በሙት መንፈስ አገር እየገዛ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) በይስሙላነት ባስቀመጠው ፕሬዚዳንት አማካኝነት ፓርላማ ብሎ በሰየመው የራሱ ስብስብ በኢትዮጵያ ያለ አንዳች ልዩነት ለገደላቸው ወገኖች አስከሬን መግዣ ብር ሰይሜአለሁ ብሏል፡፡ ከዚህ በፊት በኦሮሚያ ላፈሰሰው መድቤአለሁ ያለው 2.4 ቢሊዮን ብር እስካሁን የት እንደገባ አይታወቅም፡፡
የሙት (መለስ ዜናዊን) ፎቶ ከፊት አስቀምጦ አሁንም በአስከሬን አገሪቱን እንደሚመራ በገሃድ ያሳየው ህወሃት ለመለወጥም ሆነ ስለ ለውጥ ለማሰብ ፍላጎት እንደሌለው ነው በጥቅሉ ያመላከተው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን በእስር እያማቀቀ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት፣ ፓርቲዎች እንዳንቀሳቀሱና ኅልውና እንዳኖራቸው በርካታ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰ ምርጫ ኮሚሽን ማዋቀር፣ … የሚሉ የጥገናዊ ለውጦች ስሜት እንኳን የሌላቸውን ጉዳዮች አውስቷል፡፡
በዋናነትም በርካታ ወራትን ያስቆጠረውንና በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች እየተስፋፋ ለመጣው የለውጥ ማዕበል እስካሁን ለገደላቸው ወጣቶች አስከሬን መግዣ የሚመስል ዋጋ በማቅረብ አሁንም ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ከፍተኛ የአስተሳሰብ ድህነት ያለበት ህወሃት ከዚህ በፊት ለሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ፎቅ ሰርተናል፣ መንገድ ሰርተናል፣ ባቡር አስገብተናል፣ … የሚል የድህነት ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ሰማዕቶቻችሁን በ10 ቢሊዮን ብር ልግዛችሁ ብሏል፡፡
የዛሬ ስድስት ወር ህወሃት በአጋዚ ጦር አማካኝነት በኦሮሚያ ላፈሰሰው ደም 2.4 ቢሊዮን ብር እሰጣለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡ ጎልጉል “ህወሃት በኦሮሚያ ላፈሰሰው ደም 2.4 ቢሊዮን ብር ጉቦ ሰጠ” በሚል ርዕስ April 18, 2016 ባተመው ዜና ህወሃት ይህንን ገንዘብ ይፋ ባደረገበት ቀን “ስራ አጥቶ ወደ ግብርና የተመለሰው ኢንጂነር በዳዳ ጋልቻ በህወሃት አንጋቾች የእርሻ ስራውን ጨርሶ ሲመለስ በጥይት ተደብድቦ” መገደሉን ዘግቦ ነበር፡፡
በዚህ ዓይነት የአስተሳሰብ ድርቅ የተመታው ህወሃት ከስድስት ወር በኋላ ተመሳሳይ የፌዝ ዕቅድ ማውጣቱ በተለይ ውዶቻቸውን እንደወጡ ያጡ ወገኖች እንባቸው ሳይደርቅ እንደገና ሃዘን እንዲቀመጡ ያደርጋቸዋል በማለት ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ጋር አያይዘው በተለይ በአገር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ለሟቾች ካሣ ይከፈል የሚል “የልመና ፖለቲካቸውን” ቢያቆሙ መልካም ነው ብለዋል፡፡
ከሳምንት በፊት ቢሾፍቱ ላይ በተደረገው የኢሬቻ በዓል ላይ የሕዝብን ብሶት በገሃድ የተናገረው ወጣት “Down! Down! ወያኔ! Down! Down! TPLF!” በማለት ያሰማው ሙዚቃዊ ቅላጼ የተሞላበት መፈክርና በአጸፋው በሚሊዮን የሚቀጠረው ሕዝብ የሰጠው ምላሽ አሁንም የሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት ነው፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply