። በ60ዎቹ ጥቁሮች ድምጽ እንዲሰጡ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ጉዳይ ለበርካታ ጥቁር ወጣቶች (በተለይ በ20ዎቹ ውስጥ ለሚገኙት) ብዙም ትርጉም የማይሰጥ እየሆነ መጥቷል። በበርካታ መስዋዕትነት የተገኘውን “ድል” ስልታዊ በሆነ መልኩ ጥቁሮቹ ራሳቸው “አንፈልገውም” እንዲሉ እየተደረገ ነው።
ትምህርትን በተመለከተ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ታሪካዊው ውሳኔ በራሳቸው ጥቁሮች ዋጋቢስ እየሆነ ነው። በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይ በአሜሪካ ጠቅላይግዛቶች ለጥቁሮችና ለነጮች እየተባሉ የሚከፋፈሉት የሕዝብ ት/ቤቶች አሠራር ሕገመንግሥታዊ አይደለም በማለት ጥቁሮች ከነጮች ጋር ተቀላቅለው እንዲማሩ፤ መገለልና መድልዖው እንዲቆም ያደረገው የBrown Vs Board of Education የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከBLM እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በራሳቸው በጥቁሮች እየተቀለበሰ ነው። እነ ዶ/ር ኪንግ መገለል ይቁም ብለው የታገሉለት ትግል በአዲሶቹ የመብት አራማጅ ጥቁሮች “መገለል ይኑር” እየተባለ ነው።
ከዚሁ ከBLM እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በተለያዩ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጥቁር ተማሪዎች ለእነርሱ ብቻ የተለየ ቦታ (Segregated ‘safe spaces’) እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ይገኛል።እስካሁን በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙ 80 ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ጥቁር ተማሪዎች ከነጮች ተለይተው “የደኅንነት ቦታ” እንዲሰጣቸው እያስተባበሩ የሚገኙ የዓላማው አራማጆች ባወጡት ድረገጽ ላይ በዝርዝር አስታውቀዋል። ይህ ብቻ አይደለም፤ የBLM ሰልፍ በቶሮንቶ ካናዳ ባለፈው ሐምሌ ወር በተደረገ ጊዜ ዓላማውን ለመደገፍ የወጣች በከተማው የታወቀች ነጭ ሙዚቀኛ (Sima Xyn) ለዓላማው መርጃ እንዲሆን ይሸጥ የነበረ ካኔተራ (ቲሸርት) በቆዳዋ ቀለም ምክንያት መግዛት እንደማትችል ተነግሯታል። “ጥቁር መሆኗን ማረጋገጥ” እስካልቻለች ይህ ጥቁሮችን ብቻ የሚመለከት ትግል ማገዝም እንደማትችል ተነግሯታል። በሲያትል የBLM ረዳት መሥራች የሆነችው ማሪሳ ጆንሰን (Marissa J. Johnson) ባለፈው የካቲት ወር ለፎክስ ዜና እንደተናገረችው “የጥቁር ሕይወት ግድ ይላል” ከሚባል ይልቅ “የሁሉም ሕይወት ግድ ይላል” ማለት አንድን ዘር በማዋረድ መስደብ እንደማለት ነው ብላለች። (“all lives matter” is a racial slur)
በጥቁሮች የሰብዓዊ መብቶች ትግል ወቅት ዶ/ር ኪንግ በተለይ በተደጋጋሚ ለጥቁሮችም፣ ለነጮችም፣ ለቢጫዎችም፣ … እያለ ትግሉ ሁሉን ዓቀፍና የሁሉን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው በማለት ከጥቁሮች ዘር ውጭ ያሉ እጅግ በርካታዎችን ቀልብ እንዳልሳበ በBLM እንቅስቃሴ አራማጆች (አክቲቪስቶች) (የትግል ፈቃድ ያወጡ ይመስል) ጥቁርነታቸውን ማረጋገጥ የማይችሉ ሰዎች ትግሉን መደገፍ እንደማይፈቀድላቸው በግልጽ የማግለል ንግግር እያደረጉ ይገኛል። ዶ/ር ኪንግ “ሕልም አለኝ” በማለት በተናገረው ልብ ስቃይ ዲሰኩር የቆዳ ቀለም፣ ዘር፣ ሃይማኖት ሳይለይ ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚኖሩባትን አሜሪካ አልማለሁ ነበር ያለው። የBLM ስንቶች የተሰዉለትን ሕልም ወደ ቅዠት እየቀየሩት ነው፡፡
የBLM እንቅስቃሴ አራማጆች ትግሉ “የጥቁሮችና ለጥቁሮች” ነው በማለት የበርካታዎችን ቀልብ በጭፍን ለመሳብ የሞከሩትን ያህል ከበስተኋላ ሆነው ትግሉን በገንዘባቸው የሚደጉሙትና የሚዘውሩት ነጭ ባለሃብቶች እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዋሽንግተን ታይምስ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ እንደዘገበው ከ133 ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ዕርዳታ በለዘብተኛ የነጭ ድርጅቶች ተለግሷል።
እኤአ በ2013 ዓም የ17ዓመት ወጣት የነበረው ጥቁር አሜሪካዊው ትሬቮን ማርቲን ጆርጅ ዚመርማን በተባለ ነጭ በግፍ ከተገደለ በኋላ ገዳዩ በፍርድ ቤት ታይቶ ተከሳሹ በነጻ እንዲለቀቅ የተወሰነ ጊዜ ይህ #BlackLivesMatter እንቅስቃሴ በማኅበራዊ ሚዲያ # (ሃሽታግ ምልክት) እየተደረገ፤ ምንም አልያዝኩም ለማለት እጅን ወደላይ በማንሳት ማሳየት የእንቅስቃሴው መለያ ሆኖ ተለቀቀ። በአጀማመሩ የጥቁሮችን ሕይወት እንደሚታደግ በመናገር ብዙ ዜጎች በሃቅ ቢደግፉትም እያካሄደ ያለው እንቅስቃሴ ጥቁሮች በክብር ያገኙትን መብት በራሳቸው በጥቁሮች “አንፈልግም” ብለው እንዲመልሱ፤ መብታቸውን እንዲዋርዱ፤ በመብት መከበር ስም በፍቃዳቸው መድልዖ እንዲደረግባቸው፤ በነዶ/ር ኪንግ የተገኘው ድል ያልተዋጠላቸው ተበቃይ ወገኖች ጊዜ ጠብቀው ዓላማቸውን እንዲያሳኩ የፈቀደ ትግል እየሆነ መጥቷል። በዘመን አመጣሹ የመብት መከበር ሽፋን ጥቁሮች በራሳቸው ፍቃድ መብታቸው እንዲገፈፍ ሲጠይቁ፤ በየአደባባዩ ሲጮሁ ማየትን የመሰለ ድርብ ድል ለጠላቶቻቸው የለም። የአገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ ማስበላት ይሏል ይህ ነው!
በእፉኚት የሚመሰለው የእምነት ቤት ፖለቲካዊ ግብ ግብ
የዛሬ 500 ዓመት አካባቢ የሮም ካቶሊክ ቤ/ክ የምትከተለውን ትምህርት በመቃወም ማርቲን ሉተር የተባለ ጀርመናዊ የካቶሊክ መነኩሴ ድምጹን አሰማ። በሃይማኖቱ ቀናዒ የነበረው ሉተር ካቶሊካዊ ዕምነቱን ከፍ ለማድረግና ብቁ ለመሆን በማሰብ እምነቱ ከሚጠይቀው በላይ የሚፈጽም ለአምላኩ ያደረ ነበር።
ለመጽደቅ እና ሃይማኖታዊ ተግባሩን ለመፈጸም በ1512ዓም ወደ ሮም በሄደ ጊዜ በተዓምራዊ መንገድ ከኢየሩሳሌም ወደ ሮም ተወሰደ ተብሎ የሚታመነውን ቅዱስ ደረጃ (Scala Sancta – ክርስቶስ ለፍርድ ወደ ጲላጦስ ሲቀርብ የወጣውን) በእንብርክኩ በሚወጣበት ጊዜ ከዚህ በፊት ያነበበው “ጻድቅ በእምነቱ ይድናል” (ሮሜ 1፡17) የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደ ነጎድጓድ በጭንቅላቱ ሲያስተጋባ በእንብርክኩ የወጣውን ደረጃ በእግሩ ወረደው።
ከዚያም ወደ ጀርመን በመመለስ ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ የካቶሊክ ቤ/ክ የምታስተምረው ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አይስማሙም ያላቸውን 95 ነጥቦች ኦክቶበር 31፤ 1517 ዓም በቪተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በር ላይ ለሕዝብ እይታ ለጠፈ። በዚህም “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ፤ እምነት ብቻ (Sola scriptura by Scripture alone, Sola fide by faith alone)” በማለት የፕሮቴስታንት እምነት በይፋ ተጀመረ። በመቀጠልም የሉተር ተከታዮች ራሳቸውን ሉተራን በማለት እምነታቸውን ማስፋፋት ጀመሩ።
በሉተር ተቃውሞ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት የካቶሊክ ቤ/ክ በተለያዩ አገራት ተከታዮችን ለማፍራት፤ የፕሮቴስታንት እምነትን ለመቀልበስ፤ የካቶሊክ እምነት ዓለምአቀፋዊ ተጽዕኖ እንዲኖረው ለማድረግ፤ የፕሮቴስታንት እምነት መስፋፋትን ለመግታት ማኅበረ ኢየሱሳዊያን የሚል ተቋም አቋቋመች። ማኅበረ ኢየሱሳዊያን በኢትዮጵያ ለመስፋፋት በማሰብ በርካታ ሙከራዎችን እንዳደረጉና በሙስሊምና ኦርቶዶክስ አማኒያን ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ከአገር እንደተባረሩ ይታወቃል። ሆኖም ተደጋጋሚ ሙከራቸው ተሳክቶላቸውና በጦርነት የተከፈተላቸውን የመሣሪያ ማቀበል ዕድል ተጠቅመው አጼ ሱስንዮስን ካቶሊክ እንዲሆኑ ለማድረግ ችለዋል። በመጨረሻም በአጼ ፋሲል አገር ለቅቀው እንዲወጡ ቢደረጉም አልፎንዞ ሜንዴዝ የተባለው ኢየሱሳዊ ፍሬሞና በተባለች ከአድዋ 10ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኝ ከተማ በመቆየት እምነቱን ሲስፋፋ ቆይቷል። በአጠቃላይ ኢያሱሳዊያን ካቶሊካዊነትን ለማስፋፋት ባደረጉት ጥቃት በኦርቶዶክስ እምነት ላይ አሻራቸውን ጥለው ለማለፍ ችለዋል።
የሉተር ተቃውሞ ከተነሳ ከ500 ዓመት በኋላ በዚህ ዓመት (2016) የካቶሊክ ቤ/ክ በራሳቸው በሉተራን አማካኝነት ፕሮቴስታዊነትን ወደ መቃብር ሊከቱት ተዘጋጅተዋል። የሮም ካቶሊክ ቤ/ክ የሉተራን ቤ/ክንን በማሳመን የስምምነት ሰነድ እንዲፈርሙና ልክ ሉተር ተቃውሞውን በለጠፈበት ቀን በመጪው ኦክቶበር 31፤ 2016ዓም 500 ዓመታትን ጠብቀው ክብራቸውን በነጠቋቸው በራሳቸው ሉተራውያን ሊያስመልሱ ተዘጋጅተዋል። ስምምነቱ ሰላምን ለመፍጠር፣ ኅብረትን ለማምጣት፣ … ተብሎ የሚነገር ቢሆንም በካቶሊካውያኑ ዘንድ ግን ክብርን የማስመለስ ተግባር ተደርጎ ተወስዷል፡፡ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ የተጀመረበት ቀን እንደ ደስታ በዓል ቀን ሳይሆን እንደ “ታላቅ የሐዘን ቀን (Great Tragedy)” እንዲታሰብ በራሳቸው በፕሮቴስታንቶቹ ተወስኗል፤ በይፋም እየሠሩበት ነው። ሰርዶውን በአገሩ በሬ ማስበላት ማለት ይኸው ነው!
በታቀደልን መሠረት ራሳችንን እየበላን ጉዞ!?
የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋ፣ ከሃይማኖት፣ ከቀለም፣ ወዘተ የተቀየጥን መሆናችን በራሱ አንዱ የመገለጫችን ተምሳሌት ነው። ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ ሲባል በሁለቱ ላይ ብቻ እናተኩራለን – አድዋና የያሬድ ዜማ።
የአድዋ ድል በጣም ብዙ የተባለበት ስለሆነ ወደዚያ ዝርዝር አንገባም። ነገር ግን የኢትዮጵያ ጠላቶች የአድዋን ጦርነት የቀሰቀሱበት ምክንያት አገር መውሰድ ብቻ አይደለም። በጠላት ወረራ ጊዜ ነጋሪት እየተጎሰመ አዋጅ ሲነገር የሚባለውን ማስታወሱ ለዚህ ይጠቅማል።
የአድዋ ሽንፈት ለኢትዮጵያ ወራሪዎች ትልቅ ውርደት ነው፤ ውርደቱ ደግሞ ዓለምአቀፋዊ ነው። ለእኛ በጣም የተደጋገመ ታሪክ ስለሆነ ብዙም ላይደንቀን ይችል ይሆናል። “የተወጋ አይረሳ” እንዲባል የሽንፈቱ መራራነት እስከ ልጅ ልጆቻቸው ዘልቋል።
በአንድ ወቅት አንድ ወጣት የአዲስ አበባ ልጅ ከአንዲት ጣሊያናዊት ልጃገረድ ጋር ድብዳቤ መጻጻፍ ይጀምራል። በጣም ቶሎ ቶሎ ደብዳቤ ይላላኩ የነበሩት ልጆች ድንገት በመካከላቸው ግንኙነት ጠፋ። እሱ ቢጽፍም እርሷ ግን ምላሽ መስጠት አቆመች። ልጃቸው ደብዳቤ ይጻጻፍ እንደነበር ያውቁ የነበሩት አባት ልጃቸውን ሲጠይቁት ምክንያቱን ለማወቅ አለመቻሉን ይነግራቸዋል። እርሳቸውም በመጨረሻ የጻፈላት ደብዳቤ ይዘት ምን እንደነበር ይጠይቁታል። የኢትዮጵያውያን ጀግንነትና የአድዋን እንደነበር ይነግራቸዋል።
በምኒልክ ላይ የተንጋደደ አመለካከት ያላቸው ስለ ምኒልክ ብዙ መጥፎ ነገሮችን ከመናገራቸው የተነሳ የአድዋን ድል የራሳቸው ለማድረግ ሲቸግራቸው ተስተውለዋል። ዘር፣ ቋንቋ፣ ቀለም፣ … ሳይለያቸው ከተለያዩ ቦታዎች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በአድዋ ተሰውተዋል። ድሉ የምኒልክ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵውያን ነው። ሆኖም በዘመናችን የተነሱ የዘር ፖለቲካ አራማጆችና የምንሊክ ወቃሾች የመላው ጥቁር ሕዝብ አኩሪ ታሪክ የሆነውን አድዋን ድል የራሳቸው አድረገው ለመውሰድ በመቸገር ከባንዳዎች ቀጥሎ ለኢትዮጵያ ጠላቶች ድልን ማጎናጸፋቸውን የተረዱት አይመስላቸውም። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዳንድ የሕወሃት ደጋፊዎች “የምንሊክ ጦር አድዋ የደረሰው የትግራይ ሠራዊት ጣሊያንን ድል ካደረገ በኋላ ነው” በማለት ተራራ ነቅለው እንደወሰዱት ታሪክንም እንዲሁ ለማድረግ ሲጥሩ ተስተውለዋል። ታሪክን ወደ ራስ ለማንሸራተት የመጎምጀታቸው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ይህንን ጉልህ ታሪክ የማክስም ድራማ ለመተወን ቅጥረኛ የመሆን ሰምና ወርቅ የሌለው “ቅኔ”ም ነው። ይህ ሁሉ የመጣው ከምንሊክ ጥላቻ የተነሳ ሲሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የጠላትን ሃሳብ መደገፍ እንደሆነ አብሮ ማስተዋል ግድ ነው። ይህ ሲሆን ነው የቅኔው ትርጉሙ የሚገለጸው።
የአድዋን ድል እንደራሳችን አድርገን እንዳንወስድ የተቃጣብን ሌላው ሤራ የህወሃት አመራሮች ከአድዋ መሆናቸው ነው። ይህ በተለያየ መልኩ በአጋጣሚ የሆነ መስሎ ሊታየን ይችል ይሆናል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የሩዘቬልት ንግግርን ማስታወስ ከዚህ ጋር አግባብነት አለው። “በፖለቲካ ዓለም በድንገት የሚከሰት ነገር የለም፤ ካለም የተከሰተው እንደዚያ እንዲሆን ታቅዶ ስለመሆኑ መወራረድ ይቻላል።” እንደ ሩዘቬልት አነጋገር ፖለቲካ እንደ ሳይንስ ወይም እንደ ኃይላት ግጭት የሚከሰት ሳይሆን በዕቅድ የሚፈጸም ተግባር ነው። ሆኖም ለተመልካቹ እንደ ትግል፣ እንደ አብዮት፣ እንደ ዴሞክራሲያዊ ትግል፣ እንደ ሕዝባዊ ንቅናቄ … ተደርጎ እንዲታይ ይደረጋል። በሕዝብ ትግል የሚነሱ ንቅናቄዎች የሉም ማለት ሳይሆን ከተነሱ ወይ ይጠለፋሉ ወይም እውነተኛ የሕዝብ ትግል ከሆኑ እንዲኮላሹ ይደረጋሉ፡፡
ከህወሃት ሥልጣን መያዝ ጋር ተያይዞ እነ መለስ የአድዋ ተወላጆች በመሆናቸው አድዋን ወድደን እንዳንወድ እያደረገን መጥቷል። አመጣጡ ግን በቀጥታ በአድዋ ላይ ተነጣጥሮ አይደለም። ጠላቶቻችን እንዴት እንደሚያጠቁን በደንብ አጥንተው ጨርሰዋል፤ ማንነታችንን በደንብ ያውቃሉ፤ የዘር ክፍፍላችንን፣ ማንነታችንን፣ የህወሃቶችን ማንነት፣ ወዘተ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለዚህም ነው ማንነታቸውን የሸጡ፣ ስብዕናቸው የጎደፈ፣ ከመጠሪያ ስማቸው ጀምሮ ከፍተኛ የማንነት ቀውስ ውስጥ የገቡ ሰዎችን ሰብስበው ህወሃትን (ትግራይን አላልንም) ያነገሱብን። (የህወሃት ደጋፊ የሆኑ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለህወሃት ባላቸው ፍቅር የተናደዱ አንዳንድ ፖሊሲ አውጪዎች ባለሥልጣኑን “ከአድዋ ህወሃቶች የበለጠ አድዋዊ ናቸው” በማለት ሲወርፉ መሰማታቸው ለጎልጉል መረጃው ደርሷል)
የህወሃት እኩይነት፣ የኢትዮጵያ ጠላትነት፣ በሕዝብ ላይ የሚፈጽመው ኢሰብዓዊነት፣ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን እየጠላ ልግዛ የሚል መሆኑ እና ሌሎችም ተዘርዝረው የማያልቅ ድርጊቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ህወሃትም ይህንን ብቻውን ይዞ አልተቀመጠም። መርዙን ከትግራይ ህዝብ ጋር በማገናኘት እና በማመሳሰል የትግራይን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንዲቃቃር አድርጓል፤ አሁንም እያደረገ ነው። መሪዎቹም በድፍረት አደባባይ እየወጡ ህወሃት ማለት የትግራይ ሕዝብ ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ደግሞ ህወሃት ነው በማለት የማጣላቱን ተግባር ተያይዘውታል። በዚህ በዕቅድ በሚደረግ ተግባር የተነሳ ትግራይ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል፤ የትግራይ ሕዝብ አንዲጠላ፤ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እጅግ በሚያጸይፉ ሁኔታዎች እንዲሰደብ፣ እንዲያውም “ወደዚያ ተገንጥለው በሄዱልን” የሚሉ አነጋገሮች እስከመስማት ደርሰናል። ይህ ዓይነት አሠራር በራሳቸው የህወሃት ሰዎች የሚደረግ መሆኑንም መዘንጋት የለብንም።
በትግራይ ህዝብ ላይ እንዲህ ዓይነት ጥላቻ በየቦታው ሲሰነዘር መሰማቱ በቂና አሳማኝ ማስረጃ ሊቀርብበት ይችላል። ሆኖም ጠለቅ ብለን የኢትዮጵያን ጠላቶች ዕቅድ የምናስተውል ከሆነ በታሪካዊ ድላችን ላይ ራሳችን እንድንወስን እያደረጉን ነው። ትግራይን አግልለን፤ የትግራይን ሕዝብ ጠልተን አድዋን ምን ልናደርጋት ነው? ትግራይ ተገንጥላ እና አገር ሆና ህዝቧን ጠልተን እንዴት ነው የአድዋን ድል የራሳችን አድርገን ለልጆቻችንና ለመጪው ትውልድ የምናስተላልፈው? በዚህ ጥላቻችንና ማግለላችን እንዴት አድርገን ነው አድዋን ለትግራይ እና ለህወሃት የምናስረክበው? ወደድንም ጠላንም አሁን ባለን የፖለቲካ አመለካከትና በትግራይ ሕዝብ ላይ በየጊዜው እየጨመረ በመጣው ጥላቻ የአድዋን ድል በራሳችን አንደበት የእኛ ታሪክ አይደለም ልንል ተቃርበናል። ለዚህ ድርጊት የምኒልክ ወቃሾች እና ኢትዮጵያዊ ማንነት የሚጸየፉ ወገኖች ፕሮፓጋንዳ ጥሩ ነዳጅ እየሆነ ነው፡፡ ጠላቶቻችን የራሳችንን ሰርዶ በራሳችን እንዲያስበሉን ራሳችንን አመቻችተናል።
ቅዱስ ያሬድ የትግራይ አክሱም ተወላጅ ነው። ታሪኩ እንደሚገባው በዓለም ዙሪያ አልተነገረለትም እንጂ በአውሮጳ ከተነሱት የሙዚቃ ጠቢባን እነ ሞዛርት፣ ቤትሆቨን፣ ብራህምስ፣ ባህ፣ ሹበርት፣ ሄንድል፣ … እኩል መጠራት የሚገባው የዓለማችን ድንቅ ሰው ነው። የሙዚቃው ልዩ መሆን፣ አወጣጡና አወራረዱ፣ ዜማው፣ ቃናው፣ ምስላዊ ገጽታው፣ ተፈጥሮአዊ ትዕንቱ፣ … ወደር የለሽ ነው።
በዚህ በዕቅድ በተወጠነብን አገራችንን በራሳችን የማፍረስ ተግባር ከቅዱስ ያሬድ ጋር የተሳሰረው ሃይማኖታዊ ማንነት አደጋ ላይ ወድቋል። በኦርቶዶክስ ቤ/ክ ላይ በተደጋጋሚ የትግራይ ተወላጆች የመንበረ ፓትሪያርኩን ሥልጣን መያዛቸው እንደ ፖለቲካው የትግራይ የበላይነትን ለማሳየትና ሃይማኖትን ለመቆጣጠር ብቻ አይደለም፤ ሃይማኖታዊ ማንነትንም አብሮ ለማጥፋት ከታቀደ የህወሃት ሃሳብ ጋርም ተዛማጅነት አለው። የሃይማኖት ጉዳይ ስስ አጀንዳ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ከማለት እንቆጠባለን።
ትግራይን ከመጥላትና የትግራይ ተወላጆችን የህወሃት ሙሉ ደጋፊና የኢትዮጵያ ጠላቶች አድርጎ በመፈረጅ፤ ይሂዱ ይገንጠሉ፤ ወዘተ እያልን በትንሹ አድዋንና ያሬዳዊ ዜማን ወድደን በፈቃዳችን ከታሪካችን በማስወገድ የማንነት ቀውስ ልንገባ በፍጥነት እየተዘጋጀን ነው። ይህ ልመና ወይም “ያለ እነርሱ አይሆንልንም” ዓይነት ፖለቲካዊ ትርከት አይደለም። ይህ “የአማራና ትግሬ ኢትዮጵያዊ ማንነት” ወይም “የኦርቶዶክስ ኢትዮጵዊነት” ጉዳይም አይደለም፡፡ ይህ የጠላትን ማንነት የመረዳትና የጉዳትን ዋጋ መዝኖ የማወቅ ብልህነት ነው።
ህወሃት ሥልጣን ላይ በቆየባቸው 25ዓመታት እጅግ ብዙ ማንነታችንን አጥተናል። በዘር ተሰፍረን ኢትዮጵያዊ ውበት የሆነው ቅይጥነታችን ጠፍቶ አባታችንን መርጠን እናታችንን እንድንተው ተግድደናል፤ ማንነታችን በምንናገረው ቋንቋ ወይም በመጠሪያ ስማችን ተወስኖ ጠብበናል፤ አንዳንዶቻችን በስማችን ብቻ አንድን ጎሣ በግድ በመደገፍና ቅይጥነታችን በመካድ በከፍተኛ የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብተናል፤ ሌሎችም እጅግ ብዙ ነገሮች ተደርገውብን አንሰናል። አሁንም በተለይ በስሜት በሚነዳው ዳያስፖራ በሚገኘው የተቃዋሚው ጎራ በትግራይና በተወላጆቹ ላይ ጥላቻና ልቅ ስድብ፤ ኢትዮጵያዊነትን የማስካድ ወይም የማሳነስና ጎሣን የማጉላት “ድንቁርና”፣ የመጥበብና ማንነትን በግድ አንድ ሳጥን ውስጥ የማስገባት የፖለቲካ አባዜ እየተስፋፋ መጥቷል፤ በአሁኑ ጊዜ እኔ በመጀመሪያ ሰው ነኝ ሲቀጥልም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ድምጽ አልባ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለመፍጠር መጀመሪያ በዘር ተደራጅቶ የራስን ዕድል ከወሰኑ በኋላ ኢትዮጵያን እንደገና የመሥራት ዋለልኛዊ ዕብደት የበርካታ “ታጋዮችን” ማንነት እየፈተነ መጥቷል! የዚያኑ ያህልም ህይወታቸውን በሰዉ በርካታ ወገኖች ደም የሚደረገው ቀልድና የፖለቲካ ቁማር ከገዳዮቹ በማያንስ የሚያስጠይቅበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ጥቃት እየደረሰብን ያለው ከህወሃት ብቻ ወይም ከህወሃትና ከጎሣ ፖለቲካ አራማጆች ብቻ አይደለም፤ አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ወይም በስሜት በመነዳት ራሳችን ነጻነት ፈላጊዎች የሆንን በአገራችን ላይ ጥቃት እያደረስን ነው፡፡ ይህ ሁሉ ራሳችን እንድናጣው ከደገስንለት ኢትዮጵያዊ ማንነት አንጻር ካልታየና ካልተገታ ጉዳታችን የከፋ፤ እንደ አገር የመኖራችን ኅልውና የመነመነ ይሆናል። በዚሁ ከቀጠልን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ጠላቶቻችን የራሳችንን ሰርዶ በራሳችን ያስበሉናል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Rasdejen says
I want Donald Trump to become the president of America because I want America to be demolished.
It is the state of America and UK which are causing the outrage to Ethiopians and many other societies around the world.
The state of America should collapse soon. The state of America in the post cold war era is enemy of humanity in disguise.
Rasdejen says
በእዉቀትም ዉጓቸዉ:-
ህወሃት የሚያደርሰዉ ገደብ የለሽ የሀገር ጥፋት እና የህዝባችን ም ሰቆቃ ስለተረዳ ችሁና የበለጠም ስለሚገባችሁ ለህዝባዊ ፍትህ ትግሉ እድልና አቅም ማግኘታችሁ በራሱ ደስታ፤ እረፍትና እርካታ ሊሰጣችሁ ይገባል። ሰዉ የልቡን መሻት ከማግኘት በላይ ግብ የለዉምና ። እናንተ የል ባችሁን መሻት ስለምትተገብሩ እጅግ ታስቀና ላችሁ እንጂ ልታሳዝኑ አይገባም። ስለሆንም ኮሸታ በሌ ለበት እየኖርን ግን ስብህናችን በ መገፈፉ ሰላም አጥተን ከምንባዝነዉ ከብዙዎቻችን ትበልጣላችሁ፤ ሰላም አላችሁ እና ሰላማችሁ አብልጦ ይብዛላችሁ፤ እድለኞች ናችሁና እድላችሁ አብልጦ ይብራ።
አዎ በህወሃት የሚደርሰዉ የህዝባችን ሰቆቃ እና የማንነታ ችን መፈረካከስ እጅጉን ይከነክና፤ይገዘግዛል። ግን ህወሃት ማን ነዉ፤ ለምን ይህን ሁሉ ያደርሳል ብለን አነጥረን በማወቅ አጥፊዉን ከ ጠፊዉ ለይተን ማሳዬት / ማሳወቅ በጣም አስፈላጊ ነዉ፤ በጽኑም አምንበታለሁ።
ህወሃት የትግራይ ነጻ አዉጭ ሳይሆን የትግራ አጥፊም መሆኑ በትክክል ሊታወቅ ይገባል። ወግኖቸ፣ – ይህ ስብስብ በጣም ትንሽ በሆኖ የባንዳ ዉላጆች ተሰይሞ በባህር ማዶ ሃይሎፍ የሚሽከረከር የታሪካዊ ጠላቶቻችን መሳሪያ የሆነ የወገን ጠላት ነዉ። የቀደምቱ ባንዳ ወገኖቻችን ባስጠያፊ ስራቸዉ በመላዉ የኢ ትዮጵያ ህዝብ ሲወገዙ፤ ሲረገሙ መኖራቸዉ ይታወቃል። ለዘላለሙም ዉግዞች ናቸዉ !
የባንዳወቹ ዉላጆ ቸ በቤተሰቦቻቸዉ ላይ የደረሰዉን የህብረተሰብ ነቀፌታ፤ ቅጣትና አይፋቄ ዉርደት ለመበቀል ሲሉ እንደ ወላጆቻቸዉ ከባህር ማዶ ጠላቶቻችን ጋር በመዎገን ለሃያ አምስት አመት ታሪካችን አሰከ ሰሪዎቹ ቦጫጭቀዉ፣ ቅርስ እና ዋቢወችን ም ሳይቀር በማጥፋት ፤ አላምን ያለዉን ወይም ያንገራገረዉን በማዋረድ ካልሆነም በማስወገድ ቃላት ሊገልጸዉ የማይችል ሰቆቃ ፈጸሙ፤ እየፈጸሙ ነዉ ። የዉርደት ህመማችዉ ን ለመፈወስ ሲሉም የበላይ ነን፤ ታሪክ ሰሪዎቹ እኛ ነን እወቁ፤ ተቀበሉ አሉን፤ አሻራ ቢጤም ለማስቀመጥ ብዙ ተንፈራገጡ። ይሁን እንጅ መለስ እና በህይወት ያሉት ህዋታዉያንም ሆኑ ባንዳ ወላጆቻቸዉ በምንም መለኪያ መልካምነት የላቸዉም ፤ ሊ ወገዙ፣ ሊታረሙ አሊያም ልንፋረዳቸዉ ይገባል እንጅ ።
ሰለሆነም በህዝባዊ ፍትህ ትግሉ ለህዋታዉያንና ለደጋፊወቻቸዉ አነሳሳቸዉን፣ ያነሳሳቸዉን እና መጨረሻ የለሌዉ መራራ ስራቸዉን ፤ወነጀላቸዉን አነጥሮ ማሳዎቅ እና እንዲመለሱ ሳይታክቱ በማስታወስ ልንወጋቸዉ ይገባል።
እነዚን የወገን ጠላቶቻችን ከጠይት ይልቅ በእዉቀት ዉ ጓ ቸዉ። ተበቃይና አባሮቻቸዉን ግንዛቤ ፣ ጸጸት እንዲያደርጉና እራሳቸዉ ወደህዝባዊ የፍትህ ትግሉ እንዲቀላቀሉ ንገሯቸዉ፤ ሳታሰልሱም ዉቀሷቸዉ ።
አዎን ከጥይት መዉጊያዉ የእዉቀት መዉጊያዉን አ ስቀድሙ፤ እናስቀድም። ከሃዲ፤ባንዳ ከቶዉንም የበላይ አይሆንም፤ ለክህደት ስራዉና ላ ደረሰዉ ሰቆቃም ተገቢዉን ህጋዊ እና ህበረተሰባዊ ቅጣት ያገኛል። ገናናዋ እትዮጵያ ዳግም ትግናለች፤ ከብርና ነጻነታችን ይመለሳል፤ ለአደ ዲሱ ቅኝ ግዛት ተገዥወች ም እንደገና የ ነጻነት ፋና እንቀዳለን።
ፍተህ ለሰዉ ልጅ ሁሉ ይሁን ! አሜን
Rasdejen says
I think TPLF is effectively using the State Emergency (SE) to contain the public upraising and the force/ for change. Primarily SE has infused unprecedented fear among the people. This has given the following opportunities to TPLF:
– Brainwashing the general public using the so called religious leaders and elders
– To search and find the leadership, network and leaders of the nationwide movement
– In due time it will air another fake documentary claiming the movement has no public root.
– To silently kill/imprison all those against it.
Hence, the upraising should move on OTHERWISE TPLF will reestablish itself